>

ሰውዬው … እና ፈርዖኖችን ያበራየው የኢንቴቤው ደማሚት! (አሰፋ ሃይሉ)

ሰውዬው … እና ፈርዖኖችን ያበራየው የኢንቴቤው ደማሚት!

አሰፋ ሃይሉ
 
“ሰው-ዬው አለ ወይ…? ሰው-ዬው አ……ለ ወይ…?” 
        (- አስቴር አወቀ)
የሰውየው…. ብቸኛ መዳኛው… ብቸኛ መከላከያው – ይሄ ይመስለኛል! ይሄ – የተንኮል ጭንቅላቱን – ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ – ለኢትዮጵያ ጥቅም ያዋለበት – ብቸኛው የኢንቴቤው ፅድቁ! ወይም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጀብዱው! 
 
ይሄ በሀገር ክህደቱ ተወዳዳሪ ያላገኘንለት የህወኀት የቀድሞ መሪ ለገሰ ዜናዊ – የመጨረሻ የተቃና ፎቶው ነው፡፡ ወይም ወደማይመለስበት ዓለም ከተሻገረበት – ከቤልጂየም ብራስልስ ሆስፒታል አልጋው ቀና ብሎ – በአካል የተነሳበት – የመጨረሻ ፎቶው ነው፡፡ በ‹‹ዳጉ›› ስልት… በወሬ ወሬ… እንደሰማሁት፡፡
መቼም የሞተ አይወቀስም በባህላችን፡፡ ወቀሳ በሚመስል አኳኋን መጀመር ግን የግድ ይላል፡፡ መቼም በማስተዛዘን እንድጀምር – ከእኔ – የጠበቀ ካለ – በፊያሜታ ጊላይ አነጋገር – ‹‹አባቴ ይሙት! ጅል ነው!›› – ብዬ አልፈዋለሁ፡፡ አሁን ወደ ጉዳዬ ልመለስ፡፡ የሞተ አይወቀስም፡፡ እሺ ይሁን፡፡ ግን ይሄን ዕድሜ ልኩን ኢትዮጵያ የምትበጣጠስበትን መንገድ ሲቀምርና ሲያሴር የነበረ እርኩስ ሰውዬ – አሁን የማነሳው ለመውቀስ አይደለም፡፡ ከሠራቸው ክፋቶች ሁሉ ውስጥ የሠራትን አንዲት ብቻ ደግ ነገር ለማንሳት ነው ዛሬ የሰውየውን ስም የማነሳው፡፡
ይህ ሰው – ‹‹ሰውዬው›› – በሕይወት ዘመኑ እንደ ሀገር መሪ ‹‹ለ ኢ ት ዮ ጵ ያ ›› የሠራው ውለታ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ ድሮ ‹‹የትጥቅ ትግል›› ብሎ በሰየመው ዘመኑ… ታማኝ ተላላኪዋና የጥፋት ጉዳይ አስፈፃሚዋ ሆኖ… ኢትዮጵያ ዓይኗን የጣለችባቸውን ነገሮች ሁሉ እየተከታተለ… የጣና በለስን የግድብ ፕሮጀክት ሳይቀር በደማሚት እያፈነዳ፣ ኢትዮጵያን እየወጋ፣ ኢትዮጵያውያንን እያደማ.. ብዙውን የወጣትነት ዕድሜውን በበረሃ የጥፋት መስክ እየተመላለሰ – የኖረው – ይህ ሰው – ሰውዬው – በመጨረሻ የሕይወቱ ዘመን – ያቺኑ ፀረ-ኢትዮጵያዋን ግብፅን – በትልቁ ‹‹እምጷ ቀሊጥ!›› – ብሏት ያለፈ መሪ ስለሆነ ብቻ! ለዚህ ስል ብቻ… ስሙን በበጎ ባነሳለት ቅር አይለኝም!! ውሃን ከሥሩ፣ ነገርን ባንፃሩ… ነውና… ከምንጩ ተነስቼ የሆነውን ባጭሩ እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ፡፡
ነገሩ ብዙ ታሪክ አለው፡፡ በይፋ ህጋዊ ቅቡልነት አግኝቶ የሚጀምረው ግን በ1929 ነው፡፡ የዛሬ 90 ዓመት ገደማ፡፡ ግብፅ በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1929 ላይ ከቅኝ ገዢዋ (እና ቀኝ እጇ) እንግሊዝ ጋር ቁጭ ብላ ያለማንም ተቆጪ በአባይ ላይ ሙሉ መብት የሰጣትን የአባይ ስምምነት ተፈራረመች፡፡ ያን በእጇ ካስገባች ከ30 ዓመት በኋላ ደሞ – ሱዳንን ካልያዘች ችግር ውስጥ እንደምትገባ ስለጠረጠረች – በአረባዊ ወንድማማችነት ስም – እና በአባይ ላይ በምትገነባው በአስዋን ግድብ የተነሳ ከሱዳን ጋር የምትወዛገብበትን መሬት እንካ-በእንካ በሆነ ውለታ ሼር ለማድረግ ስለፈለገች – በፊት የአባይን መብት ጠቅልላ የያዘችው ግብፅ ሱዳንን በውሏውስጥ ጨምራ ተፈራረመች፡፡ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1959 ላይ፡፡
እና አሁንም ለራሷ ከፍተኛ የውሃ መጠን፣ ለሱዳን ደሞ የእርሷን ግማሹን የሚያህል ካቃመሰቻት በኋሳ – አሁንም አባይ ወደ ግብጽ ከመድረሱ በፊት ወንዙና የወንዙ ገባሮች በሚያልፉባቸው የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚገነባን ማናቸውንም የአባይ ውሃ ፕሮጀክት – ከፈለገች ለማስቆም፣ ከፈለገች ለማስቀየር፣ ከፈለገችም ለመሻርና ለመከልከል ብቸኛ ድምፅን-በድምፅ-የመሻር-ሥልጣንን በእጇ የጠቀለለች የአካባቢው ልዕለ ኃያል ልዕልት ሆና ቀጠለች!!
በዚህ የቪቶ ፓወሯ የተነሳ – ግብፅ በወንዙ ላይ ሌሎች ሀገሮች ሊኖራቸው የሚገባቸውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብቶች በሞኖፖል ለብቻዋ ተቆጣጥራ – ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆና – ከ1929 እስከ 1959 በብቸኛ ቅምጥል ሰነበተች፣ ከ1959 እስከ 1999 ደግሞ ለሱዳን እያቃመሰች በቅምጥል እንቅልፍ ላይ ለአርባ ዓመታት ሰነበተች!! በ1999 ምን ተከሰተ?
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1999ኝማ ግብፅን ከእንቅልፏ ያባነነ ብቻ ሳይሆን፣ በቁጣና በፍርሃት ቅዠት ያንዘፈዘፈ ነገር በኢንቴቤ (ድሮ ኢዲ አሚን ዳዳ ከፍልስጥዔማውያን ጠላፊዎች ጋር በማበር በእስራኤሎች ላይ በቀለደበት፣ እና ሞሳድ ደግሞ በተራው በኢዲ አሚን ዳዳ ላይ በቀለደበት – በዚያው በኢንቴቤ – በዩጋንዳ ዋና ከተማ)!! በኢንቴቤ ግብፅን አስደንግጦ ያስቀረ ክስተት ተፈፀመ፡፡ በ1999 ግብፅን በኢንቴቤ ያስደነገጣት ኢዲ አሚን ዳዳ አይደለም፡፡ ሞሳድም አይደለም፡፡ ከሞሳድም፣ ከኢዲ አሚንም በሴራ ብቃቱ የከፋው…. ታጋይ ለገሠ ዜናዊ ነው ያስደነገጣት!!
ለተንኮልና ለክፋት ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጭንቅላት እንዳለው መቼም ሁሉም የሚስማማለት ነው፡፡ ታጋይ ለገሰ ዜናዊ፡፡ ግን ያንን ለክፋት 24 ሰዓት ያለመታከት የሚጠቀምበትን ጭንቅላቱን በስሟ ለመጥራት ለሚተናነቀው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ያውለዋል ብሎ ማሰብ – ከአይጥ ጉድጓድ ጥሬ ይገኛል ብሎ እንደመጠበቅ ነበር፡፡ ግን ያልተጠበቀው ሆነ፡፡ አጅሬ ለዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲያሤር ከርሞ – ድንገት ከነሤራውና ተንኮሉ – ግብፅ ላይ ሳይታሰብ ከተፍ አለባት፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
በ1999 በአሜሪካ አነሳሽነት፣ በዎርልድ ባንክ አበዳሪነትና ለጋሽነት የተቋቋመ – የአባይ ኢኒሼቲቭ የሚባል ነበረ፡፡ የኃያሏ አሜሪካ ፍላጎት ነበርና – የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ በዚያ የአባይ መንግሥታት ኢኒሼቲቭ ውስጥ አባል ሆነው ነበር፡፡ ከኤርትራ በቀር፡፡ ወዲ አፎም፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አባ አፄ በጉልበቱ፣ የወዲ ዜናዊ ታላቅ ወንድም፣ አፍሪካዊው ሰሜን ኮሪያ ‹‹ገንገም ስታይል›› – እርሱ ብቻ – አባል አልሆንም – ለኢኒሼቲቩ አልፈርምም – ግን በታዛቢነት እገኛለሁ ብሎ ቀረ፡፡ ከእርሱ በቀር – ሌሎቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ – የናይል ቤሲን ኢኒሼቲቩ አባል ሆኑ፡፡
አባላቱ በጠቅላላ አስር ናቸው፡፡ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ዲአርሲ (ኮንጎ)፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ እና ግብፅ ራሷ፡፡ አስረኛ ደግሞ ያኔ ያልተፈጠረችውና ኋላ የተቀላቀለችው ደቡብ ሱዳን፡፡ አስራ አንደኛ የተወሰኑ ለአባይ የሚገብሩ ጅረቶች ያሏት ኤርትራ በታዛቢነት፡፡ አሜሪካ ኢኒሼቲቩን በዓለም ባንክ ከፍተኛ ልገሳ አስጀመረች፡፡ የወንዙ ልዕልት ግብፅም ድሮ ከእንግሊዝዬ ጋር እንደተጫወተችው ያለ ጨዋታ፣ ዳግም ከአሜሪካዬ ጋር ልትጫወት ወጧ እንዳማረላት ሴት በኢኒሼቲቩ መቀመጫዋን ነሰነሰች፡፡
ግብፅ ገና ከ1959ኙ የአባይ ውል ህልሟ አልነቃችም፡፡ እልም ያለ እንቅልፏን እየለጠጠች ነው፡፡ ግብፅ እንዲያ ያለረብሻ እንቅልፏን በምትለጥጥበት ሰዓት – ይሄ የተረገመ ሰውዬ – ማለቴ የኛው ጉድ ለገሠ ዜናዊ – ኮሽታም ሳያሰማ፣ አንዳችም ኮቴ ሳይተው፣ አሜሪካኖችም ሳይሰሙ፣ ሞሳዶችም ሳያነፈንፉ፣ ኬጂቢም ሳይደርሰው፣ ጀምስ ቦንድም ዝር ሳይል…. በዓለም ተሰምቶ በማይታወቅ እጅግ ምሥጢራዊ አካሄድና ሤራ – ግብፆች ዕድሜ ልካቸውን ሲፎክሩበት የኖሩትን ብቸኛ የአባይ ወንዝ የአንበሳ ድርሻ ተጠቃሚነት መተማመኛ ውል – ድንገት ባንድ ጀንበር – በደማሚት አደባየው፡፡ እኒያን ግብፅን የአባይ ቅኝ ገዢ አድርገው ያቆዩዋትን አረመኔ ውሎች – አረመኔው ለገሠ ዜናዊ – ድንገት በፀሐይ ፊት እንደተጠጋ የበረዶ ግግር – አቀለጠው፡፡ ወይም አተነነው፡፡
በኢንቴቤ የሆነው ይህ ነው፡፡ የክፋቱ ጌታ – የሸሩ ንጉሥ – ወዲ ዜናዊ – ሰውየው – ከአባይ ቤሲን ኢኒሼቲቭ አስሩ አባል ሀገሮች – ስድስቱን አስፈረማቸው፡፡ እና እነዚህ ከተፋሰሱ አብዛኛውን አብላጫ ድምፅ የያዙት ጥቁር አፍሪካውያን ሀገራት – የድሮዎቹን ፈርዖናዊ ውሎች… እንዳልነበር አድርገው ፍርስ፣ እና ፍርስርስ አደረጉት፡፡ የግብፅ ውል በኢንቴቤ ላይ – ተቀዳዶ – ወደ መሬት ተበተነ፡፡ ማለቴ ተበታተነ፡፡ (‹‹አንተ ሠይጣን! በእየሱስ ስም…! ተነስና መሬት ውደቅ! ግን… አቧራ እንዳይነካህ!!›› የሚለው ቀልድ ትዝ አለኝ!) የግብፆችም ውል መሬት ወደቀ፡፡ አቧራ ይንካው አይንካው ግን የሚያውቀው – ይሄ እርጉም ሃዋርያው (ሰውየው!) ብቻ ነው!!
‹‹አንበጣ ብትቆጣ፣ እግሯን ጥላ ትወጣ!›› እንደሚባለው – ድንገተኛው ደማሚት እጅጉን ያስቆጣት፣ እና ያስደነበራት ግብፅ – በአባይ ላይ እኩል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አጥብቀው በሚሹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት መከበቧን ስታውቀው – በ2010 ላይ – እግሯን ጥላ ወጣች!! ታላቁን እፍርት ፈፀመች!! ከዚህ ኢኒሼቲቭ ወጥቼበታለሁ በማለት! እና… ግብፅ ቡቲካ! ብለው ጀመሩ የቀሩት!! ደግሞ የሚገርምህ – የ6ቱ ፈራሚዎች ቁርጥ ያለ አቋም፡- ‹‹ግብፅ ይሄ ከሠሃራ በታች በሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን ላይ እንደ ቅኝ ገዢ ልሁን የምትለውን ነገር ታቁምልን! አሁን ቅኝ ገዢ የለም! ሁላችንም እኩል ነን! (እና ባጭሩ… ቂን ቂን አትበይ…!)›› ነበረ ያሏት፡፡
እና – እላለሁ አንዳንዴ ሳቄም እየመጣ – በላዔ ሰብን በአንዲቷ ደግነቱ ብቻ በፍርድ ሚዛኑ ላይ ወላዲተ አምላክ እፍ እንዳለችለትና የእዝጌሩን ፍርድ በትንፋሿ እንዳቃናችለት ሁሉ – የኛው በላዔ ሰብም – ማለቴ የክፋቱ ጌታ አቦይ ለገሠ ዜናዊም – በኢትዮጵያ ላይ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለፈፀማቸው መቶ ሚሊዮን ወንጀሎች፣ ሴራዎችና ተንኮሎች – በሠማይ ቤት ችሎት ቀርቦ – በእነ ሚካኤል፣ ኡራኤል፣ ሩፋኤል ጥፋቱ እየተነበበ… አቡነ አረጋዊ ጥፋቱን እያስተባበሉ… ፀጥ እረጭ ባለ የሰማይ ቤት ችሎት… ክስ ቢሰማበት – ምናልባት… የሰውየው…. ብቸኛ መዳኛው… ብቸኛ መከላከያው – ይሄ ይመስለኛል! ይሄ – የተንኮል ጭንቅላቱን – ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ – ለኢትዮጵያ ጥቅም ያዋለበት – ብቸኛው የኢንቴቤው ፅድቁ! ወይም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጀብዱው!
(ከዚህ በተረፈ… ይሄ ህዳሴ… ህዳሴ… እያሉ የሚነበነበው… አባይን የደፈረ ጀግና ምናምን እየተባለ የሚደሰኮረው… የሚቀለመደው… እና ሌላ ሌላውም ጦስና ጥምቡሳስ ሁሉ… – በእኔ አስተያየት – ያኔ በኢንቴቤ ከሆነው – የአባይን አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን – የታሪክን አቅጣጫ ከቀየረው ክስተት ጋር ሲነፃፀር – ይሄ ይሄ… በቃ ወሬው ይበዛል! ገለባ ነው! የታከተ ፕሮፓጋንዳ ነው! ቡጋንዳ! ወይም ቡዳ! ነው፡፡)
በነገራችን ላይ… ግብፅ – ጭልጥ ያለ የቅኝ ግዛት እንቅልፏን ተኝታ – ሳታስበው በኢትዮጵያ የተወሰደባትን የአባይ ብኩርና ለማስመለስ – ከእንቅልፏ በባነነችባቸው በባለፉት ጥቂት ዓመታት – እጅግ ታላቅ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ – እና እጅግ ግዙፍ የዲፕሎማሲ ጦር ሠራዊት በመገንባት – ሠለቸኝ ደከመኝ ሳትል – በእነዚህ ሊቀ ሠይጣን ለገሠ ባስፈረማቸው ሀገሮች – እጅግ የበዙ ምልልሶችን፣ ስምምነቶችን፣ ልምምጦችን፣ የጋራ ኢኒሼቲቮችን፣ የእርዳታ ስምምነቶችን፣ ወዳጅነቶችን፣ እና ሌሎችም ሚሊየን ትናንሽና ትላልቅ ጉድኝቶችን አጠናክራለች!!! ይህንኑ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዋን ሥራዬ ብሎ ለተከታተለ ባለሺህ ፈርጆች ሠይፍ ይዛ የተቀየረባትን ታሪክ መልሳ ለመቀየር እየማሰነች እንደሆነ በሚገባ ይረዳል፡፡
ሰሞኑን ከወደ ኢትዮጵያ ብዙ ነገር እየሰማን ነው፡፡ ብዙ ድንፋታ ይሰማል፡፡ ብዙ ፉከራ ይደመጣል፡፡ ብዙ ያላቻ ጋብቻ እንካ ሠላንቲያዎች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ በበኩሌ ግብጽን እንዲህ ብዬ መጠየቅ ያምረኛል…፡-
‹‹ንስር ሆይ፣ ቱርኬ ሆይ፣
የፈሰሰ ውሃ፣ ይታፈሳል ወይ..?››፡፡
ለእኛው ሰውዬ (ለቅቤው!) ደግሞ… እንዲህ ማለት ያምረኛል…፡-
 ‹‹አንተ ግብፅ ላይ፣ አንተ ካይሮ ላይ፣
‹‹ወላሂ ለአዚም! ያልከው መሪ ሆይ…፣
ድንፋታው ቀርቶብህ፣ ወዳጅነትህን፣ ከያገራቱ ጋር፣ አታጠብቅም ወይ?
ወዲ አፎምንስ..፣ ከታዛቢ ወንበር፣ ባባልነት ስበህ፣ አታስፈርምም ወይ?››
ስለ ውዲቱ ሀገሬ ኢትዮጵያ – የሚጠብቃት አምላኳ በጥበቡ ይጠብቃት ዘንድ፡-
‹‹ቸሩ ሆይ.. ቸሩ ሆይ ናና…!
አማኑኤል… አማኑኤል ናና..!
የእስራኤል መና… ቸሩ ሆይ ናና!!››
እያልኩ – ከሚሊዮኖች እንደ አንዱ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ወገን – ተማፅኖዬን ሁሉ ለማያልቅበት ፈጣሪ – እያሰማሁ – ለዛሬ ተሰናበትኩ!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!  
Filed in: Amharic