>

ህዝቧን በሙሉ የመብራት ተጠቃሚ ያደረገችው ግብጽ የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት መቃወሟ ኢ-ፍትሀዊ ነው (የአልጀዚራው ተንታኝ  መሀመድ አልአሩሲ)

ህዝቧን በሙሉ የመብራት ተጠቃሚ ያደረገችው ግብጽ የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት መቃወሟ ኢ-ፍትሀዊ ነው –

የአልጀዚራው ተንታኝ  መሀመድ አልአሩሲ
———————————-
የግብጽ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ የመብራት ተጠቃሚ ሆኖ ከ60 ሚሊየን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለመብራት እየኖረ በአባይ ወንዝ ላይ የሚካሄድን ፕሮጀክት መቃወም ኢ-ፍትሀዊ ስለሆነ ያንን ለዓለም ህዝብ ማስረዳትና ድብቁን አጀንዳ ማጋለጥ የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ መሀመድ አልአሩሲ ተናገረ።
የአልጀዚራ አረብኛ ተንታኝ ጋዜጠኛ እና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚሰራጩ ዘገባዎች ላይ የኢትዮጵያን አቋም በመያዝ እውነታውን ለአረቡ ዓለም ለማስታወቅ በስፋት የሚሰራው መሀመድ አልአሩሲ እንደተናገረው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የተፋሰሱን የታችኛው አገራት የማይጎዳ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ግብጾች ይሄንን እውነታ በመካድ የሚያካሂዱትን ዘመቻ መመከት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ሊሆን ይገባዋል።
ከ60 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ድረስ ያለመብራት ይኖራል ያለው ጋዜጠኛ መሀመድ፤ በተቃራኒው ግብፅ ውስጥ ሁሉም ሰው ያማረ ኑሮ ከመብራት ጋር ይኖራል፤ ይህንን እውነታ መቀየር ደግሞ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት ነው ሲል ተናግሯል፡፡ “ግብፅ እያራመደች ያለውን ሃሳብ በሚገባ ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠት፣ ሁሉም ሚዲያ ከመንግስት ጎን በመሆን በአንድ ልብ መስራት ያስፈልገናል፡፡  የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም እንደ ግብፅ ሚዲያዎች ስለአባይ በደንብ መዘገብ ይኖርባቸዋልም ብሏል ጋዜጠኛ መሃመድ፡፡
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሁላችንም በአንድ ልብና በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል” ሲልም አክሏል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በምትታተመው የዓልአለም ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን በመጻፍ ለዓረቡ ዓለም እውነታውን ለማስረዳት ጥረት እያደረገ ያለው ጋዜጠኛ መሀመድ፤ እነዚህ ጽሁፎቹና በቴሌቪዥን የሚሰጣቸው ትንታኔዎች የዓረቡ ዓለም ቀደም ብሎ በግብጽ ሚዲያዎች የተዛባ ዘገባ ይዞት የነበረውን እውነታ ቀስ በቀስ ማስቀየር እንዳስቻሉ ነው የተናገረው። በዚህ ጥረቱ የተደሰቱት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለመሃመድ አልአሩሲ ስልክ በመደወል እንዳመሰገኑትና እንዳበረታቱት አስታውቋል። በታላቁ ህዳሴ ግድብና በአባይ ወንዝ ጉዳይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በስልክ በስፋት መነጋገሩን የገለጸው መሃመድ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ እንዳንተ ያሉ ሀገራቸውን የሚወዱ ሰዎች ያስፈልጓታል” ሲሉ እንዳመሰገኑት ገልጿል።
በአባይ ዙሪያ የሚሰራቸውን ስራዎች እየተከታተሉ መሆናቸውንና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ እንደገለጹለት የተናገረው ጋዜጠኛ መሀመድ፤ “ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ማድረግ እንፈልጋለን፣ በዚህ ሂደት ያንተ ተግባር ትልቅ እገዛ ስላለው በርታ” ማለታቸውንም ገልጿል። “ውልዴቴና እድገቴ በውጭው ዓለም ቢሆንም ኢትዮጵያ በምዕራቡ ዓለም መልካም ገፅታ አልነበራትም፡፡
ከዚህ ቀደም አብዛኛው የአረብ ሀገራት ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ደሃ እንደሆነች ነው ሲዘግቡ የኖሩት፡፡ ይህ ተግባራቸው ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ በደንብ እውነታውን ማስረዳት ችያለሁ፤ በቀጣይም ይሄን ማድረግ ያስፈልጋል” ነው ያለው መሀመድ። “በመጣው ለውጥና ባገኘሁት እድል ተጠቅሜ ስለኢትዮጵያ፣ ስለህዳሴው ግድብና ስለአባይ ወንዝ ያለውን እውነታ በተገቢው መንገድ ለአረቡ ሚዲያ ማሳየት ስለፈለኩ ነው ወደዚህ ተግባር የገባሁት” ያለው ጋዜጠኛው፤ በቀጣይም አቅሙ በፈቀደውና በቻለው መጠን ሁሉ ስለህዳሴው ግድብ ያለውን እውነታ አጉልቶ ለማሳየትና ለማስረዳት ጠንክሮ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። ጋዜጠኛ መሀመድ አልሩሲ ከወር በፊት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የአረብኛ ተንታኞችና ጋዜጠኞች መድረክ ላይ መሳተፉና ሃሳቡን ማንጸባረቁ ይታወሳል፤  (ምንጭ፡-ኢፕድ)
Filed in: Amharic