>
5:18 pm - Tuesday June 15, 8088

የሕግ የበላይነት በደርግ እና በወ/ኦያኔ፤ እንዲሁም የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እና የኢትዮጵያ አየርመንገድ፦ (ክፍሉ ሁሴን)

የሕግ የበላይነት በደርግ እና በወ/ኦያኔ፤ እንዲሁም የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እና የኢትዮጵያ አየርመንገድ፦

ክፍል 1
ክፍሉ ሁሴን
ለዚህ ጽሁፍ በዋነኝነት መነሻ የሆነኝ በሶስት ክፍል ያየሁት “በኢትዮጵያ አየርመንገድ ጣሪያ ስር ጉድ” በሚል ርዕስ የተሰራው ዘገባ ሲሆን ወያኔ ኢትዮጵያን ከጠቀለለ ጀምሮ አየርመንገዱ እየተበላሸ መሄዱን ባውቅም ከዚህ ዘገባ ቀጥሎ ቀደም ሲል ሳላየው ያመለጠኝ ሳሙኤል የተሻወርቅ የሚባል ነዋሪነቱ ጀርመን የሆነ ተፌ የንግድ ሰውና የአየር ቲኬት ሽያጭ ወኪል ለመረጃ ቲቪ የሰጠውን ቃለመጠይቅ ዩቲዩብ አምጥቶ “ከመረቀልኝ” በኋላ የፈጠረብኝ ድንጋጤ ነው።
በመጀመሪያው አዲስ ዘይቤ ላይ ካየሁት ባለሶስት ክፍሉ ዘገባ ልጀምር። ከዚህ ውስጥም ፍጹም ጋጠወጥ እና ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ በአየርመንገዱ ሰራተኞች ላይ ተፈጸመ ለተባለው ሰቆቃ ቅድሚያ ልስጥ። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተመረቁ በርካታ ምሁራን፤ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያሉበትና የአየርመንገዱ የሥራ ዘርፍም አለማቀፍ ይዘት ያለው ንግድ እንደመሆኑ መጠን ቀላል ቁጥር ያሌላቸው የኩባንያው ባልደረባዎች ከትምህርታቸው እና ከሙያቸው በተጨማሪ አለማቀፍ ተሞክሮ (international exposure) ያላቸው እንደመሆኑ መጠን በዚህ ዘመን እዚያው ኩባንያው ቅጥር ግቢ ውስጥ በስብስቴ ዘበን (medieval era) እንዳለ ጥጋበኛ ቱጃር አሽከሮችን የማሰሪያና የመግረፊያ ቦታ ተከልሎ በጠራራ ፀሐይ በወጣት የአየርመንገዱ ሰራተኞች ላይ ግፍ ሲፈጸም ከፍተኛ ቁጣ (sense of outrage) አለመቀስቀሱ መመጻደቅ ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያዊ ጀግንነትም እንደሌለን፤ ሰብዓዊ እሴታቻንንም የሚያጎለብት ትምህርት፣ ሙያ፣ ወይም ተሞክሮ እንዳላካበትን የሚያሳይና እጅግ የሚያሳፍር ሁኔታ ላይ እንዳለን የሚያሳብቅ ነው። ይህ ሁሉ ሰቆቃ በአየርመንገዱ ቅጥር ግቢ የሚፈጸመው ፋሽስት ደርግ ኢሰፓን መንግዬ ዴሞክራሲን አውጄያለሁ በሚለው ወ/ኦያኔ ነው። በዚህ የወ/ኦያኔ ስር ያሉት የለበጣ ፍ/ቤቶችና አቃብየነ ሕጎች ሁሉ ይህንኑ ሕገ ወጥነት ያበረታታሉ እንጂ ኢሰብአዊ ወንጀል ነው አይሉም።
በደርግ ጊዜ በቀጥታ ራሴ የተሳተፍኩበትን አንድ ምሳሌ ላምጣ። በ1981 ዓ.ም ጎረምሳ ሳለሁ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጠበቃ ለመሆን ተቀጥሬ ወደ ድሬዳዋ አመራሁ። ከኔ በፊት የነበረው ጠበቃ በእድሜ ጠና ያለና በወግ አጥባቂነት የተነሳ አለቆች የሚሉትን ሁሉ መፈጸም ስነ ምግባር የሚመስለው የነበረ ከመሆኑም በላይ በወቅቱ እንደ ኑሮ ብልሀት በሚታየው ስልት የፋብሪካው የኢሰፓ መሰረታዊ ድርጅት አባልም በመሆን ጓድ እንቶኔ ሲባል ሞቅ የሚለው ዓይነት ሰው ነበር። በመሆኑም በአስተዳደር ጉድለት የተነሳ ሰራተኞች ለሚያቀርቡት ክስ ሁሉ ሀተታ እየጻፍክ በየፍ/ቤቱ መልስ ስጥ ሲሉት አመራር ላይ ያሉት ሰዎች እየተቀበለ፤ በኋላ እንደሰማሁት የሰራተኛው ቅሬታ በሱ ላይ እየተከማቸ አደጋ ሊፈጠር ሲቃረብ በልዩ ዘዴ አዲስ አበባ ወደ ኮርፖሬሽኑ ይዛወርና እኔ በሱ ቦታ ተተክቼ እሄዳለሁ።
ከተረከብኳቸው ጉዳዮች መቼም የማልረሳው “አመልካች፦ እነድጋፌ ኃይለማሪያም (3 ሰራተኞች)፤ ተጠሪ፦ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ (ድጨጨፋ)” የሚል ዶሴ ሲሆን ሰራተኞቹ “አላግባብ ከስራ ስለተሰናበትን ያልተከፈለን ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎንና ጥቅማ ጥቅማችን ተጠብቆ እንመለስ” በሚል ሲሆን ክስ ያቀረቡት ጓድ እንቶኔ ደሞ በድጨጨፋ በኩል “የድርጅቱን እቃ አላግባብ ደብቀው ሊወጡ ሲሉ እጅግ ከፍንጅ ተይዘው ስለሆነ የተባረሩት ሊመለሱ አይገባም” ሲል ተከራከረ። ጉዳዩ በጊዜው 64/68 ተብሎ ይታወቅ በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ መሰረት በሥራ ክርክር ኮሚቴ (trade dispute committee) ይባል በነበረው መሰረት ሲሆን የሚታየው ኮሚቴው ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በቀጠሮ፣ በእንጥልጥል ላይ እያለ ጓድ እንቶኔ ለኔ አስረክቦ ይሄዳል። ኮሚቴው እኔ ከተረብኩ ጥቂት ሳምንታት በኋላ “ሰራተኞቹ አላግባብ ስለተሰናበቱ የ11 ወር ገደማ ውዝፍ ደመወዛቸው ተከፍሎና ጥቅማ ጥቅማቸው ተጠብቆ ወደስራቸው ይመለሱ” ሲል ሕጋዊና ፍትሃዊ ውሳኔ ይሰጣል። ነገር የመጣው ይህን ሪፖርት ካደረኩ በኋላ ነው።
የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊው ጓድ እንተን ዶሴው ላይ በተካተተው የውሳኔ ግልባጭ ላይ “ጓድ ክፍሉ ይግባኝ ይጠየቅ!” የምትል ቀጭን ትዕዛዝ ይጽፍና ይልክልኛል። መችም ጎረምሳ መሆን ጥሩ ነው፤ ደግሞም በዚያን ጊዜ ምሽት፣ ልጅ የምለው ነገር ስላልነበረኝ፤ ከቶውንም ከሥራ ብባረር ተመልሼ የምዘፈዘፍባቸው፣ የኮራ የደራ ቤተሰብ ስለነበረኝ ለመምሪያ ኃላፊው መልሼ በፍጹም ጥጋብና ንቀት “ጓድ” የሚለውን ካድሬዎች የሚቆለማመጡበትን ማዕረግ ትቼ “አቶ እንተን ይግባኝ የሚጠይቅበት መሰረት የለም!” ስል በቀጭኑ ጽፌ መለስኩለት። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጸሃፊው እየተጣደፈችና እየተርበተበተች “ጓድ እንተን በአስቸኳይ ይፈልጉሃል!” አለችኝ። ዘና ብዬ ቢሮው ስደርስ ቶኪቻው ገና እንደገባሁ ጋል፣ ጋል እያለ “አንተ መልስ ስጥ! ይግባኝ ጠይቅ!” ስትባል መፈጸም ነው እንጂ ሌላ አስተያየት መስጠት አትችልም!” ሲል ደነፋ። በማግስቱ ስራ አስኪያጁ ጋር ከሶኝ ቀረብኩ። ላሳጥረውና ይግባኝ አልልም ያልኩበትን ምክንያት ሰጥቼ ከአየርመንገዱ የዛሬ አሰቃቂ ተግባር ጋር የሚገናኝበትን ላሳይ።
ሰራተኞቹ እነድጋፌ ለመብታቸው ቀናኢ ስለነበሩ በራሳቸው በማይተማመኑ ፎርማኖችና ካድሬዎች ቂም ስለተያዘባቸው በስራ ሰዓት መውጫ ላይ የፋብሪካውን እቃ ደብቀው ሊወጡ ሲሉ ተያዙ በሚል የውሸት ውንጀላ ይለጠፍባቸውና በፋብሪካው በነበረ “የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴ ክፍል” ተወስደው የእምነት ቃል ስጡ ተብለው ሰቆቃ ይፈጸምባቸዋል። ስቃይ ሲበዛባቸው ሰርቀናል ብለው ይፈርማሉ። ይህ እንደ ማስረጃ ተደርጎ በወንጀል ክስ እንዲመሰርትባቸው ታስረው ለፖሊስ ይላካሉ። በወቅቱ ንዝህላል የነበረ ፖሊስም የእምነት ክህደት ሲጠይቃቸው እዚህም እንገረፋለን ብለው የእምነት ቃል ይሰጣሉ። ከዚያም ፖሊስ ክስ ይመስረትባቸው ብሎ ለድሬዳዋ ራስ ገዝ አቃቤ ሕግ ሹም ጉዳዩን ይመራዋል። የራስ ገዙ የአቃቤ ሕግ ሹም ግን በከፍተኛ ቁጣ እና ግሳፄ ከወንጀለኛ ሥነ ሥርዓት ሕግ እና ከደርጉ የኢህዲሪ ሕገ መንግስት በመጥቀስ አብዮት ጥበቃ ወንጀል ለመመርመር፤ የእምነት፣ ክህደት ቃል ለመቀበል በሕግ አንዳችም ስልጣን የሌለው ከመሆኑም ባሻገር ይልቁንም በሰራተኞቹ ላይ የፈጸመው ኢሰብዓዊ ተግባር ራሱን የቻለ በወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ሆኖ ሳለ የድሬዳዋ ራስ ገዝ ፖሊስ ይህን በሕገ ወጥና በማስገደድ መንገድ የተገኘ ቃልን ተንተርሶ ሰራተኞቹ ይከሰሱ ማለቱ በኢህዲሪ ሕገ መንግስት ላይ ስለ ሰብዓዊ መብቶችና ስለ ሕጋዊ ሥራት (due process) የተደነገገቱን ያላገናዘበ ነው ሲል ክፉኛ ተችቶ ሰራተኞቹ ወዲያውኑ እንዲፈቱ አዘዘ። ዛሬ አብዛኛው የሕግ ባለሙያ ለአገዛዝ በሚገረድበት ዘበን በዚያን ጊዜ የድሬዳዋ ራስ ገዝ አቃቤ ሕግ ሹም የነበረውን አቶ መስፍን እቁበዮሐንስን እዚህ ላይ ስሙን ጠርቼ ላመሰግነው እወዳለሁ።
እኔም ሰራተኞቹ ወደስራ እንዲመለሱ በተወሰነላቸው ላይ ይግባኝ አልልም በማለቴ ተከስሼ የቀረብኩበት የወቅቱ የድጨጨፋ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው መሬት ይቅለለውና በጥሞና የኔን ምክንያት ሰምቶ በውሳኔው መሰረት ሰራተኞቹ ወደስራቸው እንዲመለሱ በመወሰኑ እያመሰገንኩት ደርግ ፍርድ ቤት ሳያቀርብ በፖለቲካ ሰው ቢያስርም፣ ቢገድልም አንዴ ወደሕግ ቦታ ከሄደ ግን ወያኔ በሕግ ጣልቃ እየገባ በፍትህ እንደሚያላግጠው ዓይነት ባህሪ እንዳልነበረው ከዛሬው በአለማቀፍ ንግድ የተሰማራው አየርመንገድ ካለው የኮንቴይነር እስር ቤት ጋር ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በግቢው ከነበረው የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴ መግረፊያ ክፍል ጋር እያነጻጸራችሁ እንድትቆዝሙበት እየተውኳችሁ በክፍል ሁለት፦
ለአድማስ አየር አገልግሎት በኢትዮጵያ አየርመንገድ የበረራ ማሰልጠኛ ት/ቤት ስልጠና ላይ የነበረ ፓይለት መሬት ይቅለላቸውና ሻለቃ ሁሴን አህመድ ስልጠና ይሰጡባት የነበረውን አውሮፕላን ይዞ ሊኮበልል ከሞከረ በኋላ ተይዞ በሻለቃ ሁሴንም ሆነ በኮብላዩ ሰልጣኝ ፓይለት አስተማሪ ሻለቃ መሉጌታ ሀብተስላሴ (እሳቸውንም መሬት ይቅለላቸው) ላይ በምርመራ ስም አላስፈላጊ ወከባ እንዳይደረግባቸው በደርግ ጊዜ በሕጉ መሰረት የተደረገላቸውን ጥበቃ፤ እንዲሁም በጭነት አውሮፕላንና ከመንገደኞች ሻንጣ ጋር ተለጥፈው በደርግ ጊዜ በኮበለሉ ሰራተኞች የተነሳ እንደዛሬው እንደ ወያኔ ጊዜ እስር፣ ሰቆቃ ቀርቶ በአየርመንገዱ ሰራተኞች ላይ ግልምጫ የሚያደርስ እንዳልነበረ በማተት እና የፍራንክፈርቱ ኤጀንት ሳሙኤል የተሻወርቅ ስለተወልደ ገብረማሪያም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ደብሊን፣ አይርላንድ ላይ ታስሮ በእሱ አማላጅነት ስለተፈታበት ያወሳት አየርመንገዱ ሎስ አንጄለስ፣ ካሊፎርኒያ በረራ እንደጀመረ በፓይለቶችና የበረራ አስተናጋጆች ቅብጠት የተነሳ አየርመንገዱ ቅሌት ውስጥ ቢገባም ቅቢጢዎቹ ከወርቁ ዘር ስለሆኑ ሳይነኩ እንዴት እንደተረፉ በአደባባይ የሚታማውንም እዚህ አንስቼ እሄድበታለሁ።
Filed in: Amharic