>

"ኢትዮጵያ ከፈተና የምትወጣበት መንገድ. . ."ክፍል ሦስት (በተማም አባቡልጉ - የህግ ባለሙያ)

“ኢትዮጵያ ከፈተና የምትወጣበት መንገድ. . .”

  በተማም አባቡልጉ   (የህግ ባለሙያ)
ክፍል ሦስት 

የአገራችን ፈተና ከተቸከለባቸው ዋነኛ ቦታዎችና ቀዳሚ ከሆኑት መካከል ዛሬ ችግር መፍታት የተሳናቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች በአንድ ፓርቲ አባላት የተሞሉ እና ምንም አይነት ሌላ ሃሳብ የማይስተናገድባቸው መሆናቸው ወይም ከፓርቲያቸው አመለካከት ውጪ ያሉ አመለካከቶችን የሚያስተናግድ አሰራር እና ባህሪ የሌላቸው መሆኑ ችግሩን የበለጠ ያከፋዋል፡፡ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔው በገዢዎቹ አባላት የተሞላ እንጂ ሌሎች ያሉበት ወይም ገለልተኝነት ያላቸው ባለመሆኑና በሚያካሂዱት የውይይት መድረክም የተቃዋሚ ፓርቲ ኀይሎችን ወይም ሃሳባቸው እንዲደመጥ የሚፈልጉ ዜጎችንና ምሑራንን የማወያየት ተግባር ስለማይከውን፤  ለተፈለገው ዓላማ  ማስፈጸሚያ በሚያሳትፋቸው ለራስ ፍላጎት በልዩ ሁኔታ እድል በሚሰጣቸው ሰዎች ተለክቶ አሳታፊነት አለው ሊያሰኘው አይችልም፡፡
ሕገ-መንግሥቱ መንግሥት የሚገዛበት (የሚመራበት) ነፍስ ያለው የመተዳደሪያ ሰነድ ሣይሆን ማስፈራሪያና እንደ ጣዖት እየተመለከበት ብቻ እንዲቀጥል ከተደረገባቸው መንገዶች አንዱ የተለያዩ የመንግሥት የሥልጣን አካላትና የፌዴራሉና የክልል መንግሥታት እየተጠባበቁ የሚሠሩበት መርህ (Principle of checks and balances) በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ያለመኖር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ ሕገ-መንግሥት ሥር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መመስረት እንዳይቻል ያደረገ መሆኑን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ገልጫለሁ፡፡ በአሜሪካ ሬዲዮ ላይም ‹በዚህ ሕገ-መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር መሞከር ጤፍ ዘርቶ ስንዴ እንዲበቅል እንደመጠበቅ ነው› ያልኩትም ከዚህ በመነሳት ነበር፡፡ ከቄሱ በላይ ክርስቲያን ለመሆን የሞከረው የኢህአዴግ ፓርላማ የሰሞኑ ሁኔታም ከዚህ የመጣ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታም አይለውጠውም፡፡
ሁሉም የመንግሥት አካል የየራሱን ሥልጣንና የሥራ ድርሻ አውቆ ተግብሮ ስለማያውቅ የሰጡትን እየተቀበለ ያስተናግዳል፤ ተወስኖ በቀረበለት ላይ ማህተሙን ያኖራል፤ ከዚህ አስተሳሰብ ያልተላቀቁና ‹እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው›  በሚል ብሂል የሚመሩ የዛሬዎቹ ገዢዎችና ተላላኪዎቻቸዉ በወደቀ እምነታቸዉ ላይ ወጥተው እየጋለቡ ሁላችንንም ወደገደል አፋፍ አድርሰውናል፡፡ እየሆነ ያለውም ግራ መጋባታቸውን እንጂ ዲሞክራሲያዊ እየሆኑ መምጣታቸውን አያመለክትም፡፡ ‹ሞተን እንገኛለን እንጂ ከማንም ጋር አንነጋገርም› እያሉ የፈለጉትን አዋቂ ነኝ ባይ ሃሳብ አምጣ ቢሉት የተለመደውን መቀጠላቸው መሆኑን አናጣውም፤ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ለመነጋገር ሣይፈቅዱ የቱንም ኤክስፐርት በግላቸው ጠርተው ማነጋገራቸው አገሪቷ የነሱ ብቻ ላለመሆኗና የሌሎችም ሃሳብ በአገሪቷ ጉዳይ ላይ አስፈላጊ መሆኑን መቀበላቸውን አያሳይም፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ያጣችው ደግሞ አገሪቷ የሁሉም መሆኗንና የሌሎችም ሃሳብ ዋጋ ያለው መሆኑን የሚያምን እንጂ የሱን ሃሳብ ሊያቆነጁለት የሚችሉትን ሰዎች ሰብስቦ የሚያወያይ ገዢ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የዛሬዎቹም  ባለጊዜ ገዢዎች አካሄድ የተለየ አይደለም፡፡ ዛሬ የምንከራከርበት የህወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግስትም የተረቀቀውና የፀደቀው በዚህ መልክ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የተለመደው ‹‹አሮጌውን ወይን ባዲሱ አቁማዳ›› የሚሉት ዓይነት አሳዛኝና የአብዮቱ መቀልበስ የመጨረሻ ደረጃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹ከአደርባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ይሻላል› እንዲል በዓሉ ግርማ ባለፉት ዓመታት ብዙ አደርባዮች ይህቺን አገር ጥለው ለመውደቅ የሚያደርጉትን እሽቅድምድም ታዝበናል፡፡
ዲሞክራሲያዊ የሆኑትን ጨምሮ በየትኛውም አገር ያሉ የተለያየ ሥልጣን ያላቸው አካላት የሚያጣላቸው ሥልጣኔ ነው በሚሉት ሥራቸው ላይ ሌላው አካል ጣልቃ ገባብኝ የሚለው ሲሆን በዓለም ላይ የራሱን ሥልጣን ሳይጠቀምበት ተግባሩን እንዴት መወጣት እንዳለበት ከሌላ አካል በመጠየቅ ጣልቃ እንዲገባበት በአዋጅ የጠየቀ ለሌላ አካል የሥልጣኔን ሕገ-መንግስታዊነት ንገረኝ ያለ ብቸኛው የኢትዮጵያ ፓርላማ ሕግ ሣያወጣ የሕ- መንግስት ትርጉም መጠየቁ የነበርንበትንና ዛሬም ያልተላቀቅነውን የጭቆናና የጨቋኞች ፈረስነታቸውን ያረጋግጥልናል፡፡ ግራ የተጋቡ ግራ አጋቢዎች የአገሪቷን የመሪነት ቦታ ሲይዙ የሚሆነው እንዲህ ነው፡፡ ድሮ መለስ ዜናዊ ያለውን ሁሉ ሕግ የሚያደርጉ አካላት የለመዱት ሲጎድል እንደዚያ የሚላቸዉ ሲጠፋ ሌላ አለቃ መፈለጋቸው ይጠበቃል፡፡
አለቃቸው ሕዝብና የሕዝብ ፍላጎት ያለመሆኑንና እንዲሆንም ያለመፈለጋቸውን ግን ሳንታዘብ አልቀረንም፡፡ ብዙዎች የነሱ ብሔር ሕገ-መንግስቱን ባለማውጣቱ እነሱን እንደማይወክል ይገልፃሉ፤ እንዲቀየርም ይጠይቃሉ፡፡ የነሱ ብሔር ተወካይ በማውጣቱ ላይ ቢኖርበት እንኳ ይህንን ሕገ-መንግስት ሕዝባዊና የዜጎችን ነፃነት የሚያስጠብቅ ሊሉት ግን አይችሉም፡፡ ይህንን ሕገ-መንግስት የየቱም ብሔር ተወካይ አላወጣውም፤ ምናልባት ከኦነግ በቀር የማንም (ፓርቲ) ሃሳብ አልተካተተበትም፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ህወሓት/ኢህአዴግን እንጂ የቱንም ብሔር አይወክልም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በጨቋኝነት የፈረጁትን አማራን ጨምሮ የትኛውም ብሔር (ሕዝብ) የራሱን ሕገ-መንግሥት አውጥቶ ወይም ሕዝባዊ ሕገ-መንግስት ኖሮት አያውቅም፡፡ ሁሌም ገዢዎች ሕገ-መንግሥት ይሰጡት ነበር፤ ሕገ-መንግሥት የሚሰጠው ሕዝብ ደግሞ ነፃ ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህንን በመጽሐፌም በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችም በተደጋጋሚ ስለገለጽኩኝ አሁን ብዙ የምልበት አይሆንም፡፡
ማናችንንም ያላገለለ ሕገ-መንግስት ኖሮን ስለማያውቅ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያኖች የምንለያይ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም አሁን ያለውን ጨምሮ እስከ ዛሬ በነበሩት ሕገ-መንግስቶች ዙሪያ የኢትዮጵያን (ሁሉንም ወይም የትኛውንም) ሕዝብ ለማሰባሰብ መፈለግ ለሁላችንም ወይም ለዚያ ሕዝብ ባርነትን ከመፈለግና በባርነት ዙሪያ ተሰባሰብ ከማለት አይለይም፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥና የጋራችንን ራዕይ የያዘ በጋራ እንዴት በሀገራችን መኖር እንደምንሻ የሚገልጽ የጋራ ሰነድ በመፍጠር ዙሪያ እንሰባሰብ ማለት ወደ አንድነትና ነፃነት የሚወስደን ብቸኛዉ መንገድ ነው እላለሁ፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አገሩንና ሕዝቡን የሚወድ ሁሉ ከዚህ የተለየ ምርጫ ያለው አይመስለኝም፡፡  ትግራይን ጨምሮ በክልሎችና በፌዴራሉ መንግሥታት መካከል የሚታየው ሁኔታ የዚህ ከላይ የተመለከትነው የሕገ-መንግስቱ (ሥርዓት) ችግር ነፀብራቅ (ውጤት) እና በዚህ የሕገ-መንግስቱ አውጪዎች ሥራ ላይ አውለውት ስለማያውቁ በዚህ ሥራ ላይ ባለመዋል በ (disuse) በቀረ ሕገ-መንግሥት ችግራችን መፍትሔ የማያገኝ ስለሆነ የሁላችንንም ሕገ-መንግሥት በማግኘት አስፈላጊነትና (ግዴታነት) ዙሪያ በጋራ በመሰባሰብ አገራችንን ከመፈራረስ እኛንም እንደ ሕዝብ ከመውደቅና ከመጥፋት ሊንታደግ የሚችልና የሚገባ ሃሳብ ነው፡፡
ማጠቃለያ ፡- ለአገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂውን መፍትሔ መፈለግ አሁን ለገጠመን ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ ከመፈለግ ጋር እኩል ጎን ለጎን መሄድ አለበት፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔውም ዘላቂውን መፍትሔ ለማግኘት በሚያስችል መልኩ (መቅረፅ) እንችላለን፡፡  በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ስብስቦች በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ አጀንዳ እንቅረጽ ብሎ ጠርቶ የማያውቅ ሁሉ ስለፓርቲዎች ብዛት እንቅፋትነት ያወራል፡፡ የፓርቲዎች ብዛት እንቅፋት የሆነው ለምንድንነው ? ብትለዉ መልስ የለውም፤ ወንበሩ አንድ (የተወሰነ) ነውና ሥልጣን ለስንቱ እናዳርስ ይላሉ፤ ይህ ለሁላችንም ስድብ ነው፡፡ ለወደፊቱ በአገሪቷ በሚካሄዱ የፖለቲካ ጨዋታዎች የጨዋታውን ሕግ ተነጋግሮ መወሰን ሥልጣን የመጋራት ፍላጎት (ጥያቄ) አይደለም፤ የጥያቄው ይዘት ያንን አያሳይምና፡፡
በሌላ በኩል ሌሎችን በሥልጣን ፈላጊነት የሚከሱት ብዙዎቹ ዋነኞቹ የሥልጣን ፈላጊዎችና ሥልጣን ወዳጆች የመሆናቸው  ወለፈንዲ የከረመ ነውና እሱን ንቀን ለአገራችንና ለራሳችን ኃላፊነት ወስደን ለዚህ ቅዱስ ዓላማ እንጠራራ፡፡ የሚያሳፍረው ሥልጣን መፈለግ ሳይሆን ሥልጣንን ለሥልጣንነቱ ብቻ መፈለግ ነውና የአገርና የሕዝብን ዓላማ የያዝን ሥልጣን ፈላጊዎች እንሁን፡፡ ይህ ደግሞ የጋራ የጨዋታ ሕግ ለመፍጠር ማንንም ሣያስቀሩ ሁሉንም ለመጥራት በመድፈር ብቻ ይገለፃልና ‹ኢትዮጵያን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ› ብለናል፡፡ አገር መውደድ ሕዝቧን መውደድ ነው፡፡ ሁሉንም ሕዝቧን መውደድ አገርን ለዜጎቿ መመለስ የሀገር ፍቅር የመጨረሻው ደረጃ ነዉ፡፡
ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የገቡና (እዚህም የነበሩ) ፖለቲከኞች በራሳቸዉ ተነሳሽነት በአገሪቷ ፖለቲካ ላይ የማይሳተፉ (እርስ በርሳቸው የማይነጋገሩ) ከሆነ ሥራቸው ምንድን ነው ?  ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ከውጪ ጠርቶ ወደ አገር ያስገባቸውን ተቃዋሚዎችን በአገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ ሊያሳትፋቸውና ለዚያም መድረክ ሊያመቻችላቸዉ ካልሆነ የጠራቸዉ በጉያው ውስጥ አድርጎ ሊቆጣጠራቸው ነው የሚለውን ስለሚያጠናክር ድርጊቱ የሚወገዝ ይሆናል፡፡
የ1966 ዓ/ም አብዮት የከሸፈው ደርግ አሳታፊ ባለመሆኑ ሲሆን የ1983 ዓመተ ምህረቱም ህወሓት የፈለገውን ጠርቶ ሌሎቹን ገፍቶ አገሪቷን ለብቻው በመቆጣጠሩ ካለንበት ውድቀት ጥሎናል፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ሌላ ውድቀት ለማስተናገድ የቀራቸዉ አቅም ይኖር እንደሁ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በያዝነው መንገድ ከቀጠልንበት ግን ሁላችንም ላለመውደቃችን ማንም እርግጠኛ አይሆንም፡፡ ትላንት የዓላማ ቢስ (የታክቲክ ስህተትን ጨምሮ) አብዮቶች ውጤት እንዲያጡ መሆናቸውን እያስታወስን ዛሬ ሁላችንም ካለንበት ሁኔታ የምንሻገርበትን ግብ በጥንቃቄ ልንመራው ይገባል፡፡
እንደ ቀደምቶቹ ሁሉ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስትም ከማንም ጋር የመወያየት ፍላጎት እንደሌለው ሰሞኑን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ስም እያደረገ ካለው ሽርጉድ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ አቋም ሊወገዝና ሊለወጥ ይገባል፤ በኢትዮጵያ ምድር የግለሰብ ወይም የጥቂት ቡድኖች አምባገነንነትን የአንድ ፓርቲ ወይም የፈላጭ ቆራጭ ንግስና ወይም የወታደር አገዛዝ ሥርዓት በመፍጠር ለመመስረት መፈለግ ነውርና ፀረ-ሕዝብነት ነው፡፡ እልቂት ከማስከተል ባለፈ ተግባራዊ ሊሆንም አይችልም፡፡ ለጊዜው መተግበር ቢቻል እንኳን ፈጽሞ ዘላቂነት ሊኖረው አይችልም፡፡
የአገሪቷን ያልተለወጠ የፖለቲካ ባህልና የልሂቃኑን የግጭት አፈታት ብቃት ማነስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ወዳለፈው የጨለማ ዘመን ለመመለስ የሚደረግ ሩጫ፤ የዜጎችን ተስፋ የማጨለም እንቅስቃሴና እየተፈፀመ ያለው የአብዮት ቅልበሳ ቆሞ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎ ሕዝባዊ መንግሥት በማቋቋም አገሪቷ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጭቆና ሽክርክሪት ወጥታ እንድትሸጋገር እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እጠይቃለሁ፡፡
ወለጋና ቦረና ባሉ ዘመዶቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው የጦር ወንጀልና በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በዜጎችና በጋዜጠኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው እስራትና እንግልትም በአስቸኳይ እንዲቆም የታሰሩም እንዲፈቱ ለዚህ ሕዝብ ነፃነት በወደቁት ኢትዮጵያውያን ስም እጠይቃለሁ፡፡
ክብር ለሰማዕቶቻችን !!
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ !! 
ኢትዮጵያ ለሕዝቧ ትመለሳለች !!
Filed in: Amharic