የህወሀት ሦስት መልኮች…!!!
ፍሬው አበበ
የምሥረታውን 45ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ዘንድሮ በየካቲት ወር ያሳለፈው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ አየሁት። ማዕከላዊ ኮሚቴው ከግንቦት 15 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው መጪውን ምርጫ ከፊታችን መስከረም ወር በፊት ለማካሄድ ቀደም ሲል በሥራ አስፈፃሚው የተሰጠው ውሳኔ ላይ ማህተም አሳርፏል። እግረመንገድም ብልፅግና ፓርቲ ላይ የተጠራቀመ ክፉ ምሬቱን አሰምቷል፤ የእርግማን ዶፍ አውርዷል። ደፈር ብሎ ጦርነት አውጆብኛል በማለትም ከሷል።
ይኸን የሚለው የትኛው የህወሓት ክንፍ ነው የሚለውን ለማየት የህወሓትን የቆየ ውስጣዊ አሰላለፍ መፈተሽ ይገባል። ህወሓት ቅርፊቱ ሲሰበር በዋነኛነት ሦስት መልኮችን ይዞ ብቅ ይላል።
ምድብ አንድ- የጠኔ ቡድን
ህወሓት የተነሳበትን ዓላማ ያልዘነጉ ትንታጎችን አቅፏል። ለነፃነት፣ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ… ሲሉ ውድ የህይወት መስዋእትነት የከፈሉ ታጋይ ወንድምና እህቶቹን ዋጋ ያልረሱ፣ በየጊዜውም አብዝተው የሚጨነቁ የሕሊና ሰዎችን ያቀፈ ነው። በየጊዜው “የተነሳንበትን ዓላማ ዘነጋን” ብለው ክፉኛ የሚያዝን፣ አብዝቶ የሚቆረቆር ነው። “የተዋደቅንበት፣ የደማንበት፣ የሞትንበት ዓላማ ወደየት አለ፣ ወደየት ሄደ?” እያለ ይጠይቃል፣ ጠብ ያለለት ነገር ግን የለም።
አነስተኛ ቁጥርን የሚወክለው ይህ ምድብ ከብዙሃኑ ጋር የትግል አንድነት መስመሩ መለያየቱ ብስጭትና ንዴት ውስጥ ከቶታል፤ ክፉኛ ጎድቶታልም። የዓላማ ሰው ነውና…. “ሌብነት ካልተያዙ ሥራ ነው፣ ከተያዙ ወንጀል ነው” በሚል አስተሳሰብ ከተበከለ የነቀዘ አመራር ጋር ሲጋጭ፣ ሲነታረክ… የሚውል ነው። ዘወትር “በሕግ አምላክ” ቢልም የሚሰማው ማግኘት ግን አልቻለም።
በዚህ ስብስብ የሚገኙት ሞጋችና ጠያቂ ሰዎች በመሆናቸው በከበርቴው ቡድን የተጠሉ ናቸው። ሁሌም በየግምገማው፣ በየስብሰባው “የድርጅታችን ዓላማ ከሽፏል፣ መንገዱን ስቷል…” በሚል በዚህ ቡድን አባላት የሚነሱ ቅሬታዎች፣ ትችቶች፣ የማስተካከያ ሃሳቦች በተለይ ለከበርቴዎቹ እንደመዝናኛ የሚወሰዱ እንጂ ከቁምነገር የሚጣፉ ሆነው አያውቁም።
የዚህ ቡድን አባላት ከዓላማ ቢሶች ጎን ባለመሰለፋቸው ብቻ ብዙዎቹ ሸሚዝ ለመቀየር እንኳን አቅም አጥተው፣ ደህይተው፣ የበይ ተመልካች ሆነው፣ በዚህ ላይ ተገፍተው ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው።
ምድብ ሁለት – ከበርቴዎቹ
ጠዋት ማታ በትግሉ ሰማዕታት ስም፣ በሕዝብ ስም የሚምል ግን ተግባሩ ተቃራኒ የሆነ ኃይል የተሰባሰበበት ነው። ነባሩ ታጋይ ጭምር በከተማ ብልጭልጭ ህይወት ተጠልፎ በበዛ ምቾት የሚንገላታበት፣ ራሳቸውን ወደ ከበርቴ መደብ ያሳደጉ ግለሰቦች የናኙበት ምድብ ነው።
ስለ ሕገመንግስት የበላይነት ሲያወራ ደጋግመህ ብታገኘውም ቅሉ አክብሮ ሲያስከብር አታየውም። ሕጋዊነት ኖሮት፣ ተላብሶት፣ ተግብሮ አታገኘውም። ስለዴሞክራሲያዊ፣ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ምርጫ አስፈላጊነት ሲደሰኩር አፍ የሚያስከፍት ቢሆንም ተግባሩ ግን በተቃራኒው ጎልቶ የሚታይ ነው። ሩቅ ሳንሄድ ይህ ምድብተኛ በአምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ “እኔና አጋሮቼ የፓርላማ ወንበር መቶ ከመቶ አሸንፈናል” ብሎ አገር ምድሩን ለማስጨብጨብ ብዙ ለፍቶ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ መቶ በመቶ መረጠኝ ያለው ሕዝብ በወራት ልዩነት አንቅሮ ሲተፋው ታየ፤ ይበቃሀል አለው። መቶ በመቶ ተጠየፈው፤ ፊት ነሳው።
ስብስቡ ሌላው የሚታወቅበት ገጹ “ተቀናቃኜ” ወይንም “ጠላቴ” ናቸው በሚል የሚጠረጥራቸውን፣ የሚፈርጃቸውን ኃይሎች በመጨፍለቅ ሰጥ ለጥ አድርጎ ስልጣኑን የማስቀጠል መርህ የሚከተል መሆኑ ነው። ለስልጣን ስሱ ነው፤ ሰጊ ነው፤ ጠርጣራ ነው። እናም ሰዎችን በትንሽ በትልቁ በመክሰስ፣ በማሳደድ አሳር ያሳያል። አንድ ወቅት ኢህአዴግ “እናትክን…” ብለህ ተሳድብሃል የሚል አስቂኝ ክስ ሁሉ መስርቶ መሳቂያ መሳለቂያ ሆኖ ነበር። አንዳንድ ወጣቶችን ደግሞ “በቃ” ብለሃል የሚል ክስም መስርቶባቸው ነበር። አዎ! “በቃ” ብዬአለሁ መብቴ ነው፣ “በቃ” ማለት የመናገር ነጻነት ውስጥ የሚያርፍ ሕገመንግሥታዊ መብት ነው፤ ወንጀል አይደለም ቢባልም በሐሰት ለማስፈረድ ያገደው አልነበረም።
በአጠቃላይ ይህ ምድብተኛ “ጠላቶቼ” ለሚላቸው እንቅልፍ የለውም። በብድርና በዕርዳታ የተገኘ የደሀ ሕዝብ ገንዘብ ይረጫል። ንፁሀንን ያሳፍናል፣ ያስራል፣ ይገርፋል፣ ይደፍራል፣ ያሳድዳል፣ ይገድላል/ያስገድላል። ሌላው ቀርቶ ዜጎች በፍርሀትና በሥጋት ሸሽተው በሄዱበት አገር ጭምር እግር በእግር እየተከተለ ለማደንና ለማሸማቀቅ እንቅልፍ አጥቶ ይሰራል።
በባህርይው ራሱን ወደከበርቴ መደብ ያስጠጋ ፈላጭ ቆራጭ ነው። ሙስናና ብልሹ አሰራር መገለጫው ሆኗል። ከገቢው በላይ ሐብት ከማፍራት አልፎ በአገሪቱ ትልልቅ ቢዝነሶች ጀርባ ስሙን በጉልህ የፃፉ ደፋሮችን ሰብስቧል።
በተሾሙ ማግስት ሰርቀው እንደገና የባለሀብትነት ካባ ደርበው ብቅ የሚሉ የትናንት ካድሬዎች የሚደገፍ ቡድን ነው። እንደገናም በከፈቱት የግል ድርጅት ጀርባ ተንጠላጥለው የመንግሥት ተቋማት ጨረታ በኔትወርክ ጠራርገው የሚወስዱ፣ ትናንሽ ሹመኞችን ጭምር እያባበሉ ሙስና ውስጥ የዘፈቁ፣ ከራሳቸው ጥቅም ባሻገር ለሌላው ወገን ደንታ የሌላቸው ጥቅመኞች የተሰገሰጉበት ምድብ ነው።
ቡድኑ ሌላው የታወቀው በጎጥ፣ በአምቻ ጋብቻ፣ በዘመድ እና በእከክልኝ ልከክልህ ስሌት የፖለቲካ ሥልጣን በማከፋፈል ነው። ከመታበዩ ብዛት ራሱን እንደምትክ የለሽ የሚመለከት ኃይል ነው። አፍ አውጥቶ “እኛ የሌለንበት አገሪቷ ትፈርሳለች” አጀንዳ በየቀኑ ሲያራግብ የሚውል የሚበዛበት ነው። ሲበዛ የነቀዘ ኃይል በመሆኑ የመጨረሻ የሥልጣን ጥማቱን ለመወጣት የትኛውንም አይነት ይጠቅመኛል የሚለውን አማራጭ ያለማንገራገር ይጠቀማል። አንድ ወዳጄ እንዳለው ኮሮና አፍ ቢኖረው አብሮ ከማሴር ወደኋላ አይልም። ሥልጣን ጥማቱ ገደብ የለሽ በመሆኑ ከአገሪቱ ጠላቶችም ጋር ቢሆን ከመደራደር ወደ ኋላ የሚመለስ አይደለም።
በየጊዜው እያደገ መጥቶ ከድርጅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል ተከማችቶበታል። ከምንም በላይ የሚያሳዝነው ጥቂት የማይባሉ ጎምቱዎቹ ታጋዮች ጭምር የዚህ ምድብ ፊት አውራሪ መሆናቸው ነው።
ምድብ ሦስት – የወላዋዮቹ ቡድን
ወደየትኛው ቡድን እንደሚጠቃለሉ ግራ የተጋቡ አባላት የበዙበት ነው። አንዳንዶቹ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ሰልፍ በቅጡ ያልገባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ዕድሉን ያላገኙ፣ ግን ነገ ተነገወዲያ ልናገኝ እንችላለን በሚል ምራቃቸውን የሚውጡ ተስፈኞች በመሆናቸው የከበርቴውን ኃይል አብዝተው ተለማማጭ ናቸው። ምድብተኞቹ ብዙውን ጊዜ በአንደኛው እና በሁለተኛው ምድብ መሀል የሚንቀዋለሉ ሲሆን አመቺ ሁኔታና ጊዜ ሲያገኙ ወደተመቻቸው ምድብ በቀላሉ የሚሸበለሉ አይነት ናቸው። ለጊዜው በሁለቱ ምድብ ውስጥ ቋሚ ተሰላፊ ባለመሆናቸው እንደ አየሩ ሁኔታ ቆዳቸውን እየቀያየሩ በመጫወት ይታወቃሉ። ያው ከያኒው እንዳለው “ ሲታሰር ወደእኔ፣ ሲፈታ ወደእሱ..” መኾኑ ነው።
እንግዲህ እነዚህ ሦስት ኃይሎች ህወሓት ላይ ተጣብቀዋል። በአንድነት ለመቆም የሚያስችላቸው ጊዜያዊ ጠላት እየፈጠሩ እስከዛሬ የተጓዙ ናቸው። እናም አሁንም ይህ ኃይል ጠላት ፍለጋውን በርትቶ ቀጥሏል።
እነሆም የጠ/ሚ ዐብይ አሕመድን አስተዳደር በጠላትነት ከመፈረጅ አልፎ “ጦርነት አውጆብኛል” የሚል አዲስ ክስ ወደማሰማት ተሸጋግሯል። አዎ!.. ሦስቱ የማይታረቁ ምድብተኞች በአንድ ላይ ለመቆም የጋራ የሚሉት ጠላት ይፈልጋሉ። ያለጠላት ብቻቸውን መቆም አይችሉም። ቢሞክሩም በቶሎ እንደሚፈራርሱ ቀድሞውኑ ገብቷቸዋልና ፍለጋውን ቀጥለዋል።
የአዲሱ ክስ ፍሬ ነገር ምንድነው?
የህወሓት ሰዎች ቅሬታ ምንጩ ግልጽና አንድ ነው። ባለፈ ጥፋት ለምን ተጠየቅን፣ ለምን ተነካን የሚል ነው። ሌላው ከቁልፍ ኃላፊነቶቻችን ለምን ተነሳን ነው። ሲጠቃለል “በጠ/ሚ ዐብይ ተከዳን” ወደሚል መደምደሚያ ይወስዱታል። ይህ መነሻ ይሁን እንጂ ቅሬታቸውን ወደሕዝብ ለማሸጋገር ምክንያቱ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ፍለጋ ብዙ ርቀት ሄደዋል።
ለዓመታት ሲያነሱት፣ ሲጥሉት የነበረው የኢህአዴግ ውህደት አጀንዳ በጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደትግበራ ሲገባ ምንም እንደማያውቁ እጥፍ ብለው በተቃራኒው የቆሙት ጠብ ያለህ በዳቦ ለማለት ነበር።
የታሰበውን ያህል መራመድ ተሳነው እንጂ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ትናንሽ ግጭቶችን ስፖንሰር ለማድረግ ተሞክሮም እንደነበር በተደጋጋሚ የተነገረ ነው። ጎረቤት አገር ኤርትራ ውስጥ እጅን አስረዝሞ ለመክተት የተደረገው ሙከራ አከርካሪውን በመመታቱ ሊመክን ቻለ እንጂ ዳፋው ለአገር የሚተርፍ ነበር።
አሁን ደግሞ የምርጫ አጀንዳ ተመዟል። የሕዝብ ጤና ጥበቃ ገደል ይግባ የተባለ መስሏል። ከምንም በላይ ላለፉት አምስት ዙር ምርጫዎች ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በተግባር ማካሄድ ዳገት የሆነበት ኃይል፤ ዛሬ ስለነጻና ዴሞክራሲዊ ምርጫ መምህር ሆኖ ብቅ ማለቱ የዓመቱ ታላቅ ስላቅ ሆኗል። ላለፉት ዓመታት ሕገመንግስቱን ጢባ ጢቢ ሲጫወትበት እንዳልኖረ ዛሬ ራሱን የሕገመንግስት ጠበቃ አድርጎ ለፋፊ ሆኖ ብቅ ሲል ሀፍረት የሚሉት ነገር በአጠገቡም አለማለፉ ይገርማል። ህወሓት ሲሻው ትናንት ያለበቂ ምክክርና የሕዝብ ተሳትፎ ሕገመንግስቱን በሚፈልገው መልክ ማሻሻሉን እየረሳ ዛሬ ላይ አይነኬ ነው የሚል ነጠላ ዜማ ያሰማናል።
በሰሞኑ መግለጫው እንዲህ ብሏል። “…ብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሃገራዊ ምርጫ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ- መንግስታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠ/ሚ/ሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል።
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለ በቂ ዝግጅትም ሆነ ያለ ግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠ/ሚ/ሩ ከህግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበትን መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግናን ህገወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል። አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው አካል የተጀመረውና ሕገ-መንግስትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል…” ይለናል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቅርብ ስለህወሃት ምርጫ ማካሄድ ጉዳይ ከመገናኛ ብዙሃን አስተያየት ተጠይቀው ነበር። “…ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ አስበው ከሆነ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም። ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንም ካሉ በኋላ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 የተቋቋመው እርሳቸው የሚመሩት ምርጫ ቦርድ በፌዴራል፣ በክልል እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የማስፈጸም ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ ውጪ የክልል መንግሥታትም ሆኑ የፌዴራል አስፈጻሚ አካል ተነስቶ ምርጫን በተመለከተ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ሕገ- መንግሥታዊ አይሆንም ብለዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽን ዓለምን እያመሰ ባለበት በዚህ ወቅት እነሱ ከዓለም ተነጥለው፤ ሳይንሳዊ ባሉት የእነሱ መንገድ ምርጫ እናካሂዳለን ብሎ አንድ የልዩነት መንገድ ወደማበጀት ተሸጋግረዋል። እናም ህወሓት ቆሜለታለሁ ከሚለው ሕዝብ በላይ የቱን ያህል የፖለቲካ ሥልጣን እንደሚበልጥበት እነሆ በተግባር አሳይቷል።
በመጨረሻም
ምንም ይሁን ምን የእስከዛሬው የፍረጃ፣ ጠላትነት፣ የመበላላት..ፖለቲካችን እንዲቀጥል መፍቀድ ወደኋላ ከመመለስ ያለፈ ፋይዳ ያለው ነገር አይኖረውም። ወደፊት ለመራመድ ህወሓትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ከሴራ ፖለቲካ ርቀው በቀናነት ሊንቀሳቀሱ፣ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ የግድ ነው።
በሌላ በኩል እንዲህ አይነት መካከሮች ለመቅረፍ የፖለቲካ ውይይቶች መቀጠል መቻል አለባቸው። ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በሰለጠነ መንገድ በመወያየት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን እና አለመግባባቶችን መፍታት ከፖለቲካ ኃይሎች ይጠበቃል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከግትር አስተሳሰብ መላቀቅ አለባቸው። በጉልበት መለካካት ወደሥልጣን ለመሳብ ማለም በዚህ በሰለጠነ ዘመን የሚታሰብ አይደለም። ውጤቱም ጥፋትና እልቂት እንጂ ሠላምና መረጋጋት ሊሆን አይችልም። በተለይ ህወሓቶች ሁሉንም ነገር ጭለማ አድርጎ ከመሳል እንዲሁም እኛ የሌለንበት ሌቱ አይነጋም አይነት ጨዋታ ወጣ ብለው ለአገራዊ ጉዳይ በትብብር ለመስራት ሊዘጋጁ ይገባል።