>
5:16 pm - Saturday May 24, 5862

የብሔር ጥያቄ እና የብሔር ሽቀላ...!!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

የብሔር ጥያቄ እና የብሔር ሽቀላ…!!!

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ

በኢትዮጵያ ውስጥ መልስ የሚሹ በርካታ የማንነት ጥያቄዎች አሉ፤ ከጥያቄዎቹ መካከል ግን ነጥሮ የወጣው ወይም እንዲወጣ የተደረገው “የብሔር ጥያቄ” ብቻ ነው። ይህ መሆኑ በነባሮቹ ታሪካዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ ጥያቄዎች፣ ቁርሾዎች እና ቅራኔዎች እንዲደራረቡና ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተባባሱ እንዲሔዱ አድርጓል። የብሔር ጥያቄ አቀንቃኞች ብሔርተኝነትን እንደ ብቸኛ መፍትሔ ያቀርባሉ። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ ችግርን በችግር የመፍታት ዘዴ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ዘለግ ያለ ዕድሜ ያላቸው የማንነት ጥያቄዎች መልሱ ብሔርተኝነት ሳይሆን ፍትሕ ነው። በዚህ መከራከሪያ ላይ በቅጡ ለመግባባት የኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄዎችን መሠረት፣ የብሔር ጥያቄ በማንነት ጥያቄዎች ውስጥ ያለውን ቦታ፣ እንዲሁም ችግሮቹን ከዚህ በፊት ለመፍታት የተሔደባቸው ዘዴዎች ለብልጣ ብልጦች የፈጠሩትን የማይገባቸው እርከን ላይ የመንጠላጠል ዕድል አፍታትቶ መነጋገር ያስፈልጋል።
የማንነት ጥያቄ ነባራዊነት
ረዥሙ የዐፄ ስርዓት በአንድ በኩል በአንድ ድንበር የታጠረ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አበርክቶ ሲያልፍ፣ በሌላ በኩል ብዙ መልስ የሚያሻቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለተከታታይ ትውልዶች ጥሎ አልፏል። የደርግ ወታደራዊ ጭቆና እና የትሕነግ (TPLF) የዘውግ ምደባ ዐፄያዊው ስርዓት ጥሎት በሔደው ሸክም ላይ ሲደመሩበት ጥያቄውን ከወትሮው የበለጠ ውስብስብ አድርገውታል።
የኢትዮጵያ ዐፄዎች አገር ንብረቱን በሙሉ የግላቸው አድርገው ነበር የሚቆጥሩት። ይህ ግዙፍ የመደብ ልዩነት ፈጥሯል። የመደብ ልዩነቱ በገዢዎች እና ተገዢዎች ዘንድ ሰፊ የሀብት እና የማኅበራዊ ማዕረግ ክፍተት ጥሎ አልፏል። የመደብ ልዩነቱን ለማስፋት መሬት ትልቁን ሚና ተጫውቷል። የመሬት ባለቤትነት ለባላባቱ የተተወ ሲሆን፣ አርሶ ባላባቱን የሚያበላው ብዙኀኑ ገባሪ ዘንድም ቢሆን የገባሪነት ማዕረጉ ለየቅል ነበር። ሰሜኑ ባብዛኛው ቋሚ ገባሪ ሲሆን፣ ደቡቡ ደግሞ በጥቅሉ ተነቃይ ገባሪ ነበር። ይህንን የመደብ ጥያቄ በመ.ኢ.ሶ.ን. ምክር ደርግ መሬት ላራሹን ሲያውጅ ከሞላ ጎደል የተቀረፈ ቢሆንም ቅሉ፣ የማኅበራዊ ማዕረግ (Social Status) ልዩነቱ ግን እየተራባ ቀጥሏል።
የዐፄዎቹ ዘመን ሌላ መገለጫ ሃይማኖት ነው፤ ክርስትና የገዢዎችም የግዛቱም ሃይማኖት ነበር። ምንም እንኳን በግዛቱ ውስጥ የእስልምና እና የአገር በቀል እምነት ተከታዮች ቢኖሩም፥ የክርስትያኖች ማዕረግ አልነበራቸውም። ይህ የሃይማኖታዊ ማንነቶች ላይ የነበረው መንግሥታዊ ቡራኬ ሌላው የማኅበራዊ ማዕረግ መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል። ትሩፋቱ የዐፄዎቹ ስርዓት ከስሞ በሴኩላር አገረ መንግሥት ከተተካ በኋላም ቀጥሏል።
የገዢ ተገዢ ግንኙነቶች ብቻ ሳይሆኑ በተገዢዎች መካከል ያለው ማኅበራዊ ግንኙነትም ፍትሓዊ አልነበረም። በፆታ፣ በቆዳ ቀለም፣ በሥራ ዘርፍ፣ በባሕል፣ ወዘተ. መድልዖዎች እና ጭቆናዎች ለረዥም ዘመን ሲፈፀሙ ከርመዋል። በስርዓቱ ወይም በማኅበራዊ ግንኙነቱ ለተመራጩ ማንነት ትሩፋቱ ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊም ጭምር ነው። ትሩፋቱ ላለው እየጨመረ ሲሔድ፣ ለሌለው ከሌለው ላይ እየነፈገ ከትውልድ ትውልድ ይወራረዳል።
የማንነት ጥያቄዎችን ፍራንሲስ ፉኩያማ ከማንም በተሻለ ገላጭ መልኩ አስቀምጠውታል። ጥያቄው ሦስት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው የዕውቅና ጥያቄ ነው፤ “እኛም እንደ ሰው፣ የተለየ ባሕል፣ ወግ፣ ማዕረግ፣ እምነት እንዳለው ማኅበራዊ ስብስብ ዕውቅና (recognition) ሊሰጠን ይገባል” የሚል ነው። ይህ እንግዲህ እንደ አንድ ስብስብ እና የተለየ ማንነታችን (distinct features of identity) ዕውቅና አልተሰጠውም የሚሉ ቡድኖች ጥያቄ ነው። ሁለተኛው የእኩል ዕውቅና ጥያቄ ነው፤ “እኛም፣ እንደ ሰው፣ ሕዝብ ወይም የማኅበረሰብ ክፍል፣ ዕኩል ወግ ማዕረግ ይገባናል እና ይከበርልን” የሚል ነው። ይህም ልዩ ማንነታቸው ታውቆላቸው ነገር ግን በንቀት/በጥላቻ የሚታዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥያቄ ነው። ሦስተኛው እና በአደገኝነት ሊፈረጅ የሚገባው ደግሞ “እኩልነት አይመጥነንም እና የበላይነት ዕውቅና ይሰጠን” የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥያቄ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች ያሉ ባይመስልም ተንሰራፍተዋል። በአማርኛ ትምክህተኝነት (chauvinism) ተብሎ የተተረጎመው አስተሳሰብ ወይም የበላይነት ስሜት (feeling of supremacy) የብዙ ቀውሶች መሠረት ነው። የሚያነታርኩንን ትምክህተኝነቶች ችላ እንበላቸውና ዓለም በተግባባበት እንኳን የወንዶች ትምክህተኝነት (male chauvinism) እና የነጮች የበላይነት (white supremacy) ስሜት ለሦስተኛው ዓይነት የማንነት “ጥያቄ” ወይም ፍላጎት ማሳያ ናቸው። ሁለቱም ሲወልድ ሲዋለድ የመጣ የገደኝነት (privilege) ትሩፋቶች ናቸው።
የብሔር ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ንዑስ አካልነት
የማኅበራዊ ማዕረግ ጥያቄዎች የብዙ ማንነቶች ድርብ ድርብርብ ጥያቄ ነው፤ ሆኖም የያ-ትውልድ ፋኖዎች “የብሔረሰብ ጥያቄ” በሚል አቃላይ (reductionist) ቋንቋ ገልጸውታል። ጥያቄው በትግል ሜዳ ሲንከባለል ከርሞ፥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ የበለጠ ተቃልሎ ሲቀርብ “የብሔር  ጥያቄ” ተብሏል፤ መፍትሔው ደግሞ ብሔርተኝነት እንዲመስል ተደርጎ ዛሬ ላይ ደርሷል። ነገር ግን የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ አንደኛ በትክክል አልተበየነም፣ ሁለተኛ ከማንነት ጥያቄዎች አንዱ እንጂ ሁሉም የማንነት ጥያቄ ማዕቀፍ እንዳልሆነ ግልጽ አልተደረገም፣ ሦስተኛ መፍትሔው በሰፊው ማዕቀፍ አልተዳሰሰም፣ አልተጠቆመም፣ አልተሞከረም። ይህንንም ዘርዝረን እንመልከተው።
የብሔር ጥያቄ በያ-ትውልድ አባላት ወጣኝነት፣ በዋለልኝ መኮንን አቀነባባሪነት “በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ” (On the Question of Nationalities in Ethiopia) በሚል ርዕስ ተጽፎ ሲነበብ ምሉዕ እንዳልሆነ (“The article […] suffers from generalizations and inadequate analysis”) ተገልጿል፤ ያንን ማንም ትኩረት ሊያደርግበት አይፈልግም። ሆኖም የመጣጥፉ ጭብጥ “የኢትዮጵያዊነት ብያኔ” ጠባብ ነው የሚል ነው። የድምዳሜው መሠረት ረዥሙ የዐፄዎቹ ስርዓት ትሩፋት በሚል ከላይ ከገለጽኩት የሚመዘዝ ነው። በገዢዎች መደብ ተመራጩ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ሃይማኖት የተለምዷዊው ኢትዮጵያዊነት ብያኔ መሆኑ አባልነት እንዳይሰማቸው ያደረጋቸው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አሉ። እነሱን ማካተት እና ኢትዮጵያዊነትን አካታች ማድረግ የቀጣይ ትውልዶች ኃላፊነት ነው።
የብሔር ጥያቄ ከዚያ በኋላ ባሉ የፖለቲካ እሰጥ አገባዎች በሦስት አጀንዳ ዙሪያ እንዲያጠነጥን ተደርጓል። አንደኛ የእኩል ዕውቅና (ቋንቋ፣ ባሕል እና እምነት) ጥያቄ፣ ሁለተኛ፣ ይህ ዕውቅና የተሰጣቸው አካላት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አስተዳደራዊ ጥያቄ፣ እና ሦስተኛ በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የተመጣጣኝ ውክልና ጥያቄ ናቸው። በዚህ መሠረት የማንነት ጥያቄዎች በሙሉ በጠባብ እና አስገዳጅ የማንነት ብያኔ ላይ ተመሥርቶ (ማለትም፦ አንደኛ፣ ብሔርን ብቸኛው የማንነት መገለጫ በማድረግ እንዲሁም ሁለተኛ የብሔርን ብያኔ የቋንቋ ዘር ግንድ (ethnolinguistic roots) በመምዘዝ) ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች በሙሉ እንዲደፈጠጡ አስገድዷል።
የብሔር ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ንዑስ አካል ነው። ለዚህም ነው በብሔር፣ ያውም ደግሞ በጠባብ የብሔር ብያኔ ላይ የቆመ የብሔር ጥያቄ ላይ ብቻ ተመሥርቶ መልስ ማፈላለግ፥ ከመልሱ ጋር ተጠፋፍቶ ለመቅረት ይዳርጋል። ብሔርተኝነት መፍትሔ መስሎ የሚታየው የኢትዮጵያን የማንነት ጥያቄ እና ከማንነት ጥያቄዎች ባሻገር ያሉትን (ለምሳሌ የመደብ ጥያቄን) በሙሉ አድበስብሶ ማለፍ ከተቻለ ብቻ ነው። ብሔርተኝነት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጥያቄ አይመልስም። ብሔርተኝነት የኢትዮጵያ ሴቶችን ጥያቄ አይመልስም። የኦሮሞ ሴቶች እና የሶማሊ ሴቶች ጥያቄ፣ የአማራ ሙስሊሞች እና የትግራይ ሙስሊሞች ጥያቄ በዘውግ ብሔርተኝነት አጥር ውስጥ ከናካቴው ቦታ እንኳን አይሰጣቸውም።
አሃዳዊ ብሔርተኝነት
“የብሔር ጥያቄ” በሚል አጭር ሐረግ የሚወሳው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ የተሰነዘረው ትችትም ይሁን፣ በአሁኖቹ ኀያላን የዘውግ ብሔርተኞች ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ አንድ ዓይነት ነው – አሃዳዊነት!
ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ሶማሊነት፣ ተጋሩነት… የሚባሉት ብሔርተኝነቶች በሙሉ ከውጭ ለሚያያቸው ተመልካች አንድ ይምሠሉ እንጂ “አንድነታቸው” የውጭ ጠላት ብለው ለፈረጁት የስብስባቸው አባል ብቻ ነው። በኦሮሞ ብሔርተኝነት በተለይ በሃይማኖት፣ እንዲሁም ባውራጃ ከፍተኛ ክፍፍሎሾች አሉ። ማዕከሉን ወለጋ ያደረገው፣ በፕሮቴስታንቲዝም አስተምህሮ የታነጸውና ራሱን ላይላይ አድርጎ የሳለው የወለጋ ኦሮሞ ብሔርተኝነት አለ፣ በተለይ ምሥራቅ ኦሮሚያ ላይ ያለው የእስልምና እምነቱን የሚያስቀድመው የሐረርጌ ኦሮሞ ብሔርተኝነት አለ፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዮቹ የመሐል አገር ኦሮሞዎች የሚቀነቀነው ለዘብተኛ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አለ። ጅማና አርሲም የየራሳቸው ገጽታ አላቸው። በብሔርተኞቹ የኦሮሙማ (ኦሮሞነት) ብያኔ ግን ሁሉም አንድ እና አንድ መሆን አለባቸው። ለኦሮሞ አንድነት (‘ቶኩማ’) ያልተገዙ/ያልገበሩ ሰዎች በወንዜነት (‘ገንዱማ’) ይወቀሳሉ፣ ይከሰሳሉ። በአጭሩ፣ በብሔርተኝነቱ ዓይን ተቀባይነት ያለው የዘውጌ አሃዳዊነት ብቻ ነው።
ጉዳዩ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ብቻ የተገደበ አይደለም። የአማራ ብሔርተኝነት የአማራ (ዘውግ) ሕዝብን በአንድ አምሳል ለመሳል ይሞክራል። ነገር ግን ይኸው የብሔርተኞቹ የማያባራ ቅራኔ አካል የሆነው የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የወሎ እርስ በርስ አለመናበብ ነው። አንድ ቋንቋ እና አንድ እምነት ተከታይ በመሆን ወጥነት አላቸው የሚባሉት ሶማሊዎች እንኳን በጎሳ ፖለቲካ ይናጣሉ።  ትግራይም በገዢዎቿ ፈርጣማ እጆች ተጨብጣም እንኳ የአውራጃዊነት ፈተና የተዳፈነ እሳት ሆኖ ይለበልባታል። ከእነዚህ እውነታዎች የምንረዳው ጉዳይ ብሔርተኝነት እንደሽንኩርት ተልጦ የማያልቅ መሆኑን ነው። ጠቅላይ የሚመስለው ማንነት ሲላጥ፥ ሁሌም ከውስጡ ሌላ ማንነት ይወጣል።
ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝም ጋር ሲጋባ የተወለደው ሌላው ችግር ክልሎችን እንደ ብሔር ንብረት መመልከቱ ነው፤ ይህም ነው ክልሎችን የሚቃወሙትን አሃዳዊነት አራማጅ መሆናቸውን ያጋለጣቸው። የክልሎቹን ሀብትም ይሁን ሥልጣን ለመቆጣጠር ሕዝባዊ ይሁንታ እና ውክልና ሁለተኛ ደረጃ ናቸው። የመጀመሪያው መሥፈርት የዘር ሐረግ ነው። ይህ ጋርዮሻዊ አሠራር በክልሎቹ ውስጥ የባለቤት እና እንግዳ ግንኙነት ፈጥሯል። ይህ ግንኙነት የሚያሳድረው ቅራኔ የነገ ትውልድ የራስ ምታት ነው።
ለማንነት ጥያቄ መልሱ ፍትሕ ነው
በዘር ሐረጌ እዛመዳቸዋለሁ ብለው በሚያስቧቸው ባለታሪኮች የሚመኩ ብሔርተኞችን እና ጭቁን ብሔሬን እወክላለሁ የሚሉ ብሔርተኞችን ነጥዬ አልመለከታቸውም። ልዩነታቸው የመነሻ እንጂ የመድረሻ አይደለም። በፍራንሲስ ፉኩያማ የማንነት ጥያቄ መሥመር የዕውቅና ጥያቄ፣ የእኩልነት ጥያቄን አስከትሎ፣ ከዚያም የበላይነት ፍላጎት የሚሆነው የማንነት ጥያቄ በብሔርተኞች እጅ ሲወድቅ ነው። ብሔርተኞች እንደ እንጉዳይ ናቸው። ራሳቸውን ችለው መቆም አይችሉም፤ የሚጠለሉበት ዛፍ ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም ወክሎ ያልሾመቸውን ሕዝብ/ብሔር እንወክለዋለን ይላሉ፣ ያንን ሕዝብ በራሳቸው ብያኔ ልክ ይሰፉታል። ከዚያ በኋላ “ሕዝባቸው” እነርሱ ባጠፉት ይወቀሳል፣ የነርሱን ጦርነት ይዋጋል፣ ወዘተ. ድል የተጎናፀፈ ጊዜ ግን ክብሩንና ሽልማቱን የሚያፍሱት ነጠላ ግለሰቦች ናቸው። ብሔርተኛው ትሕነግ ሥልጣን ላይ በቆየበት ዘመን መሪዎቹ ብዙ ሀብት አካብተዋል። የትግራይ ሕዝብ ግን በትሕነግ መሪዎች ጥፋት ተወቃሽነቱን ወስዷል፤ የትግራይ ድህነት በብሔርተኛ መሪዎቹ ሀብት አልተለወጠም። ብሔርተኝነት ላልተመረጡ የብሔር ወኪሎች አትራፊ ንግድ ነው።
የማንነት ጥያቄ ግን በመሠረቱ የፍትሕ ጥያቄ ነው። ፍትሕ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መበላለጦችን የሚጠየፍ፣ በተፈጥሮ አጋጣሚ፣ በአንድ ቦታ፣ ከሆኑ ሰዎች በመወለድ ሳይሆን በሚዛናዊ አእምሮ በመመርመር የሚገኝ፣ የተነጠቀውን የማስመለስ ብቻ ሳይሆን የነጠቀውን ለመመለስ የቆረጠ ሕሊና ይፈልጋል። ያ ሕሊና በብሔርተኛ ጭንቅላት ውስጥ አይገኝም። ብሔርተኝነት የወዳጅ እና ጠላት መሥመር ያሠምራል እንጂ የፍትሕ ሚዛን የለውም። ፍትሕ የኛ የሆነ በሙሉ ትክክል፣ የነርሱ የሆነ በሙሉ ስህተት በሚል የብሔርተኛ ትክርት አይገኝም። የማንነት ጥያቄዎችን መልስ ለማግኘት የብሔርተኝነትን ቅርፊት ሰብሮ በመውጣት ዳግም መወለድ ይፈልጋል።
Filed in: Amharic