>

ወሸባና ቀስ ከኮረና የተነሳ....!!!! (ክፍል ሁለት - አለማየሁ ማሞ)

ወሸባና ቀስ ከኮረና የተነሳ….!!!!

ክፍል ሁለት
 
አለማየሁ ማሞ
የሁላችን ሸክም ….!!!!
በዚህ የበሽታ ቸነፈር ወቅት እንዲሁ ልናደርግ ይገባል። በብሉይ ኪዳን በተለይም ዘሌዋውያን 13–14 ላይ ለምፃሞች ከሕዝቡ እንዲወጡና ሌሎችን እንዳይበክሉም ከከተማ ውጭ እንዲኖሩ ያዘዘው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ በበሽታው የተያዘ ሁሉ ከሌሎች መገለል አልያም አፋጣኝ ሕክምናና መድኃኒት ወደሚያገኝበት ሥፍራ መወሰድ አለበት።
ግን እንዲህ ዓይነቱን ሰው ልንረዳው እንጂ ጥለነው ልንሄድ አይገባም።  ይህ ደግሞ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡንም የሚጠቅም ተግባር ነው። እንዴት ቢባል ታማሚው እርዳታ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ከሚል ይልቅ ባለበት ሆኖ እንክብካቤ ካገኘ ሌሎችን የመበከሉ አጋጣሚ እጅግ ጠባብ ነው።
ችግሮች ሲፈጠሩና እልቂት ሲከሰት እናግዛቸውና አብረናቸው እንቆም ዘንድ ለሌሎች ዕዳ አለብን።  የጎረቤቴ መኖሪያ ቢቃጠል ሮጬ ሄጄ በማጥፋት እንዳግዛቸው ፍቅር ግድ ይለኛል። ግን በቂ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ካሉ ወደ ቤቴ መሄድም ይሁን መቆየት መብቴ ነው። እንዲሁም ወደ ውኃ ወይም ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ በምችለው ሁሉ ላወጣው እሞክራለሁ እንጂ ፌቴን አላዞርም፤ ግን ሌሎች ያንን እያደረጉ ከሆነ ከዕዳው ነፃ ነኝ። ተርቦ ወይም ተጠምቶ ባየው ገና ለገና እኔ ምን እበላለሁ ብዬ ምግብና ውኃ ከማቀበል አላመነታም።
ሁላችን ምን እናድርግ? 
የሚያስፈልጋችሁን ያህል መድኃኒት ውሰዱ። ቤታችሁን፣ ጓሮአችሁንና መንገዶቹን ሁሉ አጽዱ። ታምሞ የዳነ ወይም የእናንተን ርዳታ የማይፈልግን ጎረቤት አትጠጉ፤ ከአካባቢም ራቁ። እናም ልክ በምትቃጠለው ከተማ እሳትን ለማጥፋት እንደሚጥር ሰው ተንቀሳቀሱ። ለምን ብትሉ ቸነፈሩ እኮ እሳት ማለት ነው፤ ግን እንጨትና ገለባን ሳይሆን ሰውንና ሕይወትን ነው እያወደመ ያለው። እናም እንዲህ ብላችሁ ልታስቡ ይገባል። “በእርግጥም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጠላት መርዝና የተበላሸን ምግብ ልኮብናል። ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲጠብቀን እማጠነዋለሁ። ቀጥሎም የምኖርበትን ቤቴን አጥናለሁ፤ በዚህም የተበከለውን አየር አጸዳለሁ፤ የታዘዘልኝን መድኃኒት በጥንቃቄ እወስዳለሁ። አላስፈላጊ በሆነ ንክኪ እንዳልመረዝ፣ ሌሎችንም እንዳልበክልና የእኔ ቸልተኝነት ለሌሎች ሰዎች ሞት ምክንያት እንዳይሆን የግድ መገኘት ከሌለብኝ በቀር ከሥፍራዎችና ክሰዎች እርቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ሳቢያ ሊወስደኝ ከወደደ ይወስደኛል። ግን እርሱ ከእኔ የሚጠብቀውን አድርጌአለሁና ለእኔም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሞት ተጠያቂ አልሆንም፡፡ ይሁንና ባልንጀራዬ የእኔን እርዳታ የሚፈልግ ከሆነ አልርቀውም። ይልቁንም ከላይ እንዳልኩት ተጠንቅቄና ነፃነት እየተሰማኝ ላግዘው እሄዳለሁ። ይህ ደግሞ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበት እምነት እንጂ  አጉራ ዘለል ወይም እጓጉል ድፍረት አይደለም፤ እግዚአብሔርንም አይፈታተንም”።
የአማኞች ኃላፊነት!!!
በቅድሚያ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡና ቃለ እግዚአብሔርን እንዲሰሙ ማበረታታት አለብን። ያኔ እንዴት መኖር ብቻ ሳይሆን እንዴት መሞት እንዳለባቸውም ይማራሉ። በሰላሙ ቀን በሙሉ ጤንነት እያሉ ክፉና ጋጠወጥ የሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚሳለቁ ሰዎች አሉ። በሕይወት ሳሉም ይሁን ሲሞቱ ስለ ነፍሳቸው ግድ የሌላቸው  ማሰብ ስለማይችሉ በተኙበት የሚሞቱ በርካታ ወንበዴዎች ያውም ልባቸውን ያደነደኑ ወንበዴዎች አሉ ስል እያዘንኩ ነው።
 ግድየለሽ ሕይወት የኖሩና እንዲህ ያሉትን ዐበይት ጉዳዮች ቸል ያሉ ሰዎች ኃላፊነቱ የራሳቸው ነው። ስሕተቱም የራሳቸው ነው። እግዚአብሔር በቤቱ አትሮንስ ዘርግቶ መሠዊያንም አዘጋጅቶ ሲጠራቸው ኖሯል። ያንን አክፋፍተው ለኖሩት ሰዎች አሁን በየቀኑ በየተኙበት አልጋ ሥርና በየቤቱ አትሮንስ ልንዘረጋ አንችልም።
አገልግሎታችንን በተመለከተ በሌሎች አጋጣሚ አለማመን በደለኝነት አይሰማንም፤ ምክንያቱም በስብከት ቢሆን፣ በማስተማር ቢሆን፣ በምክር ቢሆን፣ በማጽናናት ቢሆን፣ በጉብኝት ቢሆን ወይም ሌላ ሐኬተኞች አይደለንም። እናም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖርና ካስፈለገም ለመሞት ለሁለቱም ዝግጁዎች መሆን ይኖርብናል።
 ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም” (ሮሜ.14:7)።
 (ጨረስኩ…)
ምክር፡- ፩ ተራራቁ የሚለው መመሪያ ታምሞ ለተኛው ጎረቤትህ ምግብና ውኃ በርቀት እንዳታቀብለው ማማካኛ አይሆንም!
(ምክር፦ – ፪ በፈጣሪ ማመንና መታከም አይጋጩም፤ አትፈላሰፍ!)
Filed in: Amharic