>

የአገር  ቤት ጨዋታ...!!!  (ዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ)

የአገር  ቤት ጨዋታ…!!! 

ዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ

  የአዲግራቱ  የምሽት ድግስ  !!! – ጆሊ_ጃኪዝም_ታካሂዳላችሁ!”
    የምሽት ዝግጅት ሲባል ደስታ፤ፈንጠዝያ  የሞላበት ተደርጎ ይታሰባል እንጂ ተኩስ፤ እሥራት ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ነገር ግን  በተቃርኖ ሕግ መሠረት  አንድን ድርጊት ሌላ ተቃራኒ ድርጊት ሊከተለው እንደሚችል ሁልጊዜ  ማሰብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የታሰበና በሓሳብ የተነደፈ  ሁሉ መቶ በመቶ ምልዓት ሊኖረው  ስለማይችል ነው፡፡ ድርጊቱ የተከናወነው በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን በዐጋመ አውራጃ በአዲግራት ከተማ ሲሆን  ጊዜው ደግሞ 1973 ነው ፡፡ አዲግራት በቀድሞ አጠራርዋ የዐጋመ አውራጃ፣ በአሁኑ ደግሞ የምሥራቅ ትግራይ ዞን ዋና ከተማ ናት፡፡ አዲግራት ከተራራ ሥር የተመሠረተችና እንደ ወርቅና ዕንቁ የምታበራ፤ እንደ ፈርጥ የምትንቦገቦግ  ከተማ ናት፡፡ በትግርኛ አዲ ግራት ማለት የእርሻ ቦታ እንደማለት ነው፡፡ በግእዝ ቋንቋም እንዲሁ ገራህት ማለት እርሻ ማለት ነው፡፡የአዲግራት  ነዋሪዎች ከሁሉም ሰው ጋር በቀላሉ የሚግባቡ፣ ፈጣኖችና እንግዳ አክባሪዎች፣ ለእውነትና ለሐቅ የሚሞቱ ቅንና ታታሪ ዜጎች ናቸው፡፡
     ለሁልጊዜም ከልቤ የማትጠፋውንና ስሟ ሲጠራ በፍቅርዋና በውበትዋ የምትማርከኝን ይህችን ነፋሻማና ለኑሮ ተስማሚ የሆነችውን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት በ1973 ዓ.ም ነው፡፡ ሞቅና ደመቅ ወደአለችው ወደ አዲግራት ከተማ የገባሁት በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን አዲግራት በገባሁ በሦስተኛው ቀን በጫናዱግ  አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛና 12ኛ ክፍል መምህር ሆኜ እንዳስተምር ተነገረኝና ሥራዬን ጀመርኩ፡፡ ቀይቼ በወቅቱ የነበረው የቀበሌ አመራር  የምኖርበት የቁጠባ ቤት ሰጠኝ፡፡ የእኔ ቤት በርካታ የቁጠባ ቤቶችና ነዋሪዎች በሚኖሩበት አንድ ግቢ ውስጥ ሲሆን ምንም ዓይነት አጥር በሌለው ግቢ ውስጥ ልብስ ታጥቦና ውጭ ተሰጥቶ ቢውል ቢያድርና ወር ሙሉ ቢቀመጥ የሚሰርቀው ምንም ዓይነት ሌባ አለመኖሩ ሁልጊዜ ሲደንቀኝ ይኖራል፡፡
    የከተማዋን ኑሮ ስለማመድ “ባላምባራስ” የሚለው ቃል እየተደጋገመ ሲጠራ ሰማሁ፡፡ ሕዝቡ ባላምባራስ ሐድጉ፣ ባላምባራስ ሥዩም፣ ባላምባራስ አሰፋ፣ ባላምባራስ ዋሴ… እያለ ሲናገር አንዱን የአዲግራት ተወላጅ መምህር፤ “አዲግራት የባላምባራሶች ሀገር ናት እንዴ? ባላምባራሶች ለምን በዙ? አልኩት”እርሱም፤“እንዴ አዲግራትኮ የራሶችና የደጃዝማቾችም ሀገር ናት፤ ራስ ወልደ ገብርኤል፤ እነራስ ስብሐት እነደጃች ኃይለ ሥላሴ   …” እያለ ይደረድርልኝ ጀመር፡፡ ቀጠለና፤ እንዳልከው ባላምባራሶች ብዙ ናቸው ፤አንድ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ አሥመራ ሲሔዱ አዲግራት አርፈው ነበር፡፡ ያገሩ ባላባት ወዲ ሰባ ጋዲስ ይባላል፡፡ በአጠራሩም ገንታ አፈሹም ይባላል፡፡ እናም ንጉሡ አዲግራት እንደደረሱ ለበርካታ ሰዎች የባለምባራስነት ማዕረግ ሰጥተዋል” አለኝ፡፡ያ ጓደኛየ ቀጠለና፤ “ባላምባራስ ዋሴ ግን የአዲግራት ተወላጅ ሳይሆኑ ጎጃሜ ናቸው” አለ፡፡“ጎጃሜው እንዴት እዚህ አገር መጥተው ኖሩ? እንዴትስ ባላምባራስ ተባሉ?” አልኩት፡፡
    “አዲግራትኮ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገር ናት” አለ፡፡ ገና ሁለት ወር ሳይሞላኝ የገና በዓል ደረሰ፡፡ እኔ ደግሞ በልማዴ የገና በዓልን የማከብረው ሌሊት ቤተ ክርስቲያን አድሬ በማስቀደስና ከቤቴ ውስጥ በመዝናናት ነው፡፡በዚህ ዓይነት  በጥንታዊነቱ ወደሚታወቀው ወደ እንዳ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ለማደር ሐሳቡ ነበረኝ፡፡ ከመኻል የጫናዱግ ሁለተኛ ደረጃ የስፖርት መምህር ክንፈ አበራ፤ “ መምህር አማርኛ ! የተወሰንን ሰዎች   የገናን በዓል በኢትዮጵያ ሆቴል ተሰባስበን ለማክበር ስለአሰብን አንተንም ጋብዘንሃል” ይለኛል፡፡“እኔ እንኳን እንዳ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ለማደር ነው የፈለግሁት” ስለው “ቦታው ላንተ ይርቅሃል፤ መንገዱ ወጣ ገባ ነው ፡፡ደግሞ ገና እንግዳ ስለሆንክ አይመችም፡፡ ከእኛ ጋር ስትጫወት ብታድር ይሻላል ሙዚቃም፤ ጭፈራም አለ፡፡ደግሞ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ዘመን ወደ ቤተ ክርስቲያን ብትሔድ ሰው ሁሉ አይዲያሊስት፤ደብተራው፤ ቀሽ ለምለም እያለ ሊፎግርህ ይችላል፡፡መዋጮው 50 ብር ነው፡፡ብሩን እኔ ከፍየልሃለው” አለኝ፡፡“የምሽት ራት፤ ሙዚቃ አዘጋጅተናል ነው የምትለኝ?” እኔኮ  ከበሮ መምታት ፤ መዘመር እንጂ ዳንስ መደነስ፤ መጨፈር አልችልም፡፡ በግዕዝ ደነሰ ማለትም ኃጢአት ሠራ ማለት ነው አልኩት፡፡ መምህር ስፖርት ክንፈ አበራም “ እንዴ? እንዴት የአዲስ አበባ ልጅ ሆነህ ዳንስ አልችልም ትላለህ?” አለና ቀለደብኝ፡፡“ አይ እኔኮ የጎጃም እንጂ የአዲስ አበባ ተወላጅ አይደለሁም ፡፡” ስለው “ ችግር የለውም ከበሮ እናመጣልህና ከበሮ መች ትሆናለህ ”ብሎ ቀለደብኝ፡፡
    በምሽቱ ፓርቲ ላይ የጫናዱግ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ መምህሩ ኩምሳ፣ የባንክ ቤት ሠራተኛው ወንድወሰን፣ የግብርና ሠራተኛው ሐሰን፤ የርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው መስፍን፤የምሽት ፓርቲውን ስፖንሰር ሆኖ ያስተባበረውና  የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት የሆነው ፀሐየ እንዳሉበት ነገረኝ፡፡ በአጠቃላይ በምሽቱ ዝግጅት  ላይ 7 ሰዎች እንደምንሳተፍ ነገረኝና በገና ዋዜማ ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በከፍተኛ የሙዚቃ ቅንብር ምሽቱ ተጀመረ፡፡ ሰባታችንም በቦታው ተገኘን፡፡ መጠጥ እየቀማመስን ለራት ስንዘጋጅግን መሬት የሚያናውጥ ተኩስ ተከፈተ፡፡በተኩሱ ያለንበት ኢትዮጵያ ሆቴል ብቻ ሳይሆን ከተማዋ ተናወጠች፡፡ ተኩሱን የአጉላ ተራራ ተቀበለና መልሶ ወደ አዲግራት ላከው፡፡ የትግራይ ነፃ አውጭዎች የከበቡን መሰለን፡፡ተደናግጠን ስንረባበሽ በበሩ በኩል “እጅ ወደ ላይ እጅ ወደ ላይ” የሚል ኃይለኛ ድምጽ ሰማን፡፡ ነገሩ ግራ የሚያጋባ ሆነ፡፡ መሣሪያ የያዙ ፖሊሶችና የአብዮት ጥበቃዎች እኛ ወዳለንበት አራስ ነብር መስለው ሲገቡ፣ አቶ ሞላ የተባሉት የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር በቀኝ እጃቸው ማካሮቭ ሽጉጣቸውን ይዘው ወደ እኛ ቀረቡና፤
     “አብዮታዊ ሠራዊት በየጦር ግንባሩ በሚፋለምበት በአሁኑ ሰዓት እናንተ እዚህ ጆሊ ጃኪዝም ታካሂዳላችሁ፡፡ ባርቲ መስርታችሁ አገር ታምሳላችሁ፡፡ እኛ ከኢሰፓኮ ሌላ ባርቲ አናውቅም፡፡ ፈሽፋሻ ሁላ፡፡ቅደም? ወደፊት? አሉ፡፡ የአዲራት ከተማ የአብዮት ጥበቃ አባላትና ፖሊሶች እያጣደፉ ወስደው ከሌሊቱ በ7 ሰዓት ጨለማ በዋጠው እስር ቤት ወረወሩን፡፡   በነጋታው የአውራጃ አስተዳዳሪውና የፖሊስ አዛዡ ባሉበት ለምርመራ እንደምንቀርብ የምትናገር አንዲት ወረቀት ወደ እኛ ተወረወረች፡፡ እንዲህ ትላለች ‘ ቃላችሁ አንድ እንዲሆን፡፡ ይኸውም መምህር ኩምሳና ምጽላል ትኩ ለመጋባት ቃል ኪዳን ስለገቡ ይህንኑ ምክንያት አድርገው ራት ስለጋበዙን ነው በምሽቱ ግብዣ ላይ የተገኘነው በሉ” ትላለች ወረቀቲቱ፡፡ ምጽላል የመምህር ኩምሳ የሴት ጓደኛ ስትሆን የወታደር ልጅ ናት፡፡ እናም ዘዴው በአባቷ በሃምሳ አለቃ ትኩ በኩል የመጣ ይመስለኛል አላውቅም፡፡ እንደተባለው  በነጋታው አወራጃ አስተዳዳሪውና የፖሊስ አዛዡ በተገኙበት ለምርመራ ተጠራን፡፡ የሁላችንም ቃል አንድ ሆነ፡፡ በወቅቱ ስለ ጆሊጃኪዝም አስከፊነት በስፋት በመገናኛ ብዙኀን ይነገር ነበርና በተለይ አውራጃ አስተዳዳሪው (ከመቶ አለቃ ዮሐንስ ሐድጎምበስ )በፊት የነበሩት      “ ፀሐይ ያየቺውን ሰው ሳያየው አይቀርም” የሚባል የትግሪኛ ተረት አለ፡፡ “ እናንተ ኢትዮጵያ ሆቴል የተሰባሰባችሁት ኩምሳና ምጽላል ቃል ለመጋባት ኪዳን ስለተገባቡ ሳይሆን  አብዮቱን ለመቀልበስ ነው፡፡ ለዚህ እኛ ትዕግሥት የለንም፤ እስከ ስድስት  ወር እና እስከ አንድ ዓመት ልናሳስራችሁ እንችላለን፡፡ ግን የተወሰናችሁት መማህራን/መምህራን ለማለት/ ስለሆናችሁ የመማር ማስተማሩ ሂደት ይጎዳል፡፡ ወደፊት ሆቴል ውስጥ ሆነ በሌላ ቦታ በዚህ ዓይነት ስብስብ   ብትገኙ እርምጃችን የከበደ ይሆናል፡፡ ለዚሁ በቂ ዋስ እየጠራችሁ ልትፈቱ ትችላላችሁ” አሉ፡፡በወቅቱ ሁሉም ዋስ እያቀረቡ ሲፈቱ እኔ እንግዳ ስለሆንኩና ሰውም ገና ስለአላወቅሁ ዋስ አጣሁኝና ተለይቼ ቀረሁ፡፡ በኋላ ምንም የማላውቀውና የአሰፋ ክንደያ ወንድም የማነ የተባለ የአዲግራት ተወላጅ ዋስ ሆኖ አስፈታኝ፡፡ የሰው አገር ሰው ለምን ተለይቶና ታስሮ ቀረ ብለው ከየማነ ጋር የነበሩት የአዲግራት  ሰዎች በመፈታቴ ተደስተው ይዘውኝ ወደ ቤቴ ስንሄድ፣ በመንገድ ላይ አንድ አውራ ደሮ ተንደረደረና ከአንዲቱ ደሮ ላይ ወጣባት፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ፤ “ኧረ አንተ አውራ ዶሮ! ጆሊጃኪዝም አካሄደ ተብለህ በአዲግራት ባለሥልጣኖች እንዳትታሰር!” ስል ሰዎቹ በጣም ሣቁ፡፡በኋላ ላይ እንደተረዳሁት ከእሥራት በቶሎ እንድንፈታ አውራጃ አስተዳዳሪውንና የፖሊስ አዛዡን ያግባባልን አሁን አሜሪካ ውስጥ የሚኖረውና የቀበሌው ሊቀ መንበር የነበረው መምህር ታፈረ ኃይለ ሥላሴ ነው፡፡ምስጋና ከእስራት ላስፈቱኝ ለአዲግራቶች  ይገባዋል፡፡
     *      *    *
‘ወይ ከሐጎስ ወይ ከጎይቶም አያልፍም’
       በ1974 ዓ ም  በጥር ወይ በየካቲት ወር  ይመስለኛል የአዲግራት ከተማ የቀበሌ አመራር ምርጫ ለማካሔድ እሑድ ከ3 ሰዓት ጀምሮ ሁሉም ነዋሪ በየቀበሌው እንዲገኝ፤ ባይገኝ በፀረ ሕዝብነት ተፈርጆ ርምጃ እንደሚወሰድበት ከቅዳሜ ማታ ጀምሮ ጥሪ ተለፈፈ፡፡እሑድ ጧትም ጥሪው ተደገመ፡፡በጫናዱግ የአዲግራት  አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምናስተምር የተወሰንን መምህራን የቀንም የማታም መርሐ ግብር   ስላለን  ሔደን ድንገት ብንመረጥ  የሥራ ጫና ይፈጠርብናል በሚልሥጋት  ስድስት ሆነንና  በጧት ተነሥተን በአድዋ ብዘት መንገድ  አድርገን ከተራራ ሥር ወደአለው የአቡነ አረጋዊ ገዳም ተጓዝን፡፡አጋጣሚውም ገዳሙን ለመሳለም  እድል ፈጠረልን፡፡
       ከተጓዦች ውስጥ  ነፍሱን ይማረውና ያድዋ ተወላጅ የነበረው ጓደኛችን ገብረ መድኅን መስፍን፤ በአካባቢው አጠራር መምህር ሳይንስ ፤ በቅጽል ስሙ እኽዳ፤ወይም ምንጊዜም አብረን ስንጓዝ ወደ ኋላ እየቀረ ያገኘውን ኹሉ ’እኽዳ’ እያለና ወደ ኋላ እየቀረ ሰላምታ የሚሰጥና አስተዳደሩ በሰጠን ልዩ መኖሪያ ቤት አብረን የምንኖር ጓደኛየ ፤ሌላው ጓደኛየ በቅጽል ስሙ ጎበዝ ሳሲ (እንደ ሳሲ ሰው ጸጉሩ ወይም ጎፈሬው የተከመረውና በአሁኑ ሰዓት ከነባለቤቱና ልጆቹ ጀርመን የሚኖረው ድብዜው ወይም የድብዛው ልጅ ማርቆሴው  ጌታሁን ጓዴ፤ መምህር ሒሳብ፤በአሁኑ ሰዓት ፕሮፌሰር ዐቢይ ይግዛው፤ መምህር እንግሊዝ፤ ቦጋለ ፈንቴ ፤መምህር እርሻ፤ እኔ ፤መምህር አማርኛና አንድ ሌላ የረሳሁት መምህር  ነበርን ፤ አቡነ አረጋዊ ገዳም ልንደርስ ስንል  ከለመለመው መስክ ላይ ሦስት የገጠር ልጆች በጨርቅ ኳስ  ሲጫወቱ አገኘናቸው፡፡
       በዚያ ወቅት ከሚሯሯጡ  ልጆች ውስጥ መምህር ‘እኽዳ ’ ድምጹን ከፍ አድርጎ አንዱን ልጅ በትግርኛ ’አታ ቆልኣ መኒ ሽምኻ ’አለው፡፡ እኔ ደግሞ ‘ገብረ መድኅን ለምን ልጁን ታስጨንቀዋለህ ? የትግሬ ስም ያው ከሐጎስ ወይም ከጎይቶም አያልፍም ’ አልኩት፡፡ ወዲያው የተጠራው ልጅ ወደእኛ እየቀረበ ሲመጣ ገብረ መድኅን( እኽዳ) ደገመና  ‘እሞ መን ኽብል’ አለው፡፡ ልጁም እየተቅለሰለሰ ‘ዋይ ሐጎስ ’አለ፡፡ሁሉም መምህራን በአካባቢው አጠራር መማህራን በእኔ ነቢይነት ይመስላል ተሣሣቁ፡፡ከዚያም ልጆችን  ተዋውቀናቸውና አንዳንድ ነገር ጠያይቀናቸው፤የጨርቅ ኳሳቸውንም በዘመናዊ ኳስ እንዲቀይሯት መግዣ ገንዘብ  አዋጥተን ሰጥተናቸው ወደ ገዳሙ አመራን፡፡
Filed in: Amharic