>
11:14 am - Saturday June 3, 2023

አማራ ባንክን የበላ ጅብ አልጮኸ አለ! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

አማራ ባንክን የበላ ጅብ አልጮኸ አለ!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


“እኔውም ዕብድ ነኝ ከወፍ የገበየሁ፤ መቀመጧን እንጂ መብረሯን የት አየሁ” ይሉ ነበር የቀድሞ ሰዎች – እንደኔው ያለ የቀባጭ ምቸውን ሲቀምሱ (‹ሣ›ን አጥብቁልኝ ታዲያ)፡፡ ውጣ ያለው ገንዘብ ግድግዳ ሲቆፍር ማደሩ የሚነገረውም ብዙውን ጊዜ እውነት ነው፡፡ የኔንማ ነገር ተውት – ዕርሟን ቡና አፍልታ ጀበናውን ሙሉ አተላ እንዳደረገችው አላዋቂ ሴት ዕርሜን አክሲዮን ብገባ ሹዋሹዋ ተሠራሁ፤ ጠጠቱ በማይለቅ ንዴት እየተንጨረጨርኩ አለሁ፡፡

ኧረ ይሄ የጉግማንጉጎች የላቦራቷር ፍጡር ኮርዬ ጉድ እያፈላ ነው! ዛሬ ብቻ 142 ሰው በቫይረሱ መያዙ ሲረጋገጥ 3 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ ፡፡ ደረጃችንም ወደ 103ኛ ወጣ፡፡ ይሄኔ በሀብት በሥልጣኔ ምናምን ቢሆን ኖሮ ወደ ውራነት በወረደ ነበር፡፡ በዚህችም የቀናብንን እንጃ ከደህና ደረጃ ወደ መጥፎ – ወደ ደህና መጥፎ ደረጃ እያዘቀዘቅን ነው፡፡ በቃችሁ ይበለን፡፡ ለነገሩ ኮሮና እንኳን ጊዜያዊ ጫጫታ ፈጥራ ለሌላ የባሰ ውርጅብኝ አጋፍጣን ነው የምትበርደው – (እየተባለ ሲወራ ሰማሁ ልበል?)፡፡ ባለፈው አንድ ጦማሬ ኮሮና ወደ ኢትዮጵያ እንደማይገባ በጥቅስ ቢጤ ጠቆም ማድረጌ ይታወሳል፡፡ እርግጥ ነው – የመንደር ሌባ “ቤታቸውን ከፍተው ሰው ሌባ ይላሉ” እንደሚለው በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገና ኅሊናቸውን ለገንዘብ የሸጡ ሆዳም ዜጎች ታማሚን ሳይቀር ከማቆያ ቦታዎች በጉቦ እያስወጡ ከለቀቁ እኛ እንጨት ወይም ድንጋይ አይደለንምና መያዛችን አይቀርም፡፡ ይህም ሆኖ ጥቂት ሽዎች ያሏት ሀገር ብዙ ሽዎችን በቫይረሱ ስታጣ 115 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ 17 ብቻ ማጣቷ እንደማነጻጸሪያ የነገር ማዋዣ አድርጌም ቢሆን እንደዋዛ የተናገርኩት ነገር እውነትነት የሚያጣ አይመስለኝም፡፡ (አሁን ይህን ደብዳቤ ልልክ ስል ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የተያዘው ሰው ቁጥር ከምንጊዜውም በልጦ 150 ሲሆን የሟቹ ቁጥርም በአንድ ጨምሮ 18 ደርሷል – ደረጃችንም 101ኛ ሆኗል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ቡሃ ላይ ቆረቆር፡፡ በዚህ ድህነታችንና በዚህ የሙስና ዘመን ይህ ክስተት ትልቅ አደጋ ነው፡፡)

በሌላ በኩልም ቢናገሩት ለሚያሳፍር አንድ ጥያቄ እማሆይ የሰጡትን መልስ ማስታወስ ተገቢ ነው – “ሲያጎርሱት የማያላምጥ የለም” ብለዋል አሉ በአሽሙር መልክ፡፡ ኤርትራ እንኳን በአቅሟ ነፍስ አውቃ አልቀበልም ያለችውን የ666 ፊታውራሪዎች እነጃክማ በህክምና መሣሪያዎችና በፊት መሸፈኛ ጭምብሎች በዓለም ዙሪያ የሚያዛምቱትን ቫይረስ ከነኮተቱ አቢይና ግብረ አበሮቹ እየተቀባበሉ አፍሪካንና መላዋን ኢትዮጵያ ለማዳረስ ቆርጠው ከተነሱ ለአንድዬ ከመጮኽ ውጪ ለጊዜው ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ የሀገራችን 65 ሀኪሞች በቫይረሱ የተያዙት ከጥንቃቄ ጉድለት ሳይሆን በህክምና አልባሳት ሆን ተብሎ በነቢልጌትስ በሚሰራጭ ኮሮና ቫይረስ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ ተናግረናል፡፡ ምሥጢራውያኑ ድርጅቶች ጦርነቶችንና ፍብርክ በሽታዎችን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ከሲሶ በላይ የሚሆነውን የዓለምን ሕዝብ ፈጅተው የራሳቸውን የሰይጣን መንግሥት ለመመሥረት ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሰው ወደ ትግበራው መግባታቸውን ካነበብነውም ከሰማነውም እያጣቀስን አንዳንዶቻችን ሰሚ አጣን እንጂ ብዙ ለፍልፈናል፡፡ ሰይጣን በተፈጥሮው ሰዎችን ማዘናጋትና ማደደብ ዋና ሥራው ስለሆነ ብዙው የሀገራችንና የዓለማችን ጎጋ ዜጋ አልገባውም፤ እንደስካሁኑ ሁኔታ ከሆነ ደግሞ አይገባውምም፡፡ ከመጋረጃ በስተጀርባና አሁን አሁን ደግሞ በማን አለብኝነት በግልጥ እየተሠራ ያለውን ለሚገነዘብ የዓለም ፍጻሜ መቃረቡን ብቻ ሳይሆን በውስጡም እንዳለን መገንዘብ አይሳነውም፡፡ “ኢትዮጵያዊ አባት አ(ስ)ምጦ የወለዳትን ልጁን ደፈረ”፣ “እናት የገዛ ልጇን አፍቅራ አባቱንና ባሏን በመግደል/በማስገደል ከልጇ ጋር ተጋባች”፣ “ወይንሸትና ጫልቱ 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ጠ/ሚኒስትሩና የካቢኔ አባሎቻቸው በተገኙበት በጁፒተር ሆቴል በድምቀት አከበሩ” … መባልን የሚሰማ ጤነኛ ሰው “በዚያን ዘመን ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ወሬ ከያቅጣጫው ትሰሙ ዘንድ ግድ ነው” የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት ትዝ ሊለው እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ እንደዚህ ያለ ሀገር ውስጥ  “አባት ወንድ ልጁን አግብቶ መኖር ጀመረ”፣ “ጆንሰን ከሚወዳት ፈረሱ ጋር ህጋዊ ጋብቻ መሠረተ”፣ “ቤኪ ከልቧ ከምታፈቅረው ውሻዋ ጋር ዘመድ አዝማድ በተገኘበት በተክሊል ተጋባች”፣ “የትናንትና ማታው የቡድን ወሲብ (orgy) ግሩም እንደነበር ተሳታፊ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ሳይቀሩ መሰከሩ” … ልቀጥል? የዐዋጁን በጆሮ እኮ ነው፡፡ እናስ እነአቢይ ትሰማላችሁ? የጌዮችና የሌዝቢያኖች መብትም መከበር ያለበት መብት ሆኖ ልክስክሱና ለዲያብሎስ አጎብዳጁ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሽርፍራፊ ገንዘብ ኅሊናውን በመሸጥ ምን እየሠራ እንደሆነ በተለይ ከመምህር ደረጀ ነጋሽ የዘወትር ልፋትና ድካም እየተገነዘብን ነው – መምህር ደሬ እግዚአብሔር በሰማይም በምድርም ዋጋህን እንዲከፍልህ እጸልያለሁ፡፡ እነአቢይ ግን በሩ ሳይዘጋ ቶሎ ይመለሱ – የቀራቸው እኮ ቤተ መንግሥት መግቢያ በር ላይ የሦዶማውያንን ዓርማ መስቀልና ህገ መንግሥቱን በማሻሻል የተመሳሳይ ፆታን ጋብቻ ማጽደቅ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን በገንዘቡ ኢትዮጵያን እንደልቡ እየፏለለባት ነው፡፡ መጨረሻውን ላዬ! የዚህ ጦርነት ውጤት በጣም ግልጽ ቢሆንም ጉዳቱ ግን ቀላል እንዳልሆነ እየታዘብን ነው፡፡ 

በዚህ በዶክተር አቢይ ላይ ደግሞ እነጌታቸው ጅጌ ሲዘምቱበት በሶሻል ሚዲያ አየሁ – ምድረ ሥልጣን ወዳድና ምድረ የግብጽ ዘሕወሓት ቅጥረኛ የሰማውን እንጃለት ሰሞኑን ዕረፍት አጥቷል – እንደቀትር እባብ መቅነዝነዝ አብዝቷል፤ አንዱ ሲያርፍ ሌላው እየተነሳ መወሻከቱንና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባላ ዲስኩሩን በሚዲያ ማቀርሸቱን ተያይዞታል – በኢትዮጵያ የፖለቲካ ካባ ተጀቡኖ “ስለአባይ ግድብ አያገባኝም” እስከማለት የደረሰ ፕሮፓጋንዳ መስማት በርግጥም የት እንዳለንና ወዴት እየሄድንም እንዳለን ያስጨንቃል፡፡ … አቶ ዶክተር ጌታቸው ራሱ ማይም ሆኖ ሰውን አልተማረም ሲል አያፍርም፡፡ ልንገርህ – ይሄ ጀዝባ ዶክተር ነኝ ባይ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ሸሽቶ በኤርትራ ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ በማያውቀው እንግሊዝኛ በተደጋጋሚ “In generally…” እያለ ከአንድ ዶክተር በጭራሽ በማይጠበቅ ሁኔታ እንግሊዝኛውን በእግሩ ሲያስኬደው እየሰማን እንኳን ስለርሱ ዶክትሬት አልተመራመርንም፡፡ (ይህን ስል ግን አቢይ ዶክተር ይሁን አይሁን የሚያገባኝ ሆኖ ወይም ለርሱ ጥብቅና ለመቆም ፈልጌ አይደለም) – እንግሊዝኛን ካነሳሁ ዘንዳ ደግሞ ይህ ቋንቋ ከዘመኑ ምሁራን ከአብዛኛዎቹ ጋር ኩርፍ ነው መሰለኝ አብዛኛው ሳይማር የተማረ ምሁር ሲሞላፈጥበት ነው የምናይ፡፡ ግን የራስን ጉድ በክርታስ ወረቀት ሸፍኖ ስለሌላ ሰው ገመና ማውራት ስለሚደብር ነው የጌች ነቀፋ የሚያስጠላኝ፡፡ አያስጠላም ጓዶች? ደግሞስ አቢይ ኦሮሞ ሆነ አልሆነ ከጠ/ሚኒስትርነቱ ጋር ምን ያገናኘዋል? አቢይ ካዝኪስታናዊ ወይም የመናዊ ቢሆን እርግጥ ነው ለምን ብሎ መጠየቅ ይቻላል  – ካለሀገሩና ካለዜግነቱ በህገ ወጥ መንገድ ተሾሞ ከሆነ፡፡ አንድን ኢትዮጵያዊ “ኦሮሞ አይደለምና ከቤተ መንግሥት ይውጣልን” ማለት ግን በትንሹ ዕብደት ከፍ ሲል ደግሞ የቁም ተዝካር የሚያስወጣ የቁም ሞት ነው – ስሰማው  በኢትዮጵዊነቴ ብቻ ሳይሆን በሰውነቴ እንዴት በሀፍረት እንደተሸማቀቅሁ አትጠይቁኝ – ደግሞም ያን የፈረደበት “ዶክተር” የሚል ቅጥያ መያዙ ይበልጥ ያናድዳል፡፡ ይህ ሰው ሚስት ካለችው አፍራበት ልክ እንደጆርጅ ፍሎይድ ሚስት ወዲያውኑ ነበር መፍታት ያለባት – አሁንም ትፍታው! እንዲህ ያለ ሙትቻ ምን ይሠራላታል? (ፐ! በሰው መፍረድ ግን እንዴት ቀላል ነው?)  ግን ግን ፖለቲካና ዘረኝነት እስከዚህን ያከረፋል – ማነው ያደነቁራል ልበል? ግዴላችሁም የአቢይ ስም ከመቶም ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ አንዱ ራሽያዊ ደግሞ ነገ ይነሣና “የአቢይ ትክክለኛ ስም ዶስቶቪስኪ ሮማኖቪስኪ ሮማኖቪች ነበር፡፡ አባቱም አቢይ ልጅ እያለ ከሶቭዬት አሰውጥተው ወደ ጋምቤላ ልከውት ነው ስሙ ‹ኡጅሉ ኢቦንግ ቱምክ› የተባለው፤ አሁን ደግሞ አብዮት ካሳዬ በላይነህ አስባሉት” ማለቱ አይቀርም፡፡ አሁንስ ይሄ አቢይ ያሳዝነኝ ገባ! አንዴ በስም፣ አንዴ በአምባገነንነት፣ አንዴ በአስመሳይነት፣ አንዴ በገዳይ-አስገዳይነት፣ አንዴ በሥልጣን አፍቃሪነት፣ አንዴ በውሸታምነት፣ አንዴ በታሪክ በራዥነት፣ አንዴ በጴንጤ ወጋኝነት፣ አንዴ በኦሮሞነት፣ አንዴ በአማራነት፣ አንዴ በትግሬነት … ብቻ የማይከሰስበት ወንጀልና ጥፋት የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምናልባት እንደመንጌ ዓይነት ኮምጨጭ ያለ አመራር ሳይሆን አይቀርም፤ ሁሉንም ለማስደሰት ፈልገህ የአመራር ቅኝትህን ካስተካከልክ አንዱንም ሳታስደስት ከሁሉም ጋር እንደተላተምህ ትኖራለህ፡፡ ሁሉንም ለማስደሰት የሚጥር ሰው ደግሞ አንደበቱ ከሀሰት ንግግርና ግብሩ ከባዶ ተስፋ ጋር የቆረቡ ስለመሆናቸው ጥርጥር አይግባህ፡፡ የመቀሌውን ወያኔ ተመልከት፤ አቢይንም እይ፡፡ ብዙ እምናገረው ነበረኝ፡፡ ግን አንድዬ ዕድሜ ከሰጠኝ በሌላ ጊዜ ልመለስበት ቀጠሮ ልያዝና ወደገደለው ልግባ፡፡ …

በዚያን ሰሞን በምሥረታ ላይ እንደሚገኝ ሲነገር ሰማሁና ከነበረኝ መናኛ አንጡራ ገንዘብ ለፓናዶል መግዣ ብቻ ትንሽዬ ሣንቲም አስቀርቼ በቀረው ወደ 30 የሚጠጉ አክስዮኖችን ገዛሁ – በምሥረታ ላይ እንደሚገኝ በተገለጸው አማራ ባንክ፡፡ በወቅቱ የአክሲዮን ግዢው አራት ቢሊዮን አምስት ቢሊዮን ገባ እየተባለ ሲነገር ስለነበር ከገንዘቡ ይልቅ ቁጭቱ ከንክኖኝ እኔም ወጉ ደርሶኝ አክሲዮን ብገዛም እስካሁን ድረስ በመንግሥት ይሁን በአስተዳደር ችግር ባንኩ ሊመሠረት አልቻለም፡፡ የገንዘብ ችግር እንዳይባል ከማንም ሌላ ባንክ የምሥረታ ታሪክ የገንዘብ መጠን ቢበልጥ እንጂ አያንስም (እየተባለ ነው)፡፡ የአማራ ነገር አያሳዝንም? የት ይሂድላቸው?

እናስ ታዲያ ችግሩ ምንድን ነው? አማራ ጋ ሲደርስ ሁሉም ነገር እረብ እሚለው ለምን ይሆን? ኮከቡ ነው ወይንስ የ40 ቀን ዕድሉ? ሙስና ነው ወይንስ የመንግሥት ተፅዕኖ? የባንኩ አመራር ችሎታና ብቃት ማነስ ነው ወይንስ ሌላ የማናውቀው ችግር አለ? በአሁኑ ወቅት እርግጥ ነው ይሄን የፈረደበትን ኮሮና እንደምክንያት ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል፡፡ ኮሮና ከመጣ ግን ጥቂት ወራትን ነው ያስቆጠረው፡፡ ችግሩ የጀመረው ከኮሮና በፊት በመሆኑ ይህን ምክንያት መስጠት ውኃ አያነሳም፡፡ ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ መሆኑን ማንም ይረዳዋል፡፡

ለምን በሕዝብ ገንዘብ ይጫወታሉ? ያጋጠማቸው ነገር ካለ ለምን አይገልጹልንምና ቁርጣችንን አያሳውቁንም? ቁርጥ ያጠግባል፡፡ የሚመለከተው አካል በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መልስ እንዲሰጥበት መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ያንን ባንክ ለማቋቋም እኔን መሰል ዜጎች ያለንን ብቻ ሳይሆን የሌለንንም ጭምር ከየትም ቧጥጠን የከፈልነው ተመችቶን አይደለም ተናደን እንጂ  – ሰፊው የአማራ ሕዝብ በጠላቶቹ ሤራ ሳቢያ ያለበትን ድቅድቅ ጨለማ ስለምናውቅ ያንን የዘመናት አፈና “የተበቀልን” መስሎን፡፡ እንደ አካሄድ ደግሞ አንድ ሰው ሁለት ነገር ሊኖረው አይችልም – በሙስና ላይ መናደድ ከዚያም መጻፍና ማጋለጥ በአንድ በኩል ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ ያልደከሙበትን ገንዘብ ማካበትና በየካምፓኒው አክሲዮን በመግዛት በሀብት መንበሽበሽ በሌላ በኩል፡፡ ንጹሕ ኅሊናና ሀብታምነት ለየቅል ናቸው፤ ኅብረት የላቸውም፡፡ የድሃን ገንዘብ ቀምቶ እንዳይንቀሳቀስና ጥቅም ላይ እንዳይውል ማሰር ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ለማንኛውም ምሥጢሩን ለሚያውቅና አንዳች ተስፋ ያለው ነገር ሹክ ለሚለኝ ወገኔ አድራሻዬ ይሄውና – ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic