>

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ  ሰኔ 1 1997 ዓ.ምን አስመልክቶ የወጣ መግለጫ :-

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 

ሰኔ 1 1997 ዓ.ምን አስመልክቶ የወጣ መግለጫ :-

 

ለ97 ሰማዕታት ቋሚ መታሰቢያ ይቁምላቸው! 


1997 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዘመናት መካከል የማይረሳ ጊዜ ነበር፡፡ እልፎች ኢትዮጵያውያን የንጋት ምልክት ያዩ መስሏቸው ለምርጫ የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወያኔ ኢህአዴግ በምርጫ ውሳኔ ስልጣኑን ለመልቀቅ ፈቃደኛ  ባለመሆኑ የሀገራችን ወጣቶች ለተቃውሞ ወጡ፡፡ ሠላማዊ ተቃውሟቸው “ ድምፃችን ይከበር፣ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ
የምትደዳረው ሕዝብ በመረጣቸው ወኪሎች ነው፣ ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ” የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው ስልጣን ላይ በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ የጭፍጨፋ ትዕዛዝ በተለይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ረገፉ፡፡
በጭፍጨፋው ለጋ ወጣቶች፣ የነገ ተስፋዎች መተኪያ የሌለውን ሕይወታቸውን አጡ፡፡ አዲስ አበባ አነባች፤ ወላጆች አዘን
ተቀመጡ ፣ እናቶችና አባቶች አነቡ፡፡
 እነዚያ ለህዝብ ድምጽ መከበርና ለዲሞክራሲ ሲሉ የተሰው ወጣቶች ከሞቱ እነሆ 15
ድፍን ዓመታት ሆኑ፡፡
እነዚህ ሰማዕታት የሞቱለት፣ ሌሎች የአካል ጉዳት፣ እስርና ስደትን የከፈሉበት የህዝባዊ መንግሥት ምስረታ አስራ አምስት ዓመታት ቢሞላውም፣ ዛሬም ለኢትዮጵያ የንጋት ምልክት አልታየም፡፡ ዛሬም የእነዚያ ሰማዕታት ደም “ነፃነትና ዲሞክራሲ” እያለ ይጮሃል፡፡
በመሆኑም፣ ዛሬ ላይ ሆነን የወገኖቻችንን መስዋዕትነት ስናስብ፣ ንፁኀን የሞቱለትን ትግል ከዳር ለማድረስ ቃል እየገባን
መሆን እንዳለበት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ያምናል፡፡ እንዲሁም፣ መስዕዋትነቱን ለከፈሉት ለእነዚያ ብርቅ
የኢትዮጵያ ልጆች ቋሚ መታሰቢያ እንዲቆም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ አቋም እንድንወስድ ሀገራዊ ጥሪ
እናስተላለፋለን፡፡
በተጨማሪም፣ የ1997 ዓ.ምቱን ጭፍጨፋ ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ፓርላማው ለታሪክ እንዲያስቀምጠው እየጠየቅን፣ ለዚህም ተግባራዊነት ይህ መግለጫ ለፓርላማው ገቢ እንዲሆን ወስነናል፡፡
ክብር መስዕዋትነት ለከፈሉ የዲሞክራሲ አርበኞቻችን 
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 
Filed in: Amharic