>

ኢዜማ " የዘውጌ ብሔርተኛ" ወይንስ "ማህበራዊ መሰረት ፍለጋ?" (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ኢዜማ ” የዘውጌ ብሔርተኛ” ወይንስ “ማህበራዊ መሰረት ፍለጋ?”

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

 

  መንደርደሪያ፣
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና “አባቴ” ብሎ በሚጠራው አባዱላ ገመዳ አማካኝነት እንደ በሬ ቅርጫ የተሸነሸነው የደቡብ ክልል ሰሞኑን በከፍተኛ ሁኔታ እያነጋገረ ነው። በተለይም ጌድዮን ለወደፊት የሚወሰን ሆኖ ለአሁኑ ግን  “በልዩ ዞን” ትደራጅ መባሉ የኦሮሙማ የመዋጥና ስልቀጣ የቀደመ እቅድ ወደ ተግባር የተቀየረበት መሆኑ ብዙዎችን አስደንግጧል። የወላይታ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት ራሳቸውን ከክልሉ ፓርላማ ማግለላቸውም ሌላኛው አስገራሚ ዜና ነው። በዚህ ምክንያት ተደጋፊ ተደማሪውን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን “የለውጡ ባቡር ወዴት እየወሰደን ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል።
ከዚህ የአብይና አባዱላ የደቡብ መሰነጣጠቅ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች የተቃውሞ መግለጫ እያወጡ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ኢዜማ ከወትሮው በተለየና ጠንከር ያለ መግለጫ በማውጣት የቅድሚያውን ይይዛል። ኢዜማ ለምን በተቆጣና እነ አቢይ አህመድን በሚያስፈራራ መንገድ መንገድ መግለጫ ማውጣት ፈለገ?… ኢዜማ ደቡብ ላይ ሲደርስ ለምን አራስ ነብር ሆነ?… ኢዜማ የዜግነት ፓርቲ ነው ወይንስ የዘውጌ ብሔርተኛ ድርጅት?… ኢዜማ ደቡብን እየሸነሸነ ከሚያከፋፍለው አብይ አህመድ ጋር የጀመረው ቀዝቃዛ ጦርነት መዳረሻው የት ይሆናል?… ኢዜማ-ወ-አብይ ተደጋፊ ተደማሪዎች ምን አቋም ይወስዳሉ?…እነዚህን የመሳሰሉ ቁም ነገሮች አንስቶ መወያየቱ የበለጠ ስዕል ይሰጣል።
1:- የደቡብ “ፓንዱራ ሳጥን”
ለማንም ግልጥ ሆኖ እንደታየው የዛሬ ሁለት አመት ገደማ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ በጥፍራችን የመቆም ያህል ደግፈነው ነበር። በሂደትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአስፈንጥዝ ንግግር ያለፈ የተጨበጠ ፍኖተ ካርታ እንደሌላቸው ስንገነዘብ ራሳችንን ወደ ” ሞጋች ደጋፊነት” ቀይረን አቅጣጫ ለማሳየት ሞክረን ነበር።
ሞጋች ደጋፊ በነበርን ሰአት የሰጠነው ምክረ-ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝበኝነቱን አጥብቆ በመያዝ የፈጠረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እሰከ ጫፍ የማንቀሳቀስ ስራ አጠናክሮ ይቀጥል የሚል ነበር። በሌላ አነጋገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝበኝነትን እንደ ታክቲክ በመውሰድ ማህበራዊ ንቅናቄ መፍጠሪያ ያድርገው የሚል ነበር። የህዝበኝነት ማህበራዊ ንቅናቄው መዳረሻም ህገ-መንግስቱን በህዝብ ሃይል እንዲታገድ ማድረግ የሚል ነበር። እርግጥም በወቅቱ በውስጥም ከአገር ውጪም የተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ የህውሓት ፕሮግራም ግልባጭ የሆነውን ህገ-መንግስት በአደባባይ ቀዳዶ ለመጣል የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነበር።
ሆኖም የጠበቅነው ህዝባዊ ንቅናቄ ተገልብጦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድርጅት ዛጐል ውስጥ እንደ ዋናተኛ ሰቶ ገባ። በእኔ እምነት የአብይ አህመድ የስህተቶች ሁሉ ስህተት ይሄ ይመስለኛል። በማስከተልም የኖቤል ሽልማቱ ሊፈጥር የሚችለው ማህበራዊ ንቅናቄ መክኖ መቅረቱ ሁለተኛው ትልቅ ስህተት ነበር። በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ የአዲስ አበባን ባለቤትነት አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ፣ ግልጽ ጦርነት እወጃ፣ ስርአት አልበኝነትን መቆጣጠር አለመቻል ጉዞውን ከድጡ ወደ ማጡ ወሰደው። ይህም ሆኖ ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ነውና ምክረ-ሃሳባችንን ከማቅረብ ወደ ኃላ አላልንም። በተለይም የደቡብ ክልልን በተመለከተ ሁኔታው “ከፓንዱራ ሳጥን” ጋር ስለሚመሳሰል በጭራሽ ባይነካኩት ብለን በመደጋገም ጮኸን ነበር።
እርግጥም የደቡብ ክልልን መነካካት የሉሲፈርን ስጦታ የያዘ ሳጥን የመክፈት ያህል ከባድ ነው። በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳይከፋፍቱት ” እኔ የሽግግር ጊዜ መሪ ስለሆንኩ በደቡብ የሚነሱ የክልልነት ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት እስኪመጣ ይቆያል” የሚል ማምለጫ ቆፍጠን ባለ መልኩ መግለጫ ይስጥ ብለን ነበር። ይሄም አልተሳካም። ያተረፈልን “ፀረ-ለውጥ” እና ” የአብይ ጠላቶች” የሚል ነበር።
እነሆ! ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፓንዱራ ሳጥኑን በሲዳማ ከፍቶታል። ይባስ ብሎ “የብልጽግና ፍሬ” በማለት የደስታ መልዕክት አስተላለፈ። ውጤቱ የዴሞክራሲ ዘመን መጀመሩና የአፈና ዘመን መቆሙን አመላካች እንደሆነ ተነገረ። በጣም አስደንጋጭ ነበር።
2:- ኢዜማ የዘውጌ ብሔርተኛ ነወይ?
ከአንዳንድ ወዳጆቼ ጋር በኢዜማ የፓለቲካ አካሄድ ላይ ስንከራከር ቆይተናል። በእኔ በኩል ሲቀርብ የነበረው መከራከሪያ የኢዜማ ጥፋት ሙሉ ለሙሉ “ኢትዮጵያዊ ማንነት” እና “የዜጋ ፓለቲካን” መሰረት ቢያደርግም በተግባር ግን ይሄን ማህበራዊ መሰረት ክዷል የሚል ነበር። ይሄ ማህበራዊ መሰረት ከዘውጌ ብሔርተኞች( የኦሮሞ ብልጽግናን ጨምሮ) ጥቃት ሲፈጸምበት ሊከላከሉለትና አለሁልህ ሊሉት አልቻሉም የሚል ነበር። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን አንዳንድ ትልቅ ተጽእኖ ያላቸው የኢዜማ መሪዎች ትልቁ ስህተት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን “ህይወትም መንገድም” አድርገው መውሰዳቸው እንደሆነ እከራከር ነበር። ለህሊናቸው ያደሩ፣ በዚህ የማያምኑና በውስጥ አምርረው የሚታገሉ አመራሮች መኖራቸውን ሳልዘነጋ!
እናም አሁን “ኢዜማ ዘውጌ ብሔርተኛ አይደለም” ብዬ በእምነት መከራከሬ ትክክል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። ለዚህ እማኝ የሚሆኑኝ ሰሞኑን የተከሰቱ የተለያዩ ምክንያቶችን ማንሳት እችላለው።
2.1. የህውሓትን ሕገ-መንግስት መቀበል
 የመጀመሪያው የአብይን መንግስት ስልጣን ለማራዘም የህውሓት/ኢህአዴግ ሕገ-መንግሥት ውስጥ ሲርመጠመጥ መመልከቴ ነው። ትላንት “ይሄ ሕገ-መንግስት ከተፃፈበት ወረቀት በላይ ዋጋ የለውም!” በሚለው ብራንድ የምናውቃቸው የፓለቲካ መሪዎች መፍትሔ ከዚህ ሕገ-መንግስት ሲፈልጉ (ያውም አስቀድሞ የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ያረፈበት መሆኑን እያወቁ) መኳተናቸው እጅግ አስገራሚ ነበር። የአቢይን ስልጣን ማራዘም ፍላጐታቸው ቢሆን እንኳን የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የኮሌራ ወረርሽኝ፣ የጠላት ወረራ፣ በቀጣይ የሚያሰጋው ረሃብ፣ ስርአት አልበኝነት፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ…ወዘተ በምክንያት ማቅረብ በቂ ነበር። በመሆኑም ኢዜማ ህገ-መንግስት ትርጓሜ ውስጥ የገባው አስቀድሞ ህገ-መንግስቱን ስለሚቀበል ነው የሚለው መከራከሪያ የሚያስኬድ ይሆናል።
2.2. የቀድሞውን አደረጃጀት እንደ ስህተት መውሰድ
ሁለተኛውን ዋነኛው ደግሞ ኢዜማ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ ነው።
“ገዥው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር ወይም ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሕገወጥ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሔ ለመቅረፍ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት) እና ካለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሒደት ነው” ይላል።
ከዚህ የኢዜማ መግለጫ መረዳት የሚቻለው ኢዜማ ደቡብ ክልል ከምሥረታው ጀምሮ ቅቡልነት ያልነበረው አደረጃጀት እንደሆነ ያምናል። አሁንም እየተኬደበት ያለው መንገድ እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሳይሆን የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት እንደሆነ የፀና እምነት አላቸው። ከሁሉም በላይ የኢዜማን መግለጫ አስደንጋጭ የሚያደርገው በደቡብ ክልል የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎች በሙሉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ስለሆኑ ሳይሸራረፉ ይከበሩ የሚለው ነው። በሌላ አነጋገር የሲዳማ ውሳኔ ለሌሎቹም ተግባራዊ ይሁን ማለት ነው።
እስቲ መጀመሪያ ወደ ሌላ ከመግባታችን በፊት የክልል የመሆን ጫፍ የደረሰችውን ሲዳማ በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል እናንሳ። የኢትዮጵያን ፓለቲካ የሚያሽከረክረው የዘውጌ ልሂቃኑ በመሆኑ የሲዳማ ጉዳይ ፈላጭ ቆራጩም የብሔረሰቡ ኤሊቶች ናቸው። ይሄ ልሂቅ ተብዬ በቅርብ ጊዜ የሲዳማ ክልል ህገ-መንግስት ያወጣል። በህገ-መንግስቱም “የክልሉ ባለቤት የሲዳማ ብሔር ነው” የሚል ይከተባል። የክልልነት ጫጉላ ካለቀ በኃላ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ዜጋ ይሆናሉ። ወይንም በግዳጅ አስምሌሽን ሲዳማ ይሆናሉ። የክልሉ ብሔራዊና የስራ ቋንቋ ሲዳምኛ ብቻ ይሆናል። የአማርኛ ቋንቋ በጠላትነት ተፈርጆ ወደ መቃብር እንዲወርድ ይደረጋል። በሂደትም እንደ ትግራይ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱ በአማርኛ የተፃፉ ታፔላዎች እየተነቀሉ ይጣላሉ። የሲዳማ ብሔረሰብን ብቻ የያዘ የፓለቲካ መስተዳድር፣ ሊግ፣ ወጣት ማህበር፣ ሴት ማህበር፣ ፓሊስ፣ ልዩ-ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ሚዲያ፣ ባንክ፣ ኢንሹራንስ ይደራጃል።
እንግዲህ ኢዜማ “የራስን እድል በራስ የመወሰንና ማስተዳደር” እታገላለሁ ሲል ከላይ ሲዳማን በምሳሌነት የተጠቀሰው እንዲሳካ እታገላለሁ ማለቱ ነው። እዚህ ላይ ሲዳማ በአብነት ተነሳ እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ ከደርዘን በላይ ክልሎች ሲፈጠሩ የሚሆነው ተመሳሳይ ነው። በመሰረቱ በሲዳማና ወላይታ፣ በሲዳማና ጉራጌ፣ በሲዳማና ከንባታ፣ በሲዳማና ሀድያ፣ በሲዳማና ስልጤ…ወዘተ ፓለቲከኞችና ኤሊቶች መካከል የአስተሳሰብ ልዩነት የለም። ሁሉም ተራቸው ሲደርስ ተመሳሳይ ነገር ይፈጽማሉ። እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰራቸው አማርኛ ውግዝ ከማሪዮስ ይባላል። የብሔረሰቡ ፓሊስ፣ ልዩ-ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ሚዲያ ብቻ ይደራጃል። አሁንም የክልል የመሆን ጫጉላ ዘመን ከተሰናበተ በኃላ “አቃፊ ነኝ” ሲል የነበረው በሙሉ አባራሪና አሲምሌተር ይሆናል።
 
2.3. እየተፈጠረ የነበረውን “ደቡብ ነኝ!” የሚል ማንነት አለመቀበል፣
ኢዜማ በደቡብ ክልል ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች እታገላለሁ ሲል በሌላ አነጋገር የመጪው ጊዜ የኢትዮጵያ አደረጃጀት ጐሳንና ብሔረሰብን ያድርግ ማለቱ ነው። ኢዜማ በዚህ ውሳኔው በሚያሳዝን መልኩ ከፈረሰው የሞፈሪያት ድርጅት ደኢህዴንም ያነሰ የዘውጌ አመለካከት ያለው መሆኑን ያረጋገጠበት ነው። ሁሉም እንደሚያስታውሰው የሞፈሪያት ፓርቲ የነበረው ደኢህዴን 20 ምሁራንን በማሰማራትና ከ17ሺህ በላይ ዜጐችን በማሳተፍ ጥናት ሰርቶ ነበር። በዚህ ጥናት የተረጋገጠው አንድ ቁምነገር ለኢዜማ ትልቅ ትምህርት ሊሆነው ይገባ ነበር። ይህ የምሁራን ግኝትና ደኢህዴን ያፀደቀው ሃሳብ ” በክልሉ የሚኖሩ ዜጐች ደቡብ ነኝ ይላሉ፤ ደቡብ ነኝ የሚል ማንነት ተፈጥሯል” የሚል ነበር።
 በመሆኑም ኢዜማ እንደሚለው የዜግነትን ፓለቲካ የሚያራምድ ከሆነ ይህንን የደኢህዴንን ግኝት እንደ ግብአት ተጠቅሞ ማክሲማይዝ ማድረግ ነበረበት። ይህንን በማድረግና የደቡብ ክልል እንዳይፈርስ በመታደግ ኦሮሙማን፣ ኦሮማራን፣ ህውሓትን የሚግደረደር ጠንካራ “ደቡብ ነኝ” የሚል የሃይል ሚዛን የሚያስጠብቅ ሃይል እንዲወጣ ማድረግ ይቻል ነበር። ለምሳሌ የማንንም የድጋፍ ድምፅ ሳይጠይቅ የህገ-መንግስት ፍርድ የሚሰጥበትን፣ የበጀት ድልድል የሚሰራበትን፣ ድንበርና ወሰን የሚወሰንበትን የፌዴሬሽን ምክር-ቤት አፈ-ጉባኤና የአብላጫ ድምፅ ውሳኔ ያለተቀናቃኝ ህገ-መንግስቱ እስካለ ድረስ ለሁልጊዜም ይቆጣጠረው ነበር።
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ እየተፈጠረ የነበረው “ደቡብ ነኝ” የሚል አዲስ ማንነት በርካታ ጠቀሜታዎች ነበሩት። ብሔረሰቦቹ የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች እሴቶችን ከማሳደግ በተጨማሪ እርስ በእርስ የሚያስተሳስራቸውን የአማርኛ ቋንቋ ይጠቀማሉ። ቋንቋውን በደንብ በማወቃቸው በፌዴራል መንግስት ደረጃ (ቢሮክራሲ፣ ፍርድ ቤት፣ ፀጥታ መዋቅር) ተሳታፊ ይሆናሉ።
እንግዲህ ኢዜማ ” ራስን በራስ ማስተዳደር” በሚል አሁን የተሳውን ማቆሚያ የሌለው የክልልነት ጥያቄ እደግፋለሁ ሲል ከላይ የተዘረዘረውን “የደቡብ ነኝ” ማንነት ጠቀሜታ ሳይረዱት ቀርተው አይደለም። ይልቁንስ የወቅቱ ፓለቲካ በጠባብ ዘውጌያዊ ብሔርተኛ የበላይነት የሚመራ በመሆኑ መርህ አልባ በሆነ መንገድ ማህበራዊ መሰረት የማሰባሰብ ሩጫ ነው።
3:- የኢዜማና አብይ አህመድ ቀዝቃዛ ጦርነት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢዜማና የብልጽግና ፕሬዚዳንት አብይ አህመድ ቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ የገቡ ይመስላሉ። ሁለቱም ሃይሎች የጋራ ደጋፊዎቻቸውን ግራ በሚያጋባ መልኩ በቃላትና መግለጫ መጠዛጠዝ ጀምረዋል። አልፎ አልፎም በውጪ አገር የሚገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች( የትላንትና የዶክተር ሽፈራው አዲሉን የፌስቡክ ጽሁፍ ልብ ይሏል) የኢዜማን መግለጫ በማወደስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስጠንቅቀዋል። ያም ሆነ ይህ በሁለቱ አካላት መካከል የተከፈተው ቀዝቃዛ ጦርነት የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህ ፍጥነት ይመጣል ብሎ የሚያስብ በጣም ጥቂት ይሆናል።
 
 3.1. አብይ በኢዜማ ላይ
አብይ በኢዜማ ላይ የመጀመሪያው የቀዝቃዛ ጦርነት ጅማሮ በኢዜማ አመራሮች ሞራልና ስብዕና ላይ መረማመድ ነው። ርግጥም አብይ አህመድ በተለያየ ጊዜያቶች ኢዜማንና አመራሩን ለማበሻቀጥ የሄደበት እርቀት በትእግስት የሚታለፍ አልነበረም። በተለይም በፓርላማ ውስጥ በወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በኩል አልፎ ኢዜማን በቃሪያ ጥፊ የመታበት አካሄድ የሚያሸማቅቅ ነበር። በዛው የፓርላማ መድረክ የኢዜማ ወላጅ አባት ተደርጐ የሚወሰደው ግንቦት ሰባትና መሪው አንዳርጋቸው ጽጌ ” የኢትዮጵያን አንዲት ጋት መሬት መያዝ ያልቻሉ” በማለት ትግላቸው እርሱን ቢስ እንደነበር በአድኖ መግደል ስልት ኩምሽሽ አድርጓል። በነገራችን ላይ አብይ አህመድ በኢህአዴግ ደረጃ የተለመደው ” አድኖ የመግደል” ስልት የሚስተካከላቸው እንደሌለ በቀላሉ መታዘብ ችያለሁ።
የቀዝቃዛው ጦርነት ሁለተኛ ምክንያት የብልጽግና ፕሬዝዳንት አብይ አህመድ ኢዜማን ቀስ በቀስ ማህበራዊ መሰረቴ ከሚለው እያናጠበው መምጣቱ ነው። የግንቦት ሰባት ሰራዊት በታቀደ መንገድ እንዳይቋቋሙ የተኬደበት አካሄድ የቀድሞ አመራሮቹ ንቅናቄውን ለቀው እንዲወጡ ከማስገደዱም በላይ ኢዜማ ከአማራ ክልል ተነቅሎ እንዲወጣ አድርጐታል። ተፈናቃዮቹ አሁንም ጭምር ዞር ብሎ የሚያያቸው አለመኖሩና ቁጭት ውስጥ መግባታቸው “የኢዜማ አመራሮች ከዚህ በኃላ በነፃነት በአማራ ክልል መንቀሳቀስ ይችላሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት አብይ አህመድ ኢዜማን ቀጥሎ ያናጠቡት ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ነው። ፓርቲያቸው ኦህዴድ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአዲስ አበባን ባለቤትነት በግላጭ ሲያውጅና አዲስአበቤን በጠላትነት ፈርጆ ሲገድል፣ በተረኝነት መሬትና መታወቂያ ሲያድል፣ የአዲስአበቤ ወጣትን ጦላይ ማጐሪያ ሲወስድ፣ ኦሮሙማ እንደፈለገ ሲፈነጭ ኢዜማ አይቶ እንዴላየ ሆኖ ነበር። ይባስ ብሎም አንዳንዶቹ ስራ አስፈፃሚዎቹ ” መግለጫ ማውጣት ድሮ ቀረ! የሚሰማን መንግስት አግኝተናል!” በማለት ዲስኩር እስከማሰማት ደረሱ።
የብልጽግና ፕሬዝዳንት አብይ አህመድ ኢዜማን በማስከተል ለማናጠብ እየሞከረ ያለው በደቡብ ክልል ከሚኖሩ ብሔረሰቦች ጋር ነው። ይህ የአብይ አካሄድ እጅጉን ያስደነገጠው ኢዜማ የደበቀውን የዘውጌ ፓርቲነት ከማጋለጡ ባልተናነሰ የማህበራዊ መሰረት ፍለጋ ላይ እየኳተነ መሆኑን አሳይቷል። እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ ክልልን በተመለከተ ከፍተኛ ጦርነት የገጠሙት ከኢዜማ ጋር አይደለም። ዋነኛው ጦርነት በጃዋር መሀመድ ከሚመራው ኦሮሙማ ጋር ነው። በግልጽ እንደሚታየው ሲዳማን በድል የተወጣው የጃዋር ኦሮሙማ ስራውን የሚያጠናቅቀው ደቡብ ክልልን እንደ ዶሮ ብልት 12 ቦታ ከሰነጣጠቀ በኃላ ነው። ለዚህም እንዲረዳው የዘውጌ ነፃ አውጪዎችን አደራጅቶ ከጀርባ ሆኖ እየመራ ነው። በሌላ በኩል አብይ አህመድ በህዝብ ብዛትና ቆዳ ስፋት ትልልቅ የሆኑትን የተሸንሻኞቹ ዋና ከተማ በማድረግ አፍ የማዘጋት ስራውን አጠናክሮ እየሰራ ነው። በዚህ ስራ ውስጥ ኢዜማ ለዶክተር አብይ የጉንፋን ያህል ችግር ፈጣሪ አይደለም።
   3.2. ኢዜማ በአብይ ላይ
ኢዜማ በበኩሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ የቀዝቃዛው ጦርነት ቦንብ ሼል የጣለው ረቡዕ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው። ኢዜማ በዚህ መግለጫውና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው በኩል “ብልጽግና ዘላቂ ውሳኔ ማስተላለፍ አይችልም” ብሎታል። እንደዚህ አይነት ውሳኔ “ባልደራስ” ከአንድ አመት በፊት የመመስረቻው እለት በባልደራስ ሆቴል ካወጣቸው ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫዎች አንዱ ነበር። በወቅቱ ባልደራስ ” በፌደራልም ሆነ በአዲስ አበባ ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠ ስላልሆነ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎች መወሰን አይችልም” የሚል ነበር። ይህን በማለቱ እና በሌሎች የአዲስአበቤ አጀንዳዎች ላይ ጥብቅና በመቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ “ግልጽ ጦርነት” አወጁበት። በሌላ በኩል ባልደራስን የሚፈሩት ግን ደግሞ ተንበርካኪ ስላልሆነ በውስጣቸው የሚያከብሩት ንቅናቄ ሆኖ ዘለቀ።
ዛሬ ደግሞ ኢዜማ ከአመት በላይ ቢዘገይም ተመሳሳይ አቋም ወስዷል። ፓርቲው ይህን ያህል ጊዜ በመዘግየቱ የደረሰበት ኪሳራ ትልቅ ቢሆንም ሒሳብ የማወራረድ ስራው የአመራሩና አባላቶቹ ነው። በሌላ በኩል ዘላቂ ውሳኔ የማይተላለፍባቸው መሰረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለውንም ለወደፊት እንዳያጣላ ከወዲሁ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የብልጽግና ፕሬዚዳንት ለሁለተኛ ጊዜ ያመለጣቸውን የህዝባዊ ማዕበል እድል ለሶስተኛ ጊዜ አግኝተው ሕገ-መንግስቱን ቢያግዱ ኢዜማ አይደግፍም? የመሬት ፓሊሲውን ቢቀይር ኢዜማ አይደግፍም? የፌዴራሉን የስራ ቋንቋ ወደ አምስት ቢቀይር ኢዜማ አይደግፍም?
                       ***
ኢዜማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ያስጠነቀቀበት ሁለተኛው ነጥብ ከደቡብ ክልል ጋር የተያያዘ ነው። የኢዜማ መግለጫ ከፊል እንዲህ ይነበባል፣
‹‹ገዥው ፓርቲ ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ በመብት ሰጪና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዥው ፓርቲ እንደሚሆን በግልጽ መታወቅ አለበት፤›› ሲል አስጠንቅቋል።
ኢዜማ በዚህ መግለጫው ላይ የደቡብ ክልል ህዝብ ” አደረጃጀት እኔ አውቅልሃለሁ በሚሉ ካድሬዎች ሊከናወን የሚቻል እንዳልሆነ መረዳት አለብህ” በማለት ያስጠነቅቃል። አላማውም ገዥው ፓርቲ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያደረገው ነው ይለናል። እንግዲህ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ እስከሚያውቀው ድረስ የደቡብን አደረጃጀት በበላይነት አየወሰኑ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የጡት አባታቸው የሆኑት ጡረተኛው አባዱላ ገመዳ ናቸው። ስለዚህ በተራ የሂሳብ ሎጂክ ከሄድን የደቡብ አደረጃጀት እየተሰራ ያለው በእኔ አውቅልሃለሁ ካድሬዎች ከሆነ እና፤ አደረጃጀቱን እየሰሩ ያሉት አብይ አህመድና አባዱላ ከሆኑ፤ የማቲማቲክሱ አመክንዮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አባዱላ አውቅልሃለሁ ካድሬዎቹ እነሱ ናቸው የሚል ውጤት ይሰጠናል። ስለዚህም ከዚህ በኃላ ደቡብን መሸንሸን ባለመቆሙ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ የሚሆነው የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት አብይ አህመድ ይሆናል!
Filed in: Amharic