>
6:50 pm - Thursday February 2, 2023

እነ አባ አይቼው ...!!!l ( በእውቀቱ ስዩም)

እነ አባ አይቼው …!!!l

( በእውቀቱ ስዩም)

እኛ የድርሰት ስራ እምንሞክር ሰዎች ስራችን ቅጥፈት ነው፤ ስንቀጥፍ ደግሞ  ቅጥፈት መሆኑን አንደብቅም፤ ግን  ቅጥፈቱን ስታነቢው ፤እየተዝናናሽ  እግረመንገድሺን ደሞ  ቄስ ወይም ፈላስፋ የማይነግርሽን የህይወት ሀቅ ልታገኚበት ትችያለሽ’! ድርሰት ማለት እውነትን እነግራለሁ ብለው ቃል ሳይገቡ እውነት መናገር ነው!
ይህ ወግ ስለ ድርሰት አይደለም! ሀቅ እናገራለን ብለው ሚድያ ላይ  ስለሚያጭበረብሩ  ሰዎች ነው  ፤
 ባገራችን ሶስት  ዋና ዋና ያጭበርባሪ መደበቂያ ዋሻዎች አሉ፤ ያገር( ወይም የብሄር)ፍቅር ስሜት ፤ ሃይማኖት እና የእድሜ ባለፀግነት!
  የሌለ   እየተተረተርህ ፤ ቀዳዳነትህ ላይ ትንሽ ያገር ፍቅር  ነስነስ ካደረግክበት  ማንም አይናገርህም፤ ለምሳሌ አንዱ ብድግ ብሎ  “የጥንት አባቶቻችን ጆቢራ  ተፈናጠው  ጨረቃ ላይ ወጥተው  እንደነበር  ጥንታዊ መዛግብት ያረጋግጣሉ “ ብሎ  ቢቀድ አብዛኛው እድምተኛ  እልል ብሎ ይቀበለዋል፤ ላርመው  ወይም ልሞግተው ብለህ ብትነሳ   ባልተወለደ  አንጀታቸው ያበራዩሃል  ፤
 የፈጣሪን ስም አብዝተህ  ካነሳህ ፤ አሁንም አሁንም ከማልህ፤  ጆሮ ጭው እሚያረግ ውሸት ብትናገር  የሚሞግትህ የለም፤ እንዲሁም አረጋዊ ከሆንክ፤  ጋቢ ለብሶ ደጅ ላይ  ቁጭ ማለት ደረጃ ላይ ከደረስህ  እንደመጣልህ  መበርነን ትችላለህ !   በደንብ ተተርትረህ ከመሸበት ታድራለህ!  የሆነ ሰውየ አለ ፤ በያ ትውልድ ታሪክ ውስጥ እዚህ ግባ እሚባል ሚና የለውም፤ ዋለልኝ አይሮፕላን ሲጠልፍ እሱ  ካፌ ቡሌ ሲጠልፍ  ነበር!  አሁን  መቸም ሙታን ተነስተው፤ አይመሰክሩኝም ብሎ ነው መሰል   በየሚድያው   ቻክኖሪስን የሚያስንቅ ገድሉን ሲቀድ አየዋለሁ !
ድሮ በልጅነታችን ወላጆቻችን አደብ ሊያስገዙን ሲፈልጉ “ አባ ጅቦ መጣልህ “ ይሉን ነበር፤ ከዚያ ጎለመስን !  አያጅቦ መጣልህ  በadult version  “ ኢሉምናቲ እና 666”  ሆኖ ከች አለልን  !  ባለፈው አንዱ ጉድ፤ ቻናሉ ላይ ላይቭ ተጎልቶ  “  ላይቭ ላይ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ሰዎች ትታዩኛላችሁ ፤ ወይ አንድ ሰው ይቀነስ ! ወይ አንድ ሰው ይጨመር!  አለበለዚያ ልቀጥል  አልችልም”፤ ሲል አየሁት !
 ሰፊው ህዝብ ደሞ  ኑሮው የፈጠረበት ፍርሃት ሳያንሰው  እኒህ ፍሪኮች  የፈበረኩትን ፍርሃት እየተበደረ ይቦካል!  ኮሮና በቢልጌትስ የተፈጠረው  በክትባት ሰበብ አእምሮአችን ውስጥ ቺፕስ ለማስቀመጥ ነው ይልሃል ደሞ  ! ባለቺፕሱ  ምን አጠምድ ብሎ  ነው አንተ  አእምሮ  ውስጥ ቺፕስ እሚያስቀምጠው? ለቺፕሱም ይታዘንለት እንጂ!
 ደብረ ማርቆስ ውስጥ፤  ድሮ፤ አንድ  ሰው  አገር እሚያስለቅቅ ውሸት ከተበረነነ “ አባ አይቼው “ የሚል ቅፅል ይሰጠው ነበር ፤ አባ አይቼው በቀዳዳነት ክብረወሰን  የሰበረ ሰው ነበር ፤     ” አንድ ቀን  ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በመኪና ሲሄዱ አዩኝና መኪና አቁመው ሊፍት ሰጡኝ፤”  ብሎ ላንድ ጠላ አጣጩ ነገረው ፤ እዚህ ላይ ቢያቆም ጥሩ ነበር ፤ “   የሁዋላ በር ከፍቼ ልገባ ስል   “ ቀጠለ አባ አይቼው “  ጃንሆይ አጠገባቸው ወደ ተቀመጠችው ምሽታቸው እየተመለከቱ ፤አይቼው ጋቢና! መነን ወደ ሁዋላ  ብለው ትዛዝ ሰጡ፤”
ሀሰት የሚወገዝበት ዘመን ነበርና የአባ አይቼው ተወግዘው ቀልለው ሞቱ፤ ዛሬ  ቢኖሩ ኖሮ በየቻናሉ እየቀረቡ እንደ ልባቸው ተረርር እያደረጉ  ከብረውና ተከብረው ይኖሩ ነበር!
Filed in: Amharic