>

ከልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ-ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ሊቀ መንበር የተሰጠ መግለጫ 


ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ-ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ሊቀ መንበር  

መግለጫ 

በዘውድ ምክር ቤታችን ሥም የታዋቂውን ዘፋኝ የአቶ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት አስመልክቶ ለቤተሰቦቹ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ እንወዳለን ። አቶ ሀጫሉ በሙዚቃ ስራ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ አስተዋጾ ያበረከተ ፣ ለኦሮሞ ባህል ያለውን ፍቅር ያስመሰከረና የአንድነትን ጥቅምና ዋጋ በተቀጣይነት እንድናሰላስልና እንድንመረምር አድርጎናል ። በአቶ ሀጫሉ አሰቃቂና ግፍ መገደል በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ ለምንኖር ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መራር ሀዘን ሆኖብናል ። ሕይወቱ ባጭሩ በመቀጨቱ ሁላችንም ከልብ አዝነናል።

መላው ዓለም በተለያዩ ማህበራዊ እክል በተወጠረችበት ወቅት ፣ የዓለም የጤና ቀውስ (ወረርሽኝ) ያስከተለው የዓለምን ኢኮኖሚና የብሔሮች ደህንነትን ማናጋት ጋር ተጨማሪ የደፋር ሰው ሕይወት ማጣት ለሀዘን ዳርጎናል ። በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች የጥላቻ ወንጀሎች በሁሉም ማህብረሰቦች ተከስተዋል፣ ገንፍለውም ወጥተዋል ። የጥላቻ ወንጀል ማህብረሰባዊ ቀውስ በመፍጠር ጥቂት ሴረኛና አፍራሽ ሃይሎችን ተጠቃሚ ሲያደርግ የተቀረውን ሕዝብ የሚያተራምስና ብዙሃኑን በፍራቻ ቆፈን የሚማግድ ነው።

ልዩነቶቻችንን የምንፈታበትና ወደ ዕርቅ የምናመራበት ሰዓት አሁን ነው። እያንዳንዳችን ሰክነን የምናስብበትና ወደ ህሊናችን የምንመለስበት ጊዜ ነው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፣ በተሳሳተ ጎዳና የሚሄዱትን ወደ ትክክለኛው መንገድ የምንመልስበትና ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ፣ ሠላምና አንድነቷን ለማስከበር እናትና አባቶቻችን የነበራቸውን በጎ ምኞትና ተስፋ እውን ለማድረግ ለልጆቻችንና ለተተኪው ትውልድ ስንል ሁላችንም በመተባበር ጠንክረን መስራት አለብን።

ታሪክን ቀይሮ መጻፍ ወይም ከተከናወነበት አውድ ውጭ ማቅረብና በጎ ላልሆነ ዓላማና ድርጊት ማዋል አደገኛ አካሄድ ነው ። ሚዛኑን በጠበቀ ሁለንተናዊ የታሪክ ትምህርት ለመማር ወጣቱ ትውልድና ልጆቻችን አልታደሉም ። ቢታደሉ ኖሮ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድና ሕዝባዊ አንድነት አፍሪካን በመምራት ለመላው ዓለም በአርአያነት ያሳዩትን አገራዊ ልዕልናና የአንድነት ጥንካሬ ይረዱ ነበር ። የኢትዮጵያችን ታላቅነት በዘውግ ላይ ተመስርቶ አያውቅም ። የኢትዮጵያ ክብርና ታላቅነት ምን ጊዜም ሲገለጽ የኖረው አገራችን ውስጥ በነበሩት የተለያዩ የአንድ ሉዓላዊ አገር እህትማማችና ወንድማማች ቤተሰብ መንፈስ ፣ እምነትና ባህል ነው።

ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ካኒዛሮ መናፈሻ ዊምበልደን በተባለ አካባቢ በእንግሊዝ ሀገር ዋና ከተማ ሎንደን ላይ የነበረውን የግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴን ሐውልትና በኢትዮጵያ በሐረር ከተማ የነበረውን የግርማዊነታቸውን አባት የልዑል ራስ መኰንንን ሐውልት የማፍረስ ተግባርና ወንጀለኛ ድርጊት እጅግ የሚያሳዝን እኩይት ተግባር ነው ። የአገራችንን ሠላምና አንድነት በተቀጣይነት እንዲጠበቅ ልዑል ራስ መኰንንና ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያና በሕዝባችን መፃኢ ዕድል የነበራቸው ሥጋት ያገራችን የውስጥ አፍራሽ ኃይሎች እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ባደረሱት የሀገር ክህደት ወንጀልና ጥቃቶች ሁሉ እውነትና ተገቢ እንደነበር ያረጋግጣል።

በሀገራችንና በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በገዛ ራሳችንና በማንነታችን ላይ ያነጣጠረ ቅጥ ያጣ የዘረኝነት ጥላቻ እንዳለ ፣ በንፁሀን ዜጎች በግፍ መገደልና እንዲሁም የተስፋ፣ የብልጽግናና የአንድነት ምልክት በሆኑት ሐውልቶቻችን በሚደረገው የማፍረስ ተግባር አዝነናል ። ምን ነው? የኦሮሞ ፈርጥ መሪዎቻችንን እነ ታደሰ ብሩን ፣ ጃጋማ ኬሎን ፣ ዋቅጂራ ሰርዳን ፣ ዳዊት አብዲን ፣ ሜዤር ቃዲዳ ጉረምሳዬ ከዓፄዎቻችን ጎን የቆሙትና የተካፈሉት ሁሉ እንዴት ይረሳል?

የኦሮሞ አክራሪ ተገንጣዮች ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የአቶ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስት ለማደናቀፍና እየተጓዘ ካለበት ሠላማዊ መንገድ ለማስወጣት ሆን ብለው ያደረጉት ሸፍጥ እንደሆነ ያስታውቃል።

የሐውልቶቹ የማፍረስ ወንጀል ጭፍን ጥላቻንና አንድ በሆነችው አገራችን ውስጥ ብዝሀነትና እኩል የዜግነት መብት የተቀረው ኢትዮጵያዊ  ሕዝባችን እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። ሕዝብን ከፋፍሎ፣ የአንድን ጎጥ የበላይነት እኩይ ዓላማ ተፈጻሚ በማድረግ ለብዙ ሺ ዘመናት የቆየውን ማህበራዊ ትስስርና ስሪታችንን ለማፍረስ ፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ፣ አፍራሽ ሃይሎች ካለማቋረጥ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ ።

በነጻ የመናገር መብቱ ሊከበርለት ይገባው የነበረው አቶ ሀጫሉ ሁንዴሳ በመገደሉ ምክንያት ተጨማሪና መጠነ-ሰፊ ብጥብጥና የጅምላ ግድያ በማካሄድ ከመቶ በላይ የንፁሀን ደም ፈሷል። የአቶ ሀጫሉን ግድያ ምክንያት በማድረግ መገንጠልንና አክራሪ ብሔርተኝነትን ያራመዱ ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ምልክቶች በማፍረስና በማጥቃት አቶ ሀጫሉን አላከበሩትም ፤ ይልቁንስ፣ በስሙ ጥላቻን በማቀንቀን ንፁሃን ዜጎችን በግፍ በመግደል ስብዕናውንና ታሪኩንም አጉድፈውታል ።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በመጠበቅ ፣ በአድዋና በማይጨው ዘመቻ አገራችንን ከውጭ ወራሪ ሃይሎች በኢትዮጵያዊ ጀግንነት በመከላከል እንደነ ራስ አበበ አረጋይ ፣ የመከላክያ ሚኒስትር ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ፣ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የክቡር ዘበኛ መሪ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ እንዲሁም ላገራችን አንድነት በጽናት የቆሙትን በርካታ ኦሮሞ አርበኞችና ወታደሮች ዘወትር ልናስባቸውና ልናስታውሳቸው ይገባል። የአገራችንን ክብርና ሉዓላዊነት እንጠብቅ ። በውጭ አገር መንግስታት ተልዕኮና ድጎማ ሠላማችንን ለማደፍረስና አንድነታችንን ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ ጎሰኛ ተገንጣዮች የኦሮሞ እድገት አደናቃፊ ጠላቶች እንጂ የታላቋ ኦሮሞ ፈርጥና አቀንቃኝ መሪዎች አይደሉም ።

የታሪክ አዋቂዎች ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ እና ራስ መኰንን እንዲሁም ሌሎች መሪዎች አንድነት ፈላጊ ፣ ሕዝብ አሰባሳቢና አስታራቂ እንደነበሩ ያውቃሉ ። ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያችን ጎሠኝነትና የጠቅላይ ግዛቶች ልዩ ጥቅም እንዳይኖር ተግተው ይሰሩ እንደነበር በማወቅ ነው አክራሪዎች ሐውልቶቹን ያፈረሱት ። ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴና ራስ መኮንን ኦሮሞችን እንዲሁም ሌሎችን ጎሣዎች ከፍ በማድረግ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግንባታና የጋራ ራዕይ ተሳትፎ እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ የሚታወቁ እንደነበሩ ሕዝባችን ሊያውቅ ይገባል። ኦሮሞን ወደ ፖሊቲካና ማህብረሰባችን ልብ ውስጥ ስለማስገባታቸው እኔው እራሴ ሕያው ምስክር ነኝ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና እንደዚሁም ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያንም ምስክር ናቸው ። ራስ መኰንንና ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ያላቸውን ትውፊትና ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ህልም ለማጨናገፍ መሞከር የሥብዕና ግዝፈትና ገናናነታቸውን ሊቀብረው አይችልም ። ትውፊትና ገድላቸው ዘላለማዊ ነው ።

አባቶቻችን በሕይወት ሳሉ አጥፍተዋል ብለን ለምናስባቸው ጥፋቶች ሁሉ ይቅር መባባል አለብን ። በጋራ እንዳንቆም የሚያግዱንን ልዩነቶቻችንን ሁሉ ማስወገድ አለብን ፡ አለበለዝያ የኛ ትውልድ ጥፋት ለልጆቻችን ይተርፋልና ። ዓለም ተቀይራለች በራስ መኰንንና ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ እንደነበረው ዘመን አይደለም ያለነው ። በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን መሠረታዊ የሕልውናና የአኗኗር ዘይቤአችንን የሚቀይሩ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙናል ። ዕውቀትና ስልጣኔአችንን የሚያዋርዱ ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ አለብን ። በማንነቱና በባህላዊ ውርሱ የሚኮራ አንድ ውህድ ቤተሰብ መገንባት አለብን ። እኛ እንደ አንድ ኩሩ ቤተሰባዊ ሕዝብ ሆነን የመኖር ችሎታችንን ለማሳደግ አቅማችን ብቁ ነን ።

የአቶ ሀጫሉ ሁዴሳ ግድያ ግልጽነትና ፍትሐዊነት ባለው ህጋዊ አሰራር መፈታት አለበት ። ገዳዮቹ በግልጽ ችሎትና በሕዝብ ፊት መዳኘት ይገባቸዋል ። የአገር አረጋዊያኖች ፣ እናቶች ፣ አባቶች ፣ የሀገር ተረካቢ ወጣቶች በአጠቃላይ መላው ኢትዮጵያዊያን የምንማጸናችሁ እጃችንን ለሠላም ፣ ለፍቅርና ለእርቅ እንድንዘረጋ ነው ። አብረን ለለመለመ ተስፋ ፣ ለብልጽግና ፣ ለአንድነትና ለክብራችን ወደፊት እንራመድ ።

ባገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለን እኢትዮጵያውያን ፣ በአቶ ሀጫሉ ድንገተኛ ህልፈት ፣ ህይወታቸውን በጅምላ ግድያ ላጡ በርካታ ወገኖቻችን ፣ ለወደመው ንብረት ፣ ለተፈጠረው ቀውስና የሠላም መደፍረስ ፣ ለሕዝባችን ጉሥቁልናና ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ሃዘን ላይ ነን ። የወደፊቱ ተስፋችን አገራችንን በአንድነት እንድንገነባና አኩሪ ታሪክና ባህሎቻችን ተገቢ ክብር እንዲሰጣቸው ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ፣ ለዕርቅና ለምሕረት በአንድ ላይ እንቁም ። ለልጆቻችን ጽኑ የተስፋ፣ የክብርና የብልጽግና መሰረት እንጣልላቸው ። ኢትዮጵያ አገራችንንና ሕዝባችንን እንታደግ።

 

ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም

“እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ”።

Filed in: Amharic