>
5:13 pm - Monday April 18, 3510

ያሜሪቃ ቱጃርና ያሜሪቃ ውጀ (መስፍን አረጋ)

ያሜሪቃ ቱጃርና ያሜሪቃ ውጀ

መስፍን አረጋ


ንዑስ ርዕሶች

 1. መንደርደርያ
 2. ያሜሪቃ ውጀ ምንነት፣ አመሠራረት፣ እና መሥራቾቹ
 3. ቅኝገዥና ቀማኛ
 4. የቀማኛ ዲሞክራሲ
 5. ያሜሪቃ የቀማኛ ዲሞክራሲ
 6. ያሜሪቃ ቀማኛና ጥቁር አሜሪቃውያን
 7. ያሜሪቃ ቀማኛና እስያዊ አሜሪቃውያን
 8. ያሜሪቃ ጥቁርና የአፍሪቃ አህጉር
 9. ያሜሪቃ ውጀና የአሜሪቃ ሕግ
 10. አንግሎ ሳክሶኖችና ሌሎች አውሮጳውያን
 11. የነጭ ላዕልተኛነት
 12. ዶናልድ ትራምፐና የነጭ ላዕልተኛነት
 13. ያሜሪቃ ውጀ – የነጭ ፈራንከንስቲን
 14. አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ

 

መንደርደርያ

ውጀ ማለት ባራዳ ዘይቤ ፖሊስ ማለት ነው፡፡  ይህን ኢመደበኛ ያራዳ ቃል መደበኛ እናደረገውና police የሚለውን የባዕድ ቃል እንተካበታለን፡፡  ለምሳሌ ያህል የውጀ እርመና (police brutality) ማለት የውጀ አረመኔነት ወይም ጭራቅት ማለት ነው፡፡  ያሜሪቃ ውጀ (american police) ማለት ደግሞ ያሜሪቃ ፖሊስ ማለት ነው፡፡   ይህ ጦማር የሚያተኩረው ባሜሪቃ ውጀ እርመና (american police brutality) ማለትም ባሜሪቃ ውጀ አረመኔነት እና በምክኒያቱ ላይ ነው፡፡     

ውጀ ከሚለው ቃል ወጀጀ (to police) የሚለውን ግስ እናገኛለን፡፡  ወጀጀ ማለት የውጀ ሥራ ሠራ ወይም አስሠራ ማለት ሲሆን፣ ግሱም ሲረባ ወጀጀ (to police)፣ ውጅጅ (policed)፣ ወጃጅ (policing)፣ ውጀጃ (policing) እያለ ይሄዳል፡፡  ለምሳሌ ያህል ቀበሌ ውጀጃ ይልቁንም ደግሞ ቀበሌ ጥበቃ (community policing) ማለት ቀበሌ ነዋሪውን በሚገባ ስለሚያሳትፍ፣ የቀበሌ ነዋሪው በደንብ የሚተማመንበት ውጀጃ ማለት ነው፡፡     

እግረመንገዳችንን ደግሞ ውጀ ከሚለው ቃል ወጀም (policy) የሚለውን ቃል እናገኛለን፡፡  ወጀም ማለት መመርያ ማለት ሲሆን፣ ግሱም ሲረባ ወጀመውጅምወጃሚውጀማ እያለ ይሄዳል፡፡  ወጀመ ማለት ወጀም (መመርያ) አወጣ ማለት ሲሆን፣ የእንግሊዘኛ አቻ የለውም፡፡  ለምሳሌ ያህል ያሜሪቃ ውጀነክ ወይም ውጀጃነክ ወጀሞች (police or policing related policies) የሚወጀሙት ያሜሪቃ ውጀ የፈለገውን ዓይነት እርመና (በተለይም ደግሞ በጥቁር ላይ) ቢፈጽም ተጠያቂ የማይሆንበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡  

ያሜሪቃ ውጀ ምንነት፣ አመሠራረትና፣ መሥራቾቹ

ያሜሪቃ ውጀ (american polics) በጥቁር አሜሪቃውያን (black americans) ላይ ከሞላ ጎደል በሙሉ ኢተጠያቂነት (with full impunity) በየዕለቱ የሚፈጽመውን ግፍ፣ ሰቆቃና አረመኔያዊ ግድያ ለመረዳት ያሜሪቃ ውጀ ምንድን ነው ወይም ደግሞ ሚናው ምንድን ነው የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ማጤን ያስፈልጋል፡፡  

ባጭሩ ለመናገር ያሜሪቃ ውጀ (american police) ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን ከታች መደብ (lower class) እና መኻል መደብ (middle class) አሜሪቃውያን በሚሰበሰብ ግብር (tax) የሚጠገር (financed) የላይ መደብ (upper class) ነጭ አሜሪቃውያን ዘበኛ እንዲሁም አካልዘብ (body guard) ማለት ነው፡፡  

ያሜሪቃ ውጀ የሚያገለግለውና የሚከላከለው (serve and protect) ያሜሪቃን ነጭ ቱጃር ብቻና ብቻ ነው፡፡  ቱጃሩን የሚከላከለው ደግሞ ቱጃሩ ከሚመጠምጣቸው ጥቁር አሜሪቃውያን እና ድኻ ነጮች ነው፡፡  የመከላከያ ዘዴወቹ ደግሞ ሁለት ናቸው፡፡  የመጀመርያው ዘዴ ጥቁር አሜሪቃውያን ነጭን እገዳደራሁ ብለው መነሳት ቀርቶ እንዳያስቡ፣ በጥቁር አሜሪቃውያን ላይ ሽብር እየለቀቀ እድሜ ልካቸውን በፍራቻና በስጋት እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡  ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያን ሲፈጥራቸው ወንጀለኛ፣ እጸኛ (drugist) ወዘተ. ናቸው የሚሉትን መሠረተቢስ ትርክቶች (narrations) የሚያጠናክሩ ድርጊቶችን ዘወትር እየፈጸመ የነጭ ላዕለተኝነትን (white supremacy) በማራገብ፣ ያሜሪቃ ነጭ ድኻ መሠረታዊ አጋሩ ከሆነው ካሜሪቃ ጥቁር ጋር ዓይና ናጫ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ 

ባጭሩ ለመናገር ያሜሪቃ ውጀ በጥቁር አሜሪቃውያን ላይ የሚያረምነው፣ ያሜሪቃን ጥቁር እያሸበረ አደብ እንዲያስገዛና፣ ያሜሪቃ ድኻ ነጭ ደግሞ ካሜሪቃ ጥቁር ጋር እንዳያብር ጥቁርን በመጥፎ እንዲስል፣ ካሜሪቃ ነጭ ቱጃር በሚሰጠው ይፋና ህቡዕ ትዛዝ መሠረት ነው፡፡  

ከመነሻው ጀምሮ ያሜሪቃ ውጀ የተመሠረተው ያመለጡ ባሮችን አድኖ በመያዝ ለፈንጋዮቻቸው እያስረከበ፣ ባርያ ፈንጋዮችን እንዲያገለግልና እንዲከላከል (to serve and protect) ነበር፡፡  ከነዚህ ባርያ ፈንጋዮች ውስጥ ደግሞ ዋና ዋናወቹ ያሜሪቃ መሥራች አባቶች (founding fathers) የሚባሉት እነ ጆርጅ ዋሽንግተንና ቶማስ ጀፈርሰን ነበሩ፡፡  

በተለይም ደግሞ አረቀቀው በሚባለው የነጻነት አዋጅ (declaration of independence) ላይ ሁሉም ሰወች በሰውነታቸው እኩል ናቸው (all men are created equal) ያለው ቶማስ ጀፈርሰን (Thomas Jefferson)፣ በዚያው የነጻነት አዋጅ ላይ ደግሞ በነጭ ሰፋሪወች አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸውን አገራይ አሜሪቃውያንን (native americans) አረመኔወች (savages) ብሎ የዘለፈ ተመጻዳቂ ከመሆኑም በላይ፣ በባርነት ሃጢያት የረከሰ የባርነት እርኩስ ነበር፡፡  

አብራሃም ሊንከልን (Abraham Lilncoln) ደግሞ የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ (of the people, by the people for the people) ሲል፣ የነጭ፣ ለነጭ፣ በነጭ (of whites by whites for whites) ማለቱ እንደነበር ግልጽ ስለነበር ማብራራት አላስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስቂኝም ይሆን ነበር፡፡  ባሮችን ነጻ ወጥታችኋል ሲል ደግሞ ያንግሎ ሳክሶኖችን (anglo-saxon) ጥቅሞች ለማስከበር የምትዋጉ ወታደሮች ትሆናላችሁ ማለቱ እንጅ፣ ላንግሎ ሳክሶኖች ብቻ ከቀረበው የዲሞክራሲ ማዕድ ትቋደሳላችሁ ማለቱ አልነበርም፡፡  አብራሃም ሊንከልን ማለትኮ እኮ ዳኮታ (Dakota) ከሚሰኙት አገራይ አሜሪቃውያን (native americans) ውስጥ ሠላሳ ስምንቱን (38) ማንካቶ (mankato, Minessota) ውስጥ ባንድ ላይ በመደዳ ሰቅሎ፣ የቀሩትን ዳኮታውያን ወደ ነብራስካ (Nebraska) ጠራርጎ በማባረር መሬታቸውን ለነጭ ወራሪወች ያከፋፈለ፣ ሌላኛው የአሜሪቃ ፊምበር (president)  እንድርያስ ጃክሰን (Andrew Jackson) ቸሮኪ (Chrokee) በሚሰኙት አገራይ አሜሪቃውያን ላይ ከፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ያልተናነሰ ወንጀል የፈጸመ ወንጀለኛ ነው፡፡   

ያሜሪቃን ብሔራዊ መዝሙር (national anthem) በ 1814 ዓ.ም ያረቀቀው ፈራንሲስ ኬይ (Francis Scott Key) ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያን በባርነት ወህኒ በሚማቅቁበት ዘመን፣ ያለ ምንም ኀፍረት አሜሪቃን የነጻወች አገር (the land of the free) ሲል፣ የነማን አገር ለማለት እንደፈለገ ግልጽ ነበር፡፡  ስለዚህም አሜሪቃ በወሬ ሳይሆን በተግባር ሁሉም ሰወች በሰውነታቸው እኩል የሆኑባት አገር እስክትሆን ድረስ፣ ይህ ያሜሪቃ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ባንድ ይቅርና በሁለት ጉልበት መንበርከክ ቢያንስ እንጅ አይበዛም፡፡      

ቅኝ ገዥና ቀማኛ

ቅኝ ገዥ የሚለውን ቃል ለማርባት ይመቸን ዘንድ በማሳጠር ቀጋዥ (colonialist) እንለዋለን፡፡  ግሱም ሲረባ ቀገዘቅግዝቀጋዥቅገዛ (colonialism) እያለ ይሄዳል፡፡  ቀገዘ ማለት ቅኝ ገዛ ማለት ነው፡፡  በተጨማሪ ደግሞ ቀጋዥ (colonialist) ከሚለው ቃል ዘመናይ ቀጋዥ (neocolonialist)፣ ዘመናይ ቅገዛ (neocolonialism)፣ ቀገዝ (colony) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን፡፡  ቀገዝ ማለት ቅኝ የተገዛ ምድር ማለት ነው፡፡   

ቀጋዥ(colonialist) ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን ቀማኛ ማለት ነው፡፡  የቅገዛ (colonialism) ዋና ዓላማ ደግሞ በቀማኛነት ሐብት ማካበት ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል አውሮጳ የቀማኞች አህጉር ባትሆን ኖሮ ያለማችን የመጨረሻዋ ድኻ አህጉር በሆነች ነበር፡፡  አሁንም ቢሆን አውሮጳን ገትሮ የያዛት በዘመናይ ቅገዛ (neocolonialism) አማካኝነት ከሌሎች አህጉሮች በተለይም ደግሞ ካፍሪቃ የምታጋብሰው የቅምኝት ሐብት ብቻ ነው፡፡  

የጣልያኑ ምክትል ቀዳሚ ሎሌ (deputy prime minister) ሉዊጂ ዲማዮ (Luigi Di Maio) በትክክል እንደገለጸው፣ የዘረኞቹ የኤዶልፍ ሂትለር እና ዊንስተን ቸርችል የዘረኝነት መምህር የነበረው፣ የቀንደኛው ነጭ ላዕልተኛ (white supermacist) የአርተር ጎቢኑ (Arthur de Gobineau) አገር የሆነችው ፈረንሳይ፣ የምዕራብ አፍሪቃ ቀገዞቿን (colonies) እንዳጣች ወዲያውኑ ተንኮታኩታ ሦስተኛውን ዓለም ያልተቀላቀለችው፣ አሁንም ቢሆን በዘመናይ ቅገዛ (neocolonialism) አማካኝነት ምዕራብ አፍሪቃን ስለምትቦጠቡጥ ብቻ ነው፡፡  

 

የቀማኛ ዲሞክራሲ

ቀማኞች ሲቀማኙ ፍቅረኞች ናቸው፡፡  ዓይናቸውን የሚጥሉት በቅምኝቱ ቱርፋቶች ላይ እንጅ በቅምኝቱ ሂደት ላይ ስላልሆነ፣ ቅምኝቱን ለማሳካት ማድረግ /የሚገባቸውን/ ሁሉ በሙሉ ስምምነትና ትብብር ያደርጋሉ፡፡  የቅምኝቱን አመራሮች የሚመርጡት ደግሞ የቅምኝቱን ቱርፋቶች አመርቂ ያደርጋሉ ብለው የሚያምኑባቸውን ብቁ ግለሰቦች ብቻና ብቻ ነው፡፡  ማናቸውም የቅምኝቱ አመራር አባል ደግሞ የቅምኝት አመራር ሚናውን በሚገባ ካልተወጣ /የሚጎዳው/ እሱ ራሱ በመሆኑ፣ ቦታውን ከሱ ለተሻለ ግለሰብ ለመልቀቅ ደስተኛ ነው፡፡  ማናቸውም የቅምኝቱ ዐባል ደግሞ ቅምኝቱን አመርቂ ለማድረግ ይበጃሉ የሚላቸውን ሐሳቦች የመግለጽ ሙሉ ነጻነት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲገልጽም በእጅጉ ይበረታታል፡፡   

ቅምኝቱ ከተከናወነ በኋላ ግን አብዛኞቹ የቅምኝቱ አባሎች በቅምኝቱ ቱርፋቶች ክፍፍል ቅር ይሰኙና በቅምኝቱ ወቅት የነበረው ፍቅር ወደ መናቆር ይለወጣል፡፡  በክፍፍሉ እጅግ የተጎዱት፣ በክፍፍሉ እጅግ በተጠቀሙት ላይ መሣርያ እስከማንሳት ይደርሳሉ፡፡  ተጠቃሚወቹ ደግሞ ጥቅማቸውን የሚያስከብር ድርጅት አቋቁመው በዘረፉት ልክየለሽ ሐብትና ንብረት አማካኝነት የበላይነት ይይዙና የቱጃሮች፣ በቱጃሮች፣ ለቱጃሮች የሆነ የቱጃር ስርዓት ይመሠርታሉ፡፡  

የዚህ የቱጃር ስርዓት ዋና ተግባር ደግሞ ለግል ሐብት ከሚገባው በላይ አጽንኦት በመስጠት፣ የቱጃሮቹን የቅምኝት ቱርፋቶች መጠበቅና ማስጠበቅ ነው፡፡  በተለይም ደግሞ ስርዓቱ በይበልጥ የሚያተኩረው በቅምኝቱ ክፍፍል እጅግም ያልተጠቀሙት የቅምኝቱ አባሎች እድላቸውን እየረገሙ ከፍፍሉን አሜን ብለው እንዲቀበሉ የሚያስገድዱ ሕጎችን በመሐገግና፣ ሕግ አስከባሪውን ኃይል በማጠናከር ነው፡፡  

በቅምኝቱ ቅር የተሰኙት የቅምኝቱ አባሎች ቅሬታ እየባሰ ሲሄድ፣ እነዚህን ቅሬተኞች ለማፈን የተሐገጉት ሕጎችና የተደነቡት ደንቦች በዚያው ልክ እየሰፉና እየጠነከሩ ይሄዳሉ፣ በቅምኝቱ ወቅት የሰፈነው ዲሞክራሲም በዚያው ልክ እየጠበበና እየተዳከመ ይሄዳል፡፡  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ሙሉ አምባገንነት ይለወጣል፡፡

የቅምኝት ዓላማን ለማሳካት የግድ ስለሚያስፈልግ ብቻ በጊዜያዊነት የሚያገለግል፣ ዓላማው ከተሳካ በኋላ በጊዜ ሂደት ወደ ሙሉ አምባገነንነት የሚለወጥ ዲሞክራሲ የቀማኞች ዲሞክራሲ ይባላል፡፡  ለምሳሌ ያህል የኦሮሞ ገዳ የሚባለው ስርዓት፣ ኦነጋውያን እንደሚሉት እውነተኛ ዲሞክራሲ ሳይሆን፣ ባሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ለተከናወነው መጠነ ሰፊ ቅምኝት እንዲያገለግል ብቻ በጊዜያዊነት ከተሠረተ በኋላ ቅምኝቱ /ሲገታ/ ወዲያውኑ የከሰመ የቀማኞች ዲሞክራሲ ነበር፡፡   

 

የሜሪቃ የቀማኛ ዲሞክራሲ

በቅምኝት የተመሠረተችው አሜሪቃ፣ ዲሞክራቲክ የሆነችው ቅምኝቱን ለማሳካት የግድ ዲሞክራቲክ መሆን ስለነበረባት እንጅ፣ ዲሞክራቲክ መሆን ስለፈለገች አይደለም፡፡  አሜሪቃ ዲሞክራቲክ የሆነችው በዲሞክራሲ ስለምታምን ቢሆን ኖሮ፣ ጥቁር አሜሪቃውያንን እና አገራይ አሜሪቃውያንን (native americans) በተመለከተ ፍጹም ኢዲሞክራቲክ ባልሆነች ነበር፡፡  ያሜሪቃ ዲሞክራሲ የቀማኞች፣ በቀማኞች፣ ለቀማኞች የሆነ ውስን ዲሞክራሲ ነው፡፡  በሌላ አባባል ያሜሪቃ ዲሞክራሲ የቀማኛ ዲሞክራሲ ነው፡፡ 

እንደ ማናቸውም የቀማኛ ዲሞክራሲ፣ ያሜሪቃ የቀማኛ ዲሞክራሲም ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ ነው፡፡  በቅምኝት ዘመን የነበረው ያሜሪቃ ዲሞክራሲ ለሁሉም ቀማኞች ፍጹም ነጻነት ያጎናጸፈ ዲሞክራሲ ነበር፡፡  ቀማኞቹ በሐብት ይበልጥና ይበልጥ እየተለያዩ ይበልጥና ይበልጥ እየተቃቃሩ ሲሄዱ ግን ዲሞክራሲው ይበልጥና ይበልጥ የሐብታሞች፣ በሐብታሞች፣ ለሐብታሞች እየሆነ መጣ፡፡   ያሜሪቃው የርስበርስ ጦርነት የተነሳውም የደቡቡ ዲክሲ (Dixie) ቀማኛ በሰሜኑ ያንኪ (Yankee) ቀማኛ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሮ መሣርያ በማንሳቱ ነበር፡፡  

የዓለም አዛዥና ናዛዥ ሁኘ፣ ሁሉን በጀ በደጀ ካላደረኩ የምትለው፣ ዜጎቿን ሰባት/ሃያ አራት የምትሰልለው የዘመኗ አሜሪቃ ደግሞ፣ ዲሞክራቲክ ከምትባል ይልቅ ዓምባገነንነት የተጠናወታት አጼፈናኝ (imperialist) ብትባል የበለጠ እንደሚገልጻት፣ ዊሊያም ቦነር (William Bonner) እና ኤዲሰን ዊጊን (Addison Wigin) እደኛው አጼጌ (Empire of Debt) በተሰኘው ድንቅ መጽሐፋቸው ላይ በሰፊው አብራርተውታል፡፡  በዚህ ከቀጠለች ደግሞ ፍጹም አምባገነን የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡   

በመሬት ቅምኝት የተመሠረተው ያሜሪቃ የቀማኞች ዲሞክራሲ፣ የመሬት ቅምኝቱ ሲያክትም አብሮ ያላከተመበት ምክኒያት፣ ቅምኝቱ አሁንም ቢሆን በተዛዋሪ ዘዴወች በተለይም ደግሞ በጠገራዊ (financial) ዘዴወች እየተከናወነ በመሆኑ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ባለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች አማካኝነት የአልምዕራብ (non-western) አገሮች አንጡራ ሐብት ወደ ምዕራብ አገሮች በተለይም ደግሞ ወደ አሜሪቃን በገፍ የሚጎርፍበት ጠገራዊ ቅምኝት (financial robbery) ዳፋው ከመሬት ቅምኝት ቢብስ እንጅ አያንስም፡፡      

ያሜሪቃ ቀማኛና ጥቁር አሜሪቃውያን

ያሜሪቃ መሥራች አባቶች (founding fathers) የሚባሉትን ሁሉንም ጨምሮ ያማሪቃ ላይ መደብ ነጮች (upper class whites) አብዛኞቹ ቱጃሮች ለመሆን የበቁት፣ ወላጆቻቸው ካገራይ አሜሪቃውያን (native americans) በነጠቁት ዲካ የለሽ መሬት ላይ የጥቁር አሜሪቃውያንን (black americans) ጉልበት በነጻ በማፍሰስ ባካበቱት የደም ሐብት ነው፡፡  አሁን ደግሞ የልጅ ልጆቻቸው በገንዘብ ባሕር የሚዋኙት በትውልድ ሐረግ የመጠጡትን ይህን የደም ሐብት መሠረት አድርገው፣ የዓለምን የሐብት ፍሰት በበላይነት የሚቆጣጠሩ ዘመናይ ቀጋዥ (neo-colonialists) በመሆን ነው፡፡

ቀማኛ ሲባል በተፈጥሮው ቱርቂ (ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ የሚያልበው ፈሪ) ስለሆነ፣ ያሜሪቃ ነጭ ቱጃር በቀማኛነት ያፈራሁትን ሐብትና ንብረት እነጠቅ ይሆናል የሚለው ስጋት ቀን ከሌት እያስጨነቀ እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡  ከዚህ ጭንቀቱ የተነሳ ሐብትና ንብረቴን ያስከብሩልኛል ብሎ የሚያስባቸውን የሕግ ዓይነቶች ሁሉ ሐግጓል፡፡  አሜሪቃን አሜሪቃ ካስባሏት ውስጥ አንዱና ዋናው ርዕሰሕጓ (ሕገ መንግስቷ constitution) ለግል ንብረት (private property) የሚሰጠው መጠን ያለፈ አጽንኦት (emphasis) የሆነበትም ምክኒያት፣ ይህ ካሜሪቃ መሥራች አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የቀማኛ እቀማለሁ የሚል መጠን ያለፈ ፍራቻ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል መንገድ የጠፋው ሰው በሌላ ሰው መሬት ላይ ሲሄድ ባለመሬቱ ቢገድለው፣ ተገዳዩ ደመ ከልብ ነው፡፡  እነጠቅ ይሆናል ብሎ ይህን ያህል የሚሰጋ የነጠቀ ብቻ ነው፡፡ 

ያሜሪቃ ነጭ ቀማኛ ባንደኛ ደረጃ የሚፈራው ጥቁር አሜሪቃዊን ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚፈራው ደግሞ በታች መደብ (lower class) ላይ የሚገኘውን ያሜሪቃን ነጭ ድኻ ነው፡፡  አገራይ አሜሪቃውያንን (native americans) አብዛኞቹን ጨፍጭፎ ስላጠፋቸው፣ የቀሩትን ጥቂቶቹን ደግሞ በእጽ እና በመጠጥ ስላኮላሻቸው በነሱ በኩል ስጋት የለባትም፡፡ 

 ካገራይ አሜሪቃውያን (native americans) የሚፈለገው መሬታቸው ብቻ ስለነበረ፣ መሬታቸውን ከተነጠቁ በኋላ ተጨፍጨፈዋል፡፡  ከጥቁር አሜሪቃውያን የሚፈለገው ደግሞ የባርነት ነጻ ጉልበታቸው ስለነበረ፣ ጉልበታም ጥቁሮች እየተመረጡ እንዲራቡና እንዲበራከቱ ተደርገዋል፡፡  

ያሜሪቃ ጥቁር ያሜሪቃን ነጭ ቱጃር በእኩይ ሥራው እንደሚንቀውና እንደሚጠየፈው፣ ነጩ ቱጃር የሠራበት ግፍ እንደ እግር እሳት እንደሚያንገበግበው፣ በሚገባ ከተማረ፣ ከበለጸገ፣ ከተደራጀና ከታጠቀ ደግሞ የነጩን ቱጃር የቀማኛ ዋሻ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመደረማመስ የሚያስችለው እምቅ ሥጋዊና መንፈሳዊ ኃይል እንዳለው፣ ነጩ ቱጃር አሳምሮ ያውቃል፡፡  ስለዚህም ያሜሪቃ ጥቁር ለታይታ ያህል እንደ ጥቂት ግለሰቦች እንጅ፣ እንደ ሕዘብ ስኬታማ እንዳይሆን ማስቀመጥ የሚችላቸውን እገዳወች ሁሉ አስቀምጧል፡፡  በፖለቲካ ረገድ ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያን በምርጫ እንዳይሳተፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቁሮችን (በተለይም ደግሞ ወጣቶችን) በተልካሻ ምክኒያቶች እየከሰሰ ሊመርጡ የማይችሉ ወንጀለኞች ያደርጋል፣ ቢመርጡም ደግሞ ጀሪምንደራ (gerrymandering) በሚባል አፓርታይዳዊ የምርጫ ቀጠና አከላለል፣  የጥቁሮችን ድምጽ ዋጋቢስ ያደርገዋል፡፡

ያሜሪቃ ዲሞክራሲ የቀማኞች፣ በቀማኞች፣ ለቀማኞች የሆነ የቀማኞች ዲሞክራሲ በመሆኑ ነው እንጅ፣ ቶማስ ጀፈርሰን  ሁሉም ሰወች በሰውነታቸው እኩል ናቸው (all men are created equal) ያለው በትክክል ተተርጉሞ አሜሪቃ ከምሥረታዋ ጀምሮ የእውነተኛ ዲሞክራሲ አገር ብትሆን ኖሮ፣ ባሁኑ ጊዜ ባሜሪቃ በሁሉም ዘርፎች (በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣  ወዘተ. ) የሁሉም የበላይ ይሆኑ የነበሩት ጥቁር አሜሪቃውያን ነበሩ፣ ላሜሪቃ እንደ ጥቁር አሜሪቃዊ የደከመላትና የደማላት የለምና፡፡  

ያሜሪቃ የቀማኛ ዲሞክራሲ ግን፣ አሜሪቃ ለነጭ እና በተወሰነ ደረጃ ለእስያውያን ብቻ እንጅ ለጥቁር አሜሪቃውያን የዝሃር ምድር (land of opportunity) እንዳትሆን በማድረግ፣ ጥቁር አሜሪቃውያን በማሕበራዊ መሰላል የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡  በሚቀጥለው ክፍል ላይ እንደምንመለከተው ደግሞ፣ ነጩ ቀማኛ ያሜሪቃን የዝሃር በሮች (doors of opportunity) ለእስያውያን የከፈተላቸው፣ ወዶ ሳይሆን ከጥቁር አሜሪቃውያን ጋር ለሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል አጋር ስላስፈለገው ብቻ ነው፡፡  እንዲህም ሆኖ ያሜሪቃ የዝሃር በሮች ለእስያውያን የሚከፈቱላቸው የነጭን የበላይነት አምነው እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል ቻይና ያሜሪቃን የበላይነት መገዳደር (challenge) ከጀመረች ጀምሮ ያሜሪቃ የዝሃር በሮች ለቻይናዊ አሜሪቃውያን መዘጋት ጀምረዋል፡፡   

ያሜሪቃ ጥቁር ያሜሪቃን ነጭን እገዳደራለሁ ብሎ መነሳት ቀርቶ እንዳያስብ፣ በተለያዩ ዘዴወች ቅስሙ መሰበር አለበት፡፡  አንዱ ቅስም የመስበርያ ዘዴ የእስያዊ አሜሪቃውያንን ስኬት ከአፍሪቃዊ አሜሪቃውያን ኢስኬት ጋር አላግባብ በማነጻጸር ጥቁሮችን ተስፋ የሌላቸው ተስፋቢሶች አድርጎ ማሳየት ሲሆን፣ ሌላው ቅስም የመሰብርያ ዘዴ ደግሞ ጥቁሮች የሚያቋቁሟቸውን የስኬት ተቋሞች በተለያዩ መንገዶች ባጭሩ እያጨናገፈ ሁልጊዜም ከምንም እንዲጀምሩና ምንም እዳይራመዱ ማድረግ ነው፡፡

ያሜሪቃ ጥቁሮች እድሉን ካገኙ የነጮችን ተመሳሳይ ተቋሞች እጅግ የሚያስንቁ የጥቁር ተቋሞችን (በተለይም ደግሞ ባንኮችን) ባጭር ጊዜ ውስጥ መገንባት እንደሚችሉ በዊልሚንግተን (Wilmington, North Carolina)፣ ተልሳ (tulsa, Oklahoma) እና በመሳሰሉት ያሜሪቃ ከተሞች ውስጥ በግልጽ አስመስክረዋል፡፡   የጥቁርን ታታሪነትና ፈጣሪነት በግልጽ የሚመሰክሩት እነዚህ ተቋሞች ግን፣ ነጩን ቱጃር ፍርሃት ስለለቀቁበት፣ በሰደድ እሳት እንዲጋዩ አድርጓቸዋል፡፡  የጋዩት ደግሞ ያሜሪቃ ውጀ ባደረገው ከፍተኛ ትብብር ነው፡፡  

ለምሳሌ ያህል ጥቁሩ ሚሊየነር (ባሁኑ ምንዛሬ ቢሊየነር) ኦደብሊው ገርሊ (O. W. Gurley)  ከተልሳ፣ ኦክላሆማ (tulsa, Oklahoma)  ባቡር ጣቢያ በስተሰሜን በገዛው ሰፌ መሬት ላይ በ 1906 ዓ.ም የመሠረተውን የጥቁር ዋል ስትሪት (Black Wall Street) ነጮች ባያወድሙት ኖሮ፣ ባሁኑ ጊዜ ያሜሪቃ የጠገራ ማዕከል (american financial center) ኒውዮርክ ሳትሆን ተልሳ የመሆኗ ዕድል የሰፋ ነበር፡፡  የጠገራ የማዕከሉ የበላዮች ደግሞ ጥቁሮች በሆኑ ነበር፡፡  የጠገራ ማዕከሉ የበላዮች ጥቁሮች ቢሆኑ ኖሮ ደግሞ፣ ጥቁር አሜሪቃውያንን በተልካሻ ምክኒያቶች ብድር በመከልከል እንዳይማሩና እንዳይሠሩ ካደረጉ በኋላ፣ ጥቁሮች የደኸዩት የመማርና የመሥራት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው ለማለት ባልተቻለ ነበር፡፡    

በነገራችን ላይ ያሜሪቃ መሰሶወች (freeways, highways)፣ ትቤቶች (schools)፣ ኮሌጆች (colleges)፣ ዩኒቨርስቲወችና (universities) እና የመሳሰሉት መንግሥታዊ ተቋሞች ሁሉም ሥራየ ብለው የሚገነቡት፣  በሚያልፉበት ወይም በሚያርፉበት ቦታ ላይ ያገራይ አሜሪቃውያንን (native americans) ታሪካዊ አሻራ የሚያጠፉበትን፣ ወይም ደግሞ እያቆጠቆጡ ያሉ የጥቁር ተቋሞችን የሚደፈጥጡበትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባቅራቢያቸው እንዲሆኑ የሚያደርጓቸውን የነጭ ንብረቶች ዋጋ ሰማይ የሚሰቅሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡     ለምሳሌ ያህል I-94 የተሰኘው መሰሶ (freeway) የተሠራው በቅዱስ ጳውሎስ ከተማ (Saint Paul, Minnesota) የሚገኘውን ሮንዶ ቀበሌ (Rondo Neighborhood) የተሰኘውን በከፍተኛ ፍጥነት እያቆጠቆጠ የነበረ የጥቁር የከስብ (business) ቀበሌ አፈራርሶ እንዲያልፍ ሁኖ ነበር፡፡ 

 

ያሜሪቃ ቀማኛና እስያዊ አሜሪቃውያን  

ካገራይ አሜሪቃውያን (native americans) እና ጥቁር አሜሪቃውያን (black americans) በስተቀር ሌሎቹ ያሜሪቃ ንዑሳን (minorities) በተለይም ደቡብ-ምሥራቅ እስያውያንን (South-east Asians) ዋና ፍላጎታቸው የነጭን የበላይነት አሚን ብለው ተቀብለው፣ በነጭ ሥር ሁነው፣ ቀማኛው ነጭ ከዘረፈው የቅምኝት ሐብት ውስጥ የሚችሉትን ያህል መቦጥቦጥ ነው፡፡  በዚህም ምክኒያት ቀማኛው ነጭ የሚያያቸው እንደ ንዑስ አጋሮቹ ወይም ደግሞ ተከፋይ አሽከሮቹ ነው፡፡   አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ቀማኛው ነጭ፣  ዓይን ውስጥ ላለመግባት ሲል ብቻ እነዚህን ደቡብ ምሥራቅ እስያውያን ከፊት አድርጎ ታላላቅ ሹመቶችን ይሾማቸዋል፣ እነሱም ሊያመልኩት እየዳዳቸው በቅንነት ያገለግሉታል፡፡  

ነጩ መናገር (መጻፍ) እየፈለገ እሱ ቢናገረው (ቢጽፈው) ተቀባይነት የማይኖረውን የሚናገሩለት (የሚጽፉለት) ዲነሽ ዲሶዛን (Dinesh D’Souza) የመሳሰሉ አፈነጮች ናቸው፡፡  መተገበር እየፈለገ እሱ ቢተገብረው ተቃውሞ የሚያስነሳውን የሚተገብሩለት ደግሞ ቦቢ ጂንዳልን (Bobby Jindal) የመሳሰሉ ጭቃሹሞች ናቸው፡፡

እጅግ የሚያስተዛዝበው ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያን ለንዑሳን መብት (minority rights) ሲታገሉ፣ እስያዊ አሜሪቃውያን አድፍጠው ይቀመጡና፣ ትግሉ ፍሬ ሲያፈራ ግን እኛም ንዑስ ነን በማለት የትግሉን ፍሬ ለመሰብሰብ በመጀመርያ ረደፍ የሚሰለፉት እነሱ መሆናቸው ነው፡፡  ያሜሪቃን የስኬት በሮች ቁልፎች ጠቅልሎ የያዘው ቀማኛው ነጭ ደግሞ፣ ጥቁሮች በትግል ባስከፈቱት በማናቸወም የስኬት በር ላይ፣ የሚያሳልፈው ባብዛኛው እስያውያንን ብቻ እየመረጠ ነው፡፡  እስያውያኑ ደግሞ ጥቁር ባስከፈተው የስኬት በር ላይ እየመረጠ ያሳለፋቸውን ነጭ እያመሰገኑ፣ የስኬት በሩን ያስከፈተውን ጥቁርን ግን መናቅ ብቻ ሳይሆን ዘረኛ ሊሆኑበት ይሞክራሉ፡፡  

ባጭሩ ለመናገር ጥቁር አሜሪቃውያን በቆራጥነት ይታገላሉ፣ እስያዊ አሜሪቃውያን ደግሞ የትግሉን ፍሬ በብልጣብልጥነት ይበላሉ፡፡  ያላመረትከውን ምርት ካምራቹ አስቀድመህ መሰብሰብ ርካሽነት ነው፡፡  በርካሽነት በሰበሰብከው ምርት አምራቹን ዝቅ አድርገህ ለመመልከት መሞከር ደግሞ የርካሽ ርካሽነት ነው፡፡  

የአንግሎ ሳክሶንን ፈለግ በመከተል ጥቁርን ዝቅ አድርገው ለመመልከት የሚሞክሩትን እስያዊ አሜሪቃውያንን በተለይም ደግሞ ሕንዶችን ጥቂት ጥያቄወችን ልጠይቃቸው እወዳለሁ፡፡  ሕንድን ቅኝ በሚገዛበት ዘመን ከእንስሳ እየቆጠረ ይንቃችሁ፣ ይጠየፋችሁ፣ ይጨፈጭፋችሁ የነበረው አንግሎ ሳክሶን፣ አሜሪቃ ስትመጡ ለምን ወደዳችሁ?  ዊንስተን ቸርችል (Winston Churchill) እነሱ አውሬ ሐይማኖታቸው ያውሬ (a beastly people with a beastly religion) ያላችሁን ለምን ትረሳላችሁ?  ይሄው ዊንስተን ቸርችል የናንተን ማልኮልም ኤክስ (Malcolm X) የሆነውን ማህተማ ጋንዲን (Mahatma Gandhi) ማየት እንኳን ያቅለሸልሸው እንደነበር (It is nauseating to see Mr. Ghandhi) ለምን ትዘነጋላችሁ?  ለማህተማ ጋንዲ የተነፈገውን የኖቤል ሽልማት የተሸለመው፣ ሕንድ ተወልዶ የሕንድ ወዝ እየጠጣ ያደገው ሩድያርድ ኪፕሊን (Rudyard Kipling)፣ የነጭ ሕዝብ ሸክም (The White man’s burden) የሚለውን የዘረኝነት ቅኔ የተቀኘው በዋነኝነት በናንተ ላይ መሆኑን እንዴት ዘነጋችሁት?  አንግሎ ሳክሶን ስለወጋ ቢረሳ፣ እናንተ የተወጋችሁት ለምን ትረሳላችሁ?  ከተጠቀመባችሁ በኋላ አሽቀንጥሮ ጥሎ መልሶ እንደማይወጋችሁ ምን ማረጋገጫ አላችሁ?     

እስያዊ አሜሪቃውያን (ምክኒያታቸው ምንም ይሁን ምን) በነጭ ሥር ለመበልጸግ እንጅ ነጭን ለመገዳደር የሚመኙ ሕዝቦች ስላይደሉ ነጩን አያሰጉትም፡፡  ቁጥራቸው አናሳ ስለሆነ ደግሞ የፈለጉትን ያህል ቢበለጽጉ፣ የቀማኛውን ነጭ የሐብት ባሕር በጭልፋ ይጨልፉታል እንጅ በበርሜል አይቀዱትም፡፡  በሌላ በኩል ግን የእስያዊ አሜሪቃውያን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ስኬታማ መሆን፣ ለቀማኛው ነጭ እጅጉን ይጠቅመዋል፡፡  የሚጠቅመው ደግሞ ያሜሪቃ ጥቁር በትግሉ ባስከፈታቸው የስኬት በሮች ላይ እስያኖቹን ብቻ እየመረጠ በማሳለፍ የእስያኖቹን ስኬት፣ በሩን ከዘጋባቸው ከጥቁሮች ኢስኬት ጋር አላግባብ እያነጻጸረ ጥቁሮችን ለማሸማቀቅ ነው፡፡  በተጨማሪ ደግሞ ጥቁሮች ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም የሚለውን መሠረተቢስ ትርክት እያናፈሰ፣ ተገዳዳሪ ጠቁሮች ሊወጡ የሚችሉባቸውን ጥቁሮች ብዙሃን የሆኑባቸውን ትቤቶች ሥራየ ብሎ እያቆረቆዘና እየዘጋ፣ ባለሙያወችን ከእስያ አገሮች ለማጋዝ ምክኒያት ይሆነዋል፡፡    

ስለዚህም ነጩ ቀማኛ ለእስያኖቹ የስኬት መንገዶችን የሚያመቻችላቸው፣ ካሜሪቃ ጥቁር ጋር ለሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል ትልማዊ (strategic) አጋሮቹ እንዲሆኑለት ብቻና ብቻ ነው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ እስያኖቹ የሚፈለጉት በተወሰኑ ጥቂት ዘርፎች ላይ ብቻ ስኬታማ ሁነው ጥቁርን ለማሸማቀቅ እንዲያገለግሉ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡  ቁጥራቸውን አብዝተው አያሌ ዘርፎች እንቆጣጠራለን ካሉ ግን፣ በነጩ ቀማኛ ዓይን ላይ መጡበት ማለት ስለሆነ፣ በጥቁር ላይ ከሚሆነው የበለጠ ዘረኛ ይሆንባቸዋል፡፡  ለአብነት ያህል በብሪቲሽ ኮሎምቢያ (British Columbia) በተለይም ደግሞ በቫንኩቨር (Vancouver) በሚኖሩት ቻይኖች ላይ ካናዳዊው ነጭ በነቂስ የተነሳባቸው፣ ከተፈቀደላቸው በላይ ስኬታማ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ 

ስለዚህም ያሜሪቃ ነጭ ቱጃር ያሜሪቃ ጥቁሮችን የሚመክር አስመስሎ እስያዊ አሜሪቃውያንን ተመልከቱ የሚለው፣ ጥቁሮችን ከትግላቸው ለማዘናጋት እንጅ፣ ጥቁሮች እንደ እስያወች ስኬታማ እንዲሆኑ አስቦ አይደለም፡፡  እንደዚህ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ፣ ጥቁሮች የሚያቋቁሟቸውን የስኬት ተቋሞች እግር በእግር እየተከታተለ ባላፈራረሰ ነበር፡፡

ያሜሪቃ ጥቁርና የአፍሪቃ አህጉር     

ያሜሪቃ ቀማኛ ያሜሪቃን ጥቁር ቅስም ለመስበር የሚጠቀምባት ሌላዋ መሣርያ ራሷ እናት አፍሪቃ ናት፡፡  ለምሳሌ ያህል ያሜሪቃ የአፍሪቃ ወጀም (american african policy) ሙሉ በሙሉ የሚያጠነጥነው የአፍሪቃን የተፈጥሮ ሐብት እየዘረፉና አፍሪቃውያንን እርስበርስ እያጨራረሱ አፍሪቃንና አፍሪቃውያንን ማቆርቆዝ፣ በዚያውም ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያንን በኀፍረት አንገት ማስደፋት በሚለው (ባንድ ዲንጋ ሁለት ወፍ በሚያስመታው) ዓላማ ላይ ነው፡፡  

አፍሪቃ በርስበርስ ጦርነት ሰላም አጥታ በድኽነት ከማቀቀች፣ ጥቁር አሜሪቃውያንን በነጻነት አፍሪቃ ከምትኖሩ በባርነት አሜሪቃ ብትኖሩ ሺ ጊዜ ይሻልችኋል፣ አላርፍ ካላችሁ ደግሞ ወደዚያው እንመልሳችኋለን እያሉ በማሸማቀቅ አደብ ለማስገዛት መሞከር ይቻላል፡፡  ነጭ አሜሪቃዊ ስኬታማ ሲሆን አሜሪቃ ልታመሰግነው ይገባል፣ ጥቁር አሜሪቃዊ ስኬታማ ሲሆን ግን አሜሪቃን ማመስገን አለበት (when a white man succeeds, America has to be thankful to him, but when a black man succeeds he has to be thankful to America) የሚሉትም በዚሁ መሠረት ነው፡፡  መባል  የነበረበት ግን ግልብጡ ነበር፡፡  ነጭ አሜሪቃዊ ስኬታማ ሲሆን፣ የስኬት መንገዱን አልጋ ባልጋ ያደረገችለትን አሜሪቃን ማመስገን ሲገባው፣ ጥቁር አሜሪቃዊ ስኬታማ በመሆን ከራሱ አልፎ ላሜሪቃ ሲጠቅም ደግሞ፣ የስኬት መንገዱን በሚቻለው መንገድ ሁሉ የዘጋችበት አሜሪቃ ልታመሰግነው ይገባታል፡፡    

ለጥቁር የሚሻለው ነጻነት ሳይሆን የነጭ ባርነት ነው ለማለት፣ የጥቁር ነጻነት ተምሳሌት የሆነቸው ጦቢያ በርስበርስ ጦርነት መደኽየት፣ ብሎም ተበጣጥሳ ስሟ ከዓለም ካርታ መጥፋት አለበት፡፡  ቅኝ ያልተገዛቸው ጦቢያ ደኽይታ፣ ቅኝ የተገዛቸው ኬንያ ከበለጸገች፣ ቅኝመገዛት አፍሪቃን ጠቀማት እንጅ አልጎዳትም ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡  

የመጀመርያውን በጥቁር የሚመራ ሪፓብሊክ (black-led republic) በ 1804 ዓ.ም ያቋቋመችው፣ ናፖሊዮንን ድል አድርጋ ከላቲን አሜሪቃና ከካሪቢያን አገሮች ሁሉ አስቀድማ ነጻነቷን የተቀዳጀችው፣ ባርነትን ለመጀመርያ ጊዜ በሕግ ያገደቸው ሄይቲ (Haiti)፣ እድሜ ዘመኗን በብጥብጥ እንድትቆረቁዝ ተደርጋ፣ በነጮች ደባ ከሄይቲ እንድትገነጠል የተደረገቸው ዶሚኒካን ሪፓብሊክ (Dominican Republic) ከሄይቲ እጅግ በተሻለ ደረጃ እንድትገኝ ከተደረገች ደግሞ፣ ጥቁሮች ራሳቸውን ማስተዳደር ስለማይችሉ በነጭ መተዳደር አለባቸው የሚለውን ትርክት ያጠናክራል፡፡  

ነጩ ቱጃር በጥቁር አሜሪቃውያን ነጻ ጉልበት ያፈራውንና ከአፍሪቃ የዘረፈውን መዋዕለ ንዋይ በገፍ የሚያፈስስባቸው የእስያ አገሮች ፈጣን እድገት ካሳዩ፣ ዘኢኮኖሚስትን (the economist) የመሳሰሉ የነጩ ቱጃር የቱልቀዳ (propaganda) መሣርያወች፣ አፍሪቃ መቸም የማታድግ ጨለማ አህጉር (the dark continent) ናት በማለት ጥቁር አፍሪቃውያንን ለማሸማቀቅ ይችላሉ፡፡  

ፓትሪስ ሉሙምባን (patrice lumumba) የመሰለ የአፍሪቃ ብሔርተኛ (African nationalist) የሆነ፣ አፍሪቃ አንድ ሁና ምዕራባውያንን እንድትገዳደር (challenge) ብቻ ሳይሆን እንድታሸንፍ የሚመኝ ሁላፍሪቃዊ (panafricanist) መሪ ሲበቅል፣ በሲአይኤ (CIA) ጉጠት ወዲያውኑ መመንገል አለበት፡፡  መለስ ዜናዊን የመሰለ፣ ጦቢያን በጣጥሶ በማዳከም የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochazka) ሕልም ለማሳካት ቀን ከሌት የሚተጋ ጉዳይ አስፈጻሚ ሲገኝ፣ የስልጣን እድሜው በተቻለ መጠን እንዲረዝም መደረግ አለበት፡፡  ዐብይ አህመድን የመሰለ ጦቢያን ለነጭና ላረብ የሚደልል፣ የጦቢያን አንጡራ ሐብት ለነጭ ቱጃሮች ለማስተላለፍ ያቆበቆበ፣ የምዕራባውያንን ነውር የሚያስፋፋ ምንደኛ ሲገኝ ደግሞ ኖቤል መሸለም አለበት፡፡ 

 

ያሜሪቃ ውጀ እና ያሜሪቃ ሕግ

ያሜሪቃ ቀማኛ ቱጃር በቀማኛነቱ ለመቀጠል ዋስትና የሚኖረው፣ አሜሪቃዊ ጥቁር ነጭን ለመገዳደር እንዳያስብ እድሜ ልኩን በፍራቻና በመሸማቀቅ እንዲኖር ሲገደድ ነው ብለናል፡፡  ይህን ጥቁርን የማስፈራራትና የማሸማቀቅ ተልዕኮ  በሕግ ማስከበር ሽፋን የሚፈጽመው ደግሞ፣ ሌላ ማንም ሳይሆን ያሜሪቃ ነጭ ቱጃር ዘበኛ እንዲሁም አካልዘብ (body guard) የሆነው ያሜሪቃ ውጀ (american police) ነው፡፡  

ስኬታማ ጥቁሮችን (ሐብታሞችን፣ ከያኒወችን፣ ስፓርተኞችን፣ ምሁራንን ወዘተ…) ያለ ምንም ምክኒያት (ከፋ ቢባል ደግሞ በተልካሻ ምክኒያት) የፊጥኝ እያሰሩ በሕዝብ ፊት ማዋረድ፣  ጥቁሮች የሚበዙበትን ሰፈር ቀን ከሌት እያዘወተሩ ኃይልን በማሳየት አዳጊ ሕጻናትን ማሳቀቅ፣ በነዚህ ሰፈሮች ውስጥ አደገኛ እጾች እንዲስፋፉ በሕቡዕ ማገዝ ወይም ደግሞ ሲስፋፉ አይቶ እንዳላዩ ማለፍ፣ እዴሜና ጾታ ሳይለዩ ጥቁሮችን ባሰቃቂ ሁኔታ በመግደል በጥቁሮች ላይ ሽበር መልቀቅ፣  … እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ ያሜሪቃ ውጀ በተሰጠው ልዩ ተልዕኮ መሠረት በጥናት የሚፈጽማቸው ወንጀሎች ናቸው፡፡  

ያሜሪቃ ውጀ ባሜሪቃ ጥቁሮች ላይ የሚፈጽማቸውን አረመኔያዊ ወንጀሎች ሁሉ የሚፈጽመው በደስታ መንፈስ ነው፡፡  የሚያስደስተው ደግሞ በሠራው ወንጀል አለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን እንደሚያተርፍበት እርግጠኛ ስለሆነ ነው፡፡  ርግጠኛ የሆነው ደግሞ ባሜሪቃ ተግባራዊ ሕግ  (applied law) ሙሉ በሙሉ ስለሚተማመን ነው፡፡   

ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንዲሉ፣ ያሜሪቃ ጽሑፋዊ ሕግ (written law) እና ተግባራዊ ሕግ  (applied law) እየቅል ብቻ ሳይሆኑ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ናቸው፡፡  ጥቁሮችን በተመለከተ ያሜሪቃ ጽሑፋዊው ሕግ መላዕካዊ ነው ባይባልም፣ ያሜሪቃ ተግባራዊው ሕግ ግን በትክክል ሰይጣናዊ ነው፡፡  ሰይጣናዊ የሆነበት ምክኒያት ደግሞ ጽሑፋዊ ሕጉን የሚተገብሩት ፍርድ ሸንጓዮች (jury) አብዛኞቹ በማይምነት ታውረው በነጭ ላዕልተኛነት (white supremacy) እንዲመረዙ የተደረጉ ድኻ ነጮች ስለሆኑ ነው፡፡  

ማናቸውም ነጭ ያሜሪቃ ውጀ (police) ማናቸውንም ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል በጥቁር (ጥቁሮች) ላይ ፈጽሞ ከጽሑፋዊው ሕግ (written law) በተመዘዘ አንቀጽ (አንቀጾች) መሠረት ተከሶ ፍርድቤት ቢቀርብ፣ በተግባራዊው ሕግ (applied law) ግን ለሠራው ወንጀል ተወድሶና ተሞግሶ በነጻ እንደሚሰናበት በርግጠኝነት ያውቃል፡፡  ለወንጀሉ የሚያገኘው ‹‹ቅጣት››፣ እየተከፈለ ረፍት እንዲወስድ መደረግ፣ በከፍተኛ ካሳ ከሥራ መሰናበት፣ በመገናኛ ብዙሃን እየቀረበና መጻሕፍትን እየጻፈ ታዋቂና ሐብታም መሆን ነው፡፡  

የጊወርጊስ ፍሎይድ (George Floyd) ገዳይ ዴሬክ ቻውቪን (Derek Chauvin) እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ፣ መነጽሩን ግንባሩ ላይ ጥሎ፣ ደረቱን ነፍቶ፣ ፎኪናውን (ፎቶ መኪናውን፣ camera) ፈት ለፊት እያየ በኩራት መንፈስ ወንጀሉን የፈጸመው፣ ጥቁሮችን በተመለከተ የበለጠ ጭራቅ ሲሆን የበለጠ እንደሚደነቅና የበለጠ እንደሚያተርፍበት ስለሚያውቅ ነው፡፡  

ዴሬክ ቻውቪንን በደጋፊወቹ ዘንድ ይበልጥ ተደናቂ የሚያደርገው ደግሞ፣ ወንጀሉን የፈጸመው አላፊ አግዳሚ እያየው፣ በፎኪና (camera) እየተቀረጸ መሆኑን እያወቀ መሆኑ ነው፡፡  የነጭ ቱጃር ዋና ዓላማ እዚህም እዚያም ጥቁሮችን መግደል ሳይሆን፣ በሁሉም ጥቁር አሜሪቃውያን ላይ ሽብር በመልቀቅ ሰጥ ለጥ ብለው እንዲገዙለት ማድረግ ነው፡፡  ስለዚህም ዴሬክ ቻውቪን የቀማኛ ቱጃሮች ጀግና ነው፣ የውጀ እርመና (police brutality) ግዴታውን በሚገባ ተወጥቷልና፡፡

ያሜሪቃው ተግባራዊ ሕግ ጥቁሩ ጀሪ ዊሊያምስ (Jerry Dewayne Williams) አንድ ኩርማን ፒዛ (one slice of pizza) በቀልድ መልክ ቢነጥቅ እድሜ ልክ የሚፈርድ፣  ነጩ ኢታን ኮች (Ethan Couch) ሰክሮ በመንዳት አራት ሰወችን ገድሎ አስራ አንድ ሰወችን ሲያቆስል ግን፣ ሐብትሳክ (affluenza) በሚል የፉገራ ሰበብ በማስጠንቀቂያ የሚያልፍ ዘረኛ ሕግ ነው፡፡  

 

አንግሎ ሳክሶኖችና ሌሎቹ አውሮጳውያን

ያሜሪቃ አንግሎ ሳክሶን ፕሮቴስታንቶችን (anglo-saxon protestants) በትውልድ አገራቸው በብሪታኒያ ላይ ከርዝራዥ ተቆጥረው፣ በሐይማኖታቸው ተጨቁነው፣ በድኽነታቸው ተንቀው፣ በወንጀለኛነታቸው ተግዘው አሜሪቃ ምድር ላይ የሰፈሩት ሰፋሪወችና የነሱ ዘር ማንዘሮች ናቸው፡፡ 

የተገፋ ደግሞ የመግፋት እድል ካጋጠመው የከፋ ገፊ ስለሚሆን፣ ያሜሪቃ አንግሎ ሳክሶኖች ከብሪታኒያ አንግሎ ሳክሶኖች እጅግ የከፉ ዘረኞችና ጨቋኞች የሆኑበት ምክኒያት ይሄው ነው፡፡  መገፋትን በደንብ ስለሚያውቁ፣ የምንገፋው ጥቁር መልሶ እንዳይገፋን በሚል ፍራቻ ባገኙት ብትር ያለ ርህራሄ ይቀጠቅጡታል፡፡  የፈሪ ብትር ሆድ ይቀትር፡፡ 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሜሪቃ ነጭ (american white) የሚለው ቃል ይወክል የነበረው አንግሎ ሳክሶን ፕሮቴስታንቶችን (anglo-saxon protestants) ብቻና ብቻ ነበር፡፡  ምሥራቅ አውሮጳውያን (east europeans) ይቅርና ምዕራብ አውሮጳውያን የሆኑት ካቶሊኮቹ አይሪሾችጣልያኖችፈረንሳዮች ከነጭ አለመቆጠር ብቻ ሳይሆን ይመደቡ የነበሩት ከጥቁር እምብዛም ባልተሻለ ደረጃ ነበር፡፡  

ለምሳሌ ያህል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሜሪቃ ፊምበሮች (presidents) ይመረጡ የነበረው፣ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ፊምበር (president) መሆን አይችልም በሚል ያልተጻፈ ሕግ መሠረት ነበር፡፡  የመጀመርያው ያሜሪቃ ካቶሊክ ፊምበር (catholic president) የተመረጠው የአሜሪቃ ሪፓብሊክ ከተመሠረተ ከ 185 ዓመታት በኋላ በ 1961 ዓ.ም ሲሆን፣ እሱም 35ኛው ያሜሪቃ ፊመበር ዮሐንስ ኬኔዲ (John F. Kennedy) ነበር፡፡  

የጥቁር አመጽ እየተጠናከረ ሂዶ የአንግሎ ሳክሶን ቀማኞችን አጥር መነቅነቅ ሲጀምር ግን፣ የነጭን ብያኔ (definition) በማስፋት የነጭን ቁጥር ማብዛት የግድ አስፈለገ፡፡  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከነጭ አይቆጠሩ የነበሩት አንግሎ ሳክሶን ያልሆኑ አውሮጳውያን በተለይም ደግሞ ምሥራቅ አውሮጳውያን፣ አይሪሾችና፣ ደበቡ ጣልያናውያን የጥቁርን አመጽ ለማፈን የግድ ስላስፈለጉ ብቻ ነጭ ናችሁ ተባሉና እዚህም እዚያም ተሾሙ፡፡  ከዚያስ?  

የዝቅተኝነት ስሜት ክፉኛ የጎዳቸው እነዚህ አልአንግሎ ሳክሶን አውሮጳውያን (non anglo saxon europeans) ያንግሎ ሳክሶን ሽንገላ አማለላቸውና፣ ውነትም ደማችው ያንግሎ ሳክሶን ደም መሆኑን ለማስመስከር ሲሉ ብቻ ካንግሎ ሳክሶን የባሱ ዘረኞች ሆኑ፡፡  ከለማበት የተጋባበት፡፡

ለምሳሌ ያህል አብዛኞቹ ጣልያናዊ አሜሪቃኖች (italian americans) ዘረኛ የሚሆኑት፣ ዘረኛ መስለው በመታየት ካንግሎ ሳክሶኑ ጋር አንድ መሆናቸውን ለማሳየት ሲሉ እንጅ፣ እንደ አንግሎ ሳክሶኑ ሰይጣን የተጠናወታቸው እኩዮች ስለሆኑ አይመስለኝም፡፡  የሚያሳዝነው ደግሞ አብናቶቻቸው (አባቶችና እናቶቻቸው፣ forebears) ሮማውያን እንደ በሬ ጠምደው ያርሱት ለነበረው ለትናንት መጤው አንግሎ ሳክሶን አጎብድደው፣ ጉዳይ አስፈጻሚው ለመሆን መቋመጣቸው ነው፡፡  ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ ጥቁር አሜሪቃውያንን በወንጀለኛነት የሚፈረጀው የዓለማችን ታላቁ ወንጀለኛ  አንግሎ ሳክሶን፣ ትናንት ጣልያናውያንን በማፍያነት ይፈርጅ  እንደነበር መርሳታቸው ነው፡፡ 

አንግሎ ሳክሶኑ ደግሞ ሲፈጥረው መሰሪ ስለሆነ፣ የነዚህን አልአንግሎ ሳክሶን አውሮጳውያን ነጭነት የሚጠራጠር እያስመሰለ፣ በጥቁር ላይ የበለጠና የበለጠ ዘረኛ በመሆን ነጭነታቸውን በየጊዜው እንዲያረጋግጡ በግልጽና በተዛዋሪ ዘዴወች በማስገደድ፣ እኩይ አዟሪት (vicious circle) ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡  

ላሜሪቃ ውጀነት (american police) በብዛት የሚመለመሉት፣ እነዚህ ነጭነታቸውን በየጊዜው ካላስመሰከሩ በነጭነታቸው የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅማጥቅሞች እንዳያጡ የሚሰጉት አልአንግሎ ሳክሶን አውሮጳውያን፣ በተለይም ደግሞ ፖሊሾች፣ አይሪሾችና ደቡብ ጣልያኖች ናቸው፡፡  ለምሳሌ ያህል ባረመኔነቱ ወደር የማይገኝለት የኒውዮርክ ውጀ (New York Police) አብዛኞቹ አባሎች፣ በተለይም ደግሞ ሹማምንቶች፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በዚሁ በኒውዮርክ ውጀ እንደ ዐይጥ ይታደኑ የነበሩት ደቡብ ጣልያኖችና አይሪሾች ናቸው፡፡     

በርከት ያሉ ያሜሪቃ ውጀወች ደግሞ በጥቁር ላይ የሚያረምኑት ነጭነታቸውን ለማስመከር ሳይሆን፣ ባደረባቸው ሥር የሰደደ ልቦናሲናዊ (psychological) ችግር ምክኒያት ነው፡፡  እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰወች ውጀ ለመሆን የሚመኙት፣ በወጣትነት ዘመናቸው ከወጣት ጓደኞቻቸው አንጻር ይሰማቸው የነበረውን ከፍተኛ የበታችነት ስሜት በሕግ ሽፋን ለመወጣት በማሰብ ነው፡፡  ስለዚህም ጀግና የሚመስሉት በሕግ ጥላና ከለላ ሥር ብቻ ነው፡፡  ከዚያ ውጭ ግን ፈሪወች ስለሆኑ፣ ለሚፈጽሙት እኩይ ተግባር ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ተመሳሳይ አጸፋ የሚያገኙ መሆኑን ከተገነዘቡ አደብ ይገዛሉ፡፡

ለምሳሌ ያህል ከሰላሳ ጊዜ በላይ መጠናለፍ ኃይል (excessive force) የመጠቀም ስሞታወች (complaings) የቀረቡበት፣ አያሌ ጊዜ ተከሶ ሁሉም ክሶች ውድቅ የተደረጉለት፣ የሚኔሶታ ምርጥ (minnesota’s finest) ነኝ እያለ በትራምፕና በትራምፕ ደጋፊወች ፊት በመንጎባለል ስላንበሳነቱ ይደሰኩር የነበረው ቦብ ክሮል (Bob Kroll)፣ በጆርጅ ፍሎይድ (George Floyd) ግድያ በማመጽ ጥቁር ሆ ብሎ ሲነሳ፣ ዓይጥ አክሎ ድምጥማጡ ጠፋ፡፡  ከፍራቻው የተነሳ የዋሽንግተን ፖስት ዘጋቢ (Washington Post reporter) አስተያየቱን ለመጠየቅ ወደ ቤቱ ሲሄድ፣ በሩን ዘግቶ ኡኡ እያለ 911 ደወለ፡፡   

ስለዚህም የቦብ ክሮል ዓይነት ውጀወችን አደብ ለማስገዛት ፍቱን መድሐኒት፣ የማልኮልም ኤክስን (Malcolm X) መንገድ በመከተል ባስፈላጊው ዘዴ (by any means necessary) መጋፈጥ ነው፡፡  ያሜሪቃ ነጭ ሁሉንም ነገር ያገኛ በኃይሉ ስለሆነ፣ የሚገባው ቋንቋ ኃይልና ኃይል ብቻ ነው፡፡  ያሜሪቃ ጥቁር ለመብቱ የሚታገለው፣ ያሜሪቃ ነጭ መቸም ቢሆን ሊገባው በማይችለው በማርቲን ሉተር ኪንግ (Martin Luther King, Jr.) ሰላማዊ መንገድ ሳይሆን፣ በማልኮልም ኤክስ አጸፋዊ መንገድ ቢሆን ኖሮ፣ ያሜሪቃ ውጀ እርመና (american police brutality) በከፍተኛ ደረጃ በቀነሰ ነበር፡፡   

ውጀነትና ወታደርነት እየቅል ናቸው፡፡   ወታደር የሚፋለመው እንደሱ መሣርያ ከታጠቀ፣ የፍልሚያ ሕጉ ለሁለቱም እኩል ከሚሠራ ባላንጣ ጋር ነው፡፡  ውጀ ግን ወንጀለኛን እፋለማለሁ የሚለው፣ እኔ የፈለኩትን  ባረግህም፣ አንተ ግን ጫፌን መንካት ቀርቶ አትኩረህ ብታየኝ አይቀጡ ቅጣት ትቀጣለህ የሚለውን ሕግ መከታ አድርጎ ነው፡፡  ስለዚህም ማንም ፈሪ ውጀ መሆን ይችላል፡፡  ወታደር ለመሆን ግን ጀግንነትን ይጠይቃል፡፡  

ጆርጅ ፍሎይድ (George Floyd) ራሱን ከሳተ በኋላ እንኳን፣ ዴሬክ ቻውቪን (dereck chauvin) ከጆርጅ ፎሎይድ አንገት ላይ ጉልበቱን ያላነሳበት አንዱ ምክኒያት፣ ከተነሳ ይገለኛል የሚለው ከመንፈሱ ጋር የተዋሃደው ጥቁርን አለቅጥ የመፍራት አባዜ ነው፡፡  ራሳቸውን የሚኔሶታ ምርጦች (minnesota’s finest) የሚሉት የሚኔሶታ ውጀወች (minnesota police)፣ በእውነትም የሚኔሶታ ምርጦች ሳይሆኑ ዴሬክ ቻውቪንን የመሳሰሉ የሚኔሶታ ዝቃጮች ናቸው፡፡  የሌሎች ያሜሪቃ ከተሞች ፖሊሶችም እንዲሁ፡፡

ከዩኒቨርስቲ ምሁር በላይ ደመወዝና ጥቅማጥቅም የሚያገኘው ያሜሪቃ ውጀ፣ በእውነትም የተቀጠረው ሰላማዊ ሕዝብን እያገለገለ ለመከላከል (to serve and protect) ቢሆን ኖሮ፣ ሰላማዊን ከሚገል ይልቅ ራሱ መሞት ነበረበት፡፡  ይበልጥ ማስቆጣትና ማስቀጣት ያለበት ሰላማዊ ሰው፣ እያገለገልኩ እከላከልሃሉ በሚለው በውጀ ሲገደል እንጅ፣ እንደሚሞት አውቆና ፈርሞ የገባ፣ ለዚህም ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈለው ውጀ በወንጀለኛ ሲገደል አይደለም፡፡  ያሜሪቃ ውጀ ግን ዋና ሥራው ጥቁርን ማሸበር ስለሆነ፣ ጥቁር ባየ ቁጥር እጁን ከቃታው ላይ ይጭናል፡፡ 

 በነገራችን ላይ ኬኬኬን (KKK) የመሳሰሉ የነጭ ብሔርተኞች (white nationalists) ጥቁር ነበሮችን (black panthers) ከመሳሰሉ የጥቁር ብሔርተኞች (black nationalists) ጋር ለመፋለም የሚመኙት፣ እነሱ እስካፍንጫቸው ታጥቀው ጥቁሮች ባዶ እጃቸውን እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው፡፡  የኬኬኬን ዝንብ እሽ ያላለው መንግስታቸው፣ ጥቁር ነብሮችን እግር በእግር እየተከታተለ ትጠቅ ያስፈታቸውና ወህኒ የወረወራቸውም ለዚሁ ነበር፡፡  

እነ ዊንስተን ቸርችልም ለቅኝ ግዛት ወደ አፍሪቃ የተሸቀዳደሙት፣ እነሱ የታጠቁትን ዘመናዊ መሣርያ አፍሪቃውያን እንዳልታጠቁ እርግጠኞች ስለሆኑ ብቻና ብቻ ነበር፡፡  ኤዶልፍ ሂትለር በተመሳሳይ መሣርያ ሲገጥማቸው ግን፣ ከቀናት ውጊያ በኋላ መሣርያቸውን እንዳለ አስረክበው፣ ፈሳቸውን ጥለው፣ ጅራታቸውን ቆልፈው ፈረጠጡና እርዳታ ፈለጋ ወዳሜሪቃና ወደ ራሺያ አቀኑ፡፡  የነጭ ቅኝ ገዥወች ጀግንነት እስከዚህ ድረስ ነው፡፡ 

የኑብያን ፒራሚዶች ከሺ ዓመታት በፊት የገነቡት፣ ሠረገላን (chariot) ለጦርነት በማዋል የመጀመርያወቹ የነበሩት፣ የታላቁ ጦረኛ የቱታንክሃመን (Tutankhamun) ልጆች የሆኑት ጥቁሮች፣ በትናንት መጤወቹ አውሮጳውያን በጦር መሣርያ ተበልጠው የተሸነፉት፣ በመንፈሳዊው ጉዳይ ላይ ፀጉር እየሰነጠቁ ዓለማዊውን (በተለይም ደግሞ የጅ ሥራውን) ጉዳይ በመናቃቸው ነበር፡፡  አፍሪቃውያንን ለቅኝ ግዛት የዳረጋቸው በደቂቃ ስደስት መቶ ጥይት የሚተፋው ማክሲም መትረየስ (Maxim machinegun) እንጅ፣ አውሮጳውያን አልነበሩም፡፡  

 

የትናንቱ ውራ አሕዛቡ ፈረንጅ

ዛሬ ከፊት ሁኖ በስልጣኔ ፈርጅ፣

ቢንቅ ቢጸየፋችሁ አሳንሶ ከውሻ ልጅ

ቢሸጥ ቢለውጣችሁ እያሰረ በፍንጅ፣ 

አዲስ በመፍጠር አይደለም አክብሮ በማንሳት እንጅ

ተንቆ የተጣለውን በናንተው ከናንተው ደጅ፡፡

እያላችሁት በይፋ በነጋሪት ባዋጅ

አናፂ አንጠረኛ ቀጥቃጭና ባለጅ

ሙያውን አስንቃችሁ አርጋችሁ አዋራጅ፡፡ 

  

የነጭ ላዕልተኛነት

ያሜሪቃ ነጭ ቀማኛ ባንደኛ ደረጃ የሚፈራው ጥቁር አሜሪቃዊን ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚፈራው ደግሞ በታች መደብ (lower class) ላይ የሚገኘውን ያሜሪቃን ነጭ ድኻ ነው ብለናል፡፡  ስለዚህም እነዚህን ሊተባበሩ የሚገባቸውን ሁለት ጭቁን ቡድኖች እንዳይተባበሩ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አጥፊና ጠፊ እንዲተያዩ ማድረግ አለበት፡፡  ይህን ለማድረግ ደግሞ ቀላሉና ፍቱኑ ዘዴ  የነጭ ላዕልተኛነት (white supremacy) የሚባለው መሠረተቢስ ትርክት (narration) ነው፡፡ 

አብናቶቻችን (አባቶቻችንና እናቶቻችን) እንደሚሉት የሰው እንጅ የጊዜ ጀግና የለውም፡፡  ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋ ይሰብራል፡፡  ጊዜ የሰጠው ዘር ደግሞ፣ ራሱን የሰው በላይ አድርጎ ላዕልሰብ (superman) ነኝ እያለ፣ ሌላውን ከታሕትሰብ (subhuman) ፈርጆ ከእንስሳ በመቁጠር፣ አበሳውን እያሳየ፣ አሣሩን እያበላ ያንገፈግፈዋል፣ እሱም ወርተራው ደርሶ፣ ከታሕትሰብ ተፈርጆ፣ በሰፈረበት ቁና እስኪሰፈር ድረስ፡፡  ዘረኝነት ማለት ደግሞ ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን፣ ቀን የወጣለት ቀን በመሸበት ላይ የሚያሳየው ንቀትና የሚፈጽመው ግፍ ማለት ነው፡፡ 

ለምሳሌ ያህል ሮማውያን በላቲንኛ (Latin) ብሪታንያ (Britannia) ብለው የሰየሙትን እንግሊዝን (England)፣ ዌልስን (Wales) እና ደቡብ እስኮትላንድን (sothern Scotland) የሚያጥቃልለውን መሬት ለአራት መቶ ዓመታት (ከ 43  ዓ. ም እስከ 410 ዓ.ም) ይቀግዙ (ቅኝ ይገዙ) በነበረበት ጊዜ፣ እንግሎ ሳክሶኖችን ከእንስሳ በመቁጠር እንደ በሬ ጠምደው ያርሱባቸው ነበር፡፡  አንግሎ ሳክሶን ቀን ሲወጣለት ደግሞ ጣልያኖችን ከርዝራዥ ቆጠራቸውና፣ አሜሪቃ እንዳይሰፍሩ የሚከለክል ሕግ እስከ መሐገግ ደረሰ  (Emergency Quota Act of 1921, and Immigration Act of 1924)፡፡  እነ ያሳቅ ኒውተንን (Isaac Newton) እንግሊዘኛ ለሳይንስ ቀርቶ ለስነጽሑፍ የማያመች ኋላቀር ቋንቋ ነው በማለት መጻሕፎቻቸውን የጻፉት በላቲንኛ እንዳልነበር ሁሉ፣ እንግሊዘኛ የማይናገር ታሕትሰብ ነው (Anyone who doesnot speak english is subhuman) ይባል ጀመር፡፡  ሙምባይ (Mumbai) የተወለደው ሩድያርድ ኪፕሊን (Rudyard Kipling) ደግሞ በጠጣው የሕንድ ወዝ ጠንብዞ የሚከተለውን አቀረሸ፡፡  

      

Take up the White man’s burden, Send forth the best ye breed

Go, bind your sons to exile, To serve your captives’ need. 

Your new-caught sullen peoples, Half-devil, half-child.

Rudyard Kipling (The White Man’s Burden, 1889)

ለዚህ ቅርሻቱ ደግሞ፣ ባንግሎ ሳክሶኖች ዘንድ ትልቅ ክብር አግኝቶ፣ ለማሕተማ ጋንዲ (Mahatma Gandhi) የተነፈገውን፣ ላንግሎ ሳክሶን ጥቅም አስከባሪወች ብቻ የሚሸለመውን የኖቤል ሽልማት ተሸለመ፡፡  ሩድያርድ ኪፕሊንግ ያልተረዳው፣ ወይም ደግሞ ተረድቶ እንዳልተረዳ የሆነው፣ ታሪክ ኡደታዊ (cyclic) በመሆኑ፣ የዛሬው ሸክም የነገ አሸካሚ እንደሚሆን ነው፡፡    

ታሪክ ስለሆነ በኡደት የሚሖስ

ጊዜውን ጠብቆ የሱ ተራ ሲደርስ

ወደላይ የወጣ ወደታች ሊመለስ

በታች የነበረ በላይ ሁኖ ሊነግሥ

ሕገ ተፈጥሮ ነው መቸም የማይጣስ፡፡

 

ሚዛን ለመጠበቅ እድገት ለማካካስ

ያነሰ ሲተልቅ የተለቀ እንደሚያንስ

ምሳሌወች ናቸው አውሮጳ ጦቢያ ፋርስ፡፡ 

 

ይሄን ሐቅ ዘንግቶ ጀርመንና እንግሊዝ

አንግሎ ሳክሶኔ ያሕዛብ አበጋዝ፣

የሱ ተራ ደርሶ ቁንጮነትን ሲይዝ

በደስታ ሰክሮ ስላለ ጥንብዝብዝ

የሚቀር መሰለው እዚያው ሲፈነጥዝ፡፡

 

የሕንድ ወዝ ጠጥቶ በስካር ታውሮ

በንቀት ተሞልቶ በትቢት ተወጣጥሮ

ኪፕሊንግ እንዳለው ስንኝ ደርድሮ፣

ሸክም የሚባለው ዛሬ ቢታይ ጠቁሮ

ነገ ነጭ ይሆናል መልኩ ተቀይሮ፡፡

 

የነጭ ላዕለተኝነት (white supremacy) ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን፣ ጊዜው የነጭ መሆኑን የሚያንጸባርቅ አመለካከት ማለት ነው፡፡  ከዚህ በተርፈ ግን አንዳችም ሳይንሳዊ ወይም ታሪካዊ መሠረት የለውም፡፡   አሁን ደግሞ በሃን ላዕለተኝነት (Han supremacy) እየተተካ ስለሆነ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ድምጥማጡ ጠፍቶ እንዳልነበረ ይቆጠራል፡፡  ብድር በምድር ነውና፣ እንግሊዝ ቻይናን እያስገደደ ኦፕየም (opium) እንዳስጨሰው፣  ቻይናም በተራው እንግሊዝን እያስገደደ ኮኬይን (cocaine) ያስምገዋል፡፡  በሰፈረው ቁና የሚሰፈረው ነጭ ደግሞ የጎጃሙ የራስ ካሳ ዓይነት የጸጸት እንጉርጉሮ ማንጎራጎር ይጀምራል፡፡

 

ሰው በድለን ነበር እኛም እንደ ዋዛ

ቁናው ቁናችን ነው ጥቂት ዙሩ በዛ፡፡ 

እስከዚያው ድረስ ግን ነጭ ሲባል በእውነትም ላዕልሰብ (superman) የሚመስላቸው ይልቁንም ደግሞ እንዲመስላቸው የተደረጉ ማይሞች ነጭን ፈጣሪ እጁን ታጥቦ የሠራው፣ ለይቶ የባረከው፣ የቀደሰው፣ የመረቀው፣ ግዛ ብዛ ያለው ይመስላቸዋል፡፡  ፈጣሪን በነጭ አምሳል ስለው ይሰግዱለታል፡፡  ፊቱ እንደ ሶለግ የሾጠጠውን፣ ቆዳው እንደ ሊጥ የለጠለጠውን፣ ነጫጭባ ፍጡር የውበት ተምሳሌት ያደርጉታል፡፡ 

 

አንዱን እያነሳ ሌላውን በመጣል

ታሪከ ያለማቆም ኡደቱን ሲቀጥል፣

ወርተራው ደርሶለት የሚሆነው ከላይ

ውበትን በይኖ በዕይታው መሳይ፣

የሱን ነገር ሁሉ ያደርግና ሰናይ

የታቹን ይለዋል ሁለመናው እኩይ፡፡

በሌላ አነጋገር የውበት ብያኔ

ሳይሆን ቋሚ ትርጉም የዘላለም ቅኔ

እያንጸባረቀ የወቅቱን ስልጣኔ

የሚለዋወጥ ነው በእስስት አስተኔ፡፡ 

 

ተፎካካሪህን አራት መቶ ዓመታት ሙሉ ባለበት እንዲቆም ቀፍድደህ፣ ባለፍክባቸው መንገዶች ላይ ትላልቅ መሰናክሎችን እያስቀመጥክ አንተ ብቻህን ለአራት መቶ ዓመታት ከሮጥክ በኋላ፣ በመካከላችሁ በተፈጠረው ከፍተኛ ርቀት እየተመካህ መታበይ ሌላ ምንም ሳይሆን አስቂኝ ቧልት (comedy) ነው፡፡  የነጭ ላዕለተኛነት (white supremacy) ማለት ደግሞ ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን፣ ይህን አስቂኝ ቧልት፣ ቧልት መሆኑን አለማወቅ ወይም ደግሞ እያወቁ እንዳላወቁ መሆን ማለት ነው፡፡  ስለዚህም የነጭ ላዕለተኛነት አቀንቃኝ ሊሆን የሚችለው ወይም ምንም የማያውቅ ጥሬ ማይም አለያ ደግሞ አውቆ እንዳላወቀ የሚሆን ቧልተኛ (comedian) ብቻ ነው፡፡  

ለምሳሌ ያህል የነጭ ላዕልተኝነት አቀንቃኙ ኤዶልፍ ሂትለር (Adolf Hitler)፣ ዘረኝነትን በተመለከተ አውቆ የተኛ ቧልተኛ ይመስለኛል፡፡  ከሂትለር በከፋ ደረጃ የነጭ ላዕልተኝነትን የሚያቀነቅነው ዊንስተን ቸርችል (Winston Churchill) ግን ዘረኝነትን በተመለከተ እንጭጭ ማይም ይመስለኛል፡፡  

ነጭ ላዕለተኞች፣ ለላዕልተኝነታቸው ከሚጠቅሷቸው ምስክሮች ውስጥ አንዱና ዋናው ያሜሪቃ ልዕለኃያልነት (superpower) ነው፡፡  ያሜሪቃ ልዕለኃያልነት ግን የነጭ ላዕልተኛነት መሠረት ሊሆን አይችልም፡፡  አሜሪቃ አያሌ ቦታ የተሰነጣጠቀች፣ አያሌ ደካማ ዘለበቶች (weak links) ባሉት በቀላሉ ሊበጣጠስ በሚችል ሰንሰለት የተሳሰረች፣ ቢከፍቷት ተልባ የሆነች አገር ስለሆነች፣ እውነተኛው ያሜሪቃ ኃይል አመለካከታዊ (perceptional) እንጅ ግኡዛዊ (physical) አይደለም፡፡  ያሜሪቃ ግኡዝ ኃይል ወይም ጽኑ ኃይል (hard power) የትም እንደማያደርሳት ቬትናም፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና ሶማልያ በግልጽ አስመስክረዋል፡፡  

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ አሜሪቃ ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ጨሳፊ (rocket) ተጨስፋ ልዕለኃያል (superpower) እንድትሆን ያስቻላት፣ ያሜሪቃ ሉሳ ኃይል (soft power) ዋና መሠረት የሆነው ያሜሪቃ ሕዝበኛ ባህል (american popular culture) ነው፡፡  አሜሪቃ ልዕለኃያል የሆነቸው ደግሞ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ (በተለይም ደግሞ ወጣቱ) አንጡራ ሐብቱን፣ አፍላ ጉልበቱንና ብሩህ አይምሮውን ወደ አሜሪቃ በገፍ ስላፈሰሰ ብቻ ነው፡፡  ይህን ያደረገው ደግሞ ባሜሪቃ ሕዝበኛ ባሕል ታውሮ ያሜሪቃን እኩይ ገጽታወች ለማየት ባለመቻሉ፣ የጥቁሮች ገሃነም የሆነቸው አሜሪቃ የሰብኣዊ መብት (human right) ገነት ስለመሰለችው፣ ያሜሪቃን የቀማኛ ዲሞክራሲ ከእውነተኛ ዲሞክራሲ ስለቆጠረ ብቻና ብቻ ነው፡፡       

ያሜሪቃን ሕዝበኛ ባህል የቀረጹት ደግሞ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ጥቁሮች ናቸው፡፡  ስለዚህም አሜሪቃ ልዕለኃያል እንደትሆን በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ዋናውን ሚና የተጫወቱት ያሜሪቃ ጥቁሮች ናቸው፡፡  በመሆናቸውም ያሜሪቃን ልዕለኃያልነት እያጣቀሰ ከነጭ ላዕልተኝነት (white supremacism) ጋር ለማጎዳኘት የሚሞክር፣ ልዕለኃያልነቱ በማንና በምን እንደተገኘ የማያቅ ማይም፣ አለያም ደግሞ እያወቀ እንዳላወቀ የሚሆን፣ አውቆ የተኛ ሸፍጠኛ ብቻ ነው፡፡   

አብዛኛው ያሜሪቃ ታች መደብ ነጭ (lower class white)፣ በተለይም ደግሞ ብልዛንገት (redneck) የሚባለው የደቡቡ ዲክሲ (Southern Dixie) ገጠሬ፣ ሙሉ እውቀቱ በሦስት ምንጮች ላይ ብቻ የተመሠረተ እንጭጭ ማይም ነው፡፡  እነዚህም ሦስት ምንጮች ቲቪ (TV)፣ ሙቪ (movie) እና ወሬሪ (ወሬ-ርዕይ፣ talk show) ናቸው፡፡  ስለዚህም ይህን ማይም ነጭ፣ የእውቀቱ ምንጭ በሆኑት በነዚህ ሦስት የቱልቀዳ (propaganda) መሣርያወች አማካኝነት መሠረተቢስ ትርክቶችን (narration) ቀን ከሌት እየተረከቱ (narrate) ወናይምሮውን (ወና አይምሮ፣ tabula rasa) በነጭ ላዕልተኝነት በመሙላት፣ የትግል አጋሩ ሊያደርገው የሚገባውን ያሜሪቃን ጥቁር በመሪር ጠላትነት እንዲያይ ማድረግ ይቻላል፣ ተችሏልም፡፡

አሜሪቃን በሰፋፊ ጃንቤቶች (mansions) እና ባያሌ መዝናኛወች መረን በለቀቀ ቅንጦት የሚንደላቀቅባት ነጩ ቱጃር፣ ያሜሪቃን ዓልማቅ (ባንዲራ) ቢጠና ኮቱ ላይ ነው የሚለጥፋት፣ ለዚያውም ባዘቦት ሳይሆን በክት ቀን ለታይታ ብቻ፡፡  የቀበሮ ጉድጓድ በሚመስል፣ በውርማ በተከበበ፣ ትንሽ ቅርንጫፍ ቢወድቅበት በሚደረመስ፣ ኮሳሳ ተንቀሳቃሽ ቤት (mobile house) ውስጥ፣ ከሰው ተለይቶ እንደ አውሬ የሚኖረው ብልዛንገት (redneck) ግን፣   ዋጋው የቤቱን ዋጋ ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ ግዙፍ ሰንደቅ (pole) ከደጃፉ ተክሎ፣  የቤቱን በር ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ ግዙፍ ዐልማቅ እያውለበለበ ለመኩራራት ይጣጣራል፡፡

የሚፈለገውም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡  ነጩ ድኻ ለምን ድኻ ሆንኩ ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ሳይሆን፣ የጥቁር የበላይ የሆንኩ ነጭ ላዕልተኛ (white supremacist) ነኝ በማለት በባዶ ሜዳ እንዲኩራራ፡፡   ዓይኑን ለድኽነት በዳረገው በነጩ ቱጃር ላይ ሳይሆን፣ እንደሱ በደኸየው አሜሪቃዊ ጥቁር ላይ ሳያነቃንቅ እንዲተክል፡፡  

አብዛኛው ያሜሪቃ ነጭ ድኻ (በተለይም ደግሞ ገጠሬው)፣ ሲቀርቡት እጅግ የሚያሳዝን ምስኪን፣ በቲቪ የሚሰማውን ሁሉ ቅንጣት ሳይጠራጠር አምኖ የሚቀበል፣ ላሳሳቾች በቀላሉ የሚጋለጥ የዋህ ሕዝብ ነው፡፡  ስለዚህም፣ ያሜሪቃ ነጭ ድኻ በነጭ ላዕልተኝነት ተመርዞ በጥቁሮች ላይ ለሚፈጽማቸው ወንጀሎች፣ ዋናው ተጠያቂ መሆን ያለበት የመረዘው ነጭ ቱጃር እንጅ፣ ተመራዡ ነጭ ድኻ አይደለም፡፡ 

ቁጥሩ የማይናቅ ነጭ ድኻ ደግሞ የተወሰነ ጥቁርነት ስላለበት፣ ነጭ ላዕልተኛ ከሆነ የሚሆነው፣ ጥቁርነቱን እንዲጸየፍና መጸየፉን በተግባር እንዲያረጋግጥ በቀጥታና በተዛዋሪ መንገድ ስለሚገደድ ነው፡፡  ነጭ ላዕልተኛነታቸውን በይፋ እየለፈፉ፣ በጥቁር ላይ አሰቃቂ ወንጀሎችን በኩራት የሚፈጽሙት፣ እነዚህ ጥቁርነት ስላለባቸው የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው የተደረጉ የስነልቡና በሽተኞች ናቸው፡፡  

የነጭ ቱጃር የቅምኝት ሐብት ዋስትና የሚኖረው፣ ድኻው ነጭ ሙሉ ትኩረቱን በነጭ ላዕለተኛነት ላይ እስካደረገ ድረስ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም የነጭ ድኻ በነጭ ላዕልትኛነት መጠመድ፣ ለነጭ ቱጃር የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡  በመሆኑም የነጭ ላዕልተኝነት እሳት እንዳይጠፋ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲንበለበል በተቻለው መጠን ያራግበዋል፡፡

 የነጭ ላዕልተኛነት አንዱና አንዱና ዋናው አራጋቢ ያሜሪቃ ውጀ (american police) ሲሆን፣ የማራገቢያ ዘዴው ደግሞ የውጀ እርመና (police brutality) ነው፡፡  ያሜሪቃ ውጀ እና ሌሉች የነጭ ላዕልተኛነት አራጋቢወች በማራገብ ተልዕኳቸው ይበልጥ የሚጠመዱት፣ ያሜሪቃ ጥቁር ራሱን ቀና ባደረገ ቁጥር ነው፡፡  ለዚህ ዐብይ ምሳሌወች ደግሞ የዊልሚንግተን ጭፍጨፋ (Wilmington massacre of 1898), የተልሳ ጭፍጨፋ (Tulsa race massacre of 1921)፣ የዲትሮይት ጭፍጨፋ (Detroit massacre, 1943)፣ እና የባራክ ኦባማ መመረጥ ናቸው፡፡  በተለይም ደግሞ ያሜሪቃ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር፣ ነጩ አሜረቃዊ በዘረኝነት ተገፋፍቶ ለምርጫ እንዲነሳሳ፣ ጥቁሩ አሜሪቃዊ ደግሞ ተሸብሮ ከመምረጥ እንዲቆጠብ፣ የነጭ ላዕልተኝነት በይበልጥ ይራገባል፡፡   

 

ዶናልድ ትራምፕና የነጭ ላዕልተኛነት

ዶናልድ ትራምፕ (Donald Trump) ነጭ ላዕልተኛ (white supermacist) ነውን?  ይህን ጥያቄ ለመመለስ ነጭ ላዕልተኛ ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡  ባንደኛው ትርጉሙ ነጭ ላዕለተኛ (white supermacist) ማለት በነጭ ላዕልተኛነት (white supremacism) የሚያምንና ዕድሉን ካገኘ ደግሞ ዕምነቱን የሚተገብር ማለት ሊሆን ይችላል፡፡  በሌላኛው ትርጉሙ ደግሞ ነጭ ላዕለተኛ ማለት በነጭ ላዕልተኛነት የማያምን፣ ነገር ግን ነጭ ላዕልተኝነትን መተግበር ለሱ እስከጠቀመው ድረስ የሚተገብር ማለት ሊሆን ይችላል፡፡  

ትናንት ሮማውያን ከታሕተሰብ (subhuman) እየቆጠሩት ባርባርያን (barbarian) ይሉት የነበረውን አንግሎ ሳክሶንን (anglo-saxon)፣ ዛሬ ቀን ስለወጣለት ብቻ በሰውነቱ ከሰወች ሀሉ የሚበልጥ ላዕልሰብ (superman) ነው ብሎ በነጭ ላዕልተኛነት ለማመን፣ ማይም ብቻ ሳይሆን፣ የማይም ማይም መሆን ያስፈልጋል፡፡  ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ የዚያን ያህል ማይም  አይደለም፡፡  ስለዚህም በሁለተኛው የነጭ ላዕልተኛነት ትርጉም ከሄድን፣ ዶናልድ ትራምፕ የነጭ ላዕለተኛነት መዕምን የሆነ ነጭ ላዕልተኛ (white supremacist) አይመስለኝም፡፡       

ዶናልድ ትራምፕ በነጭ ላዕልተኛነት የሚያምን ነጭ ላዕልተኛ (white supremacsit) መሆን አለመሆኑ አከራካሪ ቢሆንም፣ ነጭ ላዕለተኛነትን እንደሚተገብር ግን አያከራክርም፡፡  የሚተገብረው ደግሞ በደንብና በግልጽ ነው፡፡  እኔ ከሞትኩ ሠረዶ አይብቀል ባይ፣  ገደብየለሽ ራስወዳድ (narcisst) በመሆኑ ደግሞ፣ ማናቸውም ነገር እሱን እስከጠቀመው ድረስ፣ በጥቁር ሕዝብ ላይ ይቅርና፣ በነጭ ሕዝብ ላይ ይቅርና፣ በራሷ ባሜሪቃ ላይ ይቅርና፣ በራሱ የቅርብ ቤተሰቦች ላይ ይቅርና፣ በራሱ ልጆች ላይ የሚያመጣው ጉዳት ቅንጣት አያሳስበውም፡፡  ዶናልድ ትራምፕ ከሰው ለመብለጥ ይልቁንም ደግሞ በልጦ ለመታየት ሲል የማያደርገው የለም፡፡   

አብዛኛው ነጭ አሜሪቃዊ በነጭ ላዕልተኛነት ከልቡ የሚያምን ጥሬ ማይም መሆኑን፣ ዶናልድ ትራምፕ እና አማካሪወቹ እነ እስጢፋኖስ ባኖን (Steve Bannon) በደንብ ያውቃሉ፡፡  ስለዚህም ይህን ማይም አሜሪቃዊ ማሕበራዊ መሰረታቸው ካደረጉና፣ የዚህ ማይም አሜሪቃዊ ብቸኛ ጣቢያ በሆነው ፎክስ (Fox News) ላይ የነጭ ላዕልተኛነትን ቀን ከሌት እያራገቡ እሱንና እሱን ብቻ በደንብ ከቀሰቀሱ፣ በምርጫ እንደሚያሸንፉ እርግጠኞች ናቸው፡፡  በ 2016 ዓ. ም ምርጫ ያደረጉትና፣ ለ 2020 ዓ.ም ምርጫ እያደረጉት ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡  

በእኔ እሳቤ፣ ዶናልድ ትራምፕ ነጭ ላዕልተኛነትን የሚያየው ሐይማኖትን በሚያይበት ዓይኑ ነው፡፡  አብዛኛውን ሐብቱን በቁንጅና ውድድሮች (beauty contests) እና በቁማር ቤቶች (casinos) ያፈራው ዶናልድ ትራምፕ፣ ለሐይማኖት ዴንታ እንደሌለውና፣  ባብዛኛው ጥሬ ማይም የሆኑትን አጉል ተመጻዳቂ ወንጌላውያን እና ጴንጤቆስጤወችን እንደሚጸየፋቸው ግልጽ ነው፡፡  ማሕበራዊ መሠረቱን ለማጠናከር የግድ ስለሚያስፈልጉት ግን፣ መስማት የሚፈልጉትን እያሰማና፣ ማየት የሚፈልጉትን እያሳየ እንደ ከብት ይነዳቸዋል፡፡    

ስለ ዶናልድ ትራምፕ ካነሳን ዘንድ የዶናልድ ትራምፕ አርአያ (role model) ስለሆነው፣ ፀረእጽ ጦርነት (War on Drugs) በሚል ሰበብ ከፍተኛ ፀረጥቁር ዘመቻ ከፍቶ በጥቁር አሜሪቃውያን ላይ ከፍተኛ ግፍ እንዲፈጸም ስላመቻቸው ስለ ሮናልድ ሬገን (Ronald Reagan) ጥቂት እንበል፡፡  ሮናልድ ሬገን (Ronald Reagan) እይታው ከሆሊውድ አድማስ ያልዘለለ፣ እውቀቱ ከዲክሲ ብልዛንገት (Dixe redneck) የማይሻል ጥሬ ማይም እንደነበር ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡  አብዛኛው ነጭ ማይም በእጅጉ ይወደው የነበረውም ራሱን በሬገን ውስጥ ስለሚያይ ነበር፡፡  ስለዚህም ሬገን በነጭ ላዕልተኝነት ባያምን እንጅ ቢያምን አያስገርምም፡፡  ነገረ ሥራው ሁሉ የሚመሰክረው ደግሞ በነጭ ላዕልተኝነት ከልቡ የሚያምን መሆኑን ነው፡፡  በርግጥም የሚያምን ከሆነ ደግሞ፣ ባንግሎ ሳክሶኖች አመለካከት ነጭ ሲባል የአይሪሽ ደም ያላቸውን የሱን ቢጤወች እንደማይጨምር እንኳን የማያቅ አላዋቂ ነበር ማለት ነው፡፡ 

ያሜሪቃ ውጀ፣ የነጭ ፍራንከንስቲን

ፍራንከንስቲን (frankenstein) ማለት ሰው ሠራሽ የሆነ፣ ውሎ አድሮ ከሠሪው ቁጥጥር በመውጣት ሠሪውን የሚያሸብር አልፎ ተርፎም ገድሎ የሚበላ ጭራቅ (monstor) ማለት ሲሆን፣ የቃሉ መሠረት ደግሞ በደራሲ ሜሪ ሸሊ (Mary Shelley) ልቦለድ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዋና ገጽባሪ (ገጸ ባሕሪ፣ character) ነው፡፡  

ያሜሪቃ ውጀ (american police) የነጭ ላዕልተኛነት (white supremacy) ዋና አራጋቢ ስለሆነ፣ በነጭ ላዕልተኛነት እንዲመረዝ የተደረገው አብዛኛው ያሜሪቃ ድኻ ነጭ፣ በተለይም ደግሞ ዲክሲው ብልዛንገት (Dixe redneck)፣ ውጀውን የነጭ ቱጃር ዘበኛ ሳይሆን የራሱ አገልጋይና ተከላካይ (server and protector) አድርጎ በመመልከት በሁሉም ረገዶ ከፍተኛ እገዛ ያደርግለታል፡ 

ያሜሪቃ ውጀ ግን ያሜሪቃ ነጭ በሚያደርግለት ከፍተኛ ድጋፍ አለቅጥ ጠንክሮ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ራሱን ነጩን የሚያሸብር የነጩ ፍራንከንስቲን ሁኗል፡፡  የጆርጅ ፍሎይድን (George Floyd) አሰቃቂ ግዳያ ለመቃወም በወጡ ሰላማዊ ነጮች ላይ ያሜሪቃ ውጀ የፈጸማቸው አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች የሚመሰክሩት፣ ያሜሪቃ ውጀ ለነጩም ቢሆን የማይመለስ መሆኑን ነው፡፡  የሰባ አምስት ዓመት አዛውንት ያለ ርህራሄ የሚፈጠፍጥ፣ ወጣቶችን ምን ሊያረግ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ 

የሚኔሶታውን ቦብ ክሮል (Bob Kroll) በመሳሰሉ ማይም ነጭ ላዕልተኞች (white supremacists) የሚመራው ያሜሪቃ ውጀወች ማሕበር (american police union)፣ የሠራተኞች ማሕበር ሳይሆን የቀማኞች ጋንግ (gang) ነው፡፡  ከሌሎች ቀማኛ ጋንጎች የሚለየው ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው የቀማኛ ጋንግ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡  የጣልያን ፖለቲከኞችና ሹማምንቶች ማፍያን ይፈሩት ከነበረው በላይ፣ ያሜሪቃ ፖለቲከኞችና ሹማምንቶች የውጀውን ጋንግ ይፈሩታል፡፡  ይህ ጋንግ የሚጠይቀውን ሁሉ በሙሉ ፈቃደኝነት የማይፈጽም፣ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ሁሉ በጽኑ የማይደግፍ ፖለቲከኛ አይመረጥም፣ ሹመኛም አይሾምም፡፡  ከተመረጠ ወይም ከተሾመ ደግሞ አለ ስሙ ስም ተሰጥቶት፣ አለ ወንጀሉ ወንጀለኛ ተብሎ፣ በሕዝብና በቤተሰቡ ፊት በይፋ ተዋርዶ፣ ባፋጣኝ ስልጣኑን ይለቃል ወይም ከሹመቱ ይሻራል፡፡  

በተለይም ደግሞ ያሜሪቃ ውጀ በጥቁር አሜሪቃውይን ላይ የሚፈጸመውን አሰቃቂ ወንጀል፣ ወንጀል ነው ማለት ቀርቶ፣ አግባብ አይደለም ለማለት የሚደፍር ፖለቲከኛ ወይም ሹመኛ፣  በራሱ ላይ እንደፈረደ ማወቅ አለበት፡፡  ማናቸውም አሜሪቃዊ ደግሞ፣ የውጀውን ጋንግ ለመቃወም ይቅርና ለመተቸት ከቃጣ፣ የትም ሲሄድ ለውጀ ጉስቆላ (police harassment) ራሱን አዘጋጅቶ መሄድ አለበት፡፡               

ጥቁርን ለማፈን የተቋቋመው ያሜሪቃን ውጀ፣ ጥቁርን ብቻ ሳይሆን የሚቃወመውን ማናቸውን ነጭ የሚያፍን አደገኛ አፋኝ ሁኗል፡፡  ስለዚህም፣ አለቅጥ ደርጅቶ፣ በማን አለብኝ ስሜት መረን የለቀቀውን ያሜሪቃን የውጀ ጋንግ ሙሉ በሙሉ በማፈራረስ በቀበሌ ጠባቂ (community police) ለመተካት በሚደረገው ትግል ላይ፣ ሰፊው ያሜሪቃ ነጭ መሳተፍ ያለበት ለጥቁር ብሎ ሳይሆን ለራሱ ሲል ነው፡፡   ጨው ለራስህ ጣፍጥ፡፡

 

አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ

ያሜሪቃ ቀማኞች ቀማኝነታቸውን በጽኑ የሚታገልን ይቅርና በመጠኑ የሚተችን ማናቸውንም ግለሰብ ለማሸማቀቅ የሚጠቀሙባት አንድ አባባል አለች፡፡  እሷም “አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ” (America love it or leave it) የሚሏት ናት፡፡  እኔም መስፍን አረጋ ለዚህ ጦማሬ የሚሰጠኝ የመጀመርያ ምላሽ አሜሪቃን ካልፈለክ ተጠረግ የሚለው እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ የሚለው አባባል አያሌ መልዕክቶችን ያዘለ ሲሆን፣ ዋናው መልዕክት ግን “አሜሪቃ የኛ የነጭ ቀማኞች ብቻ ስለሆነች፣ ለኛ ብቻ በሚመች መንገድ እናስተዳድራታለን” የሚለው ነው፡፡  

በመጀመርያ ደረጃ ግልጹን ለመግለጽ ያህል አሜሪቃ ያገራይ አሜሪቃውያን (native americans) እንጅ የነጭ አይደለችም፡፡  ነጮች አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ ሲሉ፣ በገዛ መሬታቸው ላይ የሚገፉትን አገራይ አሜሪቃውያንን መገፋታችሁ ካስከፋችሁ ተጠረጉ ማለታቸው ነው፡፡  በኋላ የመጣ ዓይን አወጣ፡፡ 

አገራይ አሜሪቃውያን (native americans) አሜሪቃን ካልፈለጋችሁ ተጠረጉ ሲባሉ የሚሰማቸው ስሜት አስብ፡፡  አንድ ቀማኛ ቤትህን ሰብሮ ገባና እኔም እኖረበታለሁ አለህ፡፡  ቀማኛው ለጊዜውም ቢሆን ኃይለኛ ስለሆነ፣ ሳትወድ በግድህ እሽ ብለህ፣ አንተም፣ እኔም፣ ሁለታችንም እንኑርበት አልክ፡፡  ቀማኛው ደግሞ በኃይሉ ተማምኖ ምናባህ ታመጣለህ በሚል ስሜት፣ እሱ ክፍል እየበላ አንተ ክፍል ያራ ጀመር፡፡  ቤቱም ጠነባ፣ ገማ፣ ተግማማ፡፡  አንተ ደግሞ ቀማኛውን የቤቱ መጠንባት ለኔ ብቻ ሳይሆን ላንተም ለራሰህ ጠንቅ ነው እያልክ ብትመክረው ብታስመክረው አልሰማ ሲልህ ጊዜ፣ አቤቱታህን ልታሰማ አደባባይ ወጣህ፡፡  ቀማኛውም ዘበኞቹን ወደ አደባባይ ልኮ ባሰለቃሽ ጭስ እያስለቀሰ፣ በፕላስቲክ ጥይት እየበረቀሰ፣ በዱላ እየቀጠቀጠ፣ በሰደፍ እየወገረ፣ በርግጫ ረመረመህ፡፡  የቀማኛው መሪ ነን ባዮች ደግሞ ቤቱ ገማኝ ብሎ አደባባይ ከሚወጣ ለምን ቤቱን ለቆ አይወጣም አሉህ፡፡  ምን ይሰማሃል?                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                      

ካገራይ አሜሪቃውያን ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ አሜሪቃ መሬቴ ናት ማለት የሚችሉት፣ ነጮች ሳይሆኑ ለአራት መቶ ዓመታት በባርነት እሳት እየተንገረገቡ፣ ጉልበታቸውን በነጻ እያፈሰሱ የገነቧት ጥቁር አሜሪቃውያን ናቸው፡፡  ስለዚህም አሜሪቃ ለሁሉም እኩል የማትመች ሁና ደረጃ በደረጃ መመቸት ካለባት፣ መቅደም ያለባቸው አገራይ አሜሪቃውያን ቀጥሎ ደግሞ ጥቁር አሜሪቃውያን ናቸው፡፡  

አሜሪቃ የነጭ፣ በነጭ፣ ለነጭ ሁና፣ ለነጭ ብቻ እየተመቸች ዘመናትን አስቆጥራለች፡፡  ይህ ደግሞ በውድም በግድም መቆም አለበት፣ ይቆማልም፡፡  ያሜሪቃን ነጭ ቀማኛ አለቅጥ የሚያስፈራውም ይህ ሕቅ የሚያደርገው ሐቅ ነው፡፡  መቆሚያው እየተቃረበ ሲሄድ ደግሞ የቀማኛው ነጭ ፍራቻ እየጨመረ፣ ጭከኔውም በዚያው ልክ እየከፋ ይሄዳል፡፡  ወትሮም ቢሆን ይበልጥ የሚጨልመው ሊነጋጋ ሲል ነው (the darkest hours are just before dawn)፡፡  ሲደርስ ያዳርስ፡፡  

አሜሪቃን የማትፈልግ ተጠረግ የሚለው አባባል ያዘለው ሌላው መልዕክት ደግሞ “የበላዮች ስለሆን የፈለግነውን እናደርጋለን፣ ምናባህ ታመጣለህ” የሚለውን ዕብሪት ነው፡፡  ዕብሪት ደግሞ አያዛልቅም፡፡  ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩፍሰት ውድቀትን ትቀድማለች (ምሳሌ 16፡ 18)፡፡     

ዲሞክራት ከኛ ወዲያ ላሳር የሚሉት ያሜሪቃ ቀማኞች፣ አሜሪቃን የማይፈልግ ይጠረግ የሚሉት ተወዳጅ አባባላቸው ፍጹም ኢዲሞክራሲያዊ መሆኑን እንኳን የማያውቁ አላዋቂወች ናቸው፡፡  አያሌ አማራጮች ሳሉ፣ ሁለት አማራጮችን ብቻ አቅርበህ አንደኛውን የማትወስድ ከሆነ ሌላኛውን ልትወስድ ይገባሃል ማለት የለየለት አምባገነንነት ነው፡፡  አሜሪቃ የሚኖር ያሜሪቃን ሁለመና መውደድ የለበትም፤ አሜሪቃን የሚወድ ደግሞ አሜሪቃ መኖር የለበትም፡፡  አሜሪቃ እየኖርክ ያሜሪቃን ገጽታወች ልትጠላ ትችላለህ፡፡  ሩስያ እየኖርክ አሜሪቃን ልትወድ ትችላለህ፡፡  

 አሜሪቃን የሚወዳትና ላሜሪቃ የሚበጃት ንፍጧን የሚጠርግላት እንጅ፣ ከነንፍጧ የሚስማት አይደለም፡፡  አሜሪቃ ደግሞ ቁመናዋ ሸጋ ቢሆንም፣ የዘሯ እያንዘረዘራት፣ የዘረኝነት ንፍጧን ቀን ከሌት የምታዝረከርክ ንፍጣም ናት፡፡      

መስፍን አረጋ 

mesfin.arega@gmail.com             

Filed in: Amharic