>

"ሕገ-መንግስቱ ይከበር¡¡¡" የህወሀት. እድሜ ማራዘሚያ!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

“ሕገ-መንግስቱ ይከበር¡¡¡” የህወሀት. እድሜ ማራዘሚያ!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

ህውሓት እንደ ድርጅት ዘረኛ፣ ዘራፊ፣ ወንጀለኛ ድርጅት ነው። ምንም ሳይሸፋፈን ህውሓት ጥገኛና ወታደርተኝነት የተጠናወተው ድርጅት ነው። አሁንም ህውሓት እንደ ድርጅት የሚከተለው ርዕዬተ-አለም የጠላት ወዳጅ መስመር ነው። በመሆኑም በእሱ መስመር ያልተሰለፈ በሙሉ ጠላቱ ነው። ጠላት ደግሞ መጥፋት አለበት ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት ጠልፎ ለመጣል እንጂ ሰጥቶ ለመቀበል የሚያስችል የድርድር ዝግጁነት የለውም። በሌላ በኩል ህውሓት ጥርሱን የነቀለበት ጨዋታ የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው። ዜሮ ድምር ጨዋታ ማለት በሌላ አነጋገር “ሁሉን ታገኛለህ! አሊያም ሁሉን ታጣለህ!” ማለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በአሁን ሰአት ህውሓት በአክራሪ፣ ዘረኛ፣ ዘራፊና ኃላቀር ቡድን ተጠልፎ የወደቀ ፓርቲ ነው። ይሄ ቡድን ባልጠበቀው ሽንፈት ምክንያት በውስጡ ቂምና ቁርሾ ያዘለ የቆሰለ አውሬ አይነት ባህሪ ያለው ሆኗል። በታሪክም የገዛ ወንድሞቹን እንደራደር ብሎ ጠርቶ፣ ጥቦት አርዶ አብልቶ፣ በለሊት በጥይት አርከፍክፎ የሚጨፈጭፍ ነው። የቡድኑ አመራሮች ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሀዬ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ስብሃት ነጋ፣ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ፣ ዘርአይ አስገዶምን የመሳሰሉ ናቸው።  ይሄ ቡድን ከፀረ-ኢትዮጲያ ሃይሎች ከሆኑ አራተኛ ረድፍ “ጋቢሳዊ ኦሮሙማዎች” ጋር በመቀናጀት ኢትዮጲያን ለማተራመስ ስትራቴጂ ቀርጾ የሚንቀሳቀስ ነው።
ይሄ ቡድን ፓለቲካዊ ሞቱን የተጐናፀፈ ቢሆንም የጥገኝነትና ወታደራዊ አይበገሬነት ቅዠቱ ገና የሟሸሸ አይደለም። በአጭር ጊዜ ውስጥም ከአጉራ-ዘለልነቱና ከተጠናወተው ወታደራዊነት ካንሰር በኬሞ እንኳን የሚያገግም አይደለም።
የመጨረሻ ፍላጐቱም ከዚህ በኃላ በኢትዮጵያ የመሀል ፓለቲካ ውስጥ አፈር ልሶ መነሳት ስለማይችል አገሪቷን መውጪያ ወደሌለው የፓለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ አዙሪት ውስጥ በመክተት መበታተን ነው። እናም የሽምግልናው ቅኝት እና ውጤት ከላይበተቀመጠው እሳቤ የሚመራ ይሆናል።
በመሆኑ ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ሲሄዱ ህውሓት ውስጥ የበላይነት የያዘው የስዩም መስፍን ቡድን የሚቀበላቸው በአሸናፊነት እና ትእቢት መሆኑ አይቀርም። በእርግጥ ለሚዲያ ፍጆታ የፊት መስመር እነ ደብረጺዬንና ጌታቸው ረዳ መልካም አቀባበል ሲያደርጉ እንመለከታለን። ወቅቱ ኮቪድ ሆነ እንጂ የአበባ ጉንጉን ለሽማግሌዎቹ ሲጠለቅላቸውም እንመልከት ነበር።
ህውሓት ከሽማግሌዎቹ ጋር በምታደርገው ዘለግ ያለ ውይይት አሰልቺ በሆነ መንገድ የሚከተሉትን ማዕከላዊ ነጥቦች ደጋግማ ታነሳለች፣
– ” እኛ እኮ ሕገ-መንግሥት ይከበር ነው ያልነው፣… ወረርሽኙ ምርጫ ለማካሄድ የማያስችል ከሆነ ምን እናድርግ የሚለውን እንመካከር ነው ያልነው፣
– …የቀን ጅብ ተባልን፣… የትግራይ ህዝብ በታቀደ መንገድ የጥቃት ሰለባ ሆነ፣
– አብይ ከኢሳያስ ጋር የጋራ ግንባር ፈጥሮ የትግራይን ህዝብ ሊወጋ ነው፣
– …  ከፌዴራል መንግስት ስልጣን እንድንገለል ተደረግን፣
– …ወደ ትግራይ የሚገቡ መንገዶች እንዲዘጉብን ተደረገ” የሚሉ ይሆናሉ።
የውይይቱ ማሳረጊያም “ህገ-መንግስቱ ይከበር!” ይሆናል። ሽማግሌዎቹም ገንቢ ውይይት እንዳደረጉ መግለጫ ይሰጣሉ። ወደ አዲስ አበባም ሲመለሱ “ሕገ-መንግስት ይከበር!” የሚል መፈክር እያሰሙ ይሆናል። ሕገ-መንግስት ይከበር!!
Filed in: Amharic