>
5:13 pm - Friday April 19, 3495

ጐሠኛ አገዛዝ ብሔራዊ አጀንዳ የለውም/አይኖረውም (ከይኄይስ እውነቱ)

ጐሠኛ አገዛዝ ብሔራዊ አጀንዳ የለውም/አይኖረውም

ከይኄይስ እውነቱ


ሰሞኑን በ‹ሕጋዊነት›፣ በ‹ሕገመንግሥታዊነት›፣ በዐባይ ግድብ ዙሪያ የሚደመጡ ‹ውይይቶችና ክርክሮች›፣ ጽሑፎችና አስተያየቶች ሕገ መንግሥትና ሕገመንግሥታዊነትን÷ ሕግና ሕጋዊነትን ባጠቃላይ በሕግ የበላይነት መተዳደርና ማስተዳደር ባህርይው ባልሆነው አገዛዝ ያውም የጐሠኞች አገዛዝ በሠለጠነበት ሥርዓት ውስጥ ሲነሣ ሲጣል መስማቱ ይገርማልም ያማልም፡፡ የሚገርመው ባለፉት ሦስት ዐሥርታት በኢትዮጵያ የሠለጠነው አገዛዝ በጉልበት ሕግ ሲገዛ የቈየና ያለ፣ ከሕግ የበላይነት ፅንሰ ሃሳብና እሤቶቹ ጋር የማይተዋወቅ ሆኖ ሳለ ሕገመንግሥታዊነትና ሕጋዊነት የወሬ ማጠንጠኛ የመሆኑ ፌዝነት ሲሆን፤ የሚያመው ደግሞ የወያኔ ወራሲ የሆነው ኦሕዴድ የግብር አባቱን አሠረ ፍኖት በመከተል ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ዕረፍት ሳይሰጥ፣ በምድራችን የሠለጠነው ወረርሽኝ ዓለሙን በሚያስጨንቅበት ወቅት ማፈናቀሉ÷ ግድያው÷ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ÷ ግፍና ጭቆናው እንዲሁም ብሔራዊ ታሪክና ቅርስ የማጥፋት ተልእኮው ጎን ለጎን መቀጠሉ ነው፡፡ 

አገዛዙንና አጃቢዎቹን እንዲሁም በተቃራኒ የቆሙ ወገኖችን ወግኖና አቋም ይዞ የሚደረገው የቃላት ውርወራ፣ ጭቅጭቅና ንትርክ አገራዊ ለማስመሰል የሚደረገው ከንቱ ድካም የአገዛዙን ሥልጣን ለማስቀጠልና ሕጋዊ ተቀባይነትን እንዲያገኝ የሚደረግ ቧጠጣ ሲሆን፣ በተቃራኒ የተሰለፉትም ክፍተት ያገኙ መስሎአቸው ወር ተረኛ ለመሆን የተለመደ የሥልጣን ሴሰኝነታቸው ገሃድ የወጣበት ነው፡፡ በሦስተኛነት የሚታየው ደግሞ – በብቸኝነት መረጃ ይዤአለሁ ወይም አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ነኝ ብሎ የሚያስበው – ያለሙያና ዕውቀት ያሻውን የሚዘባርቀው አብዛኛው የመገናኛ ብዙኃን (መደበኛውም ሆነ ኢ-መደበኛው) አውታር ነው፡፡ እነዚህ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብም ሆነ በሕዝብ መዋጮ የሚተዳደሩ ተቋማት በዐባይ ጉዳይ ከአገዛዙ ጎን እንድንሰለፍ ይሰብኩናል፡፡ አገዛዙ ይበድለን፣ የግፍና የጭቈና ቀንበሩንም ያጽናብን፣ ዜጎች ይገደሉ፣ ይታሠሩ፣ ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀሉ፣ በደናቁርት የፀጥታ ኃይሎች ይዋከቡ በዐባይና እነሱ ‹ብሔራዊ› በሚሏቸው አጀንዳዎች ግን ከዚህ ጎሠኛ አገዛዝ ጋር መተባበር እንዳለብን ይወተውቱናል፡፡ ሕዝባችንን በከንቱ ስብከት ያደነቁሩታል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ለአገር የተጨነቁ መስለው የጭብጡን ማዕከል ግን የሳቱት ይመስለኛል፡፡ ዘረኝነትን/ጐሠኛነትን በሕግ መመሪያው ካደረገ አገዛዝ፣ የአብሮነትን እሤቶች ለማጥፋት የአንድን አገር ሕዝብ በቋንቋ በጐሣ ከፋፍሎ አጥር ከበገረ አገዛዝ፣ ለኔ ሁሉም ይገባኛል በሚልና በተረኝነት መንፈስ ለተወሰነ ጐሣ ወይም እምነት ተከታይ ብቻ አድልዎ በማድረግ ለዜጎች እኩል ዕድል የማግኘት መብትን ከሚነፍግ አገዛዝ ወዘተ. ጋር ኅብረት/አንድነት የሚኖረኝ ለምንድን ነው? እንደኔ ከዐባይ ወይም ሌላ ‹ብሔራዊ አጀንዳ› ከሚባል ጉዳይ ይልቅ የዜጎች ነፃነት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ከሁሉም በላይ በሕይወት የመኖር መብት መቅደም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ባጭሩ በሕዝብ የተመሠረተ መንግሥት ሊኖረን ይገባል፡፡ የዚያን ጊዜ ስለ ሕግ የበላይነት ልንነጋገር እንችላለን፡፡ ለዚህ ታላቅ ዓላማ ነው መሥራት ያለብን፣ መተባበርና ባንድነት መቆም የሚገባን፡፡ እምነት የምንጥልበት መንግሥት ሲኖረን ላገርና ለወገን የሚጠቅሙ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መምከር፣ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ የድርሻን መወጣት የብሔራዊ ስሜት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ኃላፊነትና ግዴታም ነው፡፡ 

ዛሬ አገዛዙ ዜጎችን አያውቅም፤ ዜጎችም አገዛዙን አያውቁም፡፡ ጨለማ ከብርሃን ጋር ኅብረት እንደሌለው ሁሉ እኛም እንደዚሁ ሆነናል፡፡ በጉልበት ካልሆነ በጋራ ፍላጎት፣ ፈቃድ፣ መግባባትና ስምምነት የሚፈጸም አገራዊ ጉዳይ የለም፡፡ አገዛዙ ማናቸውም ‹ሥራዎችን› እንደ ሌባ ጨለማን ተገን አድርጎ በድብቅ ነው የሚያከናውነው፡፡ በጨለማ የተሠራ በብርሃን መጋለጡ አይቀርምና ዜጎች ለምን ብለው ሲጠይቁ ድብደባ፣ እንግልትና እሥር ነው የሚጠብቃቸው፡፡ አገዛዙ ያደራጃቸው የፀጥታ ኃይሎች (በአገር መከላከያ ስም የተደራጀው ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ በየመንደሩ/ጎጡ በጐሣ መሠረትነት የተዋቀረው ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ) በአመዛኙ የጨለማ አበጋዞች ሆነዋል፡፡ ታማኝነታቸውም በተረኝነት መንፈስ ለሚንቀሳቀስ የጐሣ ቡድን/‹የፖለቲካ ድርጅት› ነው፡፡ 

እንኳን በአስቸኳይ ጊዜ ሁናቴ በመደበኛውም ጊዜ ሕዝብን ለማንገላታትና ለመደብደብ ‹ሥልጠና› የወሰዱ፣ በ‹ጠላት ወረዳ› የተሠማሩ የፀጥታ ኃይሎች ባለፉት 2 ዓመታት በየክፍለ ሀገራቱ ባጠቃላይ፣ በአዲስ አበባና በድሬደዋ በተለይ ሲፈጽሙ የቈዩትና አሁንም እየፈጸሙ ያሉት ሕገወጥ ተግባራት የዜጎችንና የአገዛዙን አለመተማመን በእጅጉ ካሰፋው መሠረታዊ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በዚህ በዘመነ ወረርሽ ይህን መረን የወጣ ተደጋጋሚ ድርጊት የተመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ወንድሜ ዳንኤል ቢቸግረው እነዚህን ኃይሎች ከመቅጣት ይልቅ መክረን፣ ገሥፀን፣ አስተምረን ሰብአዊ መብቶችን አክብረው ሕግን እንዲያስከብሩ እናደርጋለን ሲል ተደምጧል፡፡ ወንድሜ ጽናቱን ይስጥህ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ኃይሎች ያንተን ዓይነት ባለሙያ ለማዳመጥ ባገር ፍቅር፣ ባገር ታሪክ፣ በሙያ ትምህርትና ዲስፕሊን ታንፀው፣ ላንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቃል ኪዳን ገብተው ወደ ሥራ የተሠማሩ አይደሉም፡፡ ፊደል ቈጥረናል በሚሉ ደናቁርት ዘረኞች የፈጠራ ትርክት በዘረኝነትና በጥላቻ ተኮትኩቶ ያደገው ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ ያልዘሩትን ማጨድ÷ ያልበተኑትን መሰብሰብ ከየት ይመጣል?

የጐሣ አገዛዝ ሥልጣኑን ለማስጠበቅና ለአገዛዙ ሕጋዊ ሽፋን ለማግኘት ካልሆነ በቀር የጋራ የሚለው ብሔራው/አገራዊ አጀንዳ የለውም፡፡ እንደ ነገሥታቱ ዘመን የጋራ አገር፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ እሤቶች አሉን ብሎ አያምንም፡፡ የተፈጥሮ ጥበብና ፈሪሃ እግዚአብሔርም የለም፡፡ ስለዚህ ከሕዝብ ጋር ባንድነት የሚየቆም የሚያስተሳስር ገመድ ያለ አይመስለኝም፡፡ 

በእኔ እምነት ጐሠኞችን ጽንፈኛና ለዘብተኛ እያሉ ማስታመም የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ጐሠኝነት በተለይም የጐሠኛነት ፖለቲካና ይህንኑ መሠረት ያደረገ የአስተዳደር አወቃቀር በየትኛውም መልኩ የአገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት ጠንቅ ነው፡፡ 

እንዲህ ዓይነቱ አገዛዝ የአገርም ሆነ የሕዝብን ሉዐላዊነት ሊያስከብር/ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ የታሪክም፣ የሕግም የሞራልም ብቃት የለውም፡፡ የወያኔ ሰነድ እኮ የዜጎችን ሉዐላዊነት አያውቅም፡፡ በጐሣ መሥፈርት የሸነሸናቸው ግዛቶች ባሻቸው ጊዜ ከኢትዮጵያ አንድነት እንዲወጡ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገዛዝ እንዴት የአገርን ዳር ድንበርና ሉዐላዊነት የማስከበር የሞራል አቋም ይኖረዋል? የዜጎችን በፈለጉት የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብት የገደበና ‹መጤ› እና ‹ነዋሪ/ነባር› ብሎ ከፋፍሎ ሕዝብን በገዛ አገሩ ባይተዋር የሚያደርግ አገዛዝ በየትኛው መመዘኛ ነው ስለ ዐባይ ግድብ ጠላት መጥቶብሀል በሚል ማስፈራሪያ ለሕዝብ ጥሪ ሊያቀርብ የሚችለው? ከመነሻውስ ወያኔና ውላጆቹ ኢሕአዴጋውያን አገዛዞች በዐባይ ጉዳይ ላይ በተለይ፣ በማናቸውም ብሔራዊ ጉዳዮች ባጠቃላይ እምነት የምንጥልባቸው ናቸው ወይ? የግድቡ ሥራ እንዴት ተጀመረ? ለምን ተጀመረ? ግንባታውስ ለምን መተከል ላይ ሆነ? በግድቡ ግንባታ ሂደት ለተፈጸመው ግዙፍ ንቅዘት ተጠያቂው ማነው? ባለሙያዎችንና ዐወቂዎችን ለማማከር ባለመፈለግ ስለ ግድቡ የተደረገውና የሚደረገው ንግግርና ስምምነት ፈር እንዲስት ያደረገው ማነው? አሁንም ያለው አገዛዝ በዝርፊያ ወይም በንቅዘት ወያኔን የሚያስከነዳ እንጂ የሚተናነስ አለመሆኑን እያየን ዐባይ ዐባይ የምንልበት ጊዜ ነው ወይ? ከአገዛዝ ወጥተን መንግሥተ ሕዝብ ስንመሠርት የምንደርስበት ጉዳይ አይደለም ወይ? እንዲህ ዓይነቱ ፕሮጀክት ኃላፊነት የሚሰማው፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ሕዝባዊ መንግሥት የመኖርን ቅድመ ሁኔታ አይጠይቅም ወይ? እባካችሁ ሕዝቡን በስሜት አንንዳው፡፡ አገዛዙ በውስጥም በውጭም በከፍተኛ ኃላፊነት የመደባቸው ባለሥልጣናት በአብዛኛው በተረኛነትና በጐሣ መመዘኛ የተቀመጡ፣ በከባድ ወንጀልም የሚፈለጉ እና ጥቂት የማይባሉት ከፊደል ጋር የተጣሉ አይደሉም ወይ? አገርንና ሕዝብን ወክሎ በዓለም አቀፍ መድረክ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ዝቅተኛው መሥፈርት የሚወክሉትን አገርና ሕዝብ መውደድ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና ከሚገዳደሩ ኃይሎች ጋር እንዴት ሆነን ነው በጋራ የምንቆም?

እንገዛዋለን የሚሉትን ሕዝብ በማን አለብኝነት ሲረግጡት ሲያዋርዱት ከሰው በታች ሲያደርጉት ጠያቂ የሌለባቸው አገዛዞች ሥልጣናቸውና ተቀባይነታቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ ደንታ በማይሰጣቸው ያገር ሉዐላዊነትና ‹ብሔራዊ አጀንዳ› ስም ሆድና ጀርባ ሆነው የቈዩትን ሕዝብ ‹ከዚህ ስንወጣ ምን እንደሚገጥመን› አናውቅም በማለት ድንገተኛና አስደንጋጭ የሚመስል ድራማ በመተወን የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ አገዛዙ እንዲገጥመን ካለፈለገ፣ አሁንም ግዙፍ ጥፋቶችን እየፈጸመ ካልቀጠለ ምንም አይገጥመንም፡፡ 

ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን ይልቅ በእጅጉ የሚያሳስበን ፋሺስታዊ እና የዘር መድሎ አገዛዝ ያቆሙብን ወያኔና ኦነጋዊው ኦሕዴድ እንዲሁም የዘር ፖለቲካ አራማጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ምን ይሁን? እናንተ በሥልጣን ካልቈያችሁ አገር ባለቤት አልባ ትሆናለች? እናንተ ኋላ ቀር በምትሏቸው በነገሥታቱ ዘመን ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ዛሬ በሃያ አንደኛው መቶ ክ/ዘመን የተነሣችሁ ጐሣ አምላኪዎች ይህችን ታላቅ አገር እና ኩሩ ሕዝብ አላዋረዳችሁም? ኋላ ቀር ማነው? ኢትዮጵያ ከወያኔ ኢሕአዴግና ተወራጆቹ አገዛዞች በፊት ነበረች እነሱንም አሳልፋ ትኖራለች፡፡ 

ወገኖቼ እናስተውል!!! ሕዝብ፣ እውነተኛ ምሁራን፣ እውነተኛ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች ስለ ኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ብሔራዊ ምልክቶች፣ እምነቶችና ትውፊቶች፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ከልባቸው አሳስቧቸው የሚጨነቁት፣ የሚጮኹት፣ የሚነጋገሩት፣ የሚወያዩት፣ የሚጽፉት ዕድል ፈንታችን ጽዋ ተርታችን የሚወሰንባት አንድ የጋራ አገር አለችን፤ ከተደማመጥን፣ ከተከባበርን ሁላችን በዜግነት እኩል ዕድል የምናገኝባት፣ ሠርተን የምንከብርባት፣ ለወገን የምንተርፍባት፣ ለትውልድ መልካም ቅርስ የምናስተላልፍባት፣ በዓለም መድረክ ቀና የምንልባትና የኩራት ምንጭ የምትሆን፣ እግዚአብሔርን በመፍራት ግብረገባዊ ሕብረተሰብ የምንገነባባት፣ የሕግ የበላይነት የሚነግሥባት በሕዝብ÷ የሕዝብ÷ ለሕዝብ የሆነ መንግሥት መሥርተን የምንኖርባት አገር ከመፈለግ ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡ ለጐሣ አገዛዝ ግን እነዚህ ቁም ነገሮች ቦታ የላቸውም፡፡ ሲያነሷቸውም ከቃላት የማይዘሉ ተራ ማጭበርበሪያዎች ናቸው፡፡ ሕግ አልባነታቸው እና የጭቈና ተግባራቸው ምስክር ይሆንባቸዋልና፡፡ ስለሆነም መንግሥተ ሕዝብ እስከምናቆም ድረስ የ‹ሕገመንግሥታዊነት›/ሕጋዊነትም ሆነ የዐባይ እሰጣ ገባ ጉዳይ ውኃ ወቀጣ ከመሆን አይዘልም፡፡

Filed in: Amharic