>
5:18 pm - Friday June 15, 7945

ወሸባና ቀሣ - ከኮሮና የተነሣ!!! (አለማየሁ ማሞ)

ወሸባና ቀሣ – ከኮሮና የተነሣ!!!

አለማየሁ ማሞ

ዐርፈህ ተቀመጥ፤ በቸልታህ ሌሎች እንዲሞቱ ማድረግ ነፍሰ ገዳይነት ነው!
ቃላቱ ቀድሞም መዝገባችን ውስጥ ነበሩ። ግን አላስፈለጉንም። አሁን  ኮሮናን ተከትለው ብቅ ብለዋልና ጥቂት ማፍታታት ፈለግሁኝ። ጊዜውን ለመዋጀት ሁለት ቃላት ከካዝናችን ወጥተዋል። ወሸባ እና ቀሳ ይባላሉ።  ደስታ ተ/ወልድና የሐበሻ መዝገበ ቃላት አንጀቴን ስላራሱኝ ለጊዜው የከሳቴ ብርሃን ተሰማና የብርሃኑ ዘርጋውን መዝገበ ቃላት መጠቀም አላስፈለገኝም።
ወሸባ የሚለውን ደስታ ተ/ወልድ ወሸበ፣ ከሰው ተለየ፣ በአንድ ቤት ተዘጋ፣ ተቀምጦ ታከመ፣ ታገመ ሲሉ በገጽ 467 ሲያብራሩ ውሸባ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ደግሞ አያይዘው የመታከም ሥራ፣ በአንድ ሥፍራ ተቀምጦ መድኃኒት ማድረግ፣ መታከም፣ አፍንጫንና ጆሮ በጥጥ መወተፍ፣ ገላን ሁሉ መሸፈን ፣ በምግብም መለየት ብለውታል። ሐበሻ መዘገበ ቃላት በፊናው ውሸባ መታጠን፣ መታጠብ፣ በተገለለ ሥፍራ ተቀምጦ መድኃኒት ማድረግ፣ ወሸባ ገባ… በአንድ ቤት ተዘጋ፣ ከሰው ተለየ፣ ሕክምና አደረገ ይላል።
ይኸው የሐበሻ መዝገበ ቃላት፦ ቀሳን ሲፈታው ቀሳ ወጣ። ተጋቦት በሽታ ስላለበት..ለብቻው ተለየ፣ ተገለለ ይለዋል። ደስታ ተ.ወልድ ደግሞ ቀሳ ብቻ..ብቻነት፣ ልዩነት፣ ፈረንጆች ኳራንቲን ከሚሉት ጋር ይስማማል። ቀሳ ወጣ፣ ከቤት ወደ ዱር ሄደ። በደን ተቀመጠ። ተኛ። ታመመ። ከቤተሰብ ተለየ። የሚጋባ በሽታ ተስቦ ስለያዘው… እያሉ ይተነትኑታል።
ወሸባን ራስን ማግለል ቀሳን ደግሞ ለይቶ ማቆየት ለሚሉት ዘመነኛ ርምጃዎች የሚመጥኑ ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ። ምክንያቱም ወሸባ አካባቢያዊ ሲሆን ቀሳ ግን ርቀትን (ለምሳሌ ደን እያለ) ያመላክታል። እናም ተጠርጣሪው ወይም ታማሚው የሚወሰደው ራቅ ተደርጎ ነው። በዚህ ላይ ገባ እና ወጣ አሉ። ወሸባ ገባ ሲል ወደ ጓዳው መግባቱን ሲያስታውሰን ቀሳ ወጣ ግን ከቤቱ ወጥቶ መሄዱን ያስገነዝበናል።
እናም ከዛሬ ጀምሮ የኔ መረዳት እንዲህ ነው። ነገሩን በአገራችንና በዲያስፖራው ዐውድ ላብራራው። በየብስም ይሁን በአየር ኢትዮጵያ ስትገባ ትኩሳትህ ይለካል። ሰላም ከሆንክ ከተዘጋጁት መወሸቢያ ሥፍራዎች ወደ አንዱ ለምሳሌ ሒልተን ሆቴል ትገባለህ። ወሸባ ገባ ማለት ይሄ ነው። አሥራ አራት ቀን ቆይተህ ምልክቶቹ ካልታዩብህ ተወሻቢ ከሚለው ዝርዝር ስምህ ተፍቆ በምክር ትለቀቅና ፌጦ ፍለጋ ትሰማራለህ፤ ገና ስትገባ ወይም በነዚያ ሁለት ሳምንቶች ውስጥ ምልክቶቹ ከታዩብህ ግን ከቆምክበት ወይም ካረፍክበት ተለይተህ ከተዘጋጁት ሥፍራዎች ወደ አንዱ ተወስደህ ቀሳ ትወጣለህ። እዚያ ትታገማለህ፤ በዘመነኛው ቋንቋ ትታከማለህ።
እንዲህ አሰላሰልኩት። የሚስማማ ብቻ ይስማማበት። የተለየ አሳብ ወይም ያቃል ፍቺ ቢኖርህ አካፍለን። የግድ በኔ አሰላስሎ መስማማት ስለሌለብህ ኮሮናን ለመከላከልም ይሁን እኔን ላለመደገፍ ለሁለቱም ርቀት ጠብቅ። ግን የምለይህ በምርቃት ነው። ወሸባ ከመግባትም ይሁን ቀሳ ከመውጣት ሁሉን ቻዩ ይጠብቅህ!
ጥቁር ሞት ….
 
ይህንን “ኮረና” የተሰኘ ወረርሽኝ ሽሽት በቤቴ ተቀምጬአለሁ። እጅግ ሰላም ነው። አዎን የበዛ ሰላም ነው። እየጻፍኩ ብቻ ሳይሆን እያነበብኩም ነበርና እንዲህ ሆነ። ማርቲን ሉተር “አደገኛ ወረርሽኝ ከተከሰተበት አካባቢ ልንሸሽ ይገባልን?” በሚለው  አሳብ ላይ ለሬቨረንድ ዶ/ር ጆአን ሔስ የጻፈውን ደብዳቤ በጥሞና አነበብኩ።
ያኔ ሸሽቶ ማምለጥ ይቻል ነበር። አሁን ግን የትም ብትሄድ ተይዘህ አንድም ወሸባ (ኳራንቲን) ትገባለህ አልያም ቀሳ (ለይቶ ማቆያ) ትወጣለሁ። ስለዚህ የሽሽቱን ትርክት ዘልየዋለሁ። ነገር ግን  በደረስንበት በዚህ አስጨናቂ ዘመን ቀሳፊውን ቫይረስ የምናንበረክክበትን አቅጣጫ በማሳየት ሊያግዙን የሚችሉ በርካታ ምክሮችን አንሥቷል።
አዎን  እርሱም በዘመኑ ወረርሽኝን ለመቋቋም ይታገል ነበር።  ጥቁር ሞት በሚለው ቅጽል ስሙ በሚታወቀው ከ1346 እስከ 1353 ቆይቷል በሚባለውና ከአውሮፓ ተነሥቶ  በንግድ መርከቦች አጓጓዥነትና በአይጦች ተሸካሚነት አፍሪካና እስያን ባዳረሰው በዚሁ ወረርሽኝ  የሟቾች ቁጥር ከ75 – 200 ሚሊዮን ተገምቷል።  አንዳልኩት ሉተር ለእኛ ዘመን የሚሆኑ በርካታ ነጥቦችን እንዳነሣ አስተዋልኩ። እናም ምክሮቹን ለእናንተ ለአንባቢዎቼ ላደርስ አሰብኩ። አሳታሚውን በማስፈቀድ ተረጎምኩት።
አጓጉል እምነቶችና የቫይረሱ ሠራተኞች
 እጅግ ችኩሎችና ራሳቸውን መግዛት የማይችሉ ሞልተዋል።  ሁሉን ቸል ብለው እግዚአብሔርን በሚፈታተን እና ቸነፈሩንም በሚያባባስ ሁኔታ ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ። በበሽታው የተጠቁ ሰዎችንም ይሁን አካባቢዎችን ያለቅጥ ይዳፈራሉ። የመድኃኒትን ጠቀሜታ ያጣጥላሉ፤ በጥቅሉ ችግሩን አቅልለው በማየት የማንንም እገዛ እንደማይፈልጉ ሆነው ይሯሯጣሉ።
ደግሞም ይህ የእግዚአብሔር ቅጣት ነው፡ እናም ሊያድነን ከፈለገ መድኃኒትም ይሁን ጥንቃቄ ሳያስፈልግ እንዲሁ ሊያደርገው ይችላል ይላሉ። እውቀቱን የማይጠቀም፤ ሲያስፈልግም ሌላውን ላለመጉዳት መድኃኒት የማይወስድና ሥጋውን የሚበድል ሰው በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዳጠፋ ነፍሰ ገዳይ ነው።
የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ የራሳቸውን ጤንነት በመጠበቅ ከወረርሽኙ መዳንና ለሌሎችም መሰንበት ምክንያት መሆን ሲችሉ በቸልታና ስንፍና ለሌሎች መበከልና መመረዝ ምክንያት የሚሆኑ ሰዎች ተግባር እጅግ አሳፋሪ ነው። ደግሞም ስለ ብዙዎች ሞት በአግዚአብሔር ፊት ከመጠየቅ የማያመልጡ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው።
አንዳንዶችማ በጣም ከመክፋታቸው የተነሣ ከቤት ቤት ከመንደር መንደር ሲንቀዠቀዡ በሽታው በሚገባ አልተዳረሰም ብለው ያዘኑ ይመስላሉ ሲባል ሰምቻለሁ። ያ ደግሞ ለእነርሱ   ቀልድ ነው። እጅግ ጠማማና ክፉ ሰዎች መኖራቸውን ማመን አለብን። ዲያብሎስ መቼውንም ቢሆን ሥራ አይፈታም። እነርሱን በተመለከተ አስተያየቴ እንዲህ ነው። ከተያዙ መጀመሪያ ዳኛ ዘንድ ቀርበው ይፈረድባቸው፤ ዳኛው በተራው ለሰቃዩ ለማስተር ጃክ ይስጣቸው። ነፍሰ ገዳዮች ናቸውና። አዎን እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች እንጂ ማን ብለን ልንጠራቸው እንችላለን? አንዳንዴ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጋር ከመኖር ከዱር አራዊት ጋር መኖር ይሻላል።
የታማሚው ኃላፊነት
በተለይም ደግሞ በሽታው አግኝቶት ያገገመ ሰው ከሌሎች መራቅ አለበት፣ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር እንዲመጡበትም መፍቀድ የለበትም። ልክ እርሱ በተያዘበት ጊዜ ሌሎች እንዳገዙት ሁሉ   እሱም በተራው ከተሻለው በኋላ ሌሎችን ማገዝ አለበት፤ ያም ሌሎችን ለአደጋና ሞት እንዳይዳርግ በመጠንቀቅ ነው። ለዚህ ነው ጠቢቡ  “የትዕቢተኞች ልብ መጨረሻው አያምርም፤ አደጋን የሚወድም በዚያ ይጠፋል” ያለው (ሲራ. 3:26)።
ታምሞ ያገገመውም ይሁን ሌሎች የከተማይቱ ሰዎች ባልንጀሮቻቸው በሚፈልጉት ረገድ በማገዝ የእምነታቸውን ብርታት ቢያሳዩ በሰላሙ ጊዜ ደግሞ ቢጠነቀቁ  ይልቁንም ሁሉ በተቻለው ንክኪን ቢያስወግዱ በርግጥም የሟቾች ቁጥር ይቀንሳል።  ነገር ግን ጥቂቶች ያለቅጥ ፈርተው ባልንጀሮቻቸውን ጥለው ከሸሹ  ሌሎች ደግሞ በቂልነት ቅድመ ማስጠንቀቂያውን ቸል ካሉና የበሽታውን ስርጭት ካፋጠኑ ብዙዎች ያልቃሉ። ዲያብሎስ ቀን ይወጣለታል፤  ያኔ ማንም ከክፉው አያመልጥም፤ የሸሸውን ያሳድደዋል፤ የቀረውን ይጨመድደዋል። በሁለቱም አካሄድ ነገሩ እግዚአብሔርንና ሰዎችን የሚያሳዝን ነው። አዎን አድራጎቱ እግዚአብሔርን መፈታተን ሰዎችንም ማስጨነቅ ነው። የአንዳንዶች ድርጊት ደግሞ ከዚህም የከፋ ነው። ያንን ማድረጋቸው ያድናቸው ይመስል በሽታው እንዳለባቸው እያወቁ ለማንም ሳይነግሩ በሰዎች መካከል በመዘዋወር ስርጭቱን ያፋጥኑታል። በዚሁ ክፋታቸው በየመንገዱ ይዞራሉ፤ ወደ ሌሎች ቤት ይገባሉ። ልጆችና የቤት ሠራተኞችን በመበከል ራሳቸውን ሊያነጹ ይሞክራሉ። ይህ ያለምንም ጥርጥር የራሱ የሰይጣን ሥራ ነው ብዬ አምናለሁ። በእኩይ ሥራቸው የሚተባበራቸው ክፋታቸውንም የሚያፋጥንላቸው እርሱ ነው።
ምክር፦ ፩ ወረርሽኙን ለመግታት በሽተኛ የለ፤ አስታማሚ የለ፤ ታዛቢ የለ… የሁሉ ትብብር ያሻል::
Filed in: Amharic