>

184,000,000,000.00 ቢልዮን ብር እውን ከተማ ለማስዋብ ወይስ ለራስ ለመዋብ...???!! (ዳንኤል ቶማስ )

184,000,000,000.00 ቢልዮን ብር እውን ከተማ ለማስዋብ ወይስ ለራስ ለመዋብ…???!!

ዳንኤል ቶማስ 
*  የፒያሳው ዓድዋ ማዕከል (አጼ ምኒልክን በተቁዋም ደረጃ መስደቢያና ታሪክ ማጠልሻ ማእከል) 5.7 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ…!
 
እስቲ ተመልከቱ! ከደሃ ኢትዮጵያውያን ላይ የዓባይ ግድብን ለመጨረስ 8100 ላይ A ብላችሁ በመላክ ታላቁን የህዳሴ ግደብ እውን አድርጉ፣ የዜግነት ግዴታዎን ይወጡ…የሚል የቴክስት ጭቅጭቅ በሚስተናገድባት አገር! ከእያንዳንዱ የ 5 ብር ካርድ ከሚሞላ ደሃ  ዜጋ 3 ብር ላኩ እየተባለ በየዕለቱ በሚለመን በሚጠየቅባት አገር፤ በ2.5 ቢሊዮን ብር (እሱም 2.5 ትሪሊየን ብር ብንል ሰው ምን ይለናል? በሚል በመንግስት ሃሰተኛ የበጀት አገላለጽ)በ 2.5 ቢሊዮን ብር አብዮት አደባባይ በሚዋብባት አገር፤ “እንዴት የአዲስ አበባ ህዝብ የሚጠጣው ውሃ ሳይኖር መንግስት አደባባይ ያስውባል? ጎበዝ ሚስጥሩ ሌላ ነው….” ብሎ መግለጽና መጠቆም ምቀኝነት ከመሰለ….ልማት ጠል አስብሎ ካስፈረጀ…በርግጥም ጭቅጭቅን ጋብ ማድረግ ያስፈልጋል!
ጣና በአደገኛ አረም ተውጦ ወደ ሜዳማነት እየተቀየረ ባለባት አገር፤ የአዲስ አበባን ወንዞች መናፈሻ ለማድረግ በ30 ቢሊዮን ብር ማስዋብ! የሚል እቅድ ይዞ ይህን ያህል በጀት በፓርላማ አስጸድቆ የሚንቀሳቀስን መንግስት፤ “አረ ጎበዝ ወዴት ወዴት…ስንት አንገብጋቢና አስቸኩዋይ ነገር እያለ…?” ብሎ መሞገትና ነገሮችን ከእነ ምክንያቶቹ ከእነ ሴራዎቹ መጠቃቀስ፤ “ምን ችግር አለው? ጸረ ለውጥ! የአብይ ተቃዋሚ!” ምናምን የሚልን ኦዲየንስ ደጋግሞ መጨቅጨቅ ምን ይጠቅማል?
በነገራችን ላይ እኔ አዲስ አበባን ትቻት ከሄድኩ በሁዋላ ሌላ ወንዝ ተፈጥሮ ካልሆነ በቀር አዲስ አበባ በ30 ቢሊዮን ብር (በጀቱ ያው..ግማሽ ዓባይ ግድብ ማለት ነው) የሚዋብ ወንዝ የለም። ስለየትኛው ወንዝ እንደሚወራም ግልጽ አይደለም!
የአዲስ አበባ ዋና ዋና ወንዞች ሁለት ብቻ ናቸው። አንዱ ቀበና ነው። በአራት ኪሎ ቀኅስ በአጎዛ በፕላዛ በኡራኤል አልፎ የሚሄደው ብቸኛ ወንዝ! ሌላው በእኛው ሰፈር በመካኒሳ አቦ ያለው ልጅ ሆነን እንዋኝበት የነበረው አሁን የነጠፈው (ጊዶ ዋሻ )የምንለው ወንዝ ነው! ሌላ ምን ወንዝ አለ?እና  እነዚህን ዳርዳራቸውን ለማስዋብ 30 ቢሊዮን ብር አንሶኛልና ይጨመርልኝ ብሎ ለምክር ቤት ተጨማሪ በጀት የሚጠይቅን ግራ አጋቢ መንግስት እንዴትና ለምን? በምን መስፈርት? ስንት አስቸኩዋይና አንገብጋቢ ጉዳይ እያለ… ብሎ እየጠየቁ ማስመረር፣ ስውር ሴራውንም መንገር… የፓለቲካ ተቃውሞ ለሚመስለው፣ ምቀኝነት ሆኖ ለሚታየው ነገር ለተጋረደበት ኦዲየንስ በርግጥም ሙግቱን ጋብ አድርጎ በገዛ ዓይኖቹ እንዲያይ በገዛ አእምሮው እንዲያስብ የጥሞና ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል እንጂ!
ዓባይ አልፎበት የሚሄደውን፤ ይልቁንም ዋና የዓባይ ምንጭ የሆነውን የግዮንን ምንጭ ጣናን የተጋረጠበትን የአረም አደጋ ከመጤፍ ሳይቆጥር፤ “በታላቁ የህዳሴ ግድብ ማንም ኢትዮጵያዊ አይደራደርም! ዓባይ ህልውናችን ነው! 85%የሚመነጨው ከእኛ ነው! ወንዛችን ማልማት…!” እያለ የይምሰል የሚሸልልን፤ምንጩን ግን ሆነ ብሎ ትኩረት ነፍጎ የሚያደርቅን አካል፤ “አረ እባካችሁ ነገሩ ወዲህ ነው..” ብሎ መንገር ሌላ ሌላ ነገር ካስባለ ለማን ምን ለመንገር፣ ማንን በምን ዘርፍ ለማንቃት ይጻፋል?እዚያው ሲገነባባ አይተው ይመኑ እንጂ…የሚያስብል ነገር ያለበት ሁኔታ ነው የነበረው  ክቡራን!
እንዲህ እየተባሉ የሚገለጹ ምክንያቶች፤ምናልባትም ስልቸታዎች ናቸው ለጥቂት ጊዜ ዝም ወዳለ ቦታ ሄጀ ዝም እንድል አድርገውኝ የነበረው። በተረፈ…አለሁ!
ባራዳ ቁዋንቁዋ አክተር አይሞትም! በእግዜርኛ እግዚአብሔር ሳይጨርስ አያርፍም! ስለዚህ የጀመርነውን አሳብ በቅርቡ እስክንቁዋጭ ድረስ እንቀጥላለን ለማለት ነው..!
እና ለጥሞና የመደብኩትን ጊዜ ሳልጨርስ አላስችል ብሎኝ መመለስ! ተመልሸ ወደ መረጃ መረቦች ገባ ወጣ እያልኩ ሳይ፣ የቤተመንግስቱን ዜናዎች ስዳስስ ኢትዮጵያ ሌላ አገር ሆና ጠበቀችኝ!
ከአደባባይ ማስዋብ ጀምሮ እስከ አፍሪካ መዝሙር ረቂቅ አዋጅ! ከምናምን እስከ ምናምን ሌላ አገር! ሌላ ሌላ አጀንዳ!ልዩ ልዩ ሹመት! ጭራሽ ሃጫሉ ሁንዴሳ የእለቱ አወዛጋቢ አጀንዳ ሰጭ ሆኖ ተሹሞ፣አጀንዳ ሰጪና የማህበራዊ ሚዲያ ወሬ አስለዋጭ የመሆን ዕድሉ ገጥሞት፣ የእነ ህዝቅኤል ጋቢሳ የእነ በቀለ ገራባ ባች ሆኖ በሚዲያ ቀርቦ ስለ አህያ በቲቪ እያወራ ምናምን!
ለማንኛውም እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ከዳሰስኩ በሁዋላ ነው ወደ ገንዘብ በጀቱ ድምር የገባሁት። መንግስታችን እንደ ትልቅ ዝና ቆጥሮ ይፋ ያደረገውን የአዲስ አበባ ፕሮጀክቶች የገንዘብ በጀት ቀድማችሁኝ እንዳሰላችሁት ተስፋ አለኝ።የኢትዮጵያ የራሱዋ የብልጽግና ፕሮጀክቶች መስለው ነገር ግን የኢትዮጵያ ያልሆኑና ሊሆኑ የማይችሉ ሰው እንዳይደነግጥ በሚል የተወሰኑ ዜሮዎች ተቀንሰውባቸው በቀላል ብር እየተሰሉ የተጠቆሙትን ፕሮጀክቶች ማለቴ ነው።
እነዚህን ዝርዝሮች በጥሞና ያስተዋለ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለመረዳት ቅርብ ይሆን  ይመስለኛል። ወደየትኛውም የወጣ አስተሳሰብና ወደ ሌላ እንግዳ  ጥርጣሬ መሄድ ሳያስፈልግ እንዲሁ በጤነኛ አስተሳሰብ እነዚህን ነገሮች ማጤን በጀታቸውን ማስላትና መደመር ብሎም ምን ያህል  አንገብጋቢና የአገር ህልውና ቢሆኑ ነው? አይነት ጥያቄ በመጠየቅ ብቻ ወደ አንዳንድ ምላሾች ባቁዋራጭ  መቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ አመቻችተዋል!
በእርግጥ የአዲስ አበባ ወይም የኢትዮጵያ ችግሮች እነዚህ ናቸውን? የከተማዋና የነዋሪው አንገብጋቢ የዘመናት ጥያቄዎችስ በእርግጥ እነዚህ ነበሩ? ለውጡ(ነውጡ) ያስፈለገውስ እነዚህ ነገሮች ቅድሚያ ተሰጥቶዋቸው በፍጥነት እንዲሰሩ  ነውን?የሚያስብሉትን ማለቴ ነው።
-ቤተመንግስቱ ተዛምሞ ሊፈራርስ ተቃርቦ የነበረ ይመስል ቅድሚያ ሰጥቶ ምን ችግር አለው ቢታደስ?አቤት ሃበሻ!! አስብሎ አፍ በሚያዘጋ ሎጂካል በመሰለ መንገድ እሱን ከማስዋብ የጀመረው አካሄድ እንዲህ ባለ በጀት ቀጥሎ ይገኛል! እነዚህን ዝርዝሮች ከፊሎቹን ከሃብታሙ ቦጋለ ገጽ ነው ያየሁዋቸው። ከፊሎቹን ደግሞ ከጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ ኦፊሻል ገጽ። እና ስደምራቸው ቀደም ስለ መስለው ከነበረው ቁጥር ውስጥ 6 ዜሮዎች ጎደሉብኝ እንጂ ልክ ናቸው።
ቤተመንግስት ውስጥ አንድነት ፓርክን ለመስራት 5 ቢሊዮን ብር!
-የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤትን ለማደስ 3 ቢሊዮን ብር!
-የአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል ለመገንባት 10 ቢሊዮን ብር!
-አዲስ ነገ (addis tomorrow)የሚል ምንነቱ የማይታወቅ የተለየ ግንባታ  120 ቢሊዮን ብር! 
-አዲስ አፍሪካ የተባለ የስብሰባ ማዕከል ግንባታ 2.7 ቢሊዮን ብር!
-አንድነት ፓርክ የመኪና ማቆሚያ 2.5 ቢሊዮን ብር!
-መሶብ ታወር 25 ቢሊየን ብር!
-መገናኛ የትራንስፓርት ተርሚናል 3 ቢሊዮን ብር!
-እንጦጦ ፓርክ 1.5 ቢሊዮን ብር!
-ለገሃር መንደር 2 ቢሊዮን ብር!
-ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገነባው ለአሜሪካው ልዩ  ዩንቨርስቲ፤ የአሜሪካ ሳተላይት መገጣጠሚያ (satellite design  build)  1.5 ቢሊዮን ብር!
የፒያሳው ዓድዋ ማዕከል (አጼ ምኒልክን በተቁዋም ደረጃ መስደቢያና ታሪክ ማጠልሻ ማእከል) 5.7 ቢሊዮን ብር!
-አዲስ ለተፈጠረው ሃሰተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ መጋዘን (አዲስ አበባ የታሪክ ቤተ መጻህፍት) 2 ቢሊዮን ብር!
እነዚህ ሲደመሩ መቶ ሰማንያ አራት ቢሊዮን ብር!ስንለው ከኖርነው ብር ስንት ዜሮ ቀረን? በጣም ትንሽ!
ይህ የስብሰባ አዳራሽና የአደባባይ በጀት ነው። ግንባታውም ሆነ መናፈሻው ለኢትዮጵያና ለህዝቡ ጥቅም ሲባል የሚገነባም አይደለም። ህዝቡንም ሆነ አገሪቱን ለማሳደግና ለማስዋብም አይደለም!ንብረትነቱም የሌላ ነው! ዓላማውም ሌላ ነው!የማስተር ፕላኑ ፈጣሪና አቅራቢዎችም ሌሎች ናቸው! እንዲህ ያለውን ግንባታ ለምን ግልጋሎት እንደፈለጉትም እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት! በተረፈ ውሃ አያስገኝ መብራት የለው ኢሪጌሽን የለው አንቡላንስ አይገዛ  ኢንደስትሪ አላከተተ ነቲንግ! ጀስት የስብሰባ ማዕከል…! የጭብጨባ አዳራሽ!
እንዲህ ያለውን እንግዳና አስቸኩዋይ የሆነ እቅድና በጀት ሰምቶ የልማትና የእድገት ጉዳይ እየመሰለው የሚያጨበጭብና እልል እያለ የሚፎክር ነገሩን ከፓለቲካዊ ወገንተኝነት ጋር የተያያዘ ተቃውሞ አድርጎ እሪሪሪ ከሚል ጭፍን ደጋፊ ጋር ሁልጊዜ መሙዋገት ረፍት አይፈልግም ትላላችሁ?
በእነዚህ በቢሊየን ዶላር በሚገነቡ አስደናቂ አዳራሾች ምን ምን አይነት ስብሰባ እንደሚካሄድ እንዴት ያለ ወሬና እንዴት ያል ጭብጨባ እንደሚደረግ ምን አይነት ውሳኔ እንደሚተላለፍ  ለመገመት የማይሞክር ብዙ አድክም የሆነ ዜጋ አለ!ቢቀሰቅሱት አይደለም ውሃ ቢደፉበት የማይነቃ! እና ለዚያ ነው….ለእነሱም የእንቅልፍ ጊዜ ለእኛም ረፍት ቢጤ…በሚል ያዙትና ጠፋህ ብለው ለተጨነቁት ይህን አለሁ ሰላም ነኝ የሚል መልዕክት ሼር በማድረግ በሰላምና በጤና እንዳለሁ አሳውቁልኝ::
Filed in: Amharic