>

በሀገር ውስጥም በውጭም ለምትገኙ በግል  ለማታውቁኝም ሆነ  ለምታውቁኝም ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፡ (ነአምን ዘለቀ)

በሀገር ውስጥም በውጭም ለምትገኙ በግል  ለማታውቁኝም ሆነ  ለምታውቁኝም ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፡ –

 

ነአምን ዘለቀ፣

ቨርጂኒያ ፣ ዪስ አሜሪካ


አቶ ልደቱ አያሌውን  በሚመለከት በመደበኛም ሆነ በሶሻል ሚዲያ ስሙን እስከዛሬ አንድም ቀን አንስቼ አላውቅም። ዛሬ የሚከተለውን  ለማለት ወሰንኩኝ። አንድ ወዳጄ በየኔታ ቲዩብ ላይ አቶ ልደቱ የሰጠውን አስተያየት በትላንት እለት  ላከልኝና ተመለከትኩት። በንግግሩም እኔንና አቶ አንዳርጋቸውን “በእኔ ..” በማለት ሲወቅስ ሰማሁ። በንግግሩም ላይ “ከጃዋር..” ይላል። በእሱ ስሌት የእኛን ጉድና ምስጢር .. ለህዝብ የማጋለጥ እስትራቴጂ መሆኑ ነው።
በቅድሚያ ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ መንሴ ለሆነኝና አቶ ልደቱ ስማችንን ስላነሳበት ጉዳይ አንዳንድ መረጃዎች ልስጥ። አቶ ልደቱ “አንዳርጋቸው ጽጌና ነአምን ዘለቀ ከሁለት ወር በፊት ጃዋርን አገኙት” ይላል፣ ስማችንን  ከአንዴም ሁለቴ ያነሳል። በእሱ ላይ በሚደረገው ዘመቻ እኔና አንዳርጋቸው እንዳለንበት ይጠቁማል። ሆኖም  ጃዋርን ለማግኘት ለምን ተፈለገ?፣ አላማው ምን ነበር? እነሳሱ ወይንም ጅምሩ እንዴት ነበር የሚሉትን ጥያቄዎች ሊመልስ አላጋነሁትም።  ይህ ማድረግም ፍላጎት ሊኖረው አይችልም።  ለፈለገው ግብ ሰለማይረዳው፣ የግንኙነቱን አውድና ታሪካዊ አመጣጥ ተመልካቹ ህዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ለተፈለገው የፓለቲካ ግብ አይረዳውም። ጃዋርንስ እንዴት አወቁት? ፣ ግንኙነታቸውስ መቼና እንዴት ተጀመረ ብሎ ለሚጠይቅ ህዝብ ፣ ምንም አይነት አውድ(context) ለሌለው አድማጭና ተመልካች ግራ ሊያጋባና አቶ ልደቱ የፈለገው የነገሮች ሂደት የተዛባ  ምስል በተመልካቹ አእምሮ ለመዝራት የሚያሳካ አካሄድ ነው የተጠቀመው።  ሃቁና ሂደቶቹ ግን የሚከተሉት ናቸው ፦
1. እኔ፦  ነአምን ዘለቀ  ጃዋር መሃመድን ሳውቀው 10  (አስር)  አመት ሞልቶታል።  በ2010 ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ በሚል መሪ ርእስ በተዘጋጀ የ3 ቀናት ጉባኤ(Ethiopia and Horn of Africa Conference)  የጉባኤው  ዋና አስተባባሪ ነበርኩ።  በርካታ ምሁራንን፣ የፓለቲካ መሪዎችን፣ እክቲቪስቶች  ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ኤርትራውያን ምሁራንን፣ እንዲሁም ከፈረንጆችም  ምሁራን እና ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት የቀድሞው የአሜሪካ አምባስደር ዴቪድ ሺኒን ያካተተ ፣ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ፣ በVOA ጭምር ሰፊ ሽፋን የተሰጠው ስኬታማ ጉባኤ ነበር።   እኔና አብረውኝ የነበሩ የመድረኩ አዘጋጅ ጓዶቼ ልዩ ልዩ ተናጋሪዎችን መጋበዝ ስንጀምር  በትግሉ የምቀርባቸው ሰዎች ጃዋርን ወጣትና ንቁ ምሁር ብለው  አስተዋወቁኝ ። በአካል ተገናኝተንም ተወያየን።   በጉባኤው ላይ ተገኘቶ ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲያቀርብም ግብዣ አቀረብኩለት። ከህዝብም ጋር ለመጀመሪያ ግዜ በሰፊው የተዋወቀበት መድረክ ያ መድረክ ነበር ለማለት ይቻላል። (ጃዋር በወቅቱ ኢትዮ ትዩብ የተቀረጸውን ቪዲዮ ላይ ስሜን በማንሳት ያቀረበውን ምስጋና ፈልጎ ማየት ይቻላል’’)
2.ግንኙነታችን እኔ  ለመጀመሪያዎችይ 5 አመኣታ በ ስራ አሰፈጻሚነት ያገለገልኩበት (2010-2015)   በኢሳት ቴሌቪዥንና ሬዴዮ (ኢሳት)  ላይ በተደጋጋሚ ጃዋር የቀረበባቸው ፕሮግራሞች ጋር በተያያዘም ይቀጥልና፣ OMN የተባለውን ሚዲያ  ጃዋር ከመሰረተም በኋላ  የጸረ ወያኔ ትግሉን ዋና ኢላማውን እንዳይስት፣ አብሮ ፣ ተባብሮ ለመታገል፣ በሚዲያም ሆነ በሌላም ዘርፎች በልዩ ልዩ ጊዜዎች የተደረጉ ጥረቶችና  ውይይቶችን ያካትታል።
3.እነ አባይ ጸሃይና የወያኔው ስርአት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በሚል በኦሮሞ ህዝብ ላይ ለመጫን በተደረገው ሙከራ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከአምቦ ጀምሮ በልዩ ልዩ አካባቢዎች በተቀጣጠለበት ወቅት በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ (VOA) በጋራ ሆነን ቃለ ምልልስ የሰጠንበት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የአመጽም የእምቢተኝነትም ትግሎች ለጋራ ለማሰባሰብና ለማናበብ  የተደረጉ  በርካታ ጥረቶችና ግኙነቶች ቀጥለው ፣ እንዳንዴም ልዩ ልዩ ግጭቶች ተከስተው እሰከ 2018 ለውጡ እስኪመጣ ድረስ የቀጠሉ ነበሩ።
4.ጃዋር ኦኤሜንን(OMN) ይዞ ኢትዮጵያ ከገባም ከመንግስት ለውጥ በኋላም ጥሩ ሲናገር ይህን እንዲቀጥልበት መልክት በቴክስት በመላክ፣ በማበረታት፣ከሀገር መረጋጋት፣ ለብሄሮች አብሮነትና ሰላም  የማይበጁ ፣ ጽንፈኛ አመለካከቶች ያንጸባረቀ ሲመስለኝ ደግሞ ይህ ሀገራችንና የልዩ ልዩ ማህበረስቦች አብሮነት የማይረዳ መሆኑን እየነገርኩት ፣ ጥያቄዎችን ሳነሳለት፣ ማስታወሻም በየጊዜው ስጽፍለት ቆይቻለሁ።  ሰፊ የፓለቲካ ልዩነት ቢኖረንም፣  በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ስርአተ መንግስት (state) እንዲፈርስ እንደማይፈልግ ፣ ሁሉም ተሸናፊና አውዳሚ ሊሆን ወደሚችል ሁኔታ መገባት እንደሌለበት፣  ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ የተነጋገርንባቸው ርእሰ ጉዳዮች በመሇንቸው፣  ከጃዋር ጋር ለመግባባት ፣ ከሌሎችም ጋር መነጋገር መሞከር እንዳለበት በማመን፣  ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች ወደ ብሄራዊ መግባባት ኣንዲመጡ ካለኝ ጽኑ ፍላጎት አኳያ የተደረጉ ነበሩ። አስከ ዛሬም ድረስ ከጃዋር ጋር ግንኙነት እንዳለኝ ምንም ከህዝብ ደብቄ የማፍርበት ጉዳይ እንዳልሆነ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ከህወአቶች በስተቀር ከጃዋር ጋር ብቻ ሳሆን ከአብዛኞቹ በሀገር ውስጥም በውጭም ከሚገኙ ልዩ ልዩ  የፓለቲካ ሃይሎችና ቡድኖች፣ እንዲሁም ግለሰቦች ጋር ከትግሉ ጋር በተያያዘና ለአለፉት በርካታ አምታት ትውውቅ፣ ቅርርብና፣  ግንኙነቶች እንደነበሩኝም ለማንም መገመት አስቸጋሪ አይሆንም።
የእኔና የጃዋር ግንኙነት መነሻና መድረሻ መረጃዎች ሳይኖሩት  ፣ ራሱን “የመርህ ስው” ሌላው ሰው ደግሞ “መርህ አልባና እወደድ ባይነት” አድርጎ ለመሳልና ህዝብን ለማደናገር አቶ ልደቱ የሄደበትን ርቀት ተጨማሪ ትዝብት ውስጥ የሚከተው ትልቅ ስህተት ማድረጉን ማየት ከቻለና ወደፊቱም ከተማረበት  መልካም ነው። በአደባባይ የሚነገሩ ነገሮች ትልቅ አንድምታና ፋይዳ አላቸውና፣ ፓለቲካም ህዝብና ሀገርን የሚያክሉ ግዙፍ ጉዳዮች ማእከል ነውና፣ እሁን መድረኩን ያጠበቡና ለስልጣን የሚሮጡ ፓለቲከኞች  በተቻለ መጠን ትንሽ ሃቅን፡ ትንሽ ስነምግባርና ሞራል ቢላበሱ፣ ትንሽም የህዝብም ወደ ኋላ ሄዶ የማየት ፣ የማሰብንም ችሎታ ከግምት ውስጥ ቢያስገቡ፣  አቶ ልደቱም ሆነ ሌሎቹ  ዘወትር ቆሜለታለሁ ለሚሉት  “የዴሞክራሲ” የፓለቲካ ባህል መዳበር አንዱ ግብአት በመሆን የሚረዳ ይመስለኛል። ሆኖም የፓለቲካችንም በሽታዎች እንዱም  ይህን መሰሉ የፓለቲካ ስብእና በእጅጉ ጎዶሎ ሆነው መገኘታቸው መሆኑንም ማጤን ይገባል።   የሃቅ (facts) መሰረት የሚጎድላቸው፣ ወይንም የሌላቸው፣  ከላይ ላይ እውነት እንደሆኑ ተደረገው። ተቀነባብረው የሚቀርቡ(በሎጂክ ቋንቋ Red Herring)  ፣ ሆነ ተብሎ ነገሮችና አዛብቶና አጣሞ በማቅረብና ህዝብንም ለማደናገር ያስቻሉ ወይንም ሙከራዎች የተደረጉባቸው፣ ነገር ግን  በቅጡ ሲመረመሩ  እርስ በእርስ የሚጣረሱ፣ መሰረተ ቢስና  የሎጂክ አልባ   ጉዳዮችን በዝርዝር ገብቶ  ማንሳት ይቻላል።
ብሩቱ ተናጋሪ መሆን በራሱ፣ ብቻውን ትልቅ የፓለቲካ ሰው አያደርግም። በዚህ አጋጣሚ ለአቶ ልደቱ ያለኝ ግምት  እምብዛም  አለመሆኑን መሸሸግ አልፈልግም። በየጊዜው በወሰዳቸው የፓለቲካ አቋሞች ምክነያት ብቻ አይደለም። ከሞራል/ከስነምግባር ጋር  የተያያዘ ነው። እንደማንኛው ሰው ስዎችን የምመዝንበት የራሴ ሞራል ኮምፓስ አለኝ። በ2003 በፈረንጆች አቆጣጠር፣ የዛሬ 17 አመት  15 የሀገር ውስጥና በውጭ የነበሩት ዋና ዋና የተቃዋሚ ድርጅቶች በአባልነት የመሰረቱት እነ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስና ዶ/ር መራራ ጉዲና በሊ/መንበርነት የተፈራረቁበት፣ ከምርጫ 97 በኋላም ወደ ፓርላም ሲገቡ ይህን በመቋወም ጥዬ በመውጣት በሌላ መልኩ ትግሉን የቀጠልኩበት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት ባደረጋቸው ስብሰባዎችና ጉባኤዎች  የህብረቱ የቴክኒክና የሌሎች ድጋፎች  ኮሜቴ አስተባባሪ በመሆኔ  በዝግ ስብሰባዎች ላይ በተገኘሁባቸው ቀናት ያሳያቸው ሁኔታዎች፣ በተለይ እንደሱ ከሀገር ቤት የመጣ የህብረቱ አባል ድርጅት ከፍተኛ አመራር ጋር በግል የተነጋገሩትን አምጥቶ 30 የድርጅት መሪዎች  በነበሩበት በዚያ ጉባኤ ግለሰቡን  ለማሳጣት/ለማዋረድ የሄደበት ርቀት ትዝብት  ይጀምራል።  የምርጫ 97 ማግስት ፣ ቅንጅት ውስጥ ችግሮች ሲጀምሩ እኔና የትግል ጓደኞቼ ከአቶ ልደቱ ጋር እስከ አደረግናቸው የስልክ ልውውጦች ድረስ ይቀጥላል።   የወያኔው ጨካኝ አጋዚ የጦር ሃይል  ንጹሃንን  የአዲስ አበባ ዜጎች፣ ሴቶችና ህጻናትን  በጨፈጨፈበት፣  በጥልቅ እልህና ቁጭት ላይ በነበረንበት፣ በዋሽንግተን ዲሲም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን በሳምንታዊ ታላላቅ የተቃውሞ ትይንቶች በማድረግ  በሚገልጹበት  በዚያች ዘግናኝና ቀውጢ ጊዜ፣  በቅንጅት ውስጥ የነበረውን ችግር በምን መልኩ እያጣመመና የራሱን የፓለቲካ ፍላጎት መናጆ ለማድረግ  ያታቀደ እንደነበረ እስከተረዳሁበት ቀን ድረስ መሆኑ ነው። ከዚያ ቀን በኋላ ከአቶ ልደቱ ጋር ተነጋግረንም ፣ ተያይተንም አናውቅም፡፡
በቅርቡ የሚሰጣቸውም አስተያየቶች አልፎ አልፎ ተከታትያለሁ።  በተለይም ከህወሃትና ከሽግግር መንግስት ምስረታ  ጋር በተያያዘ በሚዲያዎች  የቀረበባቸውን  ጥቂቶቹን ተመልክቼ ፣ ይህ ህወሃት የሚባል  የክፋት፣ የጭካኔና፣ የመስሪነት ክምችት የሆነ  የፓለቲካ ሃይል ፍላጎቱ በእኩልነት እንደ አንድ ባለድርሻ ሆኖ ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ህዝብ ጥቅሞች በዴሞክራሲያዊ ስርአት መንቀሳቀስ ሳይሆን፣  እንደቀደሙ አመታት የኢትዮጵያን ሁለተናዊ –ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፣ተቋማዊ- የበላይነት መልሶ ካልተቆጣጠረ ምንም የማይዋጥለት መሆኑ ጸሃይ የሞቀው ሃቅ በሆነበት ነባራዊ ሁኔታ፣ አገርን ለማበጣብጥ፣ ለማተራመስ ከሄደበት ርቀት አኳያ (ይህንኑም ምልከታዬንም ከአንዴም ሁለቴ በሚዲያ ለህዝብ አካፍያለሁ)  አቶ ልደቱ  የሚናገረውን ያውቃል ወይ?፣ መካሪስ እንዴት  አጣ? የህዝብንስ የመመዘን፣ የማሰብ ችሎታ ከግምት ውስጥ የማያስገባው እስከመቼ ነው? ለመሆኑ እሱ ራሱ ባለፈባቸው በልዩ ልዩ የህብረት ፣ የቅንጅት ምስረታዎችና ሂደቶች ብዙዎች እንደታዘቡትና ህዝብም እንደሚያውቀው  በየሚዲያው የሚደጋግመውን “ስጥቶ መቀበል” ተግባራዊ  ለማድረግ ያልቻለ የፓለቲካ ስብእና ያለው ግለሰብ፣ በተቃራኒው ደግሞ ብዙ ትግስት፣ ድርድር፣ የህዝብና የሀገርን ጥቅም ከራስ ጥቅምና ከድርጅት ጥቅሞች በላይ ማስቀደምን ፣ ሌሎችንም ጥንካሬዎች/qualities  የሚጠይቅ የሽግግር መንግስት የመሰለ በርካታ የሀገሪቱን ችግሮች ይብሱኑ ሊያወሳስቡ የሚችል መንግስታዊ መዋቅር መሆን አለበት ብሎ መሞገት፣  ሀገራችን በገጠማት ኮቪድ ከሚባል  የወረርሽን ጠላት ጋር አለም ሁሉ ግብ ግብ በሚያደርግበትና የወደፊቱም በውል በማይታወቅበት ሁኔታ፣ህልውናን የሚፈታተኑ ልዩ ልዩ ስጋቶች በሀገሪቱ ላይ በተጋረጡበት  በአሁኑ ሰአት እንዴትና በምን መልኩ የሽግግር መንግስት መቀመር፣ ተግባራዊና ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ?  የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ  ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ከመብሰልሰል  በዘለለ ስለአቶ ልደቱ የተናገርኩት ፣ የጻፍኩትም አሰተያየት እንድም አልነበረም።
አቶ ልደቱ  የአቶ አንዳርጋቸውንና የኔ ስም  በተደጋጋሚ ባነሳበት የየኔታ ሚዲያ ቃለ ምልልሱ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠ ይመስለኛል። ፍላጎቱንም ማስቀመጡ በራሱ ችግር አይደለም። በአንጻሩ  እኔ  ወደ “ስልጣን” ለመምጣት  አልታገልኩም። 27 አመታት ያለምንም መታከትና በጽናት ዘርፈ ብዙና በሀገር ቤቱ ትግል ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩም  በርካታ የውጭ እንቅስቃሴዎች በማስተባበር የበኩሌን ድርሻ አበርክቻለሁ፣ ያለኝን ሁሉ ስሰጥ እነደቆየሁ ከጅምሩ ላለፉት 27 አመታት በተደረጉ ትግሎች የነበሩ ፣ በህይወት ያሉ ብዙ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት ሃቅ ነው። ዋና ግቡም የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሂደት እንዲጀመር ነበር። ከዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ መስዋእትነትና አበርክቶ  በኋላ(ቤተሰቤን ጨምሮ በብዙ መልኩ የተከፈለ) ከኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ከማንም አካል ምንም የጠየኩት ወሮታ፣ የፈለኩትም አንዳችም ነገር እንደሌለም ብዙዎች ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ። ከፓለቲካው ትግል ቢያንስ የተደራጀ ሰላማዊ ህጋዊ የፓለቲካ ፉክክር ማእከል ያደረግ የፓለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ ለቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 አመራር አባላት ይፋ ያደረኩት  ቀደም ብሎና ከአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና  ከአመራር አባልነት መልቀቄን ለህዝብ ይፋ ከማድረጌ በበርካታ ወራት የቀደመ ውሳኔ ነበር። በዚህ የትግል ሂደት የምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቻችሁ ወገኖቼ   በማርች ወር 2019 በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረኩትንም የሃላፊነት መልቀቂያ  የምታስታውሱ ይመስለኛል።
እንድን ጉዳይ  የአጭር ጊዜ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ያሻውን መናገር በዚህም ሆነ በዚያ ግብረ መልስ  እንደሚኖረው መረዳት አስፈላጊ ነው። ሃቁንም እውነታውን ግልጥልጥ አድርጎ መነጋገርም እንደሚቻል መታወቅ አለበት።  በተለይ የስዎችን ስም ያለአግባብ በአደባባይ በማንሳት፣  የማይክራፎንና  መድረኮችን ሰለተገኙም ሁሉም ያሻውን ውጥቶ መቀባጠር መልካም ምግባር ሊሆን አይችልም። ጥቂቶች የማይባሉ  የመስላቸውን ብቻ በሚናገሩበት፣ ለሀቅም ለእውነትም ፣ ለነገሮችም ትክክልኛ መንስኤና ሂደት ቁብ በማይሰጥበት፣  ሀቁና እውነቱ አይውጣም በሚል ስሌትም ጭምር  የፈለጉትን የፓለቲካ አላማ ለማሳካት ግብ ከማድረግ ባልዘለለ፣ ነገር ግን  ሚዛን በሌላቸው፣ ሆን ተብሎ ተዛብተው በሚቀርቡ “መረጃዎች”  ህዝብንም የሚያደናግሩ፣ የሀገሪቱንም ደህነት የሚፈታተኑ፣ የልዩ ልዩ ማህበረሰብችንም አብሮነት አደጋ ላይ የሚጥሉና ፣ የጣሉ ብዙ አሉባልታዎችና መስረተ ቢስ ሃሰቶች በስፋት በየእለቱ የሚነዙበት ሁኔታ እየሰፋ መምጣቱ ግልጽ ነው። በተለይም ሃላፊነት የማይሰማቸው አንዳንድ  የፓለቲካ ስዎች፣ እንዲሁም ሚዲያ ነን የሚሉ ከራሳቸው ሆድና ከንግድ ትርፋቸው በስቲያ የህዝብና የሀገር እጣ ፈንታ፣ ደህነትና ሰላም  ቁብ የማይሰጣቸው ልዩ ልዩ ህይሎች  ይህን ስራዬ ብለው የተያያዙት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ሊለው ይገባል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሕወሃት አምባገነናዊ አገዛዝ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን፣ መብቶቹን፣ ነጻነቱን፣ አንድነቱን፣ አብሮነቱ ተገፎና ተረግጦ፣ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች እንዲሆን የተደረገበት፣  ከቅኝ ገዢዎች ባልተናነሰ  መልኩ በገዛ ከራሱ በቀልን በሚሉና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻን የቋጠሩ፣ በዘረኝነት በታወሩ፣ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ተደርገው  ብዙ ግፍ የተሰራበትን፣ ሚሊዮኖች ወገኖቻችን የምድር ሲኦል እንዲገፉ  የተደረገበት ሁኔታ ዛሬ  መልሶ  መላልሶ ለኢትዮጵያ ህዝብ መደጋገም ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። ነገር ግን በ11ኛው ሰአት ትግሉን  ለኑሯቸው ሲሉ የተቀላቀሉ፣ እኛም በትግሉ ሂደት ያግዛሉ፣ አስተዋጽኦም ያደርጋሉ በሚል እሳቤ  የረዳናቸውና ያስጠጋናቸው ጨምሮ  ጥቂት የማይባሉ የድል አጥቢያ አርበኞች ፓለቲካውንም ሆነ  በሚዲያ መደረኮች በበዙበት በአሁኑ ወቅት፡  ህወሃት የሚባል  ኢ-ሰበአዊ፣ ጸረ-ህዝብና ጸረ ኢትዮጵያ የጥቂት የትግራይ ልሂቃንን ሁለንተናዊ የበላይነትና  መንግስታዊ ዘረፋ በኢትዮጵያ ፣ በኢትዮጵያዊነትና፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ለ 27 አመታት  አንሰራፍቶ የነበረ እጅግ እስከፊ አገዛዝን ለአፍታም እንኳን ግንባራችንን  ሳናጥፍ  በብዙ መድረኮችና ድርጅቶች የውጭን አለም ሁለተናዊ ትግል ያስተባበርን፣ ብዙ፣ ብዙ ዋጋም  የከፈለን ኢትዮጵያውያን እንኳንስ አቶ ልደቱ ማንም ቢሆን፣ ልድገመውና ማንም ስው የሞራል ልእልና ኖሮት  ሊክደውና  ሊደብቀው ፣ የፓለቲካ ቁማርም  እንዲጫወት የሚፈቀድበት ሃቅና ታሪክ ሊሆን አይችልም። ወደፊት በዝርዝርና በሌላ ሚዲያ ለማቅረብ ይቻላል።
Filed in: Amharic