>
5:13 pm - Friday April 19, 0024

ኢትዮጵያ በጡረታ የተገለሉ ዲፕሎማቶቿን በማሰባሰቡ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት አለባት!!! (ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ)

ኢትዮጵያ በጡረታ የተገለሉ ዲፕሎማቶቿን በማሰባሰቡ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት አለባት!!!

ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ


መንግስት ነባርና በጡረታ የተገለሉ ዲፕሎማቶቿን በማሰባሰቡ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ የቀድሞው የ16ኛ ሰንጥቅ ሜካናይዝድ ብርጌድና በኋላም የሶስተኛው ሜካናይዝድ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ፡፡

ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋናነት የዲፕሎማሲ ስራውን በከፍተኛ ደረጃ ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ የበቁ ሰዎች አሏት፡፡ ዘመን ሲቀየርና ፈተናዎች ሲያጋጥሙ ወደኋላ በመሄድ በዘርፉ ካሉት ዲፕሎማቶች በተጨማሪ ነባርና በጡረታ የተገለሉ ዲፕሎማቶችን በማምጣት ምክራቸውንና አስተያየታቸውን መቀበል መልካም ነው:: እነርሱ የሀገር ሀብት ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ ከድሮ ጀምሮ የራሳችንን በየመስኩ የነበሩ ብቁ ባለሙያ ዜጎች ያላቸውን አቅም በሚገባ ያለመጠቀም ችግር አለብን ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ፣ ነባርና አንደበተ ርቱእ እንዲሁም የሰከኑ ዲፕሎማቶች ስላሉኝ ያላቸውን እውቀት መጠቀም ብልህነት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም በርካቶችንም መጥቀስ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አይደለም እውቀታቸውን ሕይወታቸውን ለሀገራቸው የማይሰስቱ ብዙ ሚሊዮን ልጆች ያሏት ሀገር ነች ያሉት ጀነራሉ ፣ እነዚህንና ሌሎችንም በጡረታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ጠርቶ ተወያይቶ ለዲፕሎማሲው ስራ በአለም ዙሪያ ማሰማራት ተገቢ ነው ብለዋል:: እድሜ ዘመናቸውን ግብጽንና ሴራዋን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በምእራቡ አለም ዲፕሎማሲ ውስጥ የኖሩ ነባር ዲፕሎማቶች በአለም ዙሪያ ተሰማርተው ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕጋዊ የመልማት መብትን ለአለም በማስረዳቱ በኩል ከፍተኛ ድጋፍ ሊያበረክቱ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አሁን ካሉት ጋር ተነጋግሮ መጀመሪያ አንድ የልኡካን ቡድን ወደ ተፋሰሱ ሀገሮች፣ ሁለተኛውን ደግሞ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ሶስተኛውን ወደ አውሮፓ ህብረትና ወደተቀረው ዓለም በመላክ ወዳጆቻችን በሆኑ ሀገሮች ሁሉ ላይ ጭምር ሰፊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በያሉበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለሀገራቸው ዲፕሎማት ሆኖ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል ፡፡

የነባር አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እውቀትና ልምዳቸው ለሀገር ይጠቅማል፡፡ እነሱን አሰባስቦ መንግስትን እንዲያግዙ፣ እንዲያማክሩና አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ ለሀገርም ለመንግስትም ይጠቅማል:: እነርሱ የሀገር ሀብት ናቸው።

Filed in: Amharic