>
7:09 pm - Wednesday June 7, 2023

አቶ ጀዋርና አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ .. (ዶቼቬለ)

አቶ ጀዋርና አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ 

3ኛ ፖሊስ ጣብያ መታሰራቸውም ታውቋል!!!

ዶቼቬለ

አቶ ጀዋር መሐመድ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች ታሳሪዎች ሁሉ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ጊዮርጊስ አካባቢ ባለዉ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ባለቤታቸዉ በሦስተኛ ፖሊስ ጣብያ መታሰራቸዉን ከፖሊስ በደረሳቸዉ የስልክ ጥሪ ማረጋገጣቸዉን ተናገሩ። ፖሊስ ወደ ወ/ሮ ሃና የደወለዉ፤ «ለአቶ በቀለ ገርባ የደም ግፊት መድሐኒታቸዉን እንዲያመጡላቸዉ ለመጠየቅ ነዉ፤» ብለዋል።  ወይዘሮ ሃና የባለቤታቸዉ  «የደም ብዛት ሕመም እንደተነሳባቸዉ» ተናግረዋል።
 « ባለቤታቸዉ በሚገኙበት ሦስተኛ ፖሊስ ጣብያ መድሐኒቱን ካደረሱ በኋላም ለአቶ በቀለ ገርባ ምግብና ልብስም እንዲያመጡላቸዉ  ተደርጎ እንደወሰዱላቸዉ » ወ/ሮ ሃና ተናግረዋል። የአቶ በቀለ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ምግቡን ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣብያ ሲያደርሱ፤ ባለቤታቸዉን አቶ በቀለ ገርባን እና አቶ ጀዋር መሐመድን ከሩቅ ጎን ለጎን ቆመዉ እንዳይዋቸዉ ተናግረዋል።
ይሁንና ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር የታሰሩ ልጆቻቸዉ ይት እንዳሉ እንደማያዉቁ ወይም እንዳላይዋቸዉ ወ/ሮ ሃና ተናግረዋል። የአቶ በቀለ ገርባ ልጆች ቦንቱ እና ሳሙኤል በቀለ እንዲሁም የአቶ በቀለ ገርባ የእህት ልጅ ኪያ በላቸዉ ከአቶ በቀለ ጋር የሟቹን አርቲስት  አስክሬን ወደ  አዲስ አበባ በመመለሱ ሂደት ላይ ተገኝተዉ ተይዘዋል»ተብሎአል። «ቤተሰቡ በአንድ መኪና በእህታቸዉ ልጅ በኪያ በላቸዉ አሽከርካሪነት በኦሮምያ የብልጽግና ቢሮ አስክሬኑን በመመለስ ጉዳይ ላይ ተሳትፈዋል» ተብሎአል።
በሌላ በኩል ፤ «በአዲስ አበባ የመከላከያ ሠራዊት ገባ ተብሎ የሚፃፈዉ ነገር ትክክል አለመሆኑ»  ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል። በመረጃዉ መሰረት «ድሮም ቢሆን የመከላከያ ሰራዊት የነበረዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ነዉ።» ቀደም ሲል «የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በሃገሪቱ ከ 80 ሰዎች በላይ በመገደላቸዉ፤ ልዩ የፀጥታ ኃይላት ወደ አዲስ አበባ መግባታቸዉን የዉጭ ዘገቦች አመልክተዋል።»
ከአዲስ አበባ በደረሰን መረጃ መሰረት ግን አዲስ አበባ ከትናንትና በተሻለ መረጋጋት ላይ ትገኛለች። «ወደ አዲስ አበባ ልዩ ኃይል ገባ ፤ አልያም ተጨማሪ ሰራዊት ወደ አዲስ አበባ ገባ የሚባለዉ ነገር ፈፅሞ ሃሰት ነዉ። የዉጭ ኃይሎች ከአገር ዉስጥ ኃይሎች ጋር በመተባበር የሚነዙት ወሬ ነዉ» ተብሎአል።
Filed in: Amharic