>

"ኮሮና በእኔ ቢበቃስ? ቀኑ አይመሽም ለሊቱም አይነጋም!?!" [ከኮሮና ቫይረስ ተጠቂዉ- ዶ/ር ጋሻዉ አረጋ ማስታወሻ]

“ኮሮና በእኔ ቢበቃስ? ቀኑ አይመሽም ለሊቱም አይነጋም!?!”

[ከኮሮና ቫይረስ ተጠቂዉ ዶ/ር ጋሻዉ አረጋ ማስታወሻ]

ሰዉ የተፈተነበት፡ የተጨነቀበት፡ የተሸበረበት ጊዜ ነዉ፡፡ በአይን በማይታይ ድንበር ተሻጋሪ ተዋህሲያን ሀገሬም ስትጨነቅ፡ ጤናዋ ሲቃወስ ማየት ያመኛል፣ እንቅልፍም ይነሳኛል። ‘እኔ የሀገሬ፡ ሀገሬም የኔ ነች።’ የሚል ፅኑ አቋም አለኝ። በተሰማራሁበትም
በሙያዬም የድርሻዬን ለመውጣት ደፋ ቀና እያልኩ ነበር።
~
ሐኪም እንደመሆኔ መጠን በዚህ ሰዓት ቤት ልቀመጥ አልችልም ፤ ለአፍታ እንኳ ከሆስፒታል መራቅ አይቻለኝም። በተለይ የስፔሻሊስት ህክምና ሰልጣኝ እንደ መሆኔ መጠን ከታካሚዎች መራቅን አልሻም፡፡ ለኔ ቅዳሜና እሁድ ከመደበኛ የስራ ቀናት የተለዩ አይደሉም። ቀንና ሌሊትም እምብዛም ልዩነት የላቸዉም። ከታካሚዎቼ መራቅ ከቶ አይቻለኝም። የኔ ከአጠገባቸዉ መኖር ለታካሚዎች ደስታን የሚሰጥ ፡ መዳንን የሚያመጣ ከሆነ። ከአጠገባቸዉ አለሁ፡፡ የማወቅ ጉጉት አለ፡ የመፈወስ የእግዚአብሔር ጥበብን የመሻትና የመቸር ፁኑ ፍላጎት አለ።
~
ከሁለት ከሳምንት በፊት ያልጠበቅኩት ሆነ! ህክምናን የምሻ፡ ሐኪም የሚያስፈልገኝ፡ የምትንከባከበኝ ነርስ የምሻ ሐኪም (ይቅርታ
በሽተኛ ሆንኩ)፡፡ ከህሙማን አልጋ የተኛሁ ታካሚ ሆንኩ—ያዉም በኮሮና ተዋህሲያን የተጠቃሁ በሽተኛ!!!
~
በምሰራበት አንጋፋ የመንግስት ሆስፒታል በድንገተኛ የህክምና ክፍል ለቀናት ቆይተዉ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የተዛወሩት እናት በኮሮና ወረርሽኝ መያዛቸዉ የምርመራ ዉጤታቸዉ አመለከተ ፤ ብዙም ሳይቆዩ ህይወታቸዉ አለፈ። በዚህ ጊዜ በፅኑ ህመማን ክፍል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች አደጋ ዉስጥ ሆኑ፡፡ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት ያለ PPE ግብዓት ከመሆኑም
በላይ ፅኑ ክፍል የሚገቡ ታካሚዎች ለCOVID 19 ቅድመ ምርመራ የተደረገላቸዉ አልነበሩም።
እኔም በዚያዉ የህፃናትና የልጆች የፅኑ ህሙማን ክፍል እየሰራሁ የምገኝ በመሆኔ ከችግሩ ተጋላጭነት አልተረፍኩም።
ፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ መረበሽ ነገሰ ፤ የጤና ባለሙያዎች ተደናገጡ! ከታካሚዎ ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ያላቸዉ የጤና ባለሙያዎችም መለየትም አልቀረላቸዉምና ወሸባ ገቡ።
.
በቀጣይ ቀን በአዋቂዎች ህክምና ክፍል ዉስጥ (የኮኖና ታካሚዋ ከነበረችበት ክፍል ጎን) አንድ እናት የህይወት አድን ትብብር (CPR) ያስፈልጋቸዉ ነበር፡ በዕለቱ ግን በቂ የጤና ባለሙያ አልነበረም። እናም በአዋቂዎች ህክምና ከሚሰለጥነዉ ጓደኛዬ ጋር
በመሆን የአቅማችን ሞከርን!
.
በፅኑ ህመማን ክፍሉ የሚገኙ ታካሚዎችንና አስታማሚዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ሲደረግ የታካሚዬ አባትም፡ እናትም የኮሮና በሽታ
ተዋህሲያን ተጠቂ መሆናቸዉ ተረጋገጠ። ታዲያ እኔ ማን ነኝና ይቀርልኛል? ሐኪም ስለሆንኩ ኮሮና ይምረኛል?
~
ከሰዉ ርቄ ፡ ከፀሐይ ተደብቄ ከቤት መዋል ግድ አለኝ ፤ ከታካሚዎቼ ራቅኩ ፣ ከጓደኞቼ ራሴን አራቅኩ፡፡ የኮርኖ ምርመራ ዉጤቴን በመጠባበቅ በጠባቧ ክፍል ራሴን እስረኛ አድርጌ አገለልኩ! በራሴ ላይ ፈረድኩበት! ቀኑ ግን ለምን አይመሽም? ምሽቱስ ለምን ቶሎ አይነጋ? መራመድ ናፈቀኝ! መታሰሬ አስደበተኝ!!
.
በዕለተ ሰንበት መርዶ!!
ከምሽቱ 4፡40 አካበቢ ሆኗል። ወደ ስልኬ በማለዉቀዉ ቁጥር ተደወለ። ሰልኩን ከማንሳቴ
“ሄሎ ዶ/ ር ….”
‘አቤት “
“ከEPHI ነዉ የምንደወለዉ ፤ የምርመራ ዉጤትህ ደርሷል። ፖዘቲቭ ስለሆክ አሁን ልንወስድህ ነዉ። የት ነዉ ያለህዉ?
“ነገ በጥዋት መሄድ አልችልም?” አልኩ በተሰበረ እኔና በተማፅኖ ቅላፄ!
” አሁን እየመጣን ነዉ…. የት ነህ?”… ያለሁበትን መንደር ተናገርኩ!
.
Isn’t informing that one is a COVID-19 Positive patient a breaking bad new (BBN)? Is it the right way
that we should deliver breaking bad news for patients?
.
አዕምሮዬ ማሰብ አቆመብኝ ፤ ባለሁበት ደረቅኩ። ከመደናገጤ የተነሳ ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ ይል ጀመር ፤ አንደበቴ ቃል ማዉጣት የማይችል ዲዳ ሆነብኝ ፤ ልሳኔ ተዘጋ።
.
አይኖቼ ብርሀንን መመልከት አልቻሉም ፤ ተከደኑ! እምባዬ ከእንባ ቀረጢቱ ተዘርግፎ ኩልል ብሎ እየወረደ ነበር! እጆቼ መወናጨፍ አቅቷቸዉ የቀዘቀዙ በድን ሆኑብኝ።
.
ከአፍታ የመደንዘዝ በኋላ ከወንበሬ ተነስቼ እቃዎችን ማሰናዳት ጀመርኩ! በቦርሳዬ የፀሎት መፅሐፍት እና ላፕቶፔን ከአስገባሁ
በሁዋላ ልብስ ማሰናዳት ጀመርኩ!
መጀመሪያ የነካሁትና ከመስቀያዬ ያወረድከት ነጩን ገዋኔን ነዉ! ነጩ ገዋኔን ካወረድኩ በሁዋላ ስቴቶስኮፕን አነሳሁ….!
.
ግን የት ነዉ የምሄደዉ? አሁን ሐኪም አይደለሁም? አሁን በሽተኛ ነኝ! የምሄደዉ ሆስፒታል ነዉ! ላክም ሳይሆን ልታከም! ማ? እኮ እኔ? ሐኪም አይደለሁም፣ በሽተኛ ነኝ! ያዉም የኮሮና ተዋህሲያን ተጠቂ! እዉነቱን መቀበል ግድ ነዉ፡ ግን አምኖ መቀበል ግን
አቃተኝ! በአዕምሮዬ ውስጥ ነዉጥ ነገሰ! ጩኸትም በረከተ!!
.
.
ከምሽቱ 6፡00 እኔን ወደ ህክምና ማዕከል ሆስፒታል የሚወስዱት መኪኖች እኔ አቅራቢያ መድረሳቸዉን ደዉለዉ ነገሩኝ! ነገ ስለሚሆነዉ አላዉቅም ፤ መዳን፡ ማገገም እፈልጋለሁ! መሞትም ግን አለ! ልሞትም እችላለሁ! ከሞትኩም መቀበሬ አይቀርም!
የምቀበረዉ ቤተሰብ ሀዘን አዉጥቶ አይደለም! የምቀበረዉ ያለ ወገን ዘመድ ነዉ! ኡፍ ይኽ ሀሳብ አዕምሮዬን ናጠኝ ፤ እኔ ብሞት የእናቴን ቀጣይ ሁኔታ ባሰብኩ ጊዜ አጥንት የሚሰብር ሀዘን ተሰማኝ! ልቤ በሀዘን ተጨማዳዳ ተኮማተረች! እህቶቼስ? ሁሉ ነገሬ አባቴስ?
.
ታላቅ እህቴ ሁሉ ነገር ወንድሟን በኮሮና ብታጣ ብዬ አሰብኩ! ሳታስታምመዉ የሞተ፡ እርሟን አዉጥታ ያልቀበረችዉ ወንድሟን ባሰበች ጊዜ ነገዋ የጨለመ ፡ በሀዘን የተኮራተመ እንደሆነ ሳስብ ተንሰፈሰፍኩ። ደግሞ እኮ ” ና ናፍቀህኛል፡ አይንህን ማየት
እፈልጋለሁ።” ቀን በቀን እየለመነችኝ ከባድ ፀፀት ተሰማኝ! እህቶችየቼ፡ እናቴ፡ አባቴ እወዳችኋለሁ! ያለ እናንተ እኮ ምንም ነኝ!
.
በደግ ቀን አስቤዉ ስለማለዉቅ ሞት ማሰላሰሌን ቀጠልኩ!
እርግጥ ነዉ የሰው መጨረሻው ሞት እንደመሆኑ ሞት በራሱ አያሳዝንም። አሟሟቱ እንጂ ፤ ያለ ግዜው መቀጨት ፣ በአሳቃቂ ሁኔታ ቀባሪ አጥቶ መሞት ፣ እውቀቱን ፣ ልምዱን ችሎታውን ለአገር ጥቅም ሳያውል ወይንም ጀምሮ እሳቤዉን፡ ህልሙን ሳይሳካ መሞት ያሳዝናል። ያስቆጫልም!
.
ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” ቅዱስ ቃሉ ታወሰኝ! ወገኔን ሀገሬንም  አሰብኳት!
 ‘ሞት ላይቀር ተጠላልቶ መኖር ይብቃሽ!’
የሚል መልዕክቴን ለገስኳት።
.
እንደምንም ተረጋግቼ ፀሎቴን በማድረግ ‘የልቤን አንተ ታዉቃለህ ፣ አምላኬ ፀሎቴን ስማኝ ፣ የልመናዬን ጩኸት አድምጥ ፤
የልጅህን እንባ አብስ ፤ ምህረትን ከአንተ እሻለሁ!”
.
‘መዳን አለብኝ ፤ ጌታ ሆይ ልጅህን አድን!!’ እያልኩ ነጩን ገዋኔንና ስቴቶስኮፔን ጨምቄ ለመጨረሻ ጊዜ አነባሁ ፤ ገዌኔን በእንባዬ እንፋሎት ራሰ! እንደ ደራሽ ዉኃ የሚጎርፈዉ አንባዬም ከምንጩ ደረቀ። በድቅድቁ ጨለማ ሰልኬ በተደጋጋሚ ይጮኽ ጀመር! የስራ ባልደረቦቼ….’አይዞን! አይዞን! አይዞህ!
~
መኝታ ክፍሌ የተደረደሩ መፅህፍቶችን ፣ ደብተሮቼ ፣ ወንበሬን ፣ ጠረጴዛዬን ፣ አልጋዬን አንድ በአንድ እየነካኋቸዉ ‘በቅርቡ አገግሜ እመለሳለሁ’ አልኳቸዉ! በኪራይ ከምኖርባቸዉ ክፍሎች ቦረሳዬን አንግቼ በሌሊቱ ወጣሁ! ግን ወደ የት?? እኮ ወደ የት??
~
የዉጪ በሩን ከፍቼ ስወጣ መንደራችን
በሚንቀዠቀዡ ብልጭ ብልጭ በሚል የአምቡላንስ መብራት ይታመሳል። ከአምቡላንሱ አጠገብ ከሚገኘዉ ሌላ መኪና ዉስጥ ቀድሞ በተደወለልኝ ስልክ ተደዉሎ አምቡላንስ ከኋላ ከፍቼ እንድገባ ተነገረኝ!
.
ይኽ አምቡላንስ በቀን መጥቶ ቢያፍሰኝ በማህበረሰቡ ላይ ይፈጥር የነበረዉ ጭንቀት፡ ግርግር ባሰብኩ ጊዜ በሌሊት መወሰዴ ለመልካም እንደሆነ አሰብኩ። ትር ትር ወ ደ ሚለዉ አምቡላንሰ እግሮቼ አማተሩ።
.
አሁን ሐኪም አይደለሁም፡ የኮሮና በሽተኛ ነኝ፤ ማንም ሊቀርበኝ አይችልም፤ እኔንና የእኔን ስሜት በዚህ ሰዓት መረዳት የሚችል ብቸኛ ሰዉ ቢኖር እንደ እኔ የደረሰበት ሰዉ ብቻ ነዉ!
~
አምቡላንሱን ከኋላ ከፍቼ ስገባ ፀረ ተዋህሲያን ተረጭተዉ የተቀመጡ የረጠቡ ቀዝቃዛ አልጋዎችና የኦኮሲጅን ሲሊንደር ‘በእንኳን ደህና መጣህ¡ ‘ተቀበሉኝ፡፡ ከአንዱ የተዘረጋ አልጋ ላይ ልቀመጥ ስሰናዳ ‘ና እዚህኛዉ ጋ፡ እሱ በጣም ቀዝቃዛ ነዉ” የሚል የማዉቀው ድምፅ ተሰማኝ! የስራ ባልደረባዬ ነዉ፤ እሱም እንደ እኔዉ የጽኑ ህሙማን ክፍል ሐኪም ነዉ!
ሀሳቤም ተሰብስቦ ነበር፤ እየተሳሳቅን፡ እየተቃለድን ማዉራት ጀመረን!
.
“በሰላም አገግመን እንወጣለን ፤ አይዞን!” አልኩት ቅዝቅዝ ባለ ስሜት።
“ይመስለኛል!” አለኝ።
እዉነቱን ነዉ ፤ ስለ ምንም ነገር እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በአይን በማይታይ ተዋህሲያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ላይ ተጠቅተዋል ፤ ብዙዎችም እንደ ቅጠል ረግፈዋል! የእኔስ እጣ ፈንታ? የእሱስ?
~~
በዚህ ሰዓት የሰላም እንቅልፍ የተኙ ምንኛ የታደሉ ናቸዉ!?’ 
ከፊት ለፊቴ የተቀመጠዉን የእክሲጅን ሲሊንደር አፍጥጬ እየተመለከትኩ
“ህመሜ ጠንቶብኝ መተንፈስ አቅቶኝ አርቲፊሻል የመተንፈሽ ማሽን ካአስፈለገኝ ማሽን ላይ መሆንን አልፈቅድም፡፡ I need safe death. And I will not let any resuscitation.. .’ ” አልኩ።
.
ሲያደምጠኝ የነበረዉ ጓደኛዬም በሀሳቤ እንደሚስማማ ገለፀልኝ። እኛን ትተዉ የመተንፈሻ ማሽን ለሚያስፈልጋቸው ለሌሎች ሰዎች በተለይም ለእናት ሴቶች እንዲያደርጉት እንደምንፈርም ከስምምነት ደረስን።
.
ዝም ለማለት እንሞክራለን ፤ ግን አልቻልንም፡፡ የሀሳብ ማዕበል እየከተፈ ‘ተንፍስ፡ ተንፍስ’ ይለኛል። ሰዉ የሚያስፈልገዉ በዚህ ጊዜ ነዉ!! ወገን እንደሌለህ ሰዉ ይርበሓል!
.
“የምሞት ከሆነ የአይን ብሌኔን መለገስ አለብኝ ፤ ለሌሎች ብርሐን መሆን አለብኝ ፤ የትክለ ነቀላ ህክምናም የሚያስፈልጋቸዉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ኩላሊቴን መለገስ አለብኝ፡፡ ብዙ የኩላሊት ትክለ ነቀላ የሚፈልጉ ወገኖቸ አሉ ፤ ጉበቴንም፡ መቅኒዬንም እልግሳለሁ።”
.
ቁና ቁና እየተነፈስኩ ሳወራ ሲያደምጠኝ የነበረዉ ወዳጄ “ጥሩ ሀሳብ ነዉ ፤ ግን የኮሮና በሽተኞች መሆናችንን አትዘንጋ ፤ መለገስ ከተቻለ ግን መልካም ነዉ” አለኝ። ግራ ገባኝ ፤ ተጠይነት፡ አላስፈላጊነት ተሰማኝ!
~
የተሳፈርንበት አምቡላንስ በድቅድቁ ሌሊት ይሰግራል ፤ በእንቅልፍ ያሸለበችዉን አዲስ አበባን እያቆራረጠ ሽቅብ ቁልቁል ይዘልባታል።
‘በዚህ ሰዓት የሰላም እንቅልፍ የተኙ ምንኛ የታደሉ ናቸዉ!?’ አልኩ በሀሳቤ! በጣም እንጂ!!
.
ከአምቡላንሱ የተሳፈረዉን ወጣትነቴን አሰብኩት ፤ ሐኪምነቴን አሰብኩት! እኔን፡ ህልሜን ቃኘሁት! ያልኖርኩ፡ ያልተገለፅኩ ተስፈኛ የሀሳብ ሰዉ መሆኔ ገባኝ! አዎ ልጅነቴን፡ ወጣትነቴን ከመጽሐፍ ገፆች ያስቀመጥኩት፣ ነገን በተስፋ የምጠብቅ…. ተስፈኛ!
ተስፋዬን፡ መንገዴን ከጫፋ ሳላደርስ ግን የኮሮና ወረርሽኝ አጠቃኝ፤ ታካሚ አረገኝ!
ከአልጋም አዋለኝ! (አላሳዝንም ወይ?)
~
ከምሽቱ 7፡30 ላይ ርዕሰ መዲናዉ ላይ ወደ አለ አንድ የጤና ባለሙያዎች ማገገሚያ ማዕከል በመድረሳችን ከተሳፈርኩበት ሀሳቤ ነቃሁ። በሀሳቤ ስንቱን አወጣሁ፡ አወረድኩት!
.
የአምቡላንሱ ሹፌር አመቻችቶ ከመታከሚያ ማዕከሉ መግቢያ በር ላይ ጣለን፡፡ ያነገትኩትን ቦርሳዬን እንደተሸከምኩ ወረድኩ፡፡
ከፊት ለፊቴ ከእግር ጥፈራቸዉ እስከ ራስ ፀጉራቸዉ የኮሮና መከላከያ PPE (Personal Protective Equipment) የታጠቁ (ሙሉ ልብስ፡ ጫማ፡ N-95 ማስክ፡ መነፀር፡ ጫማ፡ ግላብ) ሰዎች ወደ ዉስጥ እንድገባ ምልክት ሰጡኝ ፤ ከእነሱ ጀርባ በቅርብ
ርቀት ስራ ፈተዉ የተቀመጡ የአሪቲፊሻል ማስተንፈሻ (Mechanical Ventilator) ይታዩኛል።
.
በረጅሙ ተንፍሼ ቀና ብዬ ሰማያዊዉን ዉብ ሰማይ ተሰናብቼ ወደ ህክምና ማገገሚያ ማዕከሉም ታካሚ ሆኜ ገባሁ! የታካሚ አልጋም ተሰጠኝ፡፡ የኮሮና ተዋህሲያን ተጠቂ በሽተኛ መሆኔንም አረጋገጥኩ!!
..
..
ይኽ ጊዜ ፈታኝ ቢሆንም ለኔ የህይወት ትምህርት ሰጥቶኛል
ዛሬ ላይ ደርስኩ፡ ዛሬ ልዩ ቀኔ ነዉ! ቀናት አለፉ ፤ ቀን በቀን ተካ፡፡ ከፀሀይ፡ ከቤተሰብ፡ ከስራዬ ከምወዳቸዉ ጓደኞቼ ርቄ በታካሚ
አልጋዬ ላይ ሆኜ ሳምንትም አለፈ። የታካሚ አልጋ (Sick Bed) ምንነት፡ ታካሚነት ገባኝ። ስለ ህመምተኝነት ብዙ አወቅኩ!
.
ፈታኝ (የብቸኝነት) ቀናት ነጉደዉ ከኮሮና ማገገሚያ ማዕከል ለመዉጣት መቻል ምንኛ መታደል ነዉ! ከኮሮና ተጠቂነቴ ማገገሜ ቢያስደስተኝም መናገር የምፈልገዉ ግን መናገር የማልችለዉ ፤ መፃፍ የምሻዉ ግን መጻፍ የማልችለዉ የሚጠዘጥዝ ቁስል
አለብኝ!! ይኽ ጊዜ ፈታኝ ቢሆንም ለኔ የህይወት ትምህርት ሰጥቶኛል! It gives me life time lesson! I took, being a
Corona patient, as a life time experience.
.
ጌታ በምህረቱ ባይፈዉሰኝና ህይወቴን ባጣ ኖሮ የኔ ነፍስ ዋጋ የሚያሳስበዉ ማን አለ? በማዕከሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን የልብ ትርታን ለማድመጥ ሞክሪያለሁ ፣ ስነ ልቦናዊ ጫናዉን በቃላት መግለፅ አይቻልም! የተቀናጀ የስነ አዕምሮ ህክምና አገልግሎት መስጠት ቢቻል እላለሁ!
.
በመጨረሻም:-
 ወሳኙ ነገር አለመያዝ/አለመጠቃት ነዉ። ከተያዙ ወዲያ ደግሞ ዋናዉ ቁምነገር ‘መትረፋ’ መቻል ነዉ! መፈወስ መቻል ነዉ!! መኖር መታደል ነዉ! ለዚህም እድል በቅቻለሁ!!
.
በጨነቀኝ፡ በተቸገርኩ ጊዜ ከጎኔ የነበራችሁ ጓደኞቼ ፣ የስራ ባልደረቦቼ፡ መምህሮቼ በሙሉ እግዚአብሔር ያክብርልኝ! ከእኔዉ ጋር በኮሮና ማገገሚያ የነበራችሁ በሙሉ ስለ ጓደኝነታችሁ፡ ስለ አብሮነታችሁ ፈጣሪ ያክብርልኝ!! ይማራችሁ!
.
እኔን ስትከታተሉኝ የነበራችሁ የህክምና ማዕከሉ ሐኪሞችና ሙሉ የጤና ባለሙያዎች ክብር ይስጥልኝ! ሐኪምን እንደ በሽተኛ መከታተል ምን ያክል ፈታኝ እንደሆነ አዉቄለሁ፡ በተለይ እኔን! አመሰገንኳችሁ!
.
ስለ ሆነዉ ሁሉ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይማርልን! ኮሮና በእኔ ቢበቃስ ፀሎቴ ነዉ! እወዳችኋለሁ!
.
ዶ/ር ጋሻዉ አረጋ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣ የህፃናትና ልጆች ትምህርት ክፍል ሪዝደንት
Filed in: Amharic