>

አቡነ ሰላማና አጤ ቴዎድሮስ!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

አቡነ ሰላማና አጤ ቴዎድሮስ!!!

ሳሚ ዮሴፍ
…አቡነ ሰላማ ከግብጽ ሀገር ሲመጡ የተከፈለው አስር ሺ ብር ነው። የዋሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ያህል ገንዘብ ከፍሎ ጳጳስ ማስመጣቱ በየሀገሩ እየዞሩ ቅስናም ድቁናም እየሰጡ ኃይማኖቱን እንዲጠብቁለትና እንዲያስፋፉለትም ነበር።
ቴዎፍሎስ ዎልድ ሜየር እንደጻፈው አባ ሰላማ ግን ሀገር ለሀገር አልንከራተትም ብለው ትንፋሻቸውን በስልቻ እየሞሉ ወደ ጎንደርና ጎጃም ይልኩ ነበር። አንድ ሰው ለመቀሰስ በሚፈልግበት ጊዜ ከስልቻው መጠነኛ ትንፋሽ በሚፈልጉበት ጊዜ በራሱ ላይ ይነፉበትና ቄስ ሆነ ይባላል።
ጳውሎስ ኞኞ
አጤ ቴዎድሮስ
ጎንደሮች ጎጃሞች ቅብዓቶችና የጸጋ ልጆች የሚባሉት አንድ ወገን ሁነው ተሰብስበው ጳጱሱን አቡነ ሰላማን “ና ውጣ ሀገር ልቀቅ። ልቀቅ ሀገራችንን ኸዚህ አንተ ምን አለህ? ተነሣ ሂድ!” አሏቸው አቡነ ሰላማን። የጥቅምት ሚካኤል ለት ነው እሁድ። “ወንድሞቼ ዛሬ ሰንበት ነው ሚካኤል ነው። ዛሬን ልዋልና ነገ እለቅላችኋለሁ” አሉ አቡነ ሰላማ።
“በሰንበት አጋንንተ አውጽእ” ይላል መጣፍ ትወጣለህ ትሄዳለህ”‘ አሏቸው። (በሰንበት አጋንንት አወጣ- ወንጌል) ተሰብስበው በደንጊያ! አሽከሮቻቸውንም አርድዕቱንም እሳቸውንም፤ እኒያንም አለቃ ኪዳነ ወልድንም በደንጊያ!
ያን ጊዜ መንግሥት የለ፤ መሳፍንት አደሉም እነ ራስ ይማም ናቸው የወሎና የየጁ እስላሞች። አቡነ ሰላማን ማ ያድናቸው? ወጡና ሄዱ። አቀበት ወጡና ኸላይ ኻፋፍ ሲደርሱ አማተቡ ፊታቸውን፤ ጸሎት አደረጉ_ “ጎንደር ባቢሎንን ያርግሽ! በባቢሎን የተፈረደ ፍርድ ይፈረድብሽ” አሉ። (በዚያ በቀለምሲስ የተጻፈች ባቢሎን የምትባል መከራ የወረደባት ሀገር አለች) ረግመው ተነስተው ኸዱ ተሰደዱና።
ትግሬ ኸዱና ደብረ ዳሞ ወጥተው አባ አረጋይ (አቡነ አረጋዊ) ገዳም ላይ ተቀመጡ። (አቡነ አረጋዊ ከተሰዓቱ ቅዱሳን ነው ቁጥራቸው። ሀገራቸው ግሪክ ነው) ደብረ ዳሞዎች ማኅበሩ መነኮሳቱ ኸመቁናቸው ትንሽ ደርጎ አወጡላቸው። የትግሬ መኳንንትና ሴት ወይዘሮ አባት አደረጋቸው። ያጤ ዮሐንስ እናት ወይዘሮ ሰንበቱ ሲወዷቸው እንዲህ አይደለም!
አለቃ ኪዳነ ወልድ በትግሬ ሀገር ለሀገር ይሄዳሉ፤ ያቡነ ሰላማ ሹም ሁነው። አስነባቢ ናቸው፤ ቅስናና ዲቁና እሚፈልገውን እሳቸው እያዘዙ ሥልጣን ያሰጣሉ ካቡነ ሰላማ
አንድ ቀን ማኅበሩ ሣታት ቁመው አድረው፤ የወር ባል ነው፤ “አባታችን እንደምን አደሩ፣ እንደምን ሰነበቱ፣ እንበላቸው እንጠይቃቸው” ተባብለው ተነስተው ኸዱ። ካህናቱ መጡ ሲሏቸው ጊዜ አቡነ ሰላማ ወጡና ገለጥ ብለው ተቀመጡ። “እንደምን ነዎ አባታችን ብርቱ ነው?” ሲሏቸው፤
“ኧረ ዛሬ መከራ ሲያሳየኝ አደረ” አሉ።
“ምንድን?”
“እኔ የት አውቀዋለሁ? ሰይፍ መዞ ‘እንካ’ አለኝ። ሰይፍ ምን አረገዋለሁ? ምን ይሆነኛል? ‘እንካ አልኩህ ‘ ምን ይሆነኛል?
‘እንካ!’ ምን ላርገው? ‘ካሣ ይሁንህ’ የምን? ‘ካሣህ ነው እንካ’
እንዴ የምን ካሣ? ‘ካሣ ይሁንህ’ ሲለኝ ደንግጬ ብንን አልኩ።
አቡነ ሰላማ ብዙ ዘመን አደለም ኢትዮጵያ የተቀመጡ? አማርኛ ለምደዋል።
“አባታችን በደልዎ ከእግዚአብሔር ደርሦ ይሆናል! ሊክስዎ ይሆናል፣ ሊፈርድልዎ ይሆናል…እግዚአብሔር ዘንድ ደርሷል ግፍ” አሏቸው ማኅበሩ።
“እንግዲህ እሱ ያውቃል!” ሲሉ፤ ያ ሀብለ ዳሞ (ገመድ) የሚጥለው ሲበር መጣ። እመጋቢ ቤት ሲሄድ ጊዜ ቤተክሲያን ናቸው የሉም አሉት። ወደ ቤተክሲያን ሲሄድ ጊዜ ኸጳጳሱ ቤት ህደዋል አሉት። ሲሮጥ መጣ።
“ኧረ ክልጅ ካሣ ተልኬአለሁ ወዳባታችን የሚል ሰው መጥቷል!” አለ። ደነገጡ ሁሉም።
“የማን ካሣ?” አሉት አቡነ ሰላማ።
“ካሣ ኃይሉ”
“ቶሎ በል! ግባ በሉት!” አሉት አቡነ ሰላማ። መልክተኛው መጣ። አውጥቶ ሰጣቸው ያጤ ቴዎድሮስን ወረቀት።
ይድረስ ላባታችን…ልጅዎ ካሣ ኃይሉ በስዎ ጸሎት እገሌን እገሌን ድል ነሳሁ፣ በስዎ ጸሎት የማርቆስ ኃይማኖት ሊቋቋም ይመስለኛል” የሚል ወረቀት መጣ። ደስታ ሆነ። ምግቡን አምጡለት አሉ፤ የምሥራች ነው። ወረቀት ጻፉ አቡነ ሰላማ..
“ይድረስ…ለልጄ ኸካሣ ኃይሉ” አሉና “አምላከ ማርቆስ እንዲህ ያድርግልህ፣ እንዲህ ያድርግህ…ያባቶችህ የእነገሌ የእነገሌ ኃይማኖት…ሰላምታውን አደረጉና ሰደዱት።
አጤ ቴዎድሮስ ገና ናቸው። ገና ጎጃምን መትተው በየምድር(በጌምድር)  ሲገቡ ነው። ያቺን ወረቀት አጤ ቴዎድሮስ ክታብ አድርገው ኸድጋቸው ውስጥ ያረጓታል በጦርነት ጊዜ። ተዋግተው ድል ሲነሳ፤ አውጥተው ኸኮሮጆ ውስጥ ትቀመጣለች። ኸዚያ በኋላ መሣሪያ ሆነች።
ኋላ የበየምድሩን (በጌምድሩን) አደረጉና፤ ደጃች ውቤን የትግሬን፣ ድል አደረጉ አጤ ቴዎድሮስ። ትግሬን ይገዙ ነበረ ውቤ ሀገራቸው ሰሜን ነው፤ ጦራቸው የሚበልጠው ትግሬ ነው። ሠራዊቱ በሙሉ ተማረከ፤ ይኸ ነጠላው ወታደር በሙሉ ገባ።
” ደብረ ዳሞን የሚያውቅ ሰው?” አሉ አጤ ቴዎድሮስ ።
“እኔ አለሁ!” አለ አንዱ ትግሬ።
“ህድ፤ አቡነ ሰላማን አምጣልኝ፤ ቶሎ” አሉት። ዕለቱን እንዲደርሱ የሚል ወረቀት ይዞ ሄደ። አቡነ ሰላማ መጡ፤ እዚያው ሰሜን ደረስጌ እምትባል ደጃች ውቤ የሠሯት ቤተክሲያን አለች፤ ኸዚያው ጸሎቱ ተደረገና፤ አጤ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ተባሉ። ሰሜን ላይ ነው የተቀቡና የነገሡ፤ ደብረ ታቦርን ኋላ እንዲያው ከተማ አደረጉት እንጂ።
አቡነ ሰላማ ተመልሰው ኸቦታቸው፣ ኸሹመታቸው ገቡ።
አጤ ቴዎድሮስ ጋራ ናቸው ደብረ ታቦር። ኸቤተ መንግሥት እንዴት ይለያሉ? አጤ ቴዎድሮስ ጎጃሞችንና ጎንደሮችን ካህናቱን አስታረቁ ኻቡነ ሰላማ ጋር ጎንደር። “ታረቁልኝ አባታችሁ ናቸው” ብለው ደንጊያ ተሸክመው አስታረቁ- ከነገሡ በኋላ ነው።
መጽሐፈ ትዝታ 
ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ 
መንግሥቱ ለማ
አጤ ቴዎድሮስ እና አቡነ ሰላማን ምን አቀየየማቸው
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ቴዎድሮስ በሚለው መጽሐፉ ይሄንን ጽፎልናል …
…ይህን ታሪክ እዚህ ያመጣሁት አጤ ቴዎድሮስ አቡነ ሰላማን ማሰርና መፍታታቸውን ማጉላላታቸውን ብቻ በሀገራችን ተጽፎ  አንዳንድ ሰዎች የቴዎድሮስን ክፋት ያለቦታው እያጋነኑ በማውራታቸው እውነተኛውን ለማሳወቅ ነው።
አጤ ቴዎድሮስ ገና በሽፍትነት ሳሉ ራስ ዓሊን ድል ካደረጉ በኋላ የደጃች ካሣ ኃይል መበርታቱን ያዩት አቡነ ሰላማ ከዳጃች ውቤ ዘንድ እንደሆኑ “እኔን ብትቀበለኝ ቀብቼ አነግስሃለሁ” እያሉ በሚስጥር ይላልኩ ጀመር። ደጃች ካሣም ደጃች ውቤን ድል ሲያደርጉ በቃላቸው መሠረት አቡነ ሰላማ ደጃች ካሣን ቴዎድሮስ ብለው ቀብተው አነገሱ።
አቡነ ሰላማ በጎንደር ሊቃውንቶች እንደማይወደዱ አጤ ቴዎድሮስ ያውቁ ነበርና የጎንደር ሊቃውንቶችን ሰብስበው
“አባቴን ተቀበሉኝ ታረቁልኝ” ብለው ለመኑ። ሊቃውንቱም “የኃይማኖት ነገር በሥርዓት እንጂ በልመና አይሆንም፤ የእግዚአብሔርን ኃይማኖት ለሰው ብሎ በሰው ልመና መካድ ማስካድ ለኛም ለእርሶም አይገባምና በዚህ ነገር እሺ ልንልዎ አንችልም” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ አጤ ቴዎድሮስ ተናደው አጠገባቸው የነበሩትን ወታደሮች
“በል በልልኝ” ብለው አዘዙ። ወታደሩም የሊቃውንቱን ልብስ እየገፈፈ ጥምጣም እያወለቀ በሚጫወትባቸው ጊዜ አቡነ ሰላማ እዚያው ነበሩና በአድራጎቱ ተደስተው ሊቃውንቱን የሚያሰቃየውን ወታደር “እግዚአብሔር ይፍታህ” አሉት።
ይህን የአቡነ ሰላማን “እግዚአብሔር ይፍታህ” ማለት የሰማው ወታደር የሊቃውንቱንና ቀሳውሱቱን ቤት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ከተማውን በሙሉ ዘረፈ።
ከአጤ ቴዎድሮስ ጋርን ቢሆን በሰላምና በፍቅር አልኖሩም።
የጠቡ መነሻ የሆነውም ሚስዮናውያኖቹ ከራፍ እና ፍላድ የመጡ ጊዜ ነው። እነኚህ ሁለት የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ከኢትዮጵያ እንደገቡ ደብረ ታቦር ሄደው ከራሳቸው ጳጳስ ከጉባት የተጻፈላቸውን ደብዳቤ ይዘው አቡነ ሰላማ ዘንድ ቀረቡ። አቡነ ሰላማም በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት ሚስዮናውያኖቹ ስብከታቸውን እንዲሰብኩ ፈቀዱላቸው። በማግስቱም ከአጤ ቴዎድሮስ ጋር ሲያገናኙዋቸው አጤ ቴዎድሮስ “የምፈልገው ጥበበኛ የእጅ ሥራ አዋቂ ነው፤ ጠበንጃና ሌላም የሚሠራ እንጂ ሰባኪ ለሀገሬ ምን ይጠቅማታል” ቢሉ አቡነ ሰላማ
 “በሥራዬ በኃይማኖት ጉዳይ አትግባ” ብለው፤ ቴዎድሮስን ገሰጡዋቸው። ቴዎድሮስም ከዚያን ቀን ጀምሮ ቂም ያዙ።
አባ ሰላማ ከቴዎድሮስ ጋር በጎንደር በነበሩበት ጊዜ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋም ቀሳውስት አይወዳቸውም ነበር።
ከክህነት በስተቀር ለጳጳሱም አይታዘዙም ነበር።  ይህንን ያወቁት አባ ሰላማም ቁጭታቸውን በቴዎድሮስ በትር ለማስመታት እያሉ ቀሳውስቱ ሥርዓት የሌለው በመሆኑ በሥርዓት እንዲያድር እንዲያደርጉ ለቴዎድሮስ ይነግሯቸው ነበር። አጤ ቴዎድሮስ እውነት እየመሰላቸው ከቀሳውስቱ ጋር በየቀኑ ይጣሉ ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ትእዛዝ ቀሳውስቱን ያዙ ነበር።
በኋለኛው ዘመንም ቴዎድሮስ በቀሳውስቱ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻ መነሳቱን ካወቁ በኋላ ለዚህ ያበቋቸውን ጳጳሱን አባ ሰላማን መቅደላ ወስደው አሰሯቸው።
በ1850 ዓ.ም የጁ ውስጥ ኢያላ በተባለ ቦታ ሰፍረው ሳለ አንድ ሰው ወደ ንጉሡ ጮኸ የሰውየውን ጩኸት የሰሙት አጤ ቴዎድሮስም አቡነ ሰላማን “ለምን ያስጮሁብኛል?” ቢሏቸው አቡነ ሰላማ “፣አንተ በኔ ግዛት ምን አገባህ” ብለው የተገላቢጦሽ ንጉሡን ተቆጧቸው። ንጉሡም ተናደው ሲቆጡ ጳጳሱ ብለው በኃይል “ታቦት ያነሳ ይህን ሰው የተከተለ ውግዝ ይሁን” ብለው ገዘቱ። ንጉሡም ግዝቱን እንደሰሙ ያዘው ብለው ጳጵሱን አስያዟቸው። የጳጳሱን መያዝ ያዩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ግዝቱን ፈቱ። አቡነ ሰላማ ግን ለምን የገዘትኩትን ይፈታሉ ብለው ከአቡነ ቄርሎስ ጋር ተጣሉ። በእነዚህ ሰዎች መጣላት ምክንያት ታላቅ ሽብር ሊነሳ ሲል ቴዎድሮስ ነገሩን አብርደው ታረቋቸው።
አቡነ ሰላማ አምስት ዓመት ያህል በግብጽ ከሠሩ በኋላ አጤ ቴዎድሮስ ብዙ መንገላታት አድርሰውባቸው በመጨረሻው
እንደገና ከ62 ተከታዮቻቸው ጋራ በመቅደላ ተራራ አስገብተው አሰሯቸው። ከዚያም ሆነው ከሸዋው ንጉሥ ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር በምስጢር “ከዚህ አውጣኝና አነግስሃለሁ” እያሉ ሲጻጻፉ አራት ዓመት እንደቆዩ በሞት ተለዩ።
አቡነ ሰላማ ከቴዎድሮስ ቁጣና እጅ ድነው በ1860 ዓ.ም  ጥቅምት 15 ቀን ባደረባቸው የሳንባ (የሳል) በሽታ አርብ ዕለት ከቀኑ በ9 ሰዓት ሞቱ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic