>

ኮሮናን ድንክዬ ያደረገው የ‹‹ዘረኝነት ወረርሽኝ›› (ከይኄይስ እውነቱ)

 

ኮሮናን ድንክዬ ያደረገው የ‹‹ዘረኝነት ወረርሽኝ››

የአገር ቤት ‹‹ዘረኞች››/ጐሠኞች የት ናችሁ?

ከይኄይስ እውነቱ


ሰሞኑን ዓለምን ያናወጠ የዘረኝነት ድርጊት በምድረ አሜሪካ ተፈጽሞ ዓይተናል፡፡ በአፍሪቃ አሜሪካውያን ላይ ሲፈጸም የቈየው ዘረኝነት፣ መድሎ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የመጣ ድንገተኛ አይደለም፡፡ ይህ ጥቁሮችን ከሰው በታች የመመልከትና በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ግፍ በደል መፈጸም ሥር የሰደደ ሥርዓታዊ፣ መዋቅራዊ/ተቋማዊ ዘመናትን የጠገበ – የምዕራቡ ዓለም ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በአሜሪካ የሚታይ – የዘመናችን አስጸያፊና አሳፋሪ ጠባሳ፣ የሰው ልጅ ኋላ ቀርነት፣ የግብረገብነትና የሥነምግባር ዝቅጠት፣ የድንቁርና ጥግና እና የባሪያ ፍንገላ ቅሪት ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የነጮችን ዘር የበላይነት የሚያነግሥ ዓለምአቀፋዊ ሥርዓት አንድም አዲሱ የናዚ አስተሳሰብ መገለጫ ነው፡፡ ‹‹ትምሕርትና ሥልጠና›› ያላረቀው ጥቂት የማይባሉ የፖሊስ ሠራዊት አባላት አረመኔነትም የዚሁ የዘር መድሎ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ 

እኛ ኢትዮጵያውያን በገበታችን ላይ ግዙፍ ችግሮች እንዳሉብን ይታወቃል፡፡ የችግሮቻችን ዋና ማጠንጠኛውም በሕግ፣ በመንግሥት መዋቅር/ተቋማት የሚደገፈው ጐሠኝነት ነው፡፡ የዘረኝነት ሌላው ገጽታ ነው፡፡ ከውጭው ዓለም የቆዳ ቀለም ዘረኝነት አንፃር በተቀደሰችው የኢትዮጵያ ምድር የተዘራው የጐሠኝነት እሾህና አሜከላ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜን አስቈጥሯል፡፡ ዕድሜው ጨቅላ ቢመስልም ያስከተለው ጥፋት ግን የአገርን ህልውና እና የሕዝባችንን አብሮነት በእጅጉ ተፈታትኗል፡፡ ይህን መርዘኛ አስተሳሰብ ከሚያራምዱትና ተከታዮቻቸው በስተቀር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በየትኛውም አካባቢ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ኢፍትሐዊነት በራሱም ላይ እንደተፈጸመ የሚቈጥር ነው፡፡ ሰብአዊነት፣ የአዳም ልጅነት፣ በአርዓያ ሥላሴ መፈጠራችን ያስተሳስረናልና፡፡ ስለዚህም ይህንን በምድረ አሜሪካ የተፈጸመ አውሬነት አጥብቀን እናወግዛለን፣ እንቃወማለን፡፡ ጊዜው የከፋ ባይሆን፣ መንግሥት ቢኖረን፣ ጐሠኝነት ባይሠለጥንብን፣ ጐሠኛው ሥርዓት ያፈራቸው ጨካኝና ደናቁርት ‹ፖሊሶች› በአዲስ አበባም ሆነ በየክፍላተ ሀገሩ ባይሠለጥኑብን መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ መስመር በይፋ፣ ሕዝብ ደግሞ በሰላማዊ ሰልፍ ከተገፉት ጥቁር አሜሪካውያን ጎን በመቈም ኅብረታችንን በግንባር ቀደምትነት ማሳየት የሚገባን ነበርን፡፡ ለምን? የፀረ ቅኝ ግዛት፣ የፀረ ፋሺስት ተጋድሎ የተጀመረባት እና ለጥቁር ሕዝቦች ኹሉ ነፃነት፣ ኩራት ምልክት የሆነው የዓድዋ ድል ባለቤቶች ነንና፡፡ 

ባንፃሩም መላው አፍሪቃን በኅብረት ለማቀናጀት የተቋቋመው የአፍሪቃ ኅብረት ዝምታ በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ በድርጅቱ ስም የወጣ መግለጫ አላየሁም፤ አልሰማሁምም፡፡

ዛሬ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ሕዝቦች ገዳይ ወረርሽኙ አእላፍ ሕዝቦቻቸውን በገፍ እየጨረሰ ባለበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ዘረኝነትን ለመቃወም ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን ለሞት አጋልጠው ዐደባባይ ወጥተዋል፡፡ ሥር በሰደደው ዘረኝነት ከሰው በታች ከመኖር ይልቅ ኃላፊው ወረርሽኝ የሚያደርስባቸውን አደጋ በጸጋ ተቀብለው ዘረኝነትን እምቢ እያሉ ነው፡፡ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ሰብአዊነት ከነሙሉ ክብሩ ለማስጠበቅና በነፃነት ለመኖር ሲሉ የመንግሥታት አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጆችን ጥሰው፣ አስፈሪውን ኮሮና አኮስሰው፣ በሠራዊታቸው ብዛት የሚመኩ ኃያላንን ተጋፍጠው፣ ሰብአዊ ክብርን አስቀድመው፣  አሁንም ባደባባይ ሲተሙ ይስተዋላል፡፡

ሀገር-በቀሎቹ ‹ዘረኞች›/ጐሠኞች በቋንቋ ልዩነት ብቻ የአገሩን ባለቤት ሕዝብ ቁም ስቅሉን ያሳያችሁት በቀለም የተለየ ቢሆን ምን ታደርጉት ነበር? እንደ ‹ፈጣሪያችሁ› ወያኔ ዐረፍተ ዘመናችሁ እስኪገታ ልባችሁን አደንድናችሁ ትዘልቃላችሁ? ይህንንም ባገርና ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለ ነውር እንደ ‹መልካም ውርስ› ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ማስተላለፍ ትፈልጋላችሁ? እናንተ በጐሠኝነት የማታምሷት ኢትዮጵያ ከገጸ ምድር መጥፋት አለባት?

በነገራችን ላይ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤክ ሥርዓት መሠረት በዓለ ሃምሳ/በዓለ ጰንጠቆስጤ/በዓለ ጰራቅሊጦስ (ከዕርገት በ10ኛው ከትንሣኤ በ50ኛው ቀን የሚውለው) የሚባለው ታላቅ በዓል የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጨምሮ ለመጀመሪያዎቹ 120 ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዕለት መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቧል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው በርካታ ጸጋዎች መካከል አንዱ የሆነውን በማያውቁት ቋንቋ መናገርን ገልጾላቸዋል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መሠረት ዓለምን በወንጌል ቃል ለማነፅ 71 ቋንቋዎች ተገልጾላቸው ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ተሠማርተዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሀብት የሆነውን ቋንቋ አንድን ሕዝብ ለመለያየት፣ ለጥላቻ፣ አጥር ለማቆም ማዋል የዲያቢሎስ ውላጅ መሆን ነው፡፡ ቋንቋ አጥርን አልፎ ለመግባባት፣ ለመተባበርና ለአንድነት እንጂ ‹ክልል› የሚባል አጥር ለመበገር አይደለም የተሠራው፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ የሚያጽናናውን፣ የሚያረጋጋውን ቅዱስ መንፈሱን ልኮ እየታወከች ያለች ዓለማችንን በቸርነቱ ይታደግልን፡፡ 

ለክርስቲያኖች በሙሉ መልካም በዓለ ሃምሳ፡፡

Filed in: Amharic