>

የድምፂ ወያኔ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክና የአስራት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተበረበሩ!!! (ዶችቬሌ)

የድምፂ ወያኔ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክና የአስራት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተበረበሩ!!!

ዶችቬሌ 

የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ «በሶሞኑ ወንጀል»ና የጎሳና የኃይማኖት ግጭት በመቀስቀስ ይጠረጠራሉ  ያላቸዉን ሶስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስቱዲዮዎችን መበርበሩን ወይም በፖሊስ ማስበርበሩን አስታወቀ።የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተደራጁ ወንጀሎች ጉዳይ ባለስልጣናት እንዳሉት  ፍተሻና ብርበራ የተደረገባቸዉ የድምፂ ወያኔ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ (OMN) እና የአስራት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የአዲስ አበባ ስቱዱዮዎች ናቸዉ።ባለስልጣናቱ «ሰሞኑን የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት» ካሉት ከድምፃዊ ሐጫሉ ግድያና መዘዙ በፊትም «ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር፣ ሐይማኖትን ከኃይማኖት ጋር በማጋጨት «ሥራ ላይ የተሰማሩ» ሚዲያዎች አሉ ይላሉ።

 

የሶስቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስቱዲዮዎች የተበረበሩትም «ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ» ከአስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ክስ ለመመስረት የሚያስችል መረጃ ለመሰብሰብ ነዉ እንደ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጫ።ባለስልጣናቱ «ድርጊት» ያሉት የሐጫሉ ግድያና መዘዙን ይሁን ወይም ከዚያ በፊት «የተሰማሩበት ሥራ» ያሉት ይሁን-አይሁን በግልፅ አልተናገሩም።ይሁንና በብርበራዉ  «ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላቸዉ» የተባሉ መረጃዎች ማግኘታቸዉን ባለስልጣናቱ አስታዉቀዋል።ከOMN መስራቾች አንዱ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ የጣቢያዉ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ባለፈዉ ማክሰኞ ታስረዋል።የጣቢያዉ የአዲስ አበባ ስቱዲዮም ተዘግቷል።

Filed in: Amharic