>

የሀገር ቤት ጨዋታ...!!! (ዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ)

የሀገር ቤት ጨዋታ…!!!

ዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ
* የሺደብር አምላክ ያውቃል
 
የትምህርት ቤት ትዝታ
 በ1964፣ 65 እና 66 ዓ.ም በደጀን ትምህርት ቤት በተማሪዎች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ የነበሩ መምህራንን ሳስታውስ በተለይ እነ ወ/ት ይደነቁ ምትኩ፣ ወ/ት ዘነበች ሥዩም ዋዲሎ ዋዳ፣ አህሙአረሩ (የስፖርት መምህር)፣ አበራ ኃይለ ሚካኤል፣ ገብርኤል እምሩ፣ ገበየሁ መንግሥቴ፣ ጋሽ ሐሰን፣ ጋሽ ብሩና ጋሽ ንጉሡ ውቤ ተጠቃሾች ናቸው፡፡በተለይ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል የሳይንስ አስተማሪዬ የነበረውን መምህር ንጉሡ ውቤን በቅጽል ስሙ “ጋሽ ዝለቀውን” ምንጊዜም አስታውሰዋለሁ፡፡ ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር አልፎ አልፎ ስንገናኝም ስለእርሱ ማውራት እንወዳለን፡፡ “ጋሽ ዝለቀው” የተባለውም ጥያቄ ሲጠይቅ፤ “እስቲ ዝለቀው” የሚል ልማድ ስለነበረው ነው፡፡ በ1966 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል የሒሳብ አስተማሪ በመጥፋቱ ባዮሎጂ ላይ ደርቦ እንዲያስተምር ተመደበልን፡፡ የክፍላችንም ተጠሪ እርሱ ሆነ፡፡
ጋሽ ንጉሡ አጭርና ወፍራም ሲሆን ፊቱም ክብ ነው፡፡ ሲናገርም በጣም ፈጣን፣ ሳቂታ፣ ቀልደኛም ግልጽም ሰው ነው፡፡ ከቀድሞው የሐረር ጦር አካዳሚ ገብቶ በገዛ ፈቃዱ የወጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ “What is Biology?” እያለ ሲያስተምር፣ ተማሪ ሁሉ ፀጥ ረጭ ብሎ ማዳመጥ አለበት፡፡ በሚያስተምርበት ጊዜ ተማሪ ከተንጫጫ፣ ወይም ከረበሸ አንዴ ወደ መሬት፣ አንዴ ወደ ክፍሉ ጣሪያ፣ አንዴ ወደ እኛ ትላልቅ አይኖቹን እያጉረጠረጠ ብስጭትጭት ይላል፡፡ “ወይኔ አንበሳው! ይኼኔ ብርጋዴር ጄኔራል ንጉሡ ውቤ በምባልበት ሰዓት የናንተ መቀለጃ ልሁን?” ብሎ ቆጣ በማለት ይናገረንና ወዲያው ሳቅ ይላል፡፡ ጋሽ ንጉሡ አስተምሮ አስተምሮ ጥያቄ መጠየቅና የቤት ስራም ሰጥቶ መቆጣጠር ይወድዳል፡፡ እኛም ማለት አንዳንዶቻችን የእርሱን ሥነ ልቡና በደንብ  እናውቅ ነበር፡፡ ሁልጊዜ እርሱ የሚጠይቀው “እኔ” ብሎ እጅ የማያወጣውንና የማይመልሰውን ነው፡፡ የቤት ሥራ ካልሰራን አውቀን “እኔ እኔ…” ብለን ጥያቄ ለመመለስ እንጫጫለን፡፡ “የለም እናንተማ ጎበዞች ናችሁ፤ እኔ የምጠይቀው እጅ ያላወጡትንና ያደፈጡትን ነው” ይልና ከወንዶች ጥላሁንንና ባንቴን፣ ከሴቶች ደግሞ ዘውነሽን፣ ኢዛምንና ሺደርብ ጫኔን በዓይኑ ይፈልግና “እስቲ እናተ ዝለቁት” ይላል፡፡
የባዮሎጂ ይሁን የሒሳብ ክፍለ ጊዜ ትዝ አይለኝም፤ አንድ ቀን እንደልማዱ ወደ ክፍል በችኮላ እንደገባ፤ “Matter is anything that occupies space….” እያለ ሲያስተምር ቆይቶ፤ “ሺደብር አር ዩ ማተር? (Are you matter?) እስቲ ዝለቂው” ሲል ጠየቃት፡፡ ሺደብር የምትቀመጠው እኔ አጠገብ ነበርና “ምንድነው ማተር? ኖ ልበለው ወይስ የስ ልበለው?” ብላ ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ተመራመርኩና፤ “መቼም ማተር መጥፎ ወይም ቆሻሻ ነገር ይመስለኛልና ኖ አይ አም ኖት ማተር በይው” አልኳት በለሆሳስ፡፡“አንችንኮ ነው? ዝለቂው እንጂ” አለ ጋሽ ንጉሡ፤ ፊቱን ከሚጽፍበት ጥቁር ሰሌዳ ወደኛ አዙሮ፡፡ ሺደብርም፤ “ኖ አይ አም ኖት ማተር (I am not matter)” ብላ መለሰችለት፡፡ “እኔን እኔን! ምን ትከፊ ሰው ነሽ አደራሽ፡፡ እንኳን አንቺ ትልቂቱ ሴትዮ ይቅርና ይህች የያዝኳት ጠመኔ እንኳ ማተር ናት” እያለ ስለማተር ምንነት ያስተምረን ጀመር፡፡
መምህር ንጉሡ ማስተማሩን ቀጠለና፤ “ነጋቲቭ ኤንድ ነጋቲቭ ሪፔል ኢች አዘር፡፡ ነጋቲቭ ኤንድ ፖዘቲቭ አትራክት ኢች አዘር (Negative plus negative repel each other. Negative and positive attract each other…)” እያለ ሲያብራራ፤ “ጋሸ አልገባንም” አልነው፡፡ ከዚያም ከልጃገረዶች ሺደብርን፣ እትየ ይመኑን፣ አስናቀችን፣ ኤልሳቤጥንና ዘውነሽን፤ ከወንዶች ደግሞ ጥላሁንን፣ ሲሳይን፣ ዘውዱን፣ ፈጠነንና እኔን ተነሡ አለና፤ “በሉ እንግዲህ ሁላችሁም ተመራረጡና ከሴቶች ጋር ተቃቀፉ” ብሎ አዘዘን፡፡ እኔም በጣም ደስ የምትለኝንና የምወዳትን ኤልሳቤጥ አበበን አቀፍኳት፤ ሌሎችም ወንድና ሴት ሆነው ተቃቀፉና እንደ መደነስ ይቃጣን ጀመር፡፡የሚገርመኝ በትምህርት ቤት ደስ ትለኝ በነበረቺው ልጅ በኤልሳቤጥ  ፋንታ የባለቤቴም   ስም ኤልሳቤጥ  መሆኑ ነው፡፡እናም እኔና ኤልሳቤጥ እንደተቃቀፍን ጋሸ ንጉሡ ውቤ “አያችሁ ጎበዝ፤ ነጋቲቭና ፖዘቲቭ አትራክት ኢች አዘር የሚባለው ይኸው ነው፡፡ እርስ በርስ የሚሳሳቡና የሚፈላለጉ ነገሮች ሁሉ አትራክሽን /ስበት/ አላቸው” አለና፤ ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር ደግሞ እንድንተቃቀፍ አደረገ፡፡ “አሁን ደግሞ ሙቀት የለም፤ መሳሳብ የለም፤ መፈቃቀር የለም፤ አለመጣጣም እንጂ” እያለ በመቀለድ ትምህርቱን አስተማረን፡፡
በወቅቱ በሒሳብ መምህርነት የሠለጠነ የ8ኛ ክፍል አስተማሪ ስለአልተመደበልን መምህር ንጉሡ ሒሳብ ጭምር እንዲያስተምር ተደረገ፡፡ የሒሳብ ትምህርቱ ግን ለአብዛኛው ተማሪ ሊገባን ስለአልቻለ፤ “አንፈልግም ይቀየርልን” ብለን ለርእሰ መምህሩ ለአቶ ገላጋይ ትርፌ አቤት አልን፡፡ ጋሸ ንጉሡ ወደ ክፍላችን 8ኛ ኤ ገብቶ ሒሳብ ሊያስተምረን ሲል “ውጣልን አንፈልግህም ” አልነው፡፡ “ይህችን ይወድዳል ንጉሡ ውቤ” ብሎ ወደ ዲሬክተሩ ቢሮ ተንደርድሮ በመሄድ፣ አቶ ገላጋይ ትርፌን ይዞ መጣና፤ “እስቲ የኔን የሒሳብ አስተማሪነት የማትፈልጉ እጃችሁን አውጡ! የማትፈልጉ ከክፍሉ መውጣት ትችላላችሁ” አለ፡፡ ወዲያው “ያንተን የሒሳብ አስተማሪነት አንፈልግም” እያሉ አሳምነው አበራ፣ ዳንኤል ታምሩ፣ አብዱ መሐመድ፣ ዘውዱ ዑመርና መዓዛ ታፈሰ ከክፍል ሲወጡ፣ በቁመቱ ረጅምና በዕድሜም ታላቅ የሆነው ባንቴ ጥሩነህ፤ ቀውለል ቀውለል እያለ ሊወጣ ሲል፤ “አንተ ደግሞ የምትወጣው ምን ተበደልኩ ብለህ ነው? ይኼኔ’ኮ ሞሱ ባንቴ የሚባል ልጅ ታደርስ ነበር፡፡” አለው ጋሽ ንጉሡ፡፡ ባንቴ ገራገርና የዋህ ስለነበር ዝም ብሎ ወጣ፡፡
ከዚያ እኔ በእድሜዬም በሰውነቴም ግዙፍነት የተነሣ ከፈጠነ ባንታምላክ ሥልጣን ተቀብዬ የ8ኛ ክፍል አለቃ ሆኜ ስለነበር ለመውጣት ስነሣ፣ የቀረውና በቁጥር ስድሳ የሚደርሰው ተማሪ አንዴ ብድግ አለ፡፡ ይህን ጊዜ፤ “አያ ገላጋይ፤ አሁን ገና ያድማው መሪ ተገኘ፡፡ አሳምነው ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ አብዱ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ ዘውዱ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ መዓዛ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ አለቃው ሲነሣ ሁሉም ተነሣ፡፡ አቆራኙኝ፤ እጅ ከፍንጅ ይያዝልኝ” አለ፡፡ ሽደብር ጫኔ አጠገቤ ቆማ ነበርና ወደ እርስዋ እየተመለከተ፤ “አያ ገላጋይ፤ ሺደብር እንኳ ነገሩ አልገባትም፡፡ አሁን ለምንድነው የተነሳሽ? ቢሏት ‹እኔ እንጃ አለቃችን ታደለ ስለተነሣ ተነሥቻለሁ፡፡ Because he is the father of the class › ትላለች እንጂ ሌላ መልስ የላትም” ብሎ ቀለደባት፡፡
ከዚያም የአድማው “መሪዎች” የተባልን ሰባት ተማሪዎች ተመርጠን ስንቀር ሌሎች ወደ ክፍላቸው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ እኛም በሰኔ ላይ ለሚተከለው ባሕር ዛፍ አገልግሎት የሚውል መሬት ለሁለት ሳምንታት ያህል በቅጣት መልክ ቆፍረን አለሰለስን፡፡ በመጨረሻ በተሰጠን ምሕረት ወደ ክፍላችን ገባን፡፡ ያን ጊዜ የተማሪ ቅጣቱ “ሥራ” ነበር፡፡
እናም የጋሽ ንጉሡ የሒሳብ አስተማሪነት በርእሰ መምህሩ ተቀባይነት አገኘና ማስተማሩን ቀጠለ፡፡ አንዴ፤ “ኤፍ ኦፍ ኤክስ ፕላስ ኤፍ ኦፍ ኤክስ (F Of X + FOFX) ስንት ነው?” ብሎ በተለይ በሒሳብ ትምህርት ደከም ያሉትን ጥላሁንንና ሺደብርን ሲጠይቅ፤ “እኔጃ” እያሉ መለሱለት፡፡ “አይ የናንተ ነገር፣ ሶስት እንጀራ ሲደመር ሶስት እንጀራ ስንት ነው? ማለት’ኮ ነው፡፡ ኧረ ተዉ ነቃ ነቃ በሉ! የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም’ኮ እየተቃረበ ነው” አለ፡፡ እንደአጋጣሚ በዚያው ዓመት የ8ኛ ክፍል ማለፊያ ማርክ 30% ሆነና ጥላሁንና ሺደብር እቅጩን አምጥተው አለፉ፡፡ ጋሽ ንጉሡ ማለፋቸውን እንዳወቀ፤ “ሺደብርና ጥላሁን ጥሩ አምላክ አላቸው” እያለ ያስቀን ነበር፡፡
በዘመኑ በከተማው ውስጥ ፎቶ ቤት ስለአልነበረ ካሜራ ያለው ሰው እንደብርቅ ይታይ ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ከደብረ ማርቆስ ፎቶ አንሺ /ፎቶ አምዴ/ ትምህርት ቤታችን ድረስ ስለመጣ፣ ፎቶ መነሳት ብርቃችን ነበር፡፡ ጋሽ ንጉሡም ለማስታወሻ ይሆን ዘንድ የ8ኛ ኤ ተማሪዎች ከአስተማሪዎቻችን ጋር እንድንነሳ አደረገ፡፡ እኛም የእርሱን ትክሻ ተደግፈን የማስታወሻ ፎቶግራፍ ስንነሳ፣ ከሴቶች በጣም ቆንጆዎች የሚባሉት አስናቀች ውብእሸትንና ኤልሳቤጥ አበበን መርጦ ወደራሱ አቀራረባቸው፡፡ ሺደብርም አብራቸው ለመነሳት ጠጋ ስትል፤ “ሺደብር አንቺ ቆይ… ፎቶግራፍ ታበላሻለሽ” አለና ቀለደባት፡፡
እርስዋም፤ “እኔ ከማን አንሳለሁ ጋሽ! ቆንጆ ነኝኮ” እያለች በመጠጋት አብራት ተነሳች፡፡ በዚያው በ1967 ዓ.ም ንጉሡ የ8ኛ ክፍል የባዮሎጂና ሒሳብ አስተማሪ ሆኖ ተመድቦ፤ ሸዋየ ታሪኩ የተባለችው ሙዝ ለመንገደኞች እየሸጠች የምትማር ልጅ የሒሳብ ትምህርት ይከብዳታል፡፡ “ኤፍ ኦፍ ኤክስ ፕላስ ኤፍ ኦፍ ኤክስ ስንት ነው?” ሲላት ደንግጣ፤ “ጋሽ ንጉሡ ያንተ ትምርት ከባድ ነው፤ በዚህ ዓይነት 8ኛ ክፍል አልፍ ብለህ ነው!” ትለዋለች፡፡
“ሸዋየ ያንቺ ጠላት’ኮ ኤፍ ኦፍ ኤክስ +ኤፍ ኦፍ ኤክስ የሚለው ቃል ነው፡፡ በቀላል አማርኛ 8 ሙዝ ሲደመር 8 ሙዝ ስንት ነው ቢሉሽ መልሱን ቁጭ ነው የምታደርጊው፡፡ ስለማለፉ ደግሞ አትጨነቂበት፡፡ አይዞሽ ’የሺደብር አምላክ’ ያውቃል፡፡ ደጉ መንግሥታችን ዘንድሮ ደግሞ የ8ኛን ክፍል ማለፊያ 15% ሊያደርገው ይችላል፡፡ ማን ያውቃል?” ብሎ አስቋታል፡፡
ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ንጉሡን አዲስ አበባ አግኝቼው፤ “ጋሽ፤ ምነው ጸጉርህ ሸበተ?” አልኩት፡፡
“አይ ታደለ፤ በእውነቱ የበጀን አንተም ያንተን መላጣ፣ እኔም የእኔን ሽበት አለማየታችን ነው፡፡ እኔም ሽበቴን አንተም መላጣህን የምናይ ቢሆን ኖሮ እንናደድ ነበር፡፡ ደግነቱ ራሳችንን አናየውም፤ ዝንጀሮ የራስዋ መላጣ አይታያትም እንዲሉ” አለና የበለጠ አሳቀኝ፡፡
 
* መዘዘኛይቱ በቅሎ
    ራስ ኃይሉ በደጀን በኩል ወደ ሸዋ ሲያልፉና ከሸዋም ወደ ጎጃም ሲመለሱ ደጀን ላይ ረፍት ያደርጉ ነበር፡፡ወላጅ እናቴ እመዋ ትሁን አሸነፍክ  እንዳጫወተችኝ በዚያ ወቅት  ኦጋዴን ዘምቶ የተመለሰው አባቷ አቶ አሸነፍክ ዓለሙ የሑዳድ አዛዥና የደጌን ጉልተ ገዥ በነበሩት  በአቶ መንግሥት ደሴ አባት በቀኛዝማች ደሴ ጓንጉል ትእዛዝ የመንግሥት የኩዳድ ከብት እየተቀበለ ያስጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ራስ ኃይሉ ወደ ደጌን ሲመጡ የሚሰግሩባት ናት በሚል እንዲያስጠብቃት ለአባቷ ለአቶ አሸነፍክ ዓለሙ  በቅሎ ይሰጡታል፡፡ በቅሎዋ ግን መዘዘኛ ኾና በድንገት ትጠፋለች፡፡‘የጠፋቺው በቅሎ የራስ ኃይሉ ናትና ኋላ የተገኘብህ መከራ ያገኝሃል’ እየተባለ ቢለፈፍም በቅሎይቱን የበላት ጅብ ሳይጮህ ይቀራል፡፡ቀኛማች ደሴ ጓንጉልም በበቅሎዋ ፋንታ እናቴ በልጅነቷ ትጠብቃቸው የነበሩትን ሻሾና ገምባው የተባሉ ሁለት የፍየል ሙክቶች ከ4 ጠገራ ብር ጋር ገምቶ ይወስድባቸዋል፡፡ እናቴም ፍየሎቸ መቼ ነው የሚመጡት እያለች ትጠይቃለች፡፡ወዲያው ሁለቱንም ሙክቶች ቀኛማች ደሴ ወደ ደንጋብ ወስደው ይበሏቸዋል፡፡ ይህንንም  ወላጆቿ ለእናቴ ሳይነግሯት ይቀራሉ፡፡
   በዚህ ድርጊት አባቷ አቶ አሸነፍክ ዓለሙና እናቷ ወይዘሮ ጣይት ውበቱ  እያዘኑ ሲኖሩ  አቶ አያሌው ማደጊያ የተባለ ሰው ባገር አላስቀምጠኝ አለ ብሎ በቀኛዝማች ደሴ ላይ ይነሣባቸዋል፡፡በመጨረሻ በጨት ወንዝ ላይ ተማምለን እንታረቅ ይሉና እነቀኛዝማች ደሴ ጓንጉል  ዐርብ ቀን ወደ በጨት ወንዝ ሔደው ስለእርቅ ሲነጋገሩ አቶ አያሌው ማደጊያ በጉልተ ገዥው ንግግር ስለተናደደ ጥይት ተኩሶ ይገድላቸዋል፡፡ አስከሬናቸውም ወደ ደንጋብ ይመጣና ቅዳሜ በገበያው ቀን  ጉልተ ገዥው ይቀበራሉ፡፡ ይኽንንም የእናቴ እናት ወይዘሮ ጣይት ውበቱ ቅዳሜ ዕለት ወደ ደንጋብ ገበያ በደሔደችበት  ቀን ለቅሶውን ስለሰማች ቀኛዝማች ደሴ ጓንጉልን አስቀብራና እርሟን አውጥታ ወደማታ ሲሆን ወደ ቤቷ ትመለሳለች፡፡ከቤት እንደደረሰች እናቴን ትጠራና‘ትሁን ትላንትና ፍየሎችሽ  ሻሾና ገምባው ሞተው ዛሬ ተቀበሩ’ ትላታለች፡፡እናቴም በሕፃን አእምሮዋ ትጠብቃቸው የነበሩት ፍየሎች እንደ ሰው ሞተው የተቀበሩ ስለመሰላት ‘ወይኔ ፍየሎቼ ወይኔ ወይኔ —’ በማለት ስታለቅስ  እናቷ ጣይት ውበቱ  ‘ትሁን ! አይዞሽ አታልቅሽ! ሞተው የተቀበሩት  ፍየሎቹ ሳይሆኑ  ፍየሎቹን የበሉት ቀኛዝማች ደሴ ጓንጉል ናቸው’ ስትላት‘ ደሴ ጓንጉልስ ይሙት፤ እንኳን ፍየሎቼ አልሞቱ’ ብላ ተጽናናች ይባላል፡፡በእርስዋ ቤት ፍየሎቿ አልሞቱም፤ የሚሞቱት ታረዱ ሲባል ብቻ  ነው፡፡
* እናት የምትለዋን ራስህ ጨምር!!
     በ1973 እና በ1974 ዓ ም በዓጋመ አውራጃ በአዲግራት ከተማ  ጫናዱግ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምናስተምር መምህራን ከላይ ከአውራጃው ጽ/ቤት በተሰጠ ትእዛዝ መሠረት በየሳምንቱ ዐርብ ዐርብ በርእሰ መምህሩ በአቶ ገብረ ጊዮርጊስ፤ በቁልምጫ ስሙ ጂጂ አስተባባሪነት ሠርቶ አደር ጋዜጣ፤ ካፒታልና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መጽሐፍ እየተጠቀሰ  በማርክሲዝም-ሌሊኒዝም ፍልስፍና ላይ ትምህርታዊ ውይይት እናካኺድ ነበር፡፡የትኛውም መምህር ተራ ሲደርሰው በተሰጠው ርእስ ላይ አስቀድሞ አንብቦና ተዘጋጅቶ ይመጣ ነበር፡፡አንድ ቀን የማስተማርና የማወያየት  ተራው ለአንድ ጓደኛችን ደረሰውና ስለዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም በጥሩ ሁኔታ ሲያስተምር ቆየ። በመጨረሻ ላይ እንደተለመደው ስብሰባው ከመዘጋቱ በፊት  በመፌክር መታሰር ነበረበትና እያንዳንዱ ግራ እጁን እንዲያወጣ ጓደኛችን  አሳሰበን፤ እኛም በታዘዝነው መሠረት ግራ እጃችንን ወደ ላይ እንዳንከፈረርን  ድምፁን በጣም ከፍ አድርጎ ‘አብዮታዊት ህገር ወይም ሞት ’ አለ፡፡ እኛም መፈክሩን ከእርሱ ተቀብለን ከአስተጋባን በኋላ የአማርኛ መምህር የኾነው መምህር ከበደ የተባለ ጓደኛችንና የአዲግራት ልጅ  ‘ጓድ—-! መባል ያለበትኮ አብዮታዊት እናት ህገር ወይ ሞት ነው፤ እናት ቀረች ’ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ  ያ ስሙን ያልጠራሁት ጓደኛችን ያ ሁሉ  መምህር በተሰበሰበበት ‘ ዞር በል እኔን ምን አገባኝ ! እናት የምትለዋን ራስህ ጨምር፤ ግዴታ አለብኝ እንዴ’ሲል የመምህራን የውይይት መድረክ በሣቅ ተናጋ፡፡እና  በጣም እወድደውና ቅን ሰው ከነበረው ከመምህር ሜታል ዎርክ ጋር ለከፍተኛ ትምህርት አብረን ወደ ሞስኮ ብንሔድም በመጨረሻ የእርሱ ምርጫ ስዊድን፤ የእኔ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆነችና ተለያየን፡፡ባለበት ሰላም ይሁን፡፡
Filed in: Amharic