>

የውስጥ ጠላቱን ያላሸነፈ የውጭ ጠላቱን መቼም አያሸንፍም (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

የውስጥ ጠላቱን ያላሸነፈ የውጭ ጠላቱን መቼም አያሸንፍም

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


አንድ ጓደኛየ በከፍተኛ ብስጭት “መጀመሪያ መምታት ለግብጽም ሆነ ለሌሎች የውስጥም ሆኑ የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች በገንዘብ ራሳቸውን ሸጠው እርስ በርስ የሚያበጣብጡንን እንትናን፣ እንትናንና እንትናን ነው!…” እያለ እንደሽሮ በንዴት ሲንተከተክ ከአፉ ቀለብ አድርጌ ይህችን አጭር ማስታወሻ ጻፍኩ፡፡ እርሱ የሰዎቹን ስም እየጠራ ነበር የሚንፈቀፈቀው፡፡ እኔ ግን “ጃፋር፣ ገርቡና ልቀቱ” እያልኩ እንደሱ ስም በመጥራት በስም ማጥፋት ወይም በግድያ ዛቻ መከሰስ ስለማልፈልግ  ስማቸውን በሆድ ይፍጀው ተውኩት፡፡

እርግጥ ነው፡፡ ማንም ወገን የውስጥ ጠላቱን ለይቶ ካላስወገደ ምንም ዓይነት ውጊያ አያሸንፍም፤ በልማትም ሆነ በሥልጣኔ ስንዝርም ብትሆን ሊጓዝ አይችልም፡፡ ማስወገድ ሲባል ለኢትዮጵያዊ ቀድሞ የሚታየው መግደል ሊሆን ይችላል፤ ይህም የሚሆነው የብዙዎቻችን አስተዳደግ ከግድያና ከጠበንጃ ጋር ብዙ ቁርኝት ስላለው ይሆናል፤ በጨዋነት ተነጋግሮ በሃሳብ ልዩነት መሸናነፍ ብርቃችን በመሆኑም ሊሆን ይችላል፡፡ በሰለጠነ ዓለም ግን ግድያ ምርጫ ውስጥ ሊገባ የማይገባው ምናልባትም ከገባ በመጨረሻ የሚመጣ ነው፡፡ 

ስለሆነም ጓደኛየ የጠቀሳቸውን የመሰሉ የሀገራችን ጠላቶች ዋናው መለየታቸው እንጂ የአወጋገዳቸው ጉዳይ ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡ እነሱን መምከር፣ መገሰጽ፣ ማስመከርና በዚህ አልመለስ ካሉ ህግን ተከትሎ በሀገር ክህደት ወንጀል በመክሰስ የሚገባቸውን ቅጣት በትክክለኛ የፍርድ ሂደት ማስበየን ነው፡፡ እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች ሆድ እምብርት ባጣ ቁጥር፣ የጥቂት አጋሰሶች ቁሣዊ ፍላጎት ለከት ባጣ ቁጥር ሀገር ልክ እንዳሁኑ በቁሟ እንጦርጦስ መውረድ የለባትም፡፡ እነሱን ሁልጊዜ እያባበሉና እሹሩሩ እያሉ የፈለጉትን እንዲያደርጉ መፍቀድ ደግሞ ከነሱ እንደ አንዱ መሆን አለዚያም በአንድ ወይ በሌላ መንገድ እነሱንና በጠማማ መንገድ ተጉዘው ያገኙትን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ  መፍራት ነው፡፡  ከነሱ እንደ አንዱ ሆነን ወይም ፈርተን ደግሞ እንዲሁ በማስመሰል ብቻ  ይህችን ኢትዮጵያ ከገባችበት ማጥ ማውጣት አንችልም – በጭራሽ፡፡ ድካማችን ሁሉ በዜሮ እየተባዛ ከንቱ እንቀራለን እንጅ ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ዕንቁልልጭ ናቸው፡፡ የምንችለው ሀገራችንን ይበልጥ ቅርቃር ውስጥ መክተትና የነፃነቷን ቀን ማራቅ ነው፤ ሁለት ተሸናፊዎች ደግሞ አንድ የሁሉም ሊሆን የሚችልና የሚገባው ድል ሊያስመዝግቡ አይችሉም (መንግሥትና ከሃዲዎች እየተፈራሩ ቢጓዙ ሁሉም ተሸናፊ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡) ጠላትህን እጉያህ ወትፈህ፣ ከዚያም ባለፈ በዘረኝነት አረንቋ ገብተህም ይሁን የድንቁርና ሰለባ ሆነህ  ለጠላትህ የሽፋን ተኩስ እየሰጠህ፣ “አገር፣አገር” ብትል “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ዓይነት ራስን የማታለል ቂልነት ነው፡፡ በቃ፡፡

እግዚአብሔርን የምለምነው ነገር አለኝ፡፡ እርሱም “ምንም የሚሣንህ ነገር የሌለህ አምላኬ ሆይ! ሀገራቸውንና ወገናቸውን ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ የተንደላቀቀ ሰይጣናዊ ኑሮ የሚኖሩ ብኩን ዜጎች በደም የተገዛ ኑሯቸው ኅሊናቸውን እየኮሰኮሰ የአእምሮ ዕረፍት ሲነሣቸው፣ በሀገር ሸያጭ ገንዘብ የሚበሉት ወፍራም እንጀራ ደም ደም እያለ ወይም እየመረረ አልዋጥ ሲላቸውና ከሆዳቸው ወደ ሕዝባቸው ሲመለሱ በዕድሜ ዘመኔ እንድታሳየኝ እማጸንሃለሁ፡፡ አሜን፡፡”

Filed in: Amharic