>
2:34 am - Thursday July 7, 2022

የአረብ ሃገሩ ክፉ ስደት! እንደ እቃ እንጣላለን፣ መደጋገፍ ጠፋ! [ነቢዩ ሲራክ]

ገና ረፋዱ ላይ ጸሃዩ ናላን ያዞራል … የቢሮ የቤት ማቀዝቀዣዎች እንኳ ሙቀቱን ተቋቁመው የማብረድ ስራቸውን እንዳይከውኑ የሳውዲ ጅዳ በጋ ሃሩር ጸሃይ ፈተና ሆኖባቸዋል! … በዚህ የቀለጠ የበርሃ ሃሩር ጤነኛ መቋቋም ያልቻለው  ሙቀት በአንዲት ሰውነቷ የደቀቀ እህት ይወርድባታል … ቦታውም ከጅዳ ቆንስል ግቢ የቅርብ ርቀት በሚገኝ የአንድ አረብ ግቢ በር ላይ ነው  …. ስለዛሬው የማለዳ አሳዛኝ አጋጣሚ ላጫውታችሁ…! ያሻችሁ ተከተሉኝ!

የኩባንያ ስራየን በመከዎን ላይ እንዳለሁ እግረ መንገዴን ቀዝቃዛ ውሃና ማኪያቶዋን ለመነቃቂያ ፉት ልበል ለማለት በጅዳ ቆንስል ቅጽር ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው የኮሚኒቲ ካፍቴርያ ብቅ ብየ ያችኑ ማኪያቶ አዘዝኩ … ማኪያቶየን እየቀማመስኩ እንደኔው የካፍቴሪያ ታዋቂ ደንበኞች ከሆኑ ወዳጆቸ ጋር ስንጨዋወት አንድ ሌላው ወዳጃችን ግዙፍ ሰውነቱ በላብ ተጠምቆ ገባ ! … ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ በቆመበት “አንዲት እህት በር ላይ ወድቃለች ፣ ማን ይሆን የሚረዳኝ?” እያለ እኛን ትቶ ሌላ ሰው በአይኑ መፈለግ ያዘ፣ ብዙም ሳይቆይ ወጥቶ ሄደ። የካፍቴሪያው ደንበኞች እኛ ከደቂቃዎች በፊት አድምቀን ስንረባረብበት የነበረውን ያህል ወሬ ወንድማችን ስለሰጠን መረጃ ግድ የሰጠን አንመስልም ለማለት ደረቅ ቢልም ችግሩን ለምደነው ጉዳያችን ብለን ማንሳት ሳይገደን ቀረና ዝም ብለን ተፋጠጥን …

Ethiopian- by Nebyu Sirakብዙም ሳልቆይ ወደ ወደቀችው እህት አመራሁ! ብዙ ኢትዮጵያንውያን ለጉዳይ በሚመላለሱበት የቅርብ ርቀት የወደቀችውን እህት ጠጋ ብለው የሚጠይቃት አይስተዋልም። ይልቁንም እያየን ከንፈር እየመጠጥን ከምናልፈው የነገ ተረኞች ይልቅ አረቦች ቀረብ ብለው “ምነው?  ምን ሆና ነው? ለምን ወደ ቆንስላው አታስጠጓትም? ለምን አንቡላንስ አትጠሩላትም?” እያሉ ወድቃ ባዩዋት የእኛ እህት ሲጨነቁ ተመልክቻለሁ! እኛ ይህን ቀርቦ መጠየቅና መርዳት ባይቻለን ይህች እህት ቢያንስ ቀዝቃዛ ውሃ የምታገኝበትንም ሆነ ማቀዝቀዣ ወዳለው የቆንስሉ መጠለያ የአፍታ እረፍት እንድታገኝ ሙከራ ማድረግ አልቻልንም። እኔና ያ ወዳጀ ሰብሰብ እያሉ ለመጡትና ጉዳዩን በቅርብ ላዩ ለቆንስሉ ባለሟሎች ሳይቀር “ለምን ወደ መጠለያው አናስገባትም?” አልናቸው ባለሟሎቹም  “መጀመሪያ ፍቃድ ማግኘት ያስፈልጋል” ሲሉ መለሱልን ፣ “ታዲያ እናንተው ግቡና እንደ ቀረቤታችሁ የቆንስሉን ሃላፊዎች አስፈቅዱልን” የሚል ጎታጉታችን አቀረብን፣ ሃሳባችን ተቀብለው ሊያስፈቅዱ ወደ ቆንስሉ ሃላፊዎች ቢሮ ሄዱ። ተሎ አስፈቅደው ይመጣሉ ብለን በተስፋ ጠበቅናቸው፣ አልመጡም፣ ለምን ወደ ኃላፊዎች አልደውልም የሚል ሃሳብ መጥቶልኝ ወደ ቆንስል ሸሪፍና ቆንስል ሙንትሃ ደወልኩ፣ ስልኩ ይጠራል ግን አያነሱም!…

እኔና ወዳጀ እኛው ራሳችን መጠየቁ ሳይሻለን አይቀርም በሚል ስንንቀሳቀስ ፈቃድ ሊጠይቁ የላክናቸው ወንድሞች የቁራ መልዕክተኛ ሆነዋልና  በላይኛው በር ገብተው በታችኛው በር ሲወጡ በማያርፈው አይኔ አሳዛኙን ሂደት ታዘብኩ! …ቢገርመኝ በንዴት ተቁለጭልጨ ቀረሁ! ወዳጀን በአይኔ በላይኛው ገብተው በታችኛው ወደ ሾለኩት ወንድሞች አቅጣጫ እያመላከትኩ ራሴን በመነቅነቅ “ይህን ጉድ እያየህ ነው!” አይነት ጠቆምኩት፣  እሱም አይኑን ፈጠጥ ራሱን በአንድ በኩል ሽቅብ ነቅነቅ እያደረገ “እነሱ ድሮውንም እንዲህ ናቸው!” የሚል የሚመስለውን ምላሽ መለሰልኝ…

ወደ ቆንስሉ ሃላፊዎች ቢሮ አቀናሁ፣ ሰው የቢሮውን በር ግጥም አድርጎታል። ቆንስሉን እናነጋግር ስንላቸው “ማን ይሰማናል ብለህ ነው?” የሚል ድፍን ያለ ምላሽ የሰጡኝ አንዳንዶች በቦታው የነበሩ ወገኖች ጉዳያቸውን ሊያስፈጽሙ ወረፋ ይዘው ተመለከትኩ። የሚያውቁትን ጉዳይ ደግሜ አስረድቸ በወረፋው እንዲያስቀድሙኝ ብማጸናቸውም ምን ሲባል አሉኝ፣ ግራ ተጋብቸ ተንደርድሬ የሃላፊዋን ቢሮ ከፍቸ ገባሁ! ሃላፊዋ የሉም፣ ተፈናቃዮችና የመጠለያው ጉዳይ የሚያገባቸውን ወንድም አገኘሁና ጉዳዩን በማስረዳት ይህች እህት ወደ መጠለያው ወይም የጸሃይ ከለላ ወደምታገኝበት የቆንስል ወይም የኮሚኒቲው ግቢ እንድትገባ ይተባበሩን ዘንድ ተማጸንኩት! ከሁሉ በማስቀደም ልጅቱን ለመርዳት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በስብሰባ ላይ  ከነበሩት ከቆንስል ሙንትሃ ፍቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ጉዳይ ፈጻሚው አሰረዱኝ። እኔ፣ ወዳጀና የቀረነው ያገባናል ያልን ይህች ምስኪን የተጣለች እህት ከሙቀት ላይ እስካሁን የቆየችውን ያህል ከአሁን በኋላ ብትቆይ እንደማትተርፍ ተረድተናልና አፋጣኝ እርምጃ ይገኝ ዘንድ ወደ ቆንሰሉ ሃላፊ ወደ ቆንስል ሸሪፍ ከይሩ ቢሮ አመራሁ።

ቆንስሉ ሃላፊ ሞቅ ባለ ሰላምታ ተቀብለውኝ ሰላምታ ተለዋወጥን።  ከምጣቴ አስቀድሜ ስልክ ደውየ ምላሽ ሳጣ ወደ ቢሯቸው ለመምጣት መገደዴን አስረድቸ የወደቀቸውን እህት ጉዳይ ለቆንስል ሸሪፍ አስረዳኋቸው። ቆንስል ሃላፊው አቶ ሸሪፍ ስብሰባ ላይ ስለነበሩ ስልኬን በጊዜው  አለማንሳታቸውን ገልጸውልኝ ከታችኛው ቢሮ “ፈቃድ ላግኝ ” ወዳሉኝ ጉዳይ ፈጻሚ ሰራተኛ ደውለው የወደቀችውን እህት ከወደቀችበት ወደ መጠለያ እንዲያስገቡ ጠየቋቸው።  አሁንም ጉዳይ ፈጻሚው ወንድም ቆንስል ሙንተሃን ለማስፈቀድ እየጠበቋቸው መሆኑን ለሃላፊው ገለጹላቸው። ሃላፊው “መጀመሪያ እያትና የሚረዳ ነገር ካለ ትረዳ ፣ ወደ ግቢ አስገቧት፣ ይህን ለማድረግ ምንም ፈቃድ አያስፈልገውም!” ብለው ትዕዛዝ ሰጥተው ስልኩን ዘጉት፣ እኔንም ስለመረጃው አመስግነውኝ፣ እኔም ለትብብራቸው አመስግኛቸው ተለያየን…

ትዕዛዝ የተቀበሉትን ጉዳይ ፈጻሚ ይዠ ወደ ወደቀችው እህት ስንደርስ ከተጣለችበት ወደ ተሻለው የቆንስሉ ግቢ ፊት ለፊት ካለ አንድ ግቢ ታዛ አምጥተዋት ተመለከትን! በቦታው ቆንስል ሙንትሃ ሰውነቷ በውስጥ ደዌ የረገፈውን አህት ውሃ እያጠጡና እያነጋገሯት ደረስን! ቆየት ብየም ከዚህ ቀደም ቆንስሉ በትብብር ሆስፒታል አስገብቷት እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ። ያም ሆኖ ውሃ በአፏ ላይ ስታደርግ መናገር የጀመረችው እህት ከሆስፒታል አውጥተው እንደጣሏት ተናግራለች ….

ወደ ዝርዝሩ አንገባም … ከሁሉም በላይ “አይ የሰው ነገር፣ አይ ቁንጅናና ረጋፊው የሰው ገላ! ለይላ! አንች እንዲህ ሆንሽ?!” በማለት በአይኑ አንባ ግጥም እያለ የሚያደርገው የጠፋው “ሃገር ቤት አውቃታለሁ!” ያለን ወንድም ለይላ ለ15 ዓመታት ሳውዲ እንደቆየች አጫውቶኛል …ተሰባስበን “አንቡላንስ አዘናል!” ያሉንን የቆንስል ሃላፊና ምስኪኗን እህት ከበናል …ትክዝ ብየ የአረብ ሃገር ስደት መጨረሻ አሰብኩት …መጨረሻችን ይህው መሆኑ ቢያመኝ “የአረቡ ሃገር ክፉ ስደት … ስደት ክፉ ነገር ነው!” አልኩ ለራሴ በውስጤ በማልጎምጎም ዝም አልኩ! … ድንገት “ኤሽ እንደክ?” “ምን አላችሁ?” ሲል ቆንስሉን ከሚጠብቁት የሳውዲ ልዩ ኮማንዶዎች አንዱ ወደየስራችን እንድንሰማራ አዘዘን  …  ወታደሩ አዞናልና ተበታተንን… !

“ያገባናል!” ብላችሁ ለደከማችሁ ፈጣሪ ዋጋውን ይክፈላችሁ! ዝምታን ለመረጣችሁ፣ ለሸሻችሁ፣ አይታችሁ ላላያችሁ፣ ሰምታችሁ “የዝሆን ጀሮ ይስጠን” ላላችሁ ልቦና ይስጣችሁ! ሌላ የምለው የለም!

ብቻ …  እውነት እላችኋለሁ ወደ አረብ ሃገር አትሰደዱ! ክፉው የአረብ ሃገር ስደት መጨረሻው አያምርም፣ ስንቱን ወገኔን በላው?

እስኪ ቸር ያሰማን!

ነቢዩ ሲራክ

Filed in: Amharic