>

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ ወያኔን ያንቀጠቀጠ ጀግና፤ እንዴት በወራዶች እጅ ወደቀ! (ሃራ አብዲ)

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ወያኔን ያንቀጠቀጠ ጀግና፤

እንዴት በወራዶች እጅ ወደቀ!    

 •  ዝማሬዎቹ ከዉስጡ ወጥተዉ ሳያበቁ፤ ከነዝማሬዉ ፤ከነ ተስጥኦዉ ከዚህ አለም በመለየቱ በእጅጉ አሳዝኖኛል።

 ሃራ አብዲ


በአርቲስት ሃጫሉ ህልፈተ- ህይወት የተሰማኝ ሀዘን መሪር ነዉ። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራር ምቾት ከነሳኝ ዉሎ ቢያድርም የከፋ እንዳይመጣ ከመመኘት ዉጭ የማደርገዉ አልነበረም።የእድገትና የብልጽግና ምንጭ ዙፋን ላይ መቀመጥ ብቻ አድርገዉ የሚያስቡ ዉሾች እንደዚህ ያለ ወንጀል መፈጸም እንዲችሉ መሬቱ የተደላደለ ስለነበር ግን፤ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዌ ስጋት አልቀረልኝም።  ይህ የግል እምነቴ ቢሆንም እጅግ በርካቶች እንደሚጋሩት ጥርጥር የለኝም። ፤በዚህ ከቀጠለ ገና ብዙ ዋጋ እንከፍላለን። ለመሆኑ፤ ከወያኔ የብረት ክንድና ከነሀስ ጥርሳቸዉ የተረፈዉ ሃጫሉ እንዴት እንደዋዛ ከቤቱ ወጣ ባለበት ግድያ ሊፈጸምበት ቻለ? ወያኔን ያንቀጠቀጠዉ ጀግ ና፤እንዴት በወራዶች እጅ ወደቀ!                                                        

ግድያዉስ ተፈጸመ፤ እንዴት አስከሬኑ ከቡራዩ ተጠልፎ በእስቴዲዮም በሚገኘዉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሊያርፍ ቻለ? እነማን ናቸዉ ከትዉልድ ቦታዉ አምቦ ይልቅ በአዲስ አበባ መካነ-ቀብሩ እንዲፈጸም የፈለጉት እናም አስከሬኑን ጠልፈዉ የወሰዱት?

እንዴት በክብር ታጅቦ የሚሄድን አስከሬን ነጥቀዉ የመኪናቸዉን ፊት አዙረዉ ወደ እስቱዲዮም ሲበሩ መከናወን ሆነላቸዉ? መቼም መንፈስ አይደሉም ስጋ ለብሰዉ እዚያዉ አብረዉ የነበሩ ሰዎች ናቸዉ ይህንን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙት። እንዴት ዞር በሉ የሚላቸዉ ጠፋ?

 «እስከዛሬም ግም እበላለሁ እንደዛሬ የጠነባ አጋጥሞኝ አያዉቅም» አለ ጅቡ ፤ እንደሚባለዉ፤ እስከዛሬም ያገራችን ነገር እንቆቅልሽ ነበር ፤ሆኖም እንደዛሬ ዉስብስብነቱ የለየለት አይመስለኝም። 

ብዙ የሀገራችን ፖለቲካ ተንታኞች እንዳሉት እኔም የዚህን ድንቅ አርቲስት አስገዳዮች ማንነት መገመት እችላለሁ።ማንም ነገሩን ስራዬ ብሎ የተከታተለ ኢትዮጵያዊ መገመት ይችላል።ነፍሰ-በላዋ ህወሀት በሰልፉ የመጀመርያዉን ረድፍ ትይዛለች፤ የኦሮሞን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ለመነጠል የኢትዮጵያን እንጀራ የሚበሉት ዉሾቹ  አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሁለተኛዉን ረድፍ ይይዛሉ።ከዚህ የተረፈዉ ታሪክ ነዉ። «የርቱን በከ ቴሱቲ ነመ ቴችስቲ»

ሓጫሉ በሚሊንየም አዳራሽ አረፋ ያስደፈቃቸዉ ህወሀቶች የያዙበትን ቂም ለመወጣት ቀን ሲጠብቁ ነበር። በወቅቱም ለመግደል ሞክረዉ ወገኖቹ እንዳስጣሉት ይነገራል።ታዲያ እነዚያ ወገኖቹ ዛሬ የመንግስት ስልጣን በያዙበት ወቅት እንዴት ጥላ ከለላ ሳይሆኑት ቀሩ? ነዉ፤ የነሱም እጅ ይኖርበት ይሆን? መቼም የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ያለነገር አልተመረጠም።ሓጫሉ እንዳለዉ ከአድዋ ቅንቅናሞች ይልቅ ኦሮሞ ለአራት ኪሎ ቅርብ መሆኑ ሲታወጅ ወያኔዎች ለክፉ ቀን አበጃጅተዉ ባዘጋጁዋት መቀሌ ከተሙ። ቂማቸዉን ግን የማይረሱ ካንሰር ናቸዉ። ካንሰር ሪሚሺን ዉስጥ ገባ በሽተኛዉ ዳነ ተብሎ በታመነበት ጊዜ መጀመሪያ ያጠቃዉን የሰዉነት ክፍል አልፎ በሌላ የሰዉነት ክፍል ላይ ይከሰታል። እንዲህ እንዲህ እያለ መላዉን ሰዉነት በክሎ በሽተኛዉን ከዚህ ምድር ያሰናብተዋል።ወያኔዎች የኢትዮጵያ ካንሰር ናቸዉ የሚባለዉ እንዲሁ አይደለም። ካንሰር የወያኔን ባህሪ በደንብ ስለሚገልጽ እንጂ። ሁለተኛ ረድፈኞቹ የኦሮሞን ህዝብ እንወክላለን እያሉ መከራቸዉን የሚጠብሱት ዉሾች ናቸዉ። የትኛዉ የኦሮሞ ህዝብ ወክለን እንዳላቸዉ አይታወቅም። የኦሮሞ ህዝብ መልካም ህዝብ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያዊነቱ በቀር የሚያዉቀዉ ነገር የለም። እነዚህ ተምረናል፤ ነጻ ኦሮምያን እንመሰርታለን የሚሉ ከንቱዎች ለራሳቸዉ ረክሰዉ ወጣቱንም አረከሱት። እነ ህዝቅኤል ጋቢሳ፤ ጸጋዬ አራርሳ፤ ጃዋር መሀመድ፣በቀለ ገርባና መሰሎቻቸዉ ወልዳ ያሳደገቻቸዉን ፤አስተምራ መጪዉን ትዉልድ ያስተምሩልኛል ያለቻቸዉን በስልጣን ሀራራ ተይዘዉ የጠቡትን ጡት ሊቆርጡ ገጀራቸዉን መዘዙባት። እነሱ የበሉትን እንጀራ ምነዉ ዉሻ በበላዉ!! ዉሻ ለአሳዳጊዉ ታማኝ ነዉ። ለዚህ ነዉ ዉሻ በበላበት የሚጮኸዉ። ጌታዉ ሲለየዉ  ግን ዉሻ ወዶ -ገብ ይሆንና ጥራጊ የሚጥልለትን ጌታዉ አድርጎ ይቀበላል። እነ ጸጋዬ አራርሳን ዉሾች ስል ወዶ- ገቦቹ ዉሾች ማለቴ ነዉ። የአብይ አስተዳደር ምህረት አድርጎለት ኦነግ ከኤርትራ ሲመለስ ፤በትግራይ ምድር ማእድ ተጥሎለት ወታደሩን ባበላበት ጊዜ ኦነግ ከኢትዮጵያ ህዝብ እንዳልታረቀ፤ ወያኔዎች ላፈሰሱት የኦሮሞ ህዝብ፤ ለገደሉት፤ ላኮላሹት እና አካለ-ስንኩል ላደረጉት የኦሮሞ ወጣት ቁብ እንደሌላቸዉ አስመስክረዋል።በመቀጠልም እነጸጋዬ አራርሳ መቀሌ ድረስ እየበረሩ የኢትዮጵያን ህዝብ በአፓርታይድ ረግጠዉ ሲገዙ ከነበሩ፤ ይልቁንም እንወክለዋለን የሚሉትን የኦሮሞ ህዝብ ሀብቱን ከዘረፉና ልጆቹን ካረዱበት ጋር የፖለቲካ ሽርክና ገቡ። አንዴ በኦሮምኛ፤ሌላ ጊዜ በመማሬ እጸጸታለሁ በሚሉት አማርኛ የፈለጉትን መርዛቸዉን ሲረጩና ህዝብ ከህዝብ ሲያበጣብጡ እንደመሃን ልጅ እንክንክ ተባሉ እንጂ ወቀሳም አልቀረበባቸዉ። አሁን ወደ ነገሩ ምንጭ እየገባን ነዉ።የአብይ መንግስት ይህን አይነቱን ልፍስፍስ አያያዝ የአስተዳደር ዘይቤዉ አድርጎ ለምን ተከተለዉ የሚለዉ የእንቆቅልሹ ሁሉ ቁንጮ ነዉ። ለዚህ ጥያቄና መላምት ካልሆነ በስተቀር መልስ ሊኖረኝ አይችልም። መሆን የነበረበት ብዬ የማስበዉን፤ ከብዙ ወዳጆቼም ጋር የተወያየሁባቸዉን ነገሮች ከሞላ ጎደል ከሰሞኑ እመለስበታለሁ። የሆነዉ ሆኖ፤ የእነዚህ ዉሾች በፈቃዳቸዉ ለወያኔ ማደር ፤ሃጫሉን ሰላም ነስቶት ነበር። ጀግናዉ ሃጫሉ በዚህ ድርጊታቸዉ እንደተጠየፋቸዉ ግልጽ ነበር። ዉርደታቸዉን ሳይደብቅ ነግሮ ስላሸማቀቃቸዉ ፤ቀድሞዉኑ ቂም ከያዙበት ከወያኔዎች ጋር በማበር ሊበቀሉት ፈለጉ። በኦኤም ኤን ጋብዘዉ የጋቱትን መርዝ አስተፉት። ይህ ደሙን ከነሱ ለማራቅና የመርገም ጨርቃቸዉን በንጹህ ደሙ ለማንጻት ይጠቅማቸዋል። 

«ሚኒልክን ስለተሳደበ ነፍጠኞች ገደሉት» ዉሾች!!! ነፍጠኛ ማንን እንደገደለ ሃጫሉን ይገድላል? ያን ሁሉ የአማራ ህዝብ ሲያስገደል ጃዋርን ያልገደለ ነፍጠኛ፤ ለምን ብሎ ሃጫሉን ይገድላል? እነጸጋዬ አራርሳን፤ እነ ህዝቅኤል ጋቢሳን፤ እነ በቀለ ገርባን ያልገደለ ነፍጠኛ ለምን ብሎ ሀጫሉን ይገድላል? የነሱ ትምህርትና ታክቲክ መንደፍ እስከዚህ ድረስ ነዉ። ከንቱዎች። በዚህ ግርግር መሃል የእስክንድር ነጋ መታሰር ደስ አሰኝቶኛል። እሱንም ገድለዉ አማራዉን ለማስነሳት ሊያስቡ ይችላሉ። እስኬ አንገትህን ዝቅ አድርገህ ቅዝምዝማቸዉን እንድታልፍ ሊሆን ይችላል።

በመጨረሻም የሃጫሉ ደም ከወያኔዎችና ጫፍ ረገጥ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እራስ ላይ አይወርድም ብዬ አስባለሁ። እዉነት፤ በኢትዮጵያ እንጥፍጣፊ ዘይት የቀራት የህግ መቅረዝ ካለች ፤መንግስት እነማንን ጠራርጎ አስሮ ፋታ የማይሰጥ ምርመራ ማካሄድ እንዳለበት ሊስቱን ከኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ ዘገባ መቀበል ነዉ።የእዉነቱ መዳረሻ መሆን ባይችል እንኩዋን ምርመራዉን ወደትክክለኛዉ መንገድ መርቶ የገዳዮቹን ማንቁርት ያስይዛል ብዬ እገምታለሁ።

ለዛሬ ሆድ ብሶኝ ጥቂት አጉረመረምክ እንጂ፤ ወጣቱን አርቲስት ፤ ጀግናዉን የመብት ተሙዋጋች ሓጫሉ ሁንዴሳን ለመሰነበት ነበር ብቅ ያልኩት። «ዝማሬዬ በዉስጤ እንዳለ አልሙት« ይላሉ ነጮቹ። ሃጫሉ፤ ዝማሬዎቹ ከዉስጡ ወጥተዉ ሳያበቁ ከነዝማሬዉ ከነ ተስጥኦዉ ከዚህ አለም በመለየቱ በእጅጉ አሳዝኖኛል።

እግዚአብሄር ጠቢብ ነፍሱን በገነት ያኑራት። ለቤተሰቦቹና ለመላዉ አድናቂዎቹም መጽናናትን ይስጣቸዉ።

 

ሃራ አብዲ

haraabdi@gmail.com

Filed in: Amharic