>
4:38 pm - Friday December 2, 0670

«ጨዋታ ቀይሪ!» [ቅዱስ ሃብት በላቸው -ጋዜጠኛ]

Chewata qeyriእንደሚታወቀው ሰሞኑን ሕወሃቶችና ተላላኪዎቻቸው በአገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን «ስልጠና እንሰጣለን» በማለት በፋይዳ ቢሱ አብዮታዊ ዴሞክራሲያቸው ለማጥመቅ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ይኸው የሕወሃቶች የሰሞኑ ሩጫ በብዙ ተማሪዊች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት እንዳለ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አድምጠናል። በተለይም በርካታ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በዚሁ ስልጠና ተብዬ ላይ እያሰሙት ባለው የተቃውሞ ሃሳብ ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል።
በአማራ ክልል የዳግማዊ ንጉሰ ነገስት አጼ ሚኒሊክን ስም ሲወደስ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚሰጠው ስልጠና ላይ ደግሞ አጼ ምኒልክንና የአማራን ብሔር የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት አድርጎ በመሳል እየቀረበ እንዳለ ከማስረጃ ጋር አይተናል። ትግራይ ላይ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ የፈጠረው እርሱ ይመስል ያለሕወሃት ሕልውና እንደሌለው በተለመደ መልኩ በመስበክ ላይ ይገኛል …. በዚሁ የሕወሃቶች ስልጠና ተብዬ ላይ እራሳቸው አርቅቀው በይምሰል ፓርላማቸው ያፀደቁት ሕገመንግስት አፈር ድሜ እየበላ ሲሆን ዛሬ ደርሶኝ የተመለከትኩት የሙስሊሙን መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የሚመለከተው የዚሁ ስልጠና ሰነድ አግራሞቴን ስለጫረው ነው ዛሬ ብቅ ያልኩት።
ሙሉውን የገጽ 46 ምስል ያያዝኩላችሁ ቢሆንም እስኪ በደንብ ለመተንተን ይመቸን ዘንድ አንድ በአንድ እያነሳን እንሂድበት፤ ….
1) «በአዲስ አበባ ከተማ ያልተፈቀደ የሚልዮኖች ሰልፍ ለዚያውም አገራችን የአፍሪካ መሪዎችን ስብሰባ በምታስተናግድበት ወቅት እስከመጥራት የደረሱና በመንግስት ያልተፈቀደ ሰልፍ እንዳያካሂዱ ሲነገራቸው አሻፈረኝ ያሉ ናቸው። »
በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የተደነገገው አዋጅ ቁጥር 3/1983 ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት እንደሆነ እንጅ በመንግስት ፈቃድ ብቻ የሚደረግ እንዳልሆነ በግልጽ አስቀምጦታል። ደግሞስ የአፍሪካ መሪዎች ፊት ሰልፍ ማድረግ የሚከለከለው ለምንድነው?. ለማንኛውም እነኚሁ የዛሬዎቹ ገዥዎቻችን «ሕጋቸውን ነጥብ ሳንቀይር ተርጉመን ነው ያወጣነው» የሚሉትን አገር ጨምሮ በየደረሱበት በዓለም መሪዎች ፊት የስብሰባ አዳራሽ በር ላይ በሚጠብቋቸው በስደት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚቀርብባቸውን ተቃውሞ አልተመለከቱምን? …. ነው ወይስ «ሌሎቹም የአፍሪካ መሪዎች ልክ እንደኛው በሕዝባቸው ተቃውሞ ናላቸው የዞረ ነውና ዛሬ እንኳን ማረፍ ይገባቸዋል» ከሚል ስሜት ተነሳስተው ይሆን ? …
እስኪ ሕጉን አብረን እንመልከተው፦
«አዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም
ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የወጣ አዋጅ፤
ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው አካል ስላለበት ግዴታ
አንቀጽ 4፣ የማሳወቅ ግዴታ፤
1)ሰላማዊ ሰልፍ ወይንም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የሚያዘጋጀው ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን ወይንም ድርጅት የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ወይንም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከሚካሄድበት ጊዜ ቢያንስ ከ48 ሰዓታት በፊት በፅሁፍ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።
2)የማሳወቂያው ፅሁፍ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊው የፖለቲካ ስብሰባ በከተማ ከሆነ የሚደረገው ለከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት፤ ከከተማ ውጭ ከሆነ ደግሞ ለአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ይሆናል።
ደብዳቤው በፅሁፍ የደረሰው መንግስታዊው አካል ደግሞ ያለበትን ግዴታና ሃላፊነት የሚተነትነው አንቀጽ 6፣ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
አንቀጽ 6፣ የከተማው ወይንም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊነት
1)«ከተማው ወይንም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄ በጽሁፍ ሲቀርብለት ሰላምን ከማስፈን፣ ፀጥታን ከማስጠበቅና የሕዝቡን ዕለታዊ ኑሮ እንዳይሰናከል ከማድረግ አንፃር አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ የማድረግ ሃላፊነት አለበት።
2)ከተማው ወይንም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 ንዑስ ቁጥር 1 የተመለከቱትን ሁኔታዎች በማገናዘብ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ስፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለው ምክኒያቱን በመግለጽ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውስጥ በፅሁፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ሃላፊነት አለበት። ሆኖም የከተማው ወይንም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይንም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምንጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊደረግ አይችልም ማለት አይችልም።»
በዚሁ የስልጠና ሰነድ ላይ ያለአግባብ ለእስር ተዳርገው በስቃይ ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባ ቡልጉም በጎንዮሽ ተወርፈዋል። ነገር ግን አቶ ተማም አምባ-ገነኑ ስርዓት ያለአግባብ ላሰራቸው ለሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች በጥብቅና ከመቆማቸው በተጨማሪ ለገንዘብ ሳይሆን የሕግን ልዕልና ለማስከበር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮህ ላይ የሚገኙ ታላቅ ሰው መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ቢያንስ ቢያንስ እነ አቶ አበበ ወርቄን የመሳሰሉ እውቅ የህግ ባለሙያዎች ስር ዓቱ ባደረሰባቸው ተጽዕኖ አገር ጥለው ሲሰደዱ የምንጽናናባቸው እውነተኛ ጠበቆቻችን በእስር ላይ የሚገኙት ብርቅዬዎቹ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን እንዲሁም አቶ ተማም አባ ቡልጉ ናቸው ማለት ይቻላል። እስካሁን እድሉን አግኝቼ ካየኋቸው የዚሁ ሰነድ ገጾች ለመረዳት እንደቻልኩት አቶ ተማም ከአርቲስት ቴዲ አፍሮ ቀጥሎ በግለሰብ ደረጃ አሽሙር ወይም የጥላቻ ጦር የተሰበቀባቸው ሰው ናቸው።
2) ወደሌላው ሕገ መንግስቱ በጠረባ ወደተጣለበት ጉዳይ ላምራ። አሁንም ከዚሁ ገፅና ያለአግባብ የታሰሩትን የሙስሊሙን መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ከሚመለከተው ክፍል አልወጣም። እንደሚታወቀው መሪውን የመምረጥ መብቱን በሕወሃት አምባገነኖች የተነጠቀው የሙስሊሙ ማሕበረሰብ በወኪልነት የመረጣቸው እነ አቡበከር በግፍ እስር ቤት ከተጣሉ እንደዋዛ 2 ዓመታት ቢቆጠሩም ጉዳያቸው እስካሁን በካንጋሮው ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል። በፍርድ ቤት ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ደግሞ በሕግ የተከለከለ ነው። ይህ ሰነድ ግን በወገንተኝነት ተከሳሾቹን «በእስልምና ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎች፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኞች፣ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሱ … ወዘተ» እያለ በመፈረጅ ተከሳሾቹ በህግ የተደነገገውን መብታቸውን ባደባባይ ከአፈር ሲደባልቀው እናያለን። በርግጥ ካሁን ቀደምም «ጅሃዳዊ ሃረካትን» ሰርተው በቴሌቭናቸው አቅርበውልን የለ? … እንግዲህ ይሄ ሁሉ ከአንዱ ገጽ የተመዘዘ እንከን ነው። ሙሉ ሰነዱን ብንመለከት ደግሞ ስንት ጉድ እናገኝበት ይሆን? … ወጣም ወረደ ሕወሃት በዚሁ በግዴታ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ከሚያገኘው ትርፍ ጉዳቱ እጅግ የበለጠ እንደሚሆን እገምታለሁ። ገበናውን ጠንቅቆ ለማያውቀውና ከፖለቲካ ርቆ ለሚገኘው አንዳንድ ተማሪ ጭምር በግዴታ እርቃኑን እያሳየ ነውና!! … ለነገሩ ፋሲል ደሞዝስ «ጨዋታ ቀይሪ!» አይደል ያለው !

 

Filed in: Amharic