>
5:13 pm - Wednesday April 18, 3308

"ሀጫሉ ታሪክ ነጋሪ" አድርጎ  መናደድን ምን ይሉታል?  (ታዬ ቦጋለ አረጋ)

“ሀጫሉ ታሪክ ነጋሪ” አድርጎ  መናደድን ምን ይሉታል? 

-ታዬ ቦጋለ አረጋ

ሲጀመር፦ ፈረስ ለመላው ኢትዮጵያዊ ብርቅና እንግዳ ነገር አይደለም። ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ግራኝ አህመድ) እና አፄ ልብነድንግል 1529 ሽምብራ ኩሬ (ምሥራቅ ሸዋ) ላይ የተፋለሙት በሁለቱም በኩል ፈረሰኛ ሠራዊት ይዘው ነው።  ይህ ተረት ተረት ሳይሆን የመናዊው ታሪክ ፀሐፊ ሺሀብ አዲን ጦርነቱን በዐይኑ ተመልክቶ በዐረብኛ ካሰፈረው ጦማር “ፉቱህ አል ሀበሽ” ትርጉም = የሀበሻ ወረራ / The Conquest of Habesha ዐይቶ መረዳት ይቻላል።
ወላይታ ሀዲያ ጌዴኦ ስልጢ ጉራጌ ከምባታ… ከትግራይ ጫፍ አሉላ እንግዳ በፈረስ ስማቸው “አባ ነጋ” እስከ ደቡብ፤
ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ድረስ ድንቅ ፈረሰኞች፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች _ በአራቱም ጫፍ ፈረስ መኮድኮድ መጋለብና መስገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ባህልና ልምድ ነው። ለህፃናት ጭምር ፈረስ ብርቅ አይደለም። በተሽከርካሪ ስትዋቡ የምታስተውሉት ጨዋታ ጭምር ነው።
የምኒልክ ፈረስ ስም አባ ዳኘው ሲሆን፤ የምኒልክን ጀግንነት ለማወቅ ለሚፈልግ መጀመሪያ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር በመውደቋ፤ የአካባቢውን ሁናቴ በመገምገም፤ በፍጥነት ለዘመናት የኖረውን አንድነት ይበልጥ ለማስተሳሰርና ለማደርጀት፤ ሀገርን ከቅኝ ግዛት ለማዳን፦  98እጅ ያህሉን የኢትዮጵያ ሥፍራ በፍቅር፤ 1 እጅ የሚሆነው አካባቢ ያለውን ጦረኛ ኃይል በመጠቀም አዋሀዱ።1 እጅ ከአድዋ በኋላ ያለጦርነት የተዋሀደ ነው (ከላይ እንደጠቀስነው ከካፋ ሸካ በስተቀር)
በባዶ ወኔ ሳይሆን በጀግንነት የምኒልክ ኢትዮጵያዊ ጦር የትኛውም አካባቢ ያለውን የውስጥ ኃይል ሳያሸንፍ የተባበረች ኢትዮጵያን አልተመሠረተም።
ደጋግሜ እንዳነሳሁት የምኒልክ ጦር አብዛኛውን የደቡብና የምዕራብ ክፍል የተቆጣጠረው በመጀመሪያ የሸዋን ጦር (ሸዋ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አርጎባ፣ ጉራጌ፣ በኋላ ስልጢን) በመያዝ፤ በመቀጠል በሸዋ ጦር አማካይነት፦ የጊቤ ኦሮሞ ግዛቶችን (ጂማ ጎማ ጉማ ጌራ እና ሊሙ ኢናርያ) ያለጦርነት በመያዝ፣ አስከትሎም የሌቃ ወለጋ ግዛቶች (ቄለምና ነቀምት) ያለ ጥይት ድምፅ በፍቅር በመያዝ፤ አብዛኛውን የአርሲ አባ ገዳዎች ከአኖሌ 1886 በስተቀር፤ ምሥራቁን ከሐረሪ _  ጨለንቆ 1887 በስተቀር፤ ማዕከላዊ አካባቢ ከስልጢ 1884 በስተቀር በፍቅር የተቆጣጠሩት ገና የሸዋ ንጉሥ ሳሉ ነው። (በዚህ ዘመን 1872-1889) ንጉሠ ነገሥቱ የትግራዩ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ናቸው።
ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ 1894 ወላይታን የተቆጣጠሩት በፈረሰኛ ጦር፤ ከአድዋ በኋላ 1897 ካፋን የተቆጣጠሩት በተመሳሳይ በፈረሰኛ ነው። በአንድ በኩል በኃይል ተያዝኩ እያሉ፤ ተገልብጦ የምኒልክን ብርታት መካድ ይደብራል።
አድዋ ያለምኒልክ ፈፅሞ እንደማይታሰብና ብቻውን የዘመተ ብሔረሰብ አለመኖሩን ለማስተንተን ብዙ አንደክምም። የአድዋን ድል ከ80 ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ ለይቶ ከማየትና ያለመሪ ዘምቶ ያሸነፈ ጦር እንደሌለ ለመገመት ድድብና ብቻ በቂ ነው። የ80 ብሔረሰብን ድል ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች መሸለም ደግሞ የከፋ ነውርና ለሌሎች ብሔረሰቦች ያለ ተራ ንቀትን ማሳያም ይሆናል።
መላውን ኤርትራንና ትግራይን ለመቆጣጠር ጣሊያን ባደረገው ጉዞ እነ ባህታ ሓጎስ (ኤርትራ ውስጥ)፤ አሉላና መንገሻ ዮሐንስ፦ ሰንዓፈ እና ኮአቲት (ኤርትራ ውስጥ) ተፋልመው ነበር። ይሁንና የጣሊያን ጦር በወታደራዊ ቁጥርና መሣሪያ እጅግ የበዛ ስለነበር፤ በማሸነፍ መላውን ኤርትራ _ አልፎም መላውን ትግራይ እስከ ደቡባዊ ጫፍ አምባላጌ ድረስ በቁጥጥሩ ስር አደረገ።
ዳግማዊ ምኒልክ ለመላው ኢትዮጵያዊ የክተት ጥሪ አድርገው ወደ አድዋ ሲዘምቱ፤ ለጥሪው ምላሽ ያልሰጠ ኢትዮጵያዊ ብሔረሰብ እና ግለሰብ ከቶውኑ አልነበረም። (ከጣሊያን ጋር ያደሩ ጥቂት “ባንዳዎች” አስቀድሞ ጣልያን ይዟቸው ስለነበር ከመሰለፋቸው በስተቀር)
በዚህ ሂደት የአፄ ምኒልክ ጦር ከመላው ኢትዮጵያዊ የተውጣጣ ነውና ባነሱት ልክ ወርደን ተራ እሰጥ አገባ ውስጥ አንዳክርም።
አይደለም እንጂ፦ የአድዋ ድል ዋነኛ ተዋናይ እኔ ነኝ ካልህ፤ የአኖሌ ትርክት ጡት ቆረጣ ዋነኛ ተዋናይም አንተ ነህ። መርጠህ የምትወስደው ድል፤ መርጠህ የምትተወው (ክፋት) አይኖርም።
የኮሮናቫይረስና የህዳሴው ግድብ ባይኖር እንኳ ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ዕንድናይ በየጊዜው የጥላቻ አጀንዳ እያመጡ፤ ዛሬ ላለው ትውልድ ጠብታ ፋይዳ ላይኖረው ወገን ከወገን ለማናከስ የሚተጉ፤ እግዚአብሔር ይፍረድባቸው።
የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት የቆመው በዓለማቀፍ ደረጃ ለሚታወቀው የአድዋ ድል መሪነትና ጀግንነታቸው ነው። የጋራ ታሪካችንን ለማጥፋት የሚደረገውን ሸር በኦሮሞ ስም አትደበቁበት። ያሳዝናል! በዓለም ፊት መሳቂያ መሳለቂያ ልታደርጉን የእንግዴ ልጆች ተፈጠራችሁ።
እያንዳንዱ አጀንዳ ጥላቻን የሚቀሰቅስ፤ ግጭት ለመፍጠር የታቀደ፤ አብሮነትን የሚንድ … ነው። ምኒልክ የኢትዮጵያውያን የወል እንጂ የአንድ ብሔረሰብ አይደሉም። አጉል እብሪት ‘ላምጪው እንዲከፈል ኢትዮጵያዊነት ያስገድዳል’። (የዘመን አቆጣጠሮች በሙሉ የግሪጎሪ መሆናቸው ይሰመርበት።)
NB. የጥላቻ አጀንዳ አራጋቢው ተመጋጋቢ ግም ለግም ከሁሉም ብሔረሰብ የተውጣጣ መሆኑም ጨምሮ ይሰመርበት።
Filed in: Amharic