>

አጼ በረደድ (መስፍን አረጋ)

አጼ በረደድ

 

መስፍን አረጋ


ወዛደሮች ከጎራ፣ ተነስተው ለማኝ ሳያራ

ይወርዱና ቂርቂራ፣ ተሰማርተው በግድብ ሥራ፣

ለቅጽበት ሆነ ላንዳፍታ፣ /ሳይሰጣቸው/ ምንም ፋታ

ጀምረው ከወፍ ጫጫታ፣ መሽቶ በሬ እስኪፈታ

በትጋት በዋተታ፣ ይሠራሉ ያለታከታ፡፡

 

አዝማች

_ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _

ፍጠን፣ ወዛደር ፍጠን

ሥራህን ሳታከናውን

አንድ ኑሲቃ ብታባክን፣ 

ሲደርስ የክፍያ ቀን

ውርድ ከራሴ ብታዝን፡፡

_ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _ _

አለቃቸው አሰግድ፣ በሥራ ስለማያቅ ቀልድ

 ይህ ግጥም (Drill, Ye Tarriers Drill) በሚለው ያሜሪቃኖች ባህላዊ ዘፈን (Folk Song) ላይ የተመሠረተ ግጥም ነው፡፡ (ምንጭ፡ Physics, by Serway and Jewett, 6th Edition, Page 53) 

 ለማኝ ሳያራ = ማለዳ፣ ጧት፣ ወፍ ሳይንጫጫ፡፡

 ዋተተ (ወተተ)  =  ዞረ፣ ባከነ፣ ተንከራተተ፣ ወዲያና ወዲህ አለ፣ ብዙ ሥራ ሠራ፣ ባተለ (ወተት ሲንጡት እንደሚዋልል)፡፡  ዲንቢያና ፎገራ የላም አገር ትቶ፣ ወተት፣ ወተት ይላል ሰው ከተማ ገብቶ፡፡ 

 ኑሲቃ (second) ማለት ሰከንድ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው እኑስ እና ደቂቃ ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡

ሲያሰኛቸው መሸርደድ፣ ይሉታል አጼ በረደድ፡፡

 

አሰግድ ብሎ ዘና፣ በለሰለሰ ቃና

የግድብ ሥራው እንዲቃና፣ መመርያውን ሲያስጠና፣

የጊዜን ዐብይ ሚና፣ ያስረዳል በጽሞና፡፡

ካለፈ እሚባል ትናንትና፣ ጊዜ ወርቅ ነውና

ባንደኛነት በዋና፣ እንዲከበር በጸና

ሥራው ሀ ሲባል ገና፣ አሰነግሬያለህ በዜና፡፡

 

ስለዚህ የኔ ጀግና፣ በሥራ ስትል ደፋ ቀና

ሰገራን ተወውና ፣ ሽንትህ  ቢመጣ በጠና፣

ገለል ብለህ ከጎዳና፣ ሥራ ከማቆም ልትሸና፣

ዝም ብለህ በደፈና፣  ሱሪህ ላይ ልቀቀውና

ሥራ ጨርሰህ ስትዝናና፣ እጠበው በሳሙና፡፡ 

 

አዝማች ………

 

ከዕለታት ባንድ ቅጽበት፣ ሳይታሰብ በድንገት

የተቀበረ ለዐለት፣ ፈነዳና ደማሚት፣

ዘበርጋን በመወርወር፣ አንስቶ መቶ ሜትር

አገለባብጦ በማዞር፣ ዘረፈጠው ከምድር፡፡

አዝማች ………

 ሸረደደ = ዐማ፣ ነቀፈ፣ አሾፈ፣ አላገጠ፣ አፌዘ፣ ምፀት ተናገረ፡፡

 በረደደ = ጠነከረ፣ በረታ፣ ጸና፣ ቀጠቀጠ፣ መታ፡፡  በረደድ ማለት ደግሞ የጸና ፣ የበረታ፣ የከበደ፣ ጠንካራ፣ ብርቱ ማለት ነው፡፡ 

 ጽሞና =  ርጋታ፣ ፀጥታ፡፡

ዘረፈጠ = በቂጡ አስቀመጠ፣ ቁጭ አደረገ፣ ወዘፈ፣ ረፈቀ፡፡

ዘበርጋም በመታተር፣ ወጥሮ ሠርቶ ሙሉ ወር

ደመወዙን ሲቆጥር፣ ስለጎደለ አንድ ብር

ንዴቱን በመደበቅ፣ እየመሰለ የሚስቅ

የደመወዙን ማዘቅዘቅ፣ ምክኒያቱን ሲጠይቅ፣

አሰግድ በመጀነን፣ ተኮፍሶ በመዘባነን

እያየው በንቀት ዓይን፣ አስረዳው በመተንተን፡፡

 

ሥራህን ሳታከናውን፣ አንድ ኑሲቃ ብታባክን

በኋላ እንዳታዝን፣ ነግሬህ ነበር በማግነን፡፡

ስለዚህ የኔ ወገን፣ ደማሚት የፈነዳ ቀን

ተስፈንጥረህ በመጓን፣ አየር ላይ ስትቦዝን

ባጠፋኸው የጊዜ መጠን፣ ተቆርጦብሃል እቅጩን፡፡ 

 

 መስፍን አረጋ 

 mesfin.arega@gmail.com                   

 እቅጩን = እርግጡን፣ ትክክለኛውን::  

ጥየቄ፡፡  ዘበርጋ መቶ ሜትር ሽቅብ በመጓን ላባከነው ጊዜ አንድ ብር ከተቀጣ፣ የሰዓት ክፍያው (hourly pay) ምን ያህል እንደሆነ፣ የነጻ ውድቀት እኩልታወችን (equations of free fall) በመጠቀም አስላ፡፡

ታተረ = ተጋ፣ ጣረ፣ ለፋ፣ ደከመ፡፡  ታታሪ ማለት ደግሞ ጣሪ፣ ትጉህ ማለት ነው፡፡ 

 ጀነነ = ኮራ፣ ታበየ፣ ተኮፈሰ፡፡  ጅንን ማለት ደግሞ ኩሩ፣ ኩፍስ ማለት ነው፡፡

 ዘበነነ  = በኩራት አወራ፣ ዘበናይኛ ተናገረ፡፡ 

 

Filed in: Amharic