>

ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የሚያስፈልጋት እንደ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አይነት አገር ወዳድ መሪ ነው! (አቻምየለህ ታምሩ)

ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የሚያስፈልጋት እንደ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አይነት አገር ወዳድ መሪ ነው!

አቻምየለህ ታምሩ

 

መለስ ዜናዊ  ግብጽ የሚያስፈልጋትን የዓባይ ውኃ ላለማጉደል  ከሆስኒ ሙባረክ ጋር የተፈራረመው ስምምነት!!!    
 
* ወያኔዎች መለስ ዜናዊን ዓባይን ደፈረ እንደሚሉት ሳይሆን የኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ የውኃ ሀብታችን የሆነውን ዓባይን “ማንም ሳያግደን እንገድባለን” ያላሉበት ጊዜ የለም። 
መንግሥቱ ኃይለማሪያም እንኳን ባቅሙ  ኢትዮጵያን የሚታደጓትን ልጆቿን ገድሎ ቢያስደፍራትም  ዓባይን ለመገደብ ግን ያላደረገው ጥረት የለም። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለመጠቀም ጥናት ስታስጠናና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በዓባይ ወንዝ ላይ ስተሰራ አገራችንን በቀጥታ ያልደፈረችው ግብጽ የሳንሲየርና የሳንድረስት ምሩቃን በግፍ ተረሽነው በመጋዘን ጠባቂው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራ የሻለቆችና የበታች መኮንኖች ስብስብ በመንግሥትነት ተሰይሞ የጣና በለስን ፕሮዤ ሲጀምር ተከላካይ ልጆቿ እንደተገደሉባት ያወቀው የግብጹ መሪ አንዋር ሳዳት እ.ኤ.አ. በሜይ 30 ቀን 1978 ዓ.ም. ባደረገው ንግግር “ Egypt would go to war if Ethiopia planned to build a dam on Lake Tana” ሲል  በመንግሥቱ ኃይለ ማርያሟ ኢትዮጵያ ላይ ደነፋ።
ይህንን የናስርን ድንፋታ ግብጾቹ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በቀጥታ አድርገውት አያውቁም። በጥንቶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ዘመንማ ግብጽ ከኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውኃ ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን ትከፍል ነበር። ይህንን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ነገሥታት አስደናቂ ታሪክ ግብጻዊው የFayoum University የታሪክ ተመራማሪ Prof.Dr. Abdel Moneim Ibrahim Al Gimeay እ.ኤ.አ. ጁን 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአልጃዚራ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምምልስ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል፤
“Rulers of Egypt used to send gifts and gold to the emperors of Ethiopia to stop them from diverting the course of the Nile to the Red Sea away from the Mediterranean … Every time there was a new ruler in Egypt, the Ethiopian emperors would threatened him to stop the water reaching Egypt or send them gifts and golds in return.”
ባጭሩ ከነመለስ ዜናዊ ዘመን በፊት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለማልማት የማንንም አገር ይሁንታና ስምምነት የማትጠይቅ ሉዓላዊት አገር ነበረች። ኢትዮጵያ ዓባይን ስትጠቀም ለግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን በማይጎዳ መልኩ እንደሚሆን በመስማማት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሰጠው መለስ ዜናዊ ብቻ ነው። መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1993 ዓ.ም. ከግብጹ ፕሬዝደንት ሁስኒ ሙባረክ ጋር በደረሰው ባለ ስምንት አንቀጽ የኢትዮ-ግብጽ የትብብር ስምምነት አምስቱ አንቀጾች ኢትዮጵያ ግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን እንደማታጎድል ማረጋገጫ የሰጠባቸው ነበሩ። ስምምነቱ የተፈረመው ለግብጾቹ በአረብኛ ሲሆን ለኢትዮጵያውያን ደግሞ በእንግሊዝኛ ነው።
ማናቸውም አገር የተፈጥሮ ሀብቱን ሲጠቀም መጨነቅ ያለባትና መከተል የሚገባው ፖሊሲ ስለ ሌላ አገር ጥቅም ጉዳይ ሳይሆን የራሱን የተፈጥሮ ሀብት በቅድሚያ እንዴት ራሱን ማገልገል እንዳለበት ነው። በዚህ ረገድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸው ፖሊሲ እጅግ አስደናቂ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት በተለይም ዓባይን በሚመለከት የነበራቸው ፖሊሲ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ማገልጋል አለበት፤ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ተጠቅማበት የሚተርፋትን የተፈጥሮ ሀብት ሌሎች አገሮች ሲጠቀሙ ደግሞ በዋጋ መጠቀም አለባቸው የሚል ፖሊሲ ነበራቸው።
ንጉሡ ይህን የመንግሥታቸውን ፖሊሲ ይፋ ያደረጉት ግብጽና ሱዳን በ1951 ዓ.ም. ዓባይን ለሁለት ለመካፈል መስማማታቸውን ተከትሎ ነው። የግብጽንና የሱዳን ስምምነት ተከትሎ ንጉሡ ከኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበ 10 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በዓባይ ወንዝና በገባሮቹ ላይ ሊሰሩ ስለሚችሉ አሰር ግድቦች ባለ 17 ቅጽ ጥናት አስጠኑ። ይህ ንጉሡ በኢትዮጵያና በአሜሪካን በለሞያዎች እንዲጠና ያደረጉት ግዙፍ ጥናት በ1956 ዓ.ም. ባንድ ላይ ተጠቃሎ “Land and Water Resources of the Blue Nile Basin: Ethiopia” በሚል ርዕስ ታትሟል። ንጉሡ ካስጠኑትና በዓባይ ወንዝ ላይ ሊሰሩ ከታሰቡ ግድቦች መካከል አንዱ አሁን ዓባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለው ታላቁ የዓባይ ግድብ ነው።
በዚህ የንጉሡ አገር ወዳድ እርምጃ የተናበሳጨው የግብጹ ፕሬዝደንት ናስር ጀብሀ ኤርትራን ከኢትዮጵያ እንዲገነጥል በይፋ ማስታጠቅና የሱማሊያ ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን እንዲወሩ ማደፋፈር ጀመረ። ናስር ይህንን ርምጃ ሲወስድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ለ1600 ዓመታት የኖረውን የግብጽና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጋብቻ በማፋታት ኢትዮጵያ የራሷ ፓትሪያርክ እንዲኖራት አድረጉ፤ የተጠኑትን የግድብ ፕሮጀክቶች ስራም በይፋ አስጀመሩ። ጥናቱን ተከትሎ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተጠናቀቁት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች መካከል የጢስ ዓባይና የፊንጫ የኃይል ማመንጫዎች ይገኙበታል።
በዚህ የንጉሡ ደፋር እርምጃ የኢትዮጵያን አይበገሬነት የተገነዘበው ናስር ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነውን ዓባይን ባቀደችው መሰረት መጀመሪያ ሕዝቧን እንዲያገለግል፤ ሲቀጥል ከኢትዮጵያ የተረፈውን ውኃ ሌሎች አገሮች ሲጠቀሙ መክፈል አለባቸው በመባሉ በዚህ መሀል ግብጽ በውኃ ችግር እንዳትጎዳ ከሞተ በኋላ በስሙ የተጠራውን የናስር ግድብ የአስዋን ሐይቅ በመገንባት ፈጠረ። አገር ወዳዱ ንጉሠ ነገሥት ለታሪካዊ ጠላታችን ለግብጽ ጫና ሳይበረከኩ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነውን ዓባይን እንድተጠቀም ይህን ያህል ተጋድሎ አድርገዋል።
አገሩን የሚወድ መሪ ልክ እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት መጀመሪያ ኢትዮጵያን ማገልገል አለበት፤ ሲቀጥል ሌሎች አገሮች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ሲጠቀሙ መክፈል አለባቸው የሚል ፖሊሲና አቋም ሊኖረው ግድ ይላል። ተራራማዋ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ሌሶቶ የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው ከተራሮቿ የሚፈሰውን ውኃ ለደቡብ አፍሪካ አገራት በመሸጥ ነው። ደቡብ አፍሪካ አግሮች ግሮሰሪ ውስጥ የሚሸጠው ውኃ ሌሶቶ መጀመሪያ የራሷን ፍላጎት ካሟላች በኋላ የተረፋትን ሌሎች አገሮች በብዙ ብር የምትሸጥላቸው ውኃ ነው።
ከታች የታተመው ታሪካዊ ንግግር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 1951 ዓ.ም. ከጧቱ በ4 ሰዓት በፓርላማ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ውስጥ የዓባይ ውኃ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ማገልጋል እንዳለበት፤ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ተጠቅማበት የሚተርፋትን ደግሞ ሌሎች አገሮች በዋጋ ሲጠቀሙበት እንደሚገባ ያቀረቡት የመንግሥታቸው አቋም ነው።
 
 
*    *    *
እነሆ መለስ ዜናዊ  ግብጽ የሚያስፈልጋትን የዓባይ ውኃ ላለማጉደል  ከሆስኒ ሙባረክ ጋር የተፈራረመው ስምምነት!    
 ኢትዮጵያ ዓባይን ስትጠቀም ለግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን በማይጎዳ መልኩ እንደሚሆን በመስማማት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሰጠው መለስ ዜናዊ ብቻ  መሆኑን  እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1993 ዓ.ም. ከግብጹ ፕሬዝደንት ሁስኒ ሙባረክ ጋር የፈረመውን ባለ ስምንት አንቀጽ የኢትዮ-ግብጽ የትብብር ስምምነት ከመረጃም አልፎ በማስረጃ አያይዘነዋል።
ይህንን ተከትሎ ወያኔዎቹ  ዐቢይ አሕመድ እንጂ  መለስ ዜናዊ እንዲህ አይነት ስምምነት ከግብጽ ጋር አለመፈራረሙን በማስረገጥ ስለ መለስ ዜናዊ የጻፍሑት ፍጽም ነጭ ውሸት እንደሆነ ዘመቻ ከፍተዋል።
ሆኖም ግን መለስ ዜናዊ ከግብጽ ጋር የፈረመው ስምምነት ዐቢይ አሕመድ ካይሮ ሄዶ በአረብኛ ቋንቋ ግብጽ የሚያስፈልጋትን የዓባይን ውኃ መጠን እንደማያጎድል በመሀላ  ካረጋገጠው ቃል ኪዳን ጋር አንድ አይነት ነው። እንዴውም መለስ ዜናዊ ከተፈራረማቸው ስምንት አንቀጾች ውስጥ አምስቱ አንቀጾች ኢትዮጵያ ግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን እንደማታጎድል ማረጋገጫ የሰጠባቸው ናቸው።
ወያኔዎቹ ግን በፕሮፓጋንዳ ጣቢያቸው ሌት ተቀን የሚያላዝኑት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነውን ዓባይን ስትጠቀም የግብጽን ድርሻ እንደማትጎዳና የሚያስፈልጋቸውን ውኃ ለመልቀቅ በፊርማ ያረጋገጠውን መሪያቸውን ትተው ዐቢይ አሕመድ  ከ26 ዓመታት በፊት መለስ ዜናዊ በፊርማ ያረጋገጠውን በቃል ስለደገመው ሲዘምቱበት ይውላሉ። እውነታው ግን  ዐቢይ አሕመድ ካይሮ ሄዶ ያደረገው መለስ ዜናዊ ከ26 ዓመታት በፊት  ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነውን የዓባይን ወንዝ ስትጠቀም ግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን እንደማይጎዳ በፊርማ ያረጋገጠውን በቃል ደገመው። ከዚህ ውጭ ሁለቱ ሰዎች በዓባይ ጉዳይ ላይ የተለየ አቋም የላቸውም።
ለወትሮው ስምምነት ሲፈረም በሰጥቶ መቀበል መርኅ ነበር። መለስ ዜናዊና ዐቢይ አሕመድ ግን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ለግብጽ በነጻ ሰጥተው በምላሹ ለኢትዮጵያ ከግብጽ ምንም ሳይቀበሉ ስምምነቱ የሚፈጽሙ የአለም ጉዶች ናቸው።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ የሆነውን  የዓባይን ውኃ  ስትጠቀም መጀመሪያ ኢትዮጵያን ማገልጋል አለበት፤ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ተጠቅማበት የሚተርፋትን የተፈጥሮ ሀብት ሌሎች አገሮች ሲጠቀሙ ደግሞ በዋጋ መጠቀም አለባቸው የሚል ፖሊሲ ከነበራቸው ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ኢትዮጵያ ዓባይን ስትጠቀም ለግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ መጠን በማይጎዳ መልኩ እንደሚሆን ወደሚስማሙ ገዢዎች የወረድነው ለውጥ መጣ ተብሎ ነው።
ለማንኛውም ከታች የታተሙት ገጾች መለስ ዜናዊ  እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1993 ዓ.ም. ከግብጹ ፕሬዝደንት ሁስኒ ሙባረክ ጋር በደረሰው ባለ ስምንት ኢትዮጵያ ግብጽ የሚያስፈልጋትን የውኃ  መጠን እንዳማያጎድል የተስማማበት ስምምነት ነው።
Filed in: Amharic