>

«ኦሮሚያ» የሚለው ስም ተሰብሯል፤ መጠገን ይቻል ይሆን? (ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

«ኦሮሚያ» የሚለው ስም ተሰብሯል፤ መጠገን ይቻል ይሆን?

ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ

ማንም ሰው አንድ ስም ሲሰማ ወደ ሕሊናው የሚመጣ ምናባዊ ሥዕል አለ። ያ ምናባዊ ሥዕል እውነትም ሊሆን ይችላል፣ ሐሰትም ሊሆን ይችላል፣ የተጋነነ እውነት ወይም የተጋነነ ሐሰትም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው በዚህ ዘመን «ሶሪያ» ወይም «የመን» ሲል ወደ ሕሊናችን የሚመጣው የጥንቷ ታሪካዊት ሶሪያ ወይም በብዙ ነገር የምትቀርበን የመን ሳይሆን ጦርነት እና ዕልቂት ሊሆን ይችላል።
ውጪ ሀገር መኖር ከጀመርኩ ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማገኛቸው የውጪ ሀገር ሰዎች «ኢትዮጵያ» የሚለውን ስም ሲሰሙ የሚመጣባቸውን ምናባዊ ሥዕል ሳይደብቁ አካልፍለውኛል። የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያዊ ገጠመኝ እንደሚሆን አውቃለኹ። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከረሃብ፣ ከድርቅ፣ ከጦርነትና ከችጋር ጋር ተለዋዋጭ የሆነ ትርጉም ሆኖ ይከሰታል። ምንም ማድረግ አይቻልም። ሰዎቹ ያንን ምናባዊ ሥዕላቸውን እንዲለውጡ ብዙ ነገር መደረግ አለበት። ኦሮሚያስ?
ኦሮሚያ የሚለው ክልላዊ አስተዳደር ከሌሎች ክልሎች በተለይ እየገነባው የመጣው ምናባዊ ሥዕል የመፈናቀል፣ የስደት፣ የፀረ-ብሔረሰብነት፣ የሥርዓት አልበኝነት እና የወጣት ጋጠወጥነት መፈልፈያ እየተደረገ በመቀረጽ ላይ ይገኛል። በጣም የሚያሳዝነኝ ደግሞ ይህ ለክልሉ እየተሰጠው ያለው ስያሜ ከክልል አልፎ ለኦሮሞዎች ሁሉ የተሰጠ ስም ወደመሆን እያደገ መሔዱ ነው።
በብዙ ሰዎች አስተያየት «ኦሮሞነት (ኦሮሙማ) ማለት ሰቦኑማ (ወደ አማርኛ ሲተረጎም በራሰ መተማመን እና በራስ ማንነት መኩራት) ሳይሆን «ኦሮሙማ» ሌላውን ብሔረሰብ መጥላት፣ የሌላውን ሀብት ሁሉ በጉልበት መንጠቅ፣ በሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ላይ በጥላቻ መነሣሣት እና መጨፍጨፍ» እየሆነ ነው። በጌዴኦዎች፣ በጋሞዎች፣ በአማሮች፣ በጉራጌዎች፣ በትግሬዎች እና በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የሆነው ነገር የዚህ ማሳያ ሆኖ በመቅረብ ላይ ነው። ኦሮሞነት ከዚህ ዓይነቱ ወንጀል ጋር አቻ ሆኖ መቀመጡ ልቤን ይሰብረዋል። (በነገራችን ላይ ‘ሰቦኑማ’ ወደ አማርኛ ሲመለስ ብሔርተኝነት ማለት ነው ሲል ይፈታዋል BefeQadu Z Hailu)
እንበልና፣ ነገ ከነገ ወዲያ ሀገር ሰላም ሲሆን፣ ልማትና ዕድገት በኦሮሚያ እንዲስፋፋ ሲፈለግ ወደ ክልሉ መጥቶ ማን ሊያለማ ይችላል? ከብዙ ሰዎች ጋር ካለኝ የሐሳብ ልውውጥ እንደምረዳው ሰዎች እየጠየቁ ያሉት «እንኳን የሌላ ሀገር ሰው፣ እንኳን የሌላ ብሔረሰብ ሰው ይቅርና ራሱ ኦሮሞ የሆነ ሰውም በነ ጃዋር መንፈስ በተቀረጸች ኦሮሚያ ገንዘቡን ለማፍሰስ ምን ማስተማመኛ ይኖረዋል? የነ ሽመልስ አብዲሳ ማስተማመኛ ውኃ ይቋጥራል?» እያሉ ነው። ዛሬ ሌላውን ሲገድልና ሲዘርፍ በሬ እያረዱ «ቄሮ ፊ ቄረን ኬኛ» እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት ወጣት ነገ ሥራ ሲያጣ የማንን ንብረት ነው የሚዘርፈው? ነገስ እግረ መንገዱን የማንን እህት እና ሴት ልጅ ነው የሚደፍረው? መቸም የለመደውን ነገር ተው ስላሉት በአንዴ አይተውም። ሱስ ነዋ።
ስለዚህ የኦሮሞ ልሒቃን፣ አርቆ አሳቢዎች፣ ምሁራን በርግጥ አሁንም ካሉ እየሆነ ያለው ነገር ሊያስጨንቃቸው ይገባል። ትናንትና የጃዋርን ጥሪ ሰምተው ማንም ሳይቀድማቸው ለመድረስ እየተንደረደሩና እየተሽቀዳደሙ እንደተሯሯጡት ጎምቱ የፖለቲካ መሪዎች ሌላውም ምሁር የጃዋርን ጫማ ለመሳም «ገሌ» ገብቶ ካልሆነ በስተቀር ልብ ብሎ ሊያስብ ይገባዋል። እንደነ ዶ/ር አወል አሎ (Awol Kassim Allo)፣ ሰሞኑን ፊቱና ንግግሩ ላይ ባየሁት ጭንቀት ነገሮች ያልጣሙት የሚመስለው ዶ/ር ሄኖክ ገቢሳ (Henok G. Gabisa) ዓይነት ምሁራን እንወደዋለን ለሚሉት ሕዝብ ከምር ሊያስቡና የዝምታቸውን መጋረጃ ሊቀድዱ ይገባል። ኦሮሚያ የሥርዓት አልበኞች፣ የሃይማኖት ጦረኞች፣ የሴት ደፋሪዎች፣ የፀረ ሌላ ብሔረሰብ ሰዎች ማጠራቀሚያ፤ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ሲዖል እንዳትሆን ከፈለጉ ሥራ መሥራት አለባቸው። ዛሬ የቀበሩት ፈንጂ የሚፈነዳው ማንም ላይ ሳይሆን ራሱ ኦሮሞው ላይ መሆኑን ማስተዋል ይገባቸዋል። እነዚያ የተከበሩ ኦሮሞ ዘመዶቼ ዛሬ ከመቃብራቸው ተነሥተው የጃዋርን ኦሮሚያ ቢያዩ ሞታቸውን ያመሰግኑ ይመስለኛል።
አሁንም ጊዜ አለ። ለኦሮሞ ስትሉ ኦሮሚያን ሰላማዊ አድርጉ። ሌለውን ሕዝብ አክብሩ፤ ንብረቱን አትዝረፉ፣ ሥርዓት አስፍኑ። ዛሬ የምታሰቃዩት የደቡብ ሕዝቦች እና የሰሜን ሕዝቦች መተባበር እንዳይጀምር እና ራሱን ለመከላከል እናንተ ያደረጋችሁትን እንዳያደርግባችሁ፤ በዚህም በእናንተ ጥጋብ ንፁኃን ኦሮሞዎች በከንቱ እንዳይቀጡ አደብ ግዙ። አሁንም ጊዜውን ተጠቀሙበት።
*    *     *
* ኦሮሚያ ካል ውስጥ አሁን እየሆነ ያለውን አስቀድሜ ገምቻለሁ።  “ዛሬ የቀበሩት ፈንጂ የሚፈነዳው ማንም ላይ ሳይሆን ራሱ ኦሮሞው ላይ መሆኑን ማስተዋል ይገባቸዋል” ብዬ ነበር። ኦሮሞው ሕዝብ ከገንጣይ አስገንጣይ የጠባቦች ፍልስፍና ወጥቶ እንደ ጥንቱ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ እንዲኖር ካልተደረገ የደም አበላው ይቀጥላል።
* (የምትመለከቱት Video: መንግሥት የኦነግ ሸኔ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ የክልሉ ልዩ ኃይል “የገበሬ ጎጆ ሲያቃጥል” በሚል የሚወነጃጀሉበት clip ነው።) ለማንኛውም በነጃዋር ምክንያት ከ86 ሰው በላይ በተጨፈጨ ጊዜ ይህንን ብዬ ነበር። 
እግዚአብሔር ይርዳን
Filed in: Amharic