>

ሰብለና በዛብህ አባይን  ሁለት ጊዜ ሲሻገሩት! (አሌክስ አብርሃም)   

ሰብለና በዛብህ አባይን  ሁለት ጊዜ ሲሻገሩት!

አሌክስ አብርሃም

  በዛብህና ሰብለወንጌል ከጎዣም ጠፍተው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ላፍቶ የሚባለው ሰፈር ባለ አንድ ምኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ተከራይተው ማንንም በሚያስቀና ፍቅር መኖር ጀመሩ ! እግዜር ያሳለፉትን መከራና መገፋት  ቆጥሮ ሊክሳቸው ቆርጦ የተነሳ እስኪመስል ቤታቸው ገነት ሆነ!  ሰብለ የምትሰራው ዶሮ ወጥ ሽታው አምስት ብሎክ አልፈው የሚኖሩትን ነዋሪዎች ሁሉ ምራቅ ያስውጥ ነበር ! በወጣች በገባች ቁጥር ጥቁር የተፈጥሮ ፀጉሯ ጀርባዋ ላይ እንደ ጥቁር አባይ ሲገማሸር  ሚስት ከአዲስ አበባ ፀጉር ከህንድና ዱባይ ገጣጥመው መኖር የሰለቻቸው የብሎኩ ወንዶች ሁሉ በምኞት ሲጠመቁ የአዲስ አበባ ሴቶች ሰብለን ክፉኛ ጠምደው ያዟት !!
   አንድ ቀን እዛው ብሎክ ላይ ከነበዛህ ጎን  የምትኖር  የፊልም ተዋናይት የሰብለን ፀጉር እየነካች ‹‹ስንት ገዛሽው ›› አለቻት …ሰብለ በድንጋጤ ሁለት ጊዜ አማትባ ‹‹ የዲማው ጊዎርጊስ ያሳደገውን የምን ግዥ አመጣሽ?!››   በዚህና በሌሎችም ምክንያች ከሰው ባትቀላቀልም ሰብለ ሶስተኛ ፎቅ ላይ የምትኖር  ሮማን ሃለተወርቅ የምትባል አንዲት ጥሩ ጓደኛ አፍርታ ነበር…! ሮማን ጋዜጠኛ እጮኛ ነበራት … ሊጋቡ ወራት ሲቀራቸው ለአስቸኳይ ስራ ተጠርቶ በሄደበት አስመራ ፊያሜታ ግላይ የምትባል ሴት ጋር ማግጦባት ከዛ በኋላ ወንድና ዜና  አያሳየኝ ብላ ዘግታ የተቀመጠች ሴት ናት ! ከሰብለ ውጭ ሰው አትቀርብም !!
    ይህ በሆነ በዓመቱ ሰብለ ወንድ ልጅ ወለደች ! ያለፈ ታሪካችንን ይመዘግባል ሲሉ ስሙን መዝገቡ አሉት!መዝቡ ከሶስት ዓመት እድሜው ጀምሮ ኮንዶሚኒየም ደረጃ ላይ ተቀምጦ  አላፊ አግዳሚውን የሚመለከት ከልጆች ጋር የማይቀላቀል  ዝምተኛ ልጅ ሆነ! አንድ ቅዳሜ   እንደልማዱተመስጦ አላፊ አግዳሚውን ሲመለከት ሶፋ ተሸክው ደረጃ የሚወጡ ወዛሮች ገፍተውት ከሁለተኛ ፎቅ ተምዘግዝጎ ለአበባ የተቆፈረ መደብ ላይ ዱብ በማለቱ  በተዓምር ተረፈ!  የሰፈር ህፃናት ታዲያ መዝገቡ ዱባለ  የሚል ቅፅል ስም ሰጡት!
መዝገቡ ዱባለ  በተወለደ  በአምስት ዓመቱ ነበር  ሰብለ የበዛብህ ፀባይ እየተቀየረባት የመጣው ! መቸም ወሬ አይደበቅም የቆየውን ያህል ቆይቶ በዛብህ የሚያገለግልበት ቤቴ ክርስቲያን በአጃቢ የምትሄድ ከነስሟ  እቴ ሜቴ ሎሚ ሽታ የምትባል  ቆንጆ ጋር አጉል ነገር መጀመሩን ሰማች ! ሴትዮዋ  አገር ያወቃት አለሌ ናት አሉ ! ባሏን ሜዳ ላይ ጣጥላው  እዛው ጎረቤት ሌላ ወንድ ጋር ጠቅልላ የገባች ጉድ ! ጭራሽ የድፍረቷ የብልግናዋ ብዛት ቪትዝ የምትባል መኪናዋን ይዛ ኮንዶሚኒየሙ  ግቢ ድረስ ከተፍ ትል ጀመር ! በዛብህም ሰብለን እንደሌለች ሁሉ ያች ሎሚ ሽታ ምልክት  ካደረገችለት ነጠላውን አንጠልጥሎ ቁልቁል ደረጃውን ሁለት ሁለቱን እየዘለለ ሲሮጥ ሚዳቋ ያስንቃል !
ሰብለ ታግሳ ታግሳ አልሆን ሲላት ደርባባ የፍቅር ልቧ  ሲኦልን የሚያስንቅ የቁጣ ገሞራ የሚተፋ  ጉድ ጓድ ሆነ!! ሴትዮዋን ይቀርባል የተባለ እዚህ ላንቻ የሚኖር አዳም ረታ የሚባል ደራሲ አፈላልገው ሮማን ጋር ፒያሳ አራዳ ህንፃ ላይ ቀጥረው አገኙት !ሰብለ ጉዳዩን በዝርዝር አጫወተችው !
‹‹ዘመድም ወገንም የለኝ ያለኝ አንድ እሱን ልትነጥቀኝ ነው…ወደርሰዎ መምጣቴም መራበሽ እና ስሞታ ዓመሌ ሁኖ አይደለም ግፉ ቢበዛ እንጅ ››አለቸው በጥሞና ሲሰማት ቆይቶ
‹‹ይገባኛል…ይገባኛል! ጭቁኖች መብታቸውን ለማስከበር የሚነሱት ከወደቁበት የድህነት አዘቅት ለመውጣት እንጂ በሀብታሞቹ ቀንተው አይደለም፡፡ ወይም በረብሻ ሃራራ ስላደጉ አይደለም፡፡”››
‹‹ምናሉኝ ?›› አለች ሰብለ ግራ ገብቷት
‹‹ ወዲህ ነው …አየሽ ሰብለ ይሄ የሕይዎት ህንፀታዊ ገፅታ ነው…›› ብሎ ያልገባትን ብዙ ነገር ነገራት…ሰብለ ምንም አልተያዘላ ! ተስፋ ቆርጣ ተመለሰች!
በታክሲ ሲመለሱ ሮማን ለራሷ በሚመስል ድምጽ ‹‹ጋዜጠኛ ይሁን ዲያቆን  ጠበቃ ይሁን ሃኪም ወንድ በሄደበት የሚለምድ እንስሳ ነው….ሁሉን ይወዳሉ ሁሉንም ያጣሉ  ›› አለች
ሰብለ ብስጭት ብላ ‹‹ምነው የዓባይን በረሃ ሲሻገር ሽፍታ በደፋው ›› አለች !
ጥቁምታ:-
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!
Filed in: Amharic