>

በኢትዮጵያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 81 መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ አስታወቀ (DW)

በኢትዮጵያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 81 መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ አስታወቀ

DW


ሶስት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ የሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት በቀሰቀሰው ተቃውሞ እና አለመረጋጋት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 81 ደረሰ። ሰባት ሰዎች በአዲስ አበባ መገደላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ አረጋግጠዋል። የሐጫሉ ሁንዴሳ አጎት በአምቦ ከተገደሉ መካከል ይገኙበታል።

የሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት በቀሰቀሰው ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 81 መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ፖሊስ ማምሻውን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጧል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት 78 ሰላማዊ ሰዎች እና ሶስት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በአጠቃላይ 81 ሰዎች ተገድለዋል። ኮሚሽነር ጄኔራሉ በአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንም ገልጸዋል።

አርሲ፣ ጅማ፣ ባሌ ሮቤ እና አዳማ የድምፃዊ ሐጫሉ ሞት የቀሰቀሰው ተቃውሞ የበረታባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው እስከ ትናንት ብቻ 50 ሰዎች ተገድለው እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በክልሉ ከግድያ ባሻገር ንብረት የማውደም እና የማቃጠል ድርጊቶች መፈጸማቸውንም አረጋግጠዋል።

በአምቦ ከተማ የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ወደ አዲስ አበባ መመለስ አለበት በሚል በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች እና የክልሉ ፖሊስ ገልጸዋል።

የሐጫሉ አባት ልጃቸው በአምቦ እንዲቀበር ፍላጎታቸውን ቢገልጹም ተቃውሞ መነሳቱን በቦታው የነበሩ የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የፌድራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ኃይሎች በወቅቱ በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን የሚናገሩት የዐይን እማኙ የሐጫሉ አጎት “ልጆች እንዳትመቱ እያለ ወደ ፖሊሶቹ ሮጠ። ከዚያ በጥይት መቱት፤ ሞተ” ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ግን በአምቦ ከተማ የተገደሉት የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ አጎት ከተቃዋሚዎች በተወረወረ ቦምብ ነው ሲሉ አስተባብለዋል። በድምፃዊው ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን እና የጥይት ተኩስም እንደነበር ለጋዜጠኞች የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ የሐጫሉ አጎት መኖሪያ ቤታቸው ላይ በተወረወረ ቦምብ ቆስለው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ መሞታቸውንም አስረድተዋል።

ኮሚሽነር ጄኔራሉ “ሌላ ሰው ለመሞቱ የደረሰን መረጃ የለም” ይበሉ እንጂ የዐይን እማኞች በትንሹ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  የዐይን እማኙ “መዓት ሰው ነው የሞተ፤ እኔ አምስት ሰው አይቻለሁ” ብለዋል።

በአዲስ አበባ መግቢያ አካባቢዎች፣ በአራት ኪሎ፣ በቄራ፣ በካዛንቺስ እና በመገናኛ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች መስተዋላቸውን የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ዱላ እና ስለት የያዙ እና ወጣቶች የሚበዙባቸው ቡድኖች በአዲስ አበባ ሲዘዋወሩ ታይተዋል። በተለያዩ ሰፈሮችም የጥይት ተኩስ በተደጋጋሚ ለመሰማቱ ዶይቼ ቬለ ማረጋገጫ አግኝቷል። በበርካታ አካባቢዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ለጥበቃ ተሰማርተው ታይተዋል።

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

Filed in: Amharic