>

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች - ( ክፍል ስድስት) አሰፋ ሀይሉ

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች – 

( ክፍል ስድስት)

አሰፋ ሀይሉ
12ኛ/ ዓይኑን የገለጠ ፋሺስታዊ የፍትህ ሥርዓት የገነባ ጀግና!
በዓለም የታወቀ የፍትህ መርህ ነው፡፡ በዓለም የታወቀች የፍትህ ሐውልትም አለች፡፡ በየትም ዓለም – በእኛም ሀገር – የፍትህ ኃውልት ዓይኖቿን በጨርቅ የተሸበበች ናት፡፡ ይህ የሚወክለው የራሱ ታላቅ ትርጉም አለው፡፡ ፍትህ ማንንም አይታ አታዳላም – የሚል፡፡ በሕግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው፡፡ ማንም ሰው በፍትህ ፊት እስከቆመ ድረስ – ፍትህ በፊቷ የቆመውን ሰው ማንነት ተመልክታ በሰዎች መካከል የተለያየ ፍትህን አታሰፍንም፡፡ ሀብታም ይሁን ደሃ፣ ጉልበተኛ ይሁን አቅመ-ቢስ፣ ባለሥልጣን ይሁን መደዴ፣ ባለጊዜ ይሁን ጊዜየጣለው – ሁሉም በፍትህ ፊት እኩል ነው፡፡ ፍትህ ልዩነቱን አታይም፡፡ ፍትህን በሰይፍና በሚዛን ታስከብራለች፡፡ በዓለም የታወቀው ዐይኖቿ የተሸበቡት የፍትህ ሐውልት ተምሳሌት ይህ ነው፡፡
መለስ ዜናዊ መጣና ያቺን በዓለም የታወቀች ፍትህ እርቃኗን አስቀርቶ የዓይኖቿን ጨርቅ ገለጠ፡፡ እና ፍትህ በፊቷ የሚቆሙትን ሰዎች ማየትና መለየት ጀመረች፡፡ በመለስ ዜናዊ ጊዜ ፍትህ እንደዚያ ነበረች፡፡ በጠራራ ጸሀይ የሰው ነፍስ ያጠፉትን፣ የዘረፉትን፣ ሀገር የመዘበሩትን፣ በሥልጣናቸው አላግባብ የተገለገሉትን፣ ህግን የተላለፉትን፣ ውንብድናን ቋሚ መመሪያቸው አድርገው የሚኖሩትን – ብዙ ብዙ በፍትህ መዳፍ ሥር መውደቅ የነበረባቸው ወንጀለኞችን – የመለስ ፍትህ ለይታ ታውቃቸዋለችና እነርሱ ላይ ፍትህ እጆቿን አታነሳም፡፡ የሥርዓቱ ታማኝ ጋሻጃግሬዎችና ሎሌዎች – ከመከሰስ፣ ከተጠያቂነት፣ ከህግ ስጋት ነፃ ናቸው፡፡ እንዲያውም ሥርዓቱን ተማምነው የሚፈጽሙት ሸፍጥና ወንጀል እንደ ማፊያ የቃልኪዳን መሐላ እየተቆጠረላቸው ከሥልጣን ወደ ሥልጣን ይወጣጣሉ፡፡
በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ፍትህ የምትበረታው – ማንም የሥርዓቱ መከታ በሌለውና ተገዢ በሆነው በምስኪኑ ሕዝብ ላይ ነው፡፡ ፍትህ ከወንጀለኞች ሁሉ ለይታ የምታድነው ወንጀለኛ – ከሥርዓቱ ጋር አልስማማ፣ አልታዘዝ ያለውን ነው፡፡ ፍትህ በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ – የፖለቲካ ባላንጣዎችን ለይቶ ማሸማቀቂያ፣ የፖለቲካ ፀብን መበቀያ፣ የእልህ መወጫ ሆነች፡፡
በናዚ ጀርመን አገዛዝ ወቅት በጀርመን የነበረና በሒትለር አምባገነን አገዛዝ – በተለይም ባፈጠጠ የናዚ ሥርዓት ፍትህ ላይ የሰላ ሂስ በመሰንዘሩ ከመረሸን ለጥቂት ያመለጠው አንድ ኦቶ ቮን ኪርችሄይመር የተባለ የታወቀ ቀደምት ጀርመናዊ የፍትህ ምሁር – ‹‹ዘ ሞራሊቲ ኦፍ ዘ ጀስቲስ ሲስተም›› (‹‹የፍትህ ሥርዓት ህሊናው ምን ይመስላል?››) በሚል ባሳተመው ድንቅ ጥናቱ – በናዚ ጀርመን የነበረውን የፍትህ ሥርዓት – በአንድ በኩል ባላንጣዎችን ለማደንና ለማምከን ሲሆን እጅግ ውጤታማ፣ ነገር ግን ናዚን የሚደግፉ ታማኞችን ለመክሰስና በህግ ፊት ለማቅረብ፣ አቅርቦም ለማስቀጣት ሲሆን ደግሞ የሙት ሙት የነበረ – ሙት እና ስል የሆኑ መንታ ገጾች ያሉት የፍትህ ሥርዓት ነበር›› በማለት ሂትለር የገነባውን የናዚ ፍትህ ሥርዓት ባህርይ ያስረዳል፡፡
በዓለም ለበርካታ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በማመሳከሪያነት የሚያገለግሉ እጅግ ጥልቅ ጥናቶችን በመጽሐፍ በማሳተም የታወቀው ሌላው ጁልየስ ስቶን የተባለው ዕውቅ የፍትህ ተመራማሪ ደግሞ በበኩሉ – በናዚ ዘመን በጀርመን የነበረውን የፍትህ ሥርዓት – ከአንድ ነገር በስተቀር ምንም የማይጎድለው የፍትህ ሥርዓት ነበረ ይለናል፡፡ ያ የፍትህ ሥርዓቱ የጎደለው አንድ ነገር – ፍትሃዊነት የሚባለው ነገር ራሱ ነው፡፡ የሂትለር የፍትህ ሥርዓት የአንድን ፋሺስታዊ አስተሳሰብ በሌሎች ላይ ያለማወላወልና ያለርህራሄ ለመጫን – እና ለመተግበር የተቋቋመ የፍትህ ሥርዓት ነበር፡፡
ያን ዓላማውን ለማሳካት ህጎች ወጥተውለታል፡፡ ህግ አስከባሪ አስፈጻሚዎች አሉት፡፡ በህጉ መሰረት ተከሳሾችን የሚዳኙ ፍርድ ቤቶች አሉት፡፡ ሰዎችን የሚከሱ አቃቤ ህጎች አሉት፡፡ አንድ የፍትህ ስርዓት ሊኖረው የሚገቡት ነገሮች ሁሉ አሉት፡፡ ከፋሺስታዊው የናዚ አስተሳሰብ ውጪ ያለን ሌላ ማናቸውንም ዓይነት አስተሳሰብ በጀርመን ግዛት ውስጥ እንዲኖር የማይፈቅድ ሥርዓት ከመሆኑ በቀር – እንከን ያልነበረው ሥርዓት ነበረ፡፡ በዚህም የተነሳ – ይለናል ጁልየስ ስቶን – ዳኛውን ኋላ ለምን የናዚ ህግ አስፈጻሚ ሆንክ ብለህ ተጠያቂ ማድረግ አትችልም፡፡ በህግ እየተመራ ነው፡፡ አቃቤ ህጉም እንደዚያው፡፡ ፖሊሱም እንደዚያው፡፡ ሁሉም ህጋዊ ናቸው፡፡
ህጋዊ ሆነው ግን ችግሩ ፍትሁ የሚሠራው የሥርዓቱን ጠንቆች ለማስወገድ ነው፡፡ የማናቸውም ፋሺስታዊ የፍትህ ሥርዓት መገለጫ ይሄው ነው፡፡ እንከን የማይወጣላቸው ተቋማት፣ ህጎችና መመሪያዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚያ ግን የሚውሉት ባላንጣዎችን ለመዋጊያነት ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን ከሀገር ለማጥፋት ነው፡፡ በህጋዊ መንገድ ህገወጥ የሆነን የሚቃረንህን ለማጥፋት ያለመን ዓላማ ለመተግበር ነው ሥርዓቱ ሁሉ የሚሰራው፡፡ እና ሥርዓቱ ሚዛን የለውም፡፡ የናዚን ሥርዓት ከሌላው የምትለየው ይሄን የህሊና ሚዛን ጥያቄ አንስተህ ብቻ ነው፡፡ በማለት ያስረዳል፡፡
እንግዲህ በእነዚህ ምሁራን እሳቤ አንፃር ከተመዘነ – ኮንትሮባንድ የሚነግዱ የቀድሞ የሥርዓቱን ታጋዮች ከህግ እየተከላከለ ሌሎች ኮንትሮባንዲስቶችን የሚያሳድደው የመለስ ዜናዊ ሥርዓት፣ ለአንድ የፖለቲካ ባላንጣው ብሎ ሙስና ክስ ዋስትና አያሰጥም የሚል ህግ በፓርላማ የሚያፀድቀው መለስ ዜናዊ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ተጠሪነቱን ለራሱ አድርጎ የሚቀናቀኑትን ብቻ እየመረጠ የሚያጠቃበትና የሚያስፈራራበት መሣሪያ ያደረገው መለስ ዜናዊ፣ የእርሱን አፋኝ የደህንነትና የፀጥታ መዋቅር ሙሉ በሙሉ ከህግ ተጠያቂነት ከልሎ ከህግ በላይ አድርጎ የኖረው መለስ ዜናዊ፣ በአደባባይ እየገደለ ማንም ከሳሽ የሌለው የመለስ ዜናዊ መንግስት የፍትህ ሥርዓት – ፋሺስታዊ፣ ናዚያዊ ከመባል ሌላ ምን መጠሪያ ስም ሊገኝለት ይችላል? ለዚህ ነው – መለስ ዜናዊ – ዓይኑን የገለጠ – ፋሺስታዊ የፍትህ ሥርዓት የገነባ ጀግና ነበር የምንለው!!
13ኛ/ እናትና ልጅን ገድሎ ለቅሶ የከለከለ፣ ድንኳን ያፈረሰ ጀግና!
በ1997 ዓመተ ምህረት ላይ የመለስ ወያኔ-ኢህአዴግ የምርጫ ኮሮጆ መገልበጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ ወቅት – ከብዙ ከሆኑና ከተከሰቱ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል የማነሳው ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ ያውም ባጭሩ፡፡ አንደኛው በአዲስ አበባ፣ ከያሬድ ሙዚቃ ከፍ ብሎ በሚገኘው ‹‹ስድስት ኪሎ›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ ቶታል የቤንዚን ማደያው ፊት ለፊት የሆነ ነው፡፡ እዚያው ሰፈር የነበረን ወጣት – የመለስ አጋዚዎች ተኩሰው ይገድሉታል፡፡ ለምን ገደሉት? እንዴት ገደሉት? – እሱን አልገባበትም አሁን፡፡ ልጁ የተገደለው ከመኖሪያ ቤቱ በራፍ ላይ ነበረ፡፡ ከዚያ እናትየዋ ተኩስና የሰዎች ጩኸት ሰምታ ስትወጣ ልጇ ነው፡፡ የልጇን ሬሳ እያገላበጠች እሪታዋን ታስነካዋለች፡፡ እሪታዋን ብቻ ሳይሆን ከአስፋልቱ ላይ ያገኘችውን ነገር ሁሉ እየቧጠጠች አጋዚዎቹ ላይ መነስነስና ባለ በሌለ የእናት ጉልበቷ እላያቸው ላይ መስፈር ጀመረች፡፡ በቁጣና በእልህ፡፡
እነሱም በደም ፍላት ተሞልተው (ልበለው ወይስ በደም አዙሪት ሰክረው) ወጊጅልን ከፊታችን፣ ጥፊ ከዚህ አሏት፡፡ ሁለት ሶስቴ እየገፈተሩ አስፋልቱ ላይ ጣሏት፡፡ መልሳ እየተነሳች ልጄ ነው የሞተው – ጥዬው ወዴት ነው የምሄደው ኡኡኡ.. እናንተ…. እናንተ ምናምኖች…. !! ቀጠለች ትግሏንና በእልህ መተናነቋን፡፡ በመጨረሻ አንዱ አረመኔ እስኪገላግላት ድረስ ጮኸች፡፡ ተኮሰና እሷንም ከልጇ ሬሳ ጋር አነባበራት፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ይሄ የእናትና ልጅ ባንድ ጀንበር መሞት አይደለም፡፡ ኋላ የሰፈሩ ሰው በማግስቱ ድንኳን ተክሎ ማስተዛዘን ጀመረ፡፡ አጋዚዎቹ መጡና መጀመሪያ አታልቅሱ ብለው ለቅሶ ከለከሉ፡፡ ቀጥለው ደግሞ መንገድ ላይ እንዴት ድንኳን ትሰራላችሁ ብለው ድንኳኑን አስፈረሱት፡፡ በእርግጥ በሰፈሩ ሌላ ድንኳን መጣያ ስለሌለ አስፋልቱ ዳር ነበር ድንኳኑ የተጣለው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን – እምቢ ብሎ ለመቋቋም የሞከረ ሰው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ (አሁንም እንደዚያው ይመስለኛል) በወቅቱ የአድማ በታኝ ፖሊሶች ዋና መኖሪያ ካምፕ የነበረው – እዚያው አጠገብ ነበርና! ይሄ እንግዲህ ከብዙ አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛውን እውነተኛ እማኝ የሆንኩበትን ታሪክ ተውኩት፡፡ ምን ይሠራል ግፍን መልሰው መላልሰው ቢሉት ቢሉት?
ተውኩት ሁለተኛውን፡፡ ይሄን ግን ባሰብኩ ቁጥር – ወያኔዎች ደርግ አደረገ እያሉ በአረመኔነት ከሚከሱት  (እና የሰማዕታት ሙዝየም ብለው ‹‹መቼም እንዳይደገም›› የሚል መፈክር ያቆሙለት) የደርግ ግፍ – ‹‹ነፃ እርምጃ›› በሚል የወቅቱ ሁሉንም ጎራ የተጣባ አሰቃቂ አባዜ ወጣቶችን በየመንገዱ እየገደለ – እናቶችን ለሬሳ መውሰጃ ‹‹የጥይት 10 ብር ክፈሉ›› እያለ – አንድ ሬሳ በ10 ብር ለእናቶች የቸበቸበበትን የግፍ ታሪክ ነው፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በወያኔ-ኢህአዴግ ትርክት ጭራቅ ተደርጎ እንዲሳል ከተደረገባቸው ጥቁር የታሪካችን ክስተቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ግን ግን – እናትና ልጅን ባንድ ጀምበር በጠራራ ፀሀይ ገድሎ – ለቅሶ የከለከለው- የሐዘን ድንኳን ያፈረሰው – መለስ ዜናዊስ – ከዚያኛው ከቀደመው ‹‹ግፈኛ›› በምንድነው የሚለየው?
‹‹የገደለን ገድሎ ዙፋን ላይ ቢወጣ፤ 
ያምናውም ባለቀን እንዳምናው ከቀጣ፤ 
አዲስ ንጉሥ እንጂ – ለውጥ መቼ መጣ!›› 
ያለውስ አርቲስት – ህሊናን በእውነት መሸንቆጡ ኃጢአት ካልሆነበት በቀር – ምንድነው ስህተቱ? ብዙዎች የመለስ ዜናዊ አድናቂዎችና አክባሪዎች (አምላኪዎችም) ይህን እውነታ አምነው መቀበል አይፈልጉም፡፡ ስህተቱ የእሱ አይደለም ሌሎች በእሱ ሥር ያሉ ናቸው – ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይሄ በሁሉም የዓለማችን ፋሽስታዊ አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሁሉ ሲባል የኖረ ልብ ማራሪያ ምክንያት ነው፡፡ በበኩሌ ልዩነቱ አይገባኝም፡፡ ምንም ሺህ ምክንያት ቢደረደር የግፉን ምንነት፣ አንዴ የሆነውንና የተፈጠረውን ሃቅ እውነቱን አይቀይረውም፡፡
ግን ለሁሉም የምለው – አምንንም አላመንንም – እየመረረን መቀበል ያለብን እውነታ አለ፡፡ ይኸውም እውነታ – ግፍን እታገላለሁ ብሎ የተነሳው የድሮው ለገሰ ዜናዊ – ዙፋን ላይ ሲወጣ ‹‹አዲስ ንጉሥ›› ተብሎ የተቀነቀነለት ባለጊዜ መለስ ዜናዊ – እናትና ልጅን ገድሎ – ለቅሶ የከለከለ፣ ድንኳን ያፈረሰ ጀግና የመሆኑ የመረረ እውነታ ነው!! ለዛሬ አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን በቃሽ ይበላት!
የእናቶቻችንን እንባ በምህረቱ ያብስ!
ሌላ ግፍን አያሳየን፣ ግፍን ያርቅልን ፈጣሪ!
(- ይቀጥላል)
Filed in: Amharic