>

ወይ "ወኔ የተሞላችሁ ጀግኖች ናችሁ!" ተብሎ የተጻፈልን ታሪክ በፅኑ ዋሽቷል!  አሊያ ደሞ ወኔያችንን ሸንተን ጨርሰነዋል! ይኸው ነው!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ወይ “ወኔ የተሞላችሁ ጀግኖች ናችሁ!” ተብሎ የተጻፈልን ታሪክ በፅኑ ዋሽቷል!  አሊያ ደሞ ወኔያችንን ሸንተን ጨርሰነዋል! ይኸው ነው!!!
አሰፋ ሀይሉ

ዛሬን ከትናንት ሊያስበልጥ የሚተጋ ተላላ ደንቆሮ አጋጠመኝ! ዛሬ የት ነን ያለነው? ዛሬ ሰው የሚባለው ነገር፣ ዜግነት የሚባለው ከስም ያላለፈ ወግ ይቅርና፣ ለመሆኑ በሌላው ሀገር ለዱር እንስሳት ራሱ የሚሰጠው ክብር የሚባለው ነገርስ ጨርሶ አለን ወይ እኛ ለመሆኑ?
በአድዋ ለክብራቸው ከቆሙ ታላቅ የነጻነት መንፈስን ከተላበሱ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን እንዳልተፈጠርን ሁሉ፣ የጀግኖች ዘሮች እንዳልሆንን ሁሉ፣ ጀግንነትና ኩሩነት፣ ክብርና መስዋዕትነት ካባቶቻችን የወረስነው ማንነት እንዳልሆነ ሁሉ – ዛሬ ያ ሁሉ እንደጨው ከውስጣችን በንኖ – የታላላቆችን ስም የምንጠራ አሳፋሪ ትንንሾች ሆነናል! ለክብራቸው ከቆሙ ኃያላን የተገኘን ሚጢጢ ቡካቲያም ፈሪዎች ሆነናል! ክብር ያላቸውንና ለክብራቸው የቆሙትን ቀደምቶቻችንን የምናመልክ የሰው ውሪ ሆነናል! ባልሰለጠኑ መንጋዎች ተንበርክከን የምንገረፍ የመጨረሻዎቹ ክብረቢስ ወራዶች ሆነናል!
ዛሬ ላይ ያለን የኢትዮጵያ ልጆች ክብር ያለው የሰው ልጅ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙ ጠፍቶብናል! ለሀገር መኖርና ለሀገር መሞት ትርጉሙ አልቆብናል! ሰው የመሆን ታላቅነት ውስጣችን ዘልቆ እስኪገባን ድረስ ሰጥ ለጥ ብለን በከብቶች መንጋ እየተረገጥን መኖርን በፀጋ መቀበልን ጀብዱ አድርገነዋል! በህይወት መቆየትን የዓለም ትልቁ ጀግንነት አድርገነዋል! መራባትን፣ መብላትና ማራትን ትልቁ የሥልጣኔ ምልክት አድርገነዋል! ፍርሃታችን በዓለም የመጨረሻዎቹ ወራዶች ወዳልደረሱበት የውርደት ጥግ ጨምሮናል! ክብር የሌለን፣ ሀገር የሌለን፣ ህሊናችንን ጨጓራችን ውስጥ ቀብረን የምንኖር ውርደት የማይሰነፍጠን የሰው ገልቱዎች ሆነናል!
ሀገር ምድርን ካንቀጠቀጡ ጀግኖች የተገኘን ልፍስፍስ ትሎች ሆነናል! የቀደምት አባቶቻችን የሚፈራርስ ኃውልት በውስጣችን ሟሙቶ የፈራረሰውን የጀግንነት መንፈስ በቁማችን ያረዳናል! ፈሪነታችን ልክ የለውም! ወራዳነታችን ተስተካካይ አጥቷል! ፈሪ ማንነታችንን፣ ወራዳ ሰበዕናችንን፣ የባርነት ስነልቦናችንን፣ የለማኝነትና የአልቃሽነት ተፈጥሯችንን አምነን መቀበል አለብን! ታላላቅ በገንዘብ የማይተመን ዋጋ የተከፈለልን ሕዝቦች ሆነን ሳለ፣ ራሳችንን ክብረቢስ ዋጋቢስ ያደረግን የተናቅን ሶልዲዎች የማድረጋችንን ሀቅ ከልባችን አምነን መቀበል አለብን! ዋጋ የሌለውን ነገር በክብር ሥፍራ አታስቀምጠውም! የትም ጠርገህ ትጥለዋለህ! አባቶቻችንን የትም ተጠርገው የሚጣሉ ምናምንቴዎች ያደረግን ትውልዶች ሆነናል! ዋጋቢስ ሆነን ታሪካችንን ዋጋ ቢስ ያደረግን ዋጋቢሶች መሆናችንን አምነን መቀበል አለብን ዛሬውኑ!
ፈሪ ህዝብ የሚከበርለት መብት የለውም! ፈሪ ህዝብ የሚለገሰው ክብር የለውም! ፈሪ ከሰው ልጅ ክብር በታች ራሱን ያወረደ ባሪያ ነው! ለራሱ ክብር የሌለው ሰው ክብረ-ነክ የሆነ ነገር ምን እንደሆነም አይገባውም! ለራሱ ክብር የሌለው የክብርን ትርጉም አያውቅም! ወራዳ ሰው የሚከበርለት አንድም ታሪክ የለውም! ውርደትን የመረጠ ህዝብ የሚከበርለት ጀግና የለውም! ፈሪን ሕዝብ ዱላ ያነሱ ጥቂት መንገኛ ደደቦች በእንብርክክ ያስኬዱታል! ጀግና ያጣ ሕዝብ የማንም ውርጋጥ መጫወቻ ሆኖ ይቀራል!
እያንዳንዳችን ዛሬ ዓይናችንንና ህሊናችንን የጋረደው የውርደትና የፍርሃት መጋረጃ ውስጥ ተሸብበን፣ በታሪክ ፊት እየተንጰረጰርን ሰማዕታትን በከንቱ የለቀስተኞች ጩኸታችን የምንማልድ ፣ ከሰው ክብር ራሳችንን ያሳነስን ፈሪዎች – አንድ ቀን – የክብርን፣ የነፃነትን፣ የሰውን ልጅ መብት፣ የታሪክ ባለቤትነትን፣ የማንነትን፣ የሰውነትን፣ የዜግነትን ክብር ተገልጦልን እስኪገባን፣ እና እስክንጠማው ድረስ – እንዲሁ በደናቁርት እግር ስር እየሰገድን – መኖር ከተባለ – መኖራችንን እንቀጥላለን! አንበሶች ሆነን ሳለ የእንቁራሪቶች መጫወቻ ሆነን እንኖራለን! ዋጋችን ይኸው ነውና ይሄንንም አይንሳን ማለት እንጂ ያልዘሩት ላይበቅል ነገር ይሄን ማማረር ለኛ የተገባ አይደለም! ይሄም የውርደት ህይወታችን ያልጣመው አህያ ረጋግጦ ይወስድብናል! ያንንም ተመስገን ብሎ መቀበል ነው ከወራዳ ሰው የሚጠበቀው! የራሳችንን እውነት አምነን እንጋፈጠው! የወረድንበት የውርደት ቁልቁለት ይህን ያህል ነው! ሀቁ ይኸው ነው!
ወራዳ ህዝብን ተነስ አትለውም! ለመብትህ ቁም አትለውም! የጀግኖችህ አጥንት ይወጋሃል አትለውም! መረገጥና ውርደት እስኪመርረው ድረስ በደንብ መረገጥ አለበት! ይኸው ነው! በፈቃደኝነት ከመጣ ባርነት የበለጠ አስከፊ ባርነት የለም! ከተጣባን ከነቀርሳዎች ሁሉ ከከፋው የባርነት ነቀርሳ አንድዬ ፈጣሪ አጥብቆ ይማረን ብሎ መጸለይም ያባት ነው! እሳተ ነበልባል የሆነ የአባቶቻችን ትውልድ ያፈራው አመድ ነው! እሳት አመድን ወለደ! ምንም ማድረግ አይቻልም! የዚህ አመድ የሆነ ትውልድ ወገን የሆንኩ አመዳም ትውልድ በመሆኔ አፈር እስክለብስ ድረስ ያሳፍረኛል!
የአባቶቻችን የዳዊት፣ የኢዛና፣ የካሌብ፣ የፋሲል፣ የቴዎድሮስ፣ የበላይ፣ የዮሐንስ፣ የምኒልክ፣ የዘርዓይ ድረስ የጀግንነት መንፈስ ሆይ  – ካሸለብክባቸው ተራራዎች፣ ካንቀላፋህባቸው ሸለቆዎች፣ ከሰፈፍክባቸው ሰማያቶች ሁሉ ላይ ተነስ! እና ውረድ ወደ ትውልድህ! ንበር የጀግና መንፈስ! ስረጽ በትውልድህ ላይ! ተነስ የጀግና መንፈስ! ተነስ የኢትዮጵያ መንፈስ! ተነስ ያገሬ ህያው መንፈስ! ተነስ ቀስቅስ የተኛውን ልብ!
ኢትዮጵያ ታበጽዕ እደዊአ ሀበ እግዚአብሔር! 
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!
ከትውልዷ ልብ የነጠቃትን የጀግንነት መንፈስ፣ የክብር መንፈስ፣ የሰውነት መንፈስ – በክብር ይመልስላት ዘንድ!
Filed in: Amharic