>

ግልጽ ደብዳቤ ለውድ ወንድሜ ለሐብታሙ አያለው (መስፍን አረጋ)

ግልጽ ደብዳቤ ለውድ ወንድሜ ለሐብታሙ አያለው

መስፍን አረጋ


ቅጥፈት ሥጋ ለብሶ ቢታይ ቁሞ ሲሄድ

ዞር ይላል ቢጠሩት ብለው ዐብይ አህመድ፡፡

መሰሪነት ደግሞ ቢጠሩት ከሰማ

የመገርሳ ልጅ ነው የሚሰኝ ለማ፡፡

 

ውድ ወንድሜ የኢትዮ360ው አቶ ሐብታሙ አያሌው፡፡  በቅድሚያ ወያኔን በመታገል ለከፈልከው ከፍተኛ መስዋእትነትና ኢትዮ360ን ለመመሥረት ላደረከው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍተኛ አድናቆቴንና ምስጋናየን ላቀርብለህ እወዳለሁ፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዐብይ አህመድን በተመለከተ ትልቅ ስህተት እየፈጸምክ ስለመሰለኝ፣ የመሰለኝን በመሰለኝ መንገድ ባክብሮት ልገልጽለህ ወደድኩ፡፡

ዐብይ አህመድ አንዴ ሸውዶናል፡፡  ያ የራሱ ያዐብይ አህመድ ስነልቦናዊ ችግር ነው፡፡  ሁለተኛ እንዲሸውደን ከፈቀድንለት ግን ችግሩ የሱ ሳይሆን የኛ የራሳችን ነው፡፡  

 

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ

ሲዋሽ የማያፍር ዓይኑን በጨው አጥቦ፡፡

አጼ ምኒሊክን በክብር እያነሳ 

በቁማችን ሸጠን ሎቦ ዳውድ ኢብሳ፡፡

አንዴ ቢሸውደን የሱ ነው እፍረቱ

ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ፡፡

 

በኔ አመለካከት፣ ያሁኑ ዐብይ አህመድና የዛሬ ሁለት ዓመቱ ዐብይ አህመድ ያው ናቸው፡፡  ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡  ድፍን ጦቢያ እንደ መሲህ ሲመለከተው፣ ይህን ሰፊ ሕዝብ ባንድነት እየመራ የጎጠኝነትን ወንዝ አሻግሮ ወደ ቃልኪዳን ምድር በማስገባት ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ መጎናጸፍ ሲችል፣ የጦቢያን ዘውድ ንቆ የኦሮሙማን ዐመድ የመረጠ ተልካሻ ሰው፣ አብዛኛው ጦቢያዊ ፊቱን ከሱ ባዞረበት ባሁኑ ወቅት፣ እሱ ፊቱን ወደ ጦቢያ ያዞራል ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ 

 

በዲስኩሩ አክብረን ብናወጣው ላይጌ

በምግባሩ ዘቅጦ ወረደ እታችጌ

ተነስ አይባልም ክብረቢስ ባለጌ፡፡

ዐብይ አህመድ፣ ዐብይ አህመድ

ያህያ ሥጋ ባልጋ ሲሉት ባመድ፡፡

 

ዐብይ አህመድ አንደበቱና ድርጊቱ አለመጣጣም ብቻ ሳይሆን ፍጹም የሚቃረኑ (ለቋንቋየ ይቅርታ ይደረግልኝና) ሞላጫ ወይም ቀጣፊ ነው፡፡  እንዳብዛኞቹ ቀጣፊወች ግን አይደለም፡፡  ዐብይ አህመድ ሚሊዮኖችን ለማሳመን ልዩ ችሎታ ያለው የቅጥፈት ሊቅ (master liar) ወይም ምርጥ ቀጣፊ ነው፡፡  

ስለዚህም ማትኮር ያለብን የዐብይ አህመድ ዋና አጀንዳ በሆነው በትልቁ ሥዕል በኦሮሙማ ላይ እንጅ፣ አገር ወዳድ ጦቢያውያንን አፍዝዞ ለማደንገዝ ሲል ብቻ በሚደሰኩራቸው ባዶ ዲስኩሮች ወይም ደግሞ በሚያደርጋቸው ጥቃቅን በጎ ድርጊቶች ላይ አይደለም፡፡  በትልቁ ስዕል ላይ ካተኮርን ደግሞ ዐብይ አህመድን በጽኑ ልንቃወመው እንጅ፣ አንተ ሐብታሙ እንደምትለው በተወሰነ ደረጃ ልንደግፈው ከቶ አንችልም፡፡ 

ዐብይ አህመድን በተወሰነ ደረጃ ደግፉ የምትለን የኦሮሙማ የበላይ አዛዥ ከሆነው ከለማ መገርሳ ጋር ተቃቅሯል ብለህ ከሆነ፣ የተሳሳትክ ይመስለኛል፡፡ ስተትህ ደግሞ የለማ መገርሳን የመሰሪነት ጥልቀት በትክክል ያለመረዳትህ ይመስለኛል፡፡  

ለማ መገርሳ ኦሮሙማን በበላይነት የሚቆጣጠር የኦሮሙማ ስብሐት ነጋ ሲሆን፣ ዐብይ አህመድ ደግሞ የለማ መገርሳ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡  ሥራ አስፈጻሚ መሆኑን ደግሞ፣ ለማ መገርሳ ‹‹የቀድሞ የገሃድ ያሁኑ የህቡዕ አለቃየ›› ነው በማለት ራሱ ዐብይ አህመድ በራሱ አንደበት ነግሮናል፡፡  

ለማ መገርሳና ዐብይ አህመድ በህቡዕ ተባባሪ ሁነው ሳለ፣ በይፋ ግን ተቃቃሪ ለመምሰል የሚጣጣሩት ለምንድን ነው?  ለታክቲክ ነዋ!  

  ለመከራከርያ ያህል (for the sake of argument) መጭው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ብለን እናስብ፡፡ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አልአሮሞወችን (ኦሮሞ ያልሆኑ ጦቢያውያንን) በተለያዩ መንገዶች በምርጫ እንዳይሳተፉ እስካደረጉ ድረስ፣ በለማ መገርሳ ሥር ሁኖ የኦሮሙማን ገሀድ ክንፍ የሚመራው ጃዋር ሙሐመድና ፊታውራሪወቹ (በቀለ ገርባ፣ መራራ ጉዲና፣ ከማል ገልቹ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ ወዘተ. ) በኦሮምያ ሙሉ በሙሉ እንደሚያሸንፉ እርግጠኞች ናቸው፡፡  

በኦሮምያ ማሸነፍ ግን ብቻውን በቂ ስላልሆነ፣ ባማራና በደቡብ ክልሎች ለማሸነፍ ሌላ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡  ይህ ዘዴ ደግሞ አሁንም በለማ መገርሳ ሥር ሁኖ የኦሮሙማን ህቡዕ ክንፍ የሚመራውን ዐብይ አህመድን ለይምሰል ያህል በአሃዳዊነት አምርሮ በመክሰስና በመውቀስ፣ አገር ወዳድ ጦቢያውያን ብዙሃን በሆኑባቸው በነዚህ ሁለት ክልሎች ላይ የዐብይ አህመድ ብልፅግና እንዲያሸንፍ ማድረግ ነው፡፡  

በዚህ ዓይነት ክሌካቻ (ባለ ሁለት ክራንቻ፣ two-pronged) ታክቲክ፣ ለማ መገርሳ ጃዋራዊ እጁን በኦሮምያ ክልል ላይ፣ ዐብያዊ እጁን ደግሞ ባማራና በደቡብ ክልል ላይ በመጫን፣ ጦቢያን በጁ በደጁ አድርጎ የኦሮሙማን አጀንዳ በቀላሉና በሕጋዊ መንገድ ማስፈጸም ይችላል፡፡  

ስለዚህም ለማ መገርሳ ከዐብይ አህመድ ጋር ሳይቃቃር የተቃቃረ የሚያስመስለው፣ የተንኮታኮተውን የዐብይ አህመድን አልኦሮሟዊ ድጋፍ (non-oromo support) መልሶ በመካብ፣ የኦነጉን ብልጽገና ባማራና በደቡብ ክልሎች ላይ ለመጫን ብቻና ብቻ ነው፡፡  ለማ መገርሳ በሚያወራውና በሚያስወራው ደረጃ ከዐብይ አህመድ ጋር በእውነት ተቃቅሮ ቢሆን ኖሮ፣ ዐብይ አህመድን በቀላሉ መገልበጥ በሚችልበት በቁልፍ ስልጣኑ ላይ ላንድ ሰዓት እንኳን ባልቆየ ነበር፡፡ 

በመጨረሻም ስለ ኢትዮ360 ጥቂት ልበልና ደብዳቤየን ልቋጭ፡፡  ገለልተኛ የሚባል ሚዲያ ባለም ላይ የለም፣ አልነበረምም፣ አይኖርምም፡፡  ማናቸውም ሚዲያ የሚመሠረተው የመረጠውን አጀንዳ ለማራመድ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሲኤንኤን (CNN) አጀንዳ ለዘብተኛ ዲሞክራሲ (liberal democracy) ሲሆን፣ የፎክስ አጀንዳ ደግሞ በወግአጥባቂ አጥባቂነት (conservatism) የተለወሰ ነጭ ላዕልተኛነት (white supremacism) ነው፡፡    

የኢትዮ360 አጀንዳ ደግሞ (ቢያንስ ለኔ እንደሚመስለኝ) ጦቢያን ሊቆረጣጥማት ካሰፈሰፈው ከስግብግቡ የኦሮሙማ ጅብ ለመታደግ ለሚደረገው የሞት ሽረት ትግል አፈቀላጤ መሆን ነው፡፡  የስግብግቦቹ የኦሮሙማ ጅቦች የነ ታከለ ኡማ አውራ ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆን፣ በለማ መገርሳ የሚታዘዘው ዐብይ አህመድ ነው፡፡  

ስለዚህም የኢትዮ360 ብቸኛ ሥራ መሆን ያለበት የዐብይ አህመድን ፀረ ጦቢያ ሥራወች አፈንፍኖ እየፈለገ በመረጃ አስደግፎ ማጋለጥ ነው፡፡   ከዚያ በተረፈ ግን ስለ ዐብይ አህመድ ‹‹በጎ ሥራወች›› እየጠቀሱ፣ ውስን የሆነውን የኢትዮ360ን አቅም ማባከን አላዋቂነት ነው፡፡  ዐብይ አህመድን ማመስገን ማለት በማር የተለወሰ መርዝ የሰጠህን ሰው ለማሩ ማመስገን ማለት ነው፡፡  መርዝም ቢኖረው፣ ለማሩ ሲባል የግድ መመስገን አለበት ከተባለ ደግሞ እነ ኢቲቪ፣ ዋልታ፣ ፋና፣ ወዘተ.  ቀን ከሌት የሚያመሰግኑት ይበቃዋል፡፡ 

    

መስፍን አረጋ 

  mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic