>

 “የግፍ ምድር”  (ጌታቸው አበራ)

 “የግፍ ምድር”

      (ለጆርጅ ፍሎይድ እና በዘረኞችና በግፈኞች 

   በየጊዜው ውድ ህይወታቸውን ለሚያጡ ጥቁር ወንድሞቼና እህቶቼ መታሰቢያ)

 

ጌታቸው አበራ


ቅድማያቶቹ በሰንሰለት ጥፍረው በመርከብ ሲያሸጋግሩ፣

አያቶቹ ቋንጃ ሰብረው በስቅላት ገመድ ሲያንጠለጥሉ…፤

ጭካኔያቸው ዘመን ተሻግሮ ስልጣኔ እንኳን ሳያግደው፣

ከትውልድ ትውልድ ቀጥሏል የጥቁር ነፍስ ምናቸው፤

… የልጅ ልጃቸው ደግሞ ዛሬ የግፍ ዘዴውን ቀይሮ፣

የጥቁር ነፍስ ይቀጥፋል..”ጉልበት በአንገት” ሰድሮ፤ 

ከሰማየ-ሰማያት ዘልቆ – የ’አቤል’ ድምጽ ይጮኸል፣

ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነት – ለእህት ለወንድሞቼ ይላል፤

በዘረኝነት ‘ጉልበት’ በእኩዮች ጥይት ትንፋሻቸው ላጠረ፣

ከጽንፍ-አጽናፍ ተጠራርቶ ሥልጡን ያለም ሕዝብ ዘመረ፤

በታላቁ የሕዝብ መሪ በማርቲን ሉተር ኪንግ ቃለ-ሕይወት፣

‘ጨለማ በጨለማ አይገፈፍም፣ በብርሃን እንጂ በድምቀት፣

  ጥላቻም በጥላቻ አይወገድም፣ በፍቅር እንጂ በእውነት፣’

ብሎ አስተጋባ እስከ ዓለም ጫፍ ሰብአዊ ፍጡር በኅብረት፤

ሰላም፣ ፍቅር፣ እኩልነት፣ ፍትህ… በምድራችን እስኪናኙ፣

ይቀጥላል ትግሉ ተጠናክሮ፣ የሰው ልጆች በእኩል እስኪዳኙ!

 

Filed in: Amharic