በኦሮሚያ ክልል በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!
ያሬድ ሀይለማርያም
በ1994 እ.ኤ.አ ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የመሩት ሁለት ራዲዮን ጣቢያዎች ነበሩ። አንዱ በመንግስት ሥር የነበረው ራዲዮ ሩዋንዳ የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው የእልቂቱ አነሳሺና ቀስቃሽ የነበረው Radio Télévision des Milles Collines (RTLM) ተብሎ የሚጠራው ጣቢያ ነበር። ይህ ጣቢያ በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ስለነበር በአገሪቱ ውስጥ የነበሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን እና የቀኝ አክራርሪ የሆኑትን የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻዎችን (Interhamwe militia) በቀላሉ ወደ ጥላቻ በመንዳት በመምራት እና እልቂት እንዲፈጽሙም በማነሳሳት ትልቅ ሥራ ሰርቷል። ይህ ጣቢያ ከእልቂቱም በፊት ቢያንስ ለአንድ አመት ያህል ጥላቻን ሲሰብክ ቆይቷል።
ዛሬ ደግሞ ተራው የእኛ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለአመታት ጥላቻን ለኦሮሞ ወጣቶች እና ለኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ሲሰብክ የነበረው OMN የተባለው ሚዲያ የወንድማችንን አጫሉን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ተከታታይ የአመጽ እና የእልቂት ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች በክልሉ ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ልክ የሩዋንዳው RTLM እንዳደረገው ሁሉ ጥሪው ክልሉ ውስጥ ላሉ ሥራ አጥ ወጣቶች እና በሽኔ ስም ለሚጠሩት ሚሊሺያዎች ነበር። በዚህም እጅግ ለመስማትና ለማየት የሚሰቀጥጡ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ሰዎች እቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከነቤተሰቦቻቸው በእሳት ጋይተዋል፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በስለት እና በቆንጨራ ተቆራርጠው ተገድለዋል፣ እናት ከህጻን ልጇ ጋር በአንድ ገመድ ታንቃ ተገድላለች፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፣ ብዙዎች ከቤታቸው ሸሽተው በተለያዩ ጊዜያው መጠለያዎች ውስጥ ተደብቀዋል።
አንዳንድ እማኞች በመገናኛ ብዙሃን ምስክርነታቸውን እንደሰጡት እና እኛም ማረጋገጥ እንደቻልነው ለጥቃት የተሰማሩት ኃይሎች በቂ ዝግጅት ያደረጉ፣ የተለያዩ የጥቃት መሳሪያዎችን የያዙ እና የጥቃት ኢላማ የሆኑ ሰዎችን ስም እና አድራሻም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ድርጊቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በቬኦኤ እና አንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም በተወሰኑ ቦታዎች የመንግስቱ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ዝምታን መርጠው መቆየታቸው ነው። በሩዋንዳም የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲፈጸም የሆነው ይሄው ነበር። እነዚህ ኃይሎች በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ቡድኖችን እና ነገሩን በቸልታ ሲያዩ በነበሩ የክልሉ ኃላፊዎች ላይ በቂ ምርመራ ሊካሔድ እና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
OMN አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ቢዘጋም ተመሳሳይ የእልቂት ጥሪዎችን ከአገር ውጭ ባሉ ባልደረቦቹ በኩል ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ አየር ላይ ያዋላቸውን እና በዩቲዩብ የተላለፉ ዝግጅቶቹን ከአየር ላይ እያወረደ እና መረጃዎችን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፤
፩ኛ/ የእነዚህ የእልቂት ጥሪዎች ቅጂዎቻቸው ጣቢያው በመንግስት ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመንግስት እጅ ስለሚገኙ እና የብሮድ ካስቲንግ ኤጀንሲውም የእነዚህ ቅስቀሳዎች ቅጂ እንዳለው ባለሥልጣኑ ስለተናገሩ ጣቢያው መረጃ ለማጥፋት እያደረገ ያለው ጥረት ይሳካል ብዮ አላምንም። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በመንግስት በኩል በቂ ጥበቃ ተደርጎላቸው በክልሉ ውስጥ ለተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ያላቸው አስተዋጽዎ በአግባቡ ሊመረመር ይገባል፤
፪ኛ/ በOMN የተላለፉ የዘር ተኮር ቅስቀሳ ቪዲዮዎች እና ዘገባዎች በእጃችው ላይ የሚገኝ እና ጉዳዩ የሚያሳስባችው ግለሰቦች፤ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና አንዳን አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ያላችሁ ሰዎች በዚህ የኢሜል አድራሻ end.empunity.eth@gmail.com እንድታቀብሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።