>
5:09 pm - Friday March 3, 1865

ኢትዮጵያ ከአጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ -  የዋግ ሹም ጎበዜ ንግሥና !!! (ሳሚ ዮሴፍ)

ኢትዮጵያ ከአጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ –  የዋግ ሹም ጎበዜ ንግሥና !!!

ሳሚ ዮሴፍ
አጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ ሦስቱም በየአካባቢያቻው ኃያል የነበሩት ንጉሥ ምኒልክ፣ ዋግሹም ጎበዜ፣ በዝብዝ ካሣ.. እኔ ነኝ የምንገሥ በሚል ሽኩቻ ላይ ነበሩ።
 አጤ ቴዎድሮስ ለአንድነቷ የደከሙላትና የሞቱላት ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ተከፋፍላ የሦስት ነገሥታት ሀገር መሰለች። ሦስቱም በተለያዩ ሦስት አውራጃዎች ቢገኙም በአንድ ባህል፣ በአንድ ብሔራዊ የአማርኛ ቋንቋ፣ በአንድ ኃይማኖት የሚጠቀሙ ለአንዲት ኢትዮጵያ የሚያስቡ ሆነው ሳለ፤ የከፋፈላቸው አንዷ ኢትዮጵያን እኔ ላስተዳድር በሚል ነው።
ምኒልክ “የነጋሲ ልጅ፣ የቴዎድሮስ ወራሽ እኔ ነኝ ብለው”
“ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት” እያሉ እያተሙ ከውጭ ሀገር መሪዎች ጋር በሚላላኩበት ሰዓት ግዛታቸውን እስከ ወሎ አድርሰው ወረይሉን ልክ እንደ ከተማቸው አድርገውታል።
በዝብዝ ካሣም በትግራይና ትግሬ የአውራጃዎቻቸው ባለቤት ሆነው በነፃነት ተቀምጠዋል።
በዚህ ሰዓት የእንግሊዝ ጦር የመቅደላን ምሽግ ለወይዘሮ መስታወት አስረክቦ ወደ ሀገሩ ከመመለሱ በፊት መስታወት ስለገባችላቸው ዋግሹም ጎበዜ ዋናውን መናገሻ ከተማ ጎንደርን እጅ አደረጉ። በሰሜን በወገራ የመጣውን ጥሶ ጎበዜን በጦር ደምስሰው የአጎታቸውን ልጅ ዋግሹም ተፈሪን ሾሙ። በጎጃም ደጃች ተድላ ደስታን አባርረው ለባላምባራስ አዳል ተሰማ (ኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት) እህታቸውን ወይዘሮ ላቀችን ድረው የራስነት ማዕረግ ጨምረው አደላደሉ። የበጌምድሩ ራስ ወልደ ማርያምም አሜን ብለው ስለተገዙላቸው ለመንገሥ የሚጎላቸው ቀብቶ የሚያነግሥ ጳጳስ ብቻ አለመገኘት ብቻ ሆነ። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የነበሩት አቡነ ሰላማ ከሞቱ በኋላ ሌላ ጳጳስ ከግብጽ አልመጣም። ምቹው የማምጫው በር ምጽዋ በግብጾች ተይዟል። ወደዚያ መተላለፊያው የአካለጉዛይና የሐማሴን ግዛት በዙፋን ባላንጣቸው በባለቤታቸው በእቴጌ ድንቅነሽ ወንድም በደጃች ካሣ  ምርጫ ተይዟል። እንደዚሁ ሣይነግሡ በዋግሹምነት ጠቅላላውን ሀገር አስተዳድራለሁ ማለቱ ደግሞ የማይመች ሆነ። በመሆኑም ጳጳስ ባይኖርም ይንገሡ ተብሎ በዕጨጌ ገብረየሱስ እጅ ተቀብተው በ1860 ዓ.ም ነገሡ። ስመ መንግሥታቸው ተክለ ጊዮርጊስ ተባለ። (የነገሡት በ1861 ዓ.ም) ነው የሚሉም አሉ።
ከነገሡ በኋላ ኃይላቸው የበለጠ እየበረታ ስለሄደ በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን በጦርነት የተዳከመው ወሎ በተለይ የወርቂት ወገን ወደ ምኒልክ ቢያደላም የመስታወት ወገን ገብሯል። በዚህም መካከል ምኒልክ እገብራለሁ የሚል ስሜት አይኑራቸው እንጂ ከንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ጋር ደብዳቤ ተላልከዋል። ገጸ በረከትም በአቶ (ኋላ ራስ) ጎበና እጅ ልከዋል። ይህም አላላክ በእሳቸው ዘንድ እንደ ወዳጅነት ሲቆጠር በተክለ ጊዮርጊስ ወገን እንደ መገበር ተቆጥሯል።
ስለዚህ ይነስም ይብዛም እነዚህ የተጠቀሱት ሀገሮች ሲታመኑላቸው አልገዛም ብለው በጣም ያስቸገሯቸው ደጃዝማች በዝብዝ ካሣ ናቸው። ሁለቱም በአጤ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ላይ ሁለቱም በየበኩላቸው ባላቸው ቂም የተነሣ በአጤ ቴዎድሮስ ላይ ሸፍተው ካሣም በትውልድ ሀገራቸው ሹመታቸውን ያጸኑት በመጀመሪያው ወቅት በዋግሹም ጎበዜ ደጋፊነት ነው። በዚህ የስምምነት ወቅት ነው ዋግሹም ጎበዜ የካሣን እህት ወይዘሮ ድንቅነሽን ያገቡት። ካሣ ግን ቀድሞውኑ የእሳቸው ኃይል እየበረታ በሄደበትና ጠቡም ከዋግሹም ጎበዜ ጋር እየተባባሰ በሄደበት ሰዓት የእንግሊዝን ጦር ሲመጣ ተቀብለው እንዳስተናገዱት ሁሉ ሲመለስም አስደሳች አቀባበልና መስተንግዶ ከማድረግ ጋር “ከዋግሹም ጎበዜ የምከላከልበት መሣሪያ ይሰጠኝ” ብለው ጠይቀው በጀኔራል ናፒዬር ፈቃድ 12 ዘመናዊ የተራራ መድፍ፣ 900 የሚሆን የሰናድር ጠበንጃና ሽጉጥ ከብዙ ጥይት ጋር ሰጣቸው። በኋላም አዳዲሱን የጦር መሣሪያ ከወታደሮቻቸው ጋር እያስተማረ የሚያስተዋውቅ አሠልጣኝ ኪርህሃምና ሉዊ ተጨመሩላቸው።
በዚህ አንጻር የተክለ ጊዮርጊስ በአጋጣሚው መጠቀምን ያለማወቅና ቸልተኝነት የደጃች ካሣ ትጋትና ዝግጅት ያስከተለው ጦርነት በግድ ካሣን አሸናፊ ተክለ ጊዮርጊስን ተሸናፊ ሲያደርጋቸው ይታያል። ቢሆንም ደጃች ካሣ የአጤ ተክለ ጊዮርጊስን ጦር ለመመለስ ኃይላቸውን ስለተጠራጠሩ አቡነ አትናቴዎስን ከግብጽ እየመራ ባመጣላቸው በሰምሃር ባላባት በመሐመድ አብደል ራሂም በኩል የግብጹ መሪ ኢስማኤል የጦር መሣሪያ እርዳታ እንዲያደርግላቸው ጠይቀውት የፈረንሳይ መንግሥት ስለተቃወመ መቅረቱን ዱወ የሚባለው ታሪክ ፀሐፊ ያመለጊዮርጊስ እንዲሁም
ተክለ ጊዮርጊስ ካሣ ያስመጧቸውን ጳጳስ አቡነ አትናቴዎስን እንዲልኩላቸው ማስፈራራትም ማባበልም ያለበት ደብዳቤ ልከውላቸው ካሣ እምቢታቸውን ካስታወቁ በኋላ ሁለቱም ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር።
ለማይቀረው ጦርነት እየተዘጋጁ ከተክለ ጊዮርጊስ በኩል “አምቻቸውን (ካሣን) ገድለው ሚስታቸውን (ድንቅነሽን) አስለቃሽ” የሚል የፉከራ ቃል  ከደጃች ካሣ በኩል ደግሞ “አማታቸውን ገድለው እህታቸውን አስለቃሽ” የሚል መልስ እየተወራወሩ ሲዛዛቱ ቆይተው ተክለ ጊዮርጊስ የሠራዊታቸውን ብዛት ለማስረዳትና ነገሩ በዛቻ የሚከናወን መስሏቸው አንድ ስልቻ ጤፍ አስሞልተው “ወታደሬ በዚህ ልክ ነው” ብለው ላኩባቸው ይባላል፤ በአፈ ታሪክ።
ካሣም….
“ከቱርክ ይዋጋል እንኳን ከአንካሳ
የአባ ፈንቅል ልጅ ወሬሳው ካሣ” …ብለው ፎክረው፤
 ወዲያው “ወታደርህ እንደዚህ ቢበዛ በጥይት ቆልቼ ነው የምሰደው” ሲሉ ጤፉን ቆልተው ላኩላቸው ይባላል።
ሁለቱ ባላጋራዎች ሲዘጋጁ ከርመው በ1863 ዓ.ም
ተክለ ጊዮርጊስ ደጃች ካሣን ለማስገበር ባላቻው ዓላማ ከዘቢጥ ተነስተው የተከዜን ወንዝ ተሻግረው ወደ ዓድዋ ጉዞ ጀመሩ። ከስልቻ ጤፍ ጋር ያመሳሰሉት 60,000 የሚሆነው ጅምላ ጦር ጥቂት አሮጌ ጠበንጃ አብዛኛው ጦርና ጋሻ ይዞ ተከትሏቸዋል። በደጃች ካሣ በኩል የተከተላቸው ወታደር ቁጥሩ ከ12,000 እንደማይበልጥ ጸሐፊው ሁሉ አምኖበታል። ነገር ግን ይኸው ቁጥሩ ያነሰው ጦር አንደኛ፤ አምስትና ስድስት ኢንች ውፍረት ያለው ሞርታር 12 መድፍና ብዙ ዘመናዊ የስናድር ጠበንጃ ይዟል።
ሁለተኛ፤ ከጠባዩ ምሽግነት ያለውን ስፍራ ይዞ የጦር ልምድ ባላቸው በነ ኪርክሃምና ሉዊ ሠልጥኖ መሣሪያውን ደግኖ በደንብ ይጠባበቃቸዋል።
ንጉሡ አስቀድመው ወታደረቻውን በዚህ መልኩ አሰለፉት..
1ኛ_ በቀኝ በኩል የላስታ፣ የዋግ፣ ሰባት ቤት ወሎ…በዋግሹም ተፈሪ አዝማችነት
2ኛ_ በግራ በኩል የጎጃም ጦር በልጃቸው በራስ ብሩ አዝማችነት
3ኛ_ በመካከል የዋድላ፣ የደላንታ፣ የጋይንትና የበጌምድር ጦር በልጃቸው በራስ አበራ አዝማችነት
ግንባር ቀደም የሰሜን፣ የጸለምት፣ የወልቃኢት፣ የጸገዴ ጦር በራስ መሸሻ ቴዎድሮስ አዝማችነት አሰልፈው
 በሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ዓድዋ አጠገብ አሰም ከሚባለው ወንዝ (ፈለገ አሰም) ዳርቻ ከነ ጦራቸው ደርሰው ተኩስ ሲከፍቱ፤ የደጃች ካሣ መድፈኞችና ነፍጠኞች ተገን ይዘው በረጋ መንፈስ እያነጣጠሩ እንደ ልብ ጠላቶቻቸውን ያጭዱ ጀመር።
ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ በፈረስ ላይ ሆነው ጦራቸውን
 “ግፋ በለው” እያሉ ወታደሮቻቸውን እያበረታቱ  ለማዋጋት ሲሞክሩ የተቀመጡበት ፈረሳቸው በመድፍ ጥይት ተመትቶ ሲወድቅ እሳቸውም አብረው ወደቁ። ንጉሡም አወዳደቃቸው ክፉኛ ስለነበር ጭንቅላታቸው ላይ ቆሰሉ።
ወታደሮቻቸውም ንጉሡ የሞቱ መስሏቸው ወዲያ እና ወዲህ ሲራወጡ ካሣ ከነ ጦራቸው ከምሽጋቸው ወጥተው ወታደሩን እያባረሩ ሲወጉ ተክለ ጊዮርጊስንም ወዲያው ማረኳቸው።
በመጀመሪያ ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን ማርኮ ለጌታው ለደጃች ካሣ ያቀረባቸው ልጅ አጽብሐ እንደሚባል ጦርነቱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት መፍጀቱ ምርኮ ስብሰባ እስከ ሦስት ቀን መውሰዱን ከዚያ አሸናፊው ደጃች ካሣ የንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን ሰዎች ከልብ እንደማሯቸው ገልጸው “ደም በተፋሰሳችሁበት ሀገር (በትግራይ) አትደሩ የተከዜን ወንዝ ተሻግራችሁ በሰላም ወደ ሀገራችሁ ግቡ፤ እኔም እመጣለሁ” በሚል ዲስኩር ማሰናበታቸውን ዜና መዋዕላቸው ይገልጻል። ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን ግን ከነ ልጆቻቸው አምባ ሰላማ በሚባለው ስፍራ ታስረው ጥቂት ዘመን እንደኖሩ ሞቱ።
ሌላ መረጃ ደግሞ ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን የማረኳቸው
ራስ አሉላ መሆናቸውን ይጠቅሳል። ለምሳሌ “አሉላ አባነጋ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ…
“ንጉሥ ማራኪ ከነ ዘውዱ
የበዝብዝ አሽከር አሉላ ወንዱ
ከነፋስ የፈጠነ
በወንድነቱ የተማመነ
ክንዱ ብርቱ እንደ አንበሳ
በጠላት ሰፈር የሚያገሳ” ….ተብሎ ተጽፎላቸዋል። እንዲሁም ዘውዴ ገ/ስላሴ ጦርነቱ አራት ሰዓት ብቻ እንደፈጀ ገልጸዋል።
የንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ባለቤት የደጃች ካሣ እህት እቴጌ ድንቅነሽ ከባላቸው ሞት በኋላ እሄን ገጠሙ…
ተናግሬ ነበር እኔስ አስቀድሜ
አሁን ምን ልናገር ከሀዘን ላይ ቆሜ
የተሻረው ባሌ ተሿሚው ወንድሜ
ከእንግዲህስ ወዲያ አለምንም ዕድሜ
ሌሎች የገጠሙት …
ላባ በዝብዝ ግብር በቶሎ እንዲደርስ
ጥሬውን ጤፍ ቢልክ ተክለ ጊዮርጊስ
ስልቻው ተፈቶ ትግሬ ላይ ቢፈስ
አባ በዝብዝ ካሣ ቆላው እንደ ገብስ።
የወንዱ አባ ታጠቅ ተቀባይ ሁነኽ
ምነው በሦስት ዓመት ደከመ ኃይልኽ
ባባ በዝብዝ ካሣ ታጥፎ ግንባርኽ
ተሸክመህ ወርደህ አልጋህን ሰጠኽ
በሙሉ ሦስት ዓመት የተሠራው አልጋ
ከሰቆጣ ወርዶ ትግሬ ተዘረጋ።
ለምን ትለኛለህ ሰቆጣ ሰቆጣ
ጥንቱን አይደለም ወይ ለአክሱም የመጣ
ዛሬ ጊዜ አግኝቶ ከላስታ ቢወጣ።
ደጃች በዝብዝ ካሣ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን ካሸነፉ በኋላ ወዲያው በሁለተኛው ቀን የዓድዋ ስላሴን በዓል አከበሩ። ቤተክርስቲያኑንም ቀደም ብለው አሳንጸውት ነበርና ቅዳሴ ቤቱ በዚሁ ቀን ተደረገ። ከዚህ በኋላ ለበዓለ ንግሥ የሚያስፈልገውን ሲያደራጁ ቆይተው በ1864 ዓ.ም ጥር 13 ቀን አክሱም ጽዮን እንደ ደንቡ ሥርዓት ንግሥ ተደርጎ…..
 “ዮሐንስ 4ኛ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው በአቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በመላዋ ኢትዮጵያ ነገሡ።
ምንጭ:- አጤ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት
              የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጤ ቴዎድሮስ እስከ
              ቀዳማዊ ኃይለስላሴ
ክቡር ተክለፃዲቅ መኩሪያ
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic