>

ከዓለም-አቀፍ የጉራጌ ማህበር (ዓጉማ) የተሰጠ መግለጫ

ከዓለም-አቀፍ የጉራጌ ማህበር (ዓጉማ) የተሰጠ መግለጫ


* በኦሮሚያ ክልል በጉራጌ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት ባደረገ የተቃጣው ጥቃት በተመለከተ 
*
በመጀመሪያ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የኦሮምኛ ድምፃዊ በነበረው በወንድማችን ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸመው የግፍ ግድያ  እና ይህንን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ዘርን መሰረት ያደረገ ወንጀል ህይወታቸው ላጡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነፍስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመዶቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው፣ ለሚያውቋቸውና ለሚያውቁት፣ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰማን የልብ ስብራት እየገለጽን መጽናናትን ሚ፡ አርቲስት ሀጫሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የኦሮሞ ወጣቶችን በግንባር የሚጠቀስቀደምትነት ሲያነቃቁ ከነበሩት ጥቂት ሰዎች  አንዱ ሰው ነበር። አርቲስቱ የለውጥ አቀንቃኝ ባይሆን እንኳን ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልኩ የተፈጸመበት ግድያ በምንም መልኩና መመዘኛ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ስለዚህም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ በተከታታይ የደረሰበትን ለህዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባል።
እንደ ኦሮሞ ህዝብና እንደ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአርቲስት ሀጫሉ ሞት ሀዘንን በቅጡ ሳንጀምር በክልሉ በሕገ ወጥና በተራቀቀ መልኩ ከነሱ ዘር ውጪ ያለውን ማሕበረሰብ ለማጥፋት  በወጠኑና መላውን ኦሮሞ በማወይክሉ ጥቂት ቡድኖች አመራርነት  በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በኦሮሚያ ክልል ቡል ቡላ፣ ዝዋይ፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ሀረር፣ በአርሲ/ነገሌ፣ ባሌ ጎባ፣ ሻሸመኔና ሌሎችም አካባቢዎች የጉራጌ ተወላጆችና ሌሎች ብሔረሰቦችም ላይ የተፈጸመው  ዘርን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት ታሪክ ይቅር የማይለው በደልና ወንጀል በመሆኑ በወገኖቻችን ላይ የተቃጣው ጥቃት በጽኑ እናወግዛለን።
ሁሉም እንደሚያውቀው የጉራጌ ህዝብ በሄደበት እና በተጓዘበት እንዲሁም ኑሮው መሰረት ባደረገባቸው ስፍራዎች ሁሉ አካባቢውን መስሎ የሚኖር፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋ፣ ትውፊት፣ የሽምግልና ስርዓትና ሌሎችም ተመሳሳይ ባህላዊ ሁነቶች የሚያከብር፤ በአካባቢው ለፍቶ ያፈራው ሃብት ወደየትም ሳያሸሽ አካባቢውን የሚያለማ፣ በሚኖርበት አካባቢ ሁሉ የልማት አስተዋጽኦ ሲጠየቅ ቀድሞ የሚደርስ፤ ለሌሎችም ስራ የሚፈጥር፤ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተጋብቶ፣ በስጋ ተሳስሮና ተዛምዶ የሚኖር ፍጹም ሰላማዊ የሆነ ህዝብ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። የጉራጌ ህዝብ የወጣበት የጉራጌ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ጋር ረጅም ድንበር የሚዋሰን በመሆኑና ከዞኑ ውጭ የሚኖረው የጉራጌ ህዝብ አብዛኛው በኦሮሚያ ክልል የሚኖር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  የኦሮሞ ህዝብ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ በበለጠ የጉራጌ ህዝብን በደንብ ያውቀዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
አሁን በጉራጌ ህዝብ ላይ የተቃጣው ዘርን መሰረት ያደረገ ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ ድርጊት ለረጅም ዘመናት በጉርብትናም ሆነ አብሮ በመኖር የምናውቀው የኦሮሞ ህዝብ የማይወክል መሆኑን እንረዳለን። እኛ የኦሮሞ ህዝብ የምናውቀው በገዳ ስርዓቱ፣ በአቃፊነቱ፣ አብሮ ተቻችሎ፣ ተስማምቶና ተደጋግፎ የሚኖር ሰው ወዳድ፣ አክባሪና በደል የሚጠየፍ መሆኑን ነው። ሆኖም ድርጊቱ ማህበሰቡን በማይወክሉ ነገር ግን ከማህበረሰቡ በወጡ ሰዎች የተፈጸመ በመሆኑ እጅጉን አሳዝኖናል፣ ውስጣችን አቁስሎናል፣ ልባችን አሻክሮታል። የኦሮሞ ህዝብም ከጉያው በወጡ ጥቂት ወንጀለኞች በተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት እኛ የተሰማን ስሜት ይሰማዋል የሚል ሙሉ እምነት አለን።
ስለዚህም ለመላው የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሞ አባገዳዎች፣ለጉራጌ ማህበረሰብ፣ በየደረጃው ላለው የመንግስት አካልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከተሉትን ጥሪዎች እናስተላልፋለን፡፡
1.  መላው የኦሮሞ ማህበረሰብ ይህንን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ በአደባባይ እንዲያወግዝ፤ የኦሮሞ ሽማግሌዎችና አባገዳዎችም ሀዘናቸውን በይፋ እንዲገልጹ እና መንግስት አጥፊዎችን በመለየት አሁን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲያሳስቡ፤ እንዲሁም መሠል ድርጊቶች ለወደፊቱ እንዳይፈጸሙ እንዲሰሩ
2.   ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖቻችንና ቤተሰባቸው እንዲሁም የጉራጌ ማሕበረሰብ አባላትና ሽማግሌዎች ጉዳዩን በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲመለከቱትና መንግስት አጥፊዎችን በመለየት አሁን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲያሳስቡ፤
3.  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህይወታቸው ያጡ የጉራጌ ተወላጆች ቤተሰቦቻቸው በሚፈቅዱት ቦታ ስርዓት በጠበቀ መልኩ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው እንዲፈጸም እንዲያደርግ፤ እንዲሁም አካላቸው ያጡ፣ ድብደባ የተፈጸመባቸውና እና የስነ-ልቦና ችግር የደረሰባቸው የጉራጌ ተወላጆች አስፈላጊ ህክምና እንዲያገኙ  እንዲያደርግ፤
4.መንግስት ንብረታቸው የወደመባቸው፣ የተሰረቁና የመኖሪያና የንግድ ስፍራቸው የተቃጠለባቸው የጉራጌ ተወላጆች ተመጣጣኝ ካሳ በመክፈል ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ፤ እንዲሁም ህይወታቸው በግፍ ለተቀጠፉ የጉራጌ ተወላጆች ለቤተሰቦቻቸው የህይወት ካሳ እንዲከፈል
5.መንግስት ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ድርጊቶች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የነበረና ምንም ዓይነት አስተማሪ አርምጃ ያልተወሰደ መሆኑን መነሻ በማድረግ እና  የቀድሞ የወንጀል ፋይሎችንም በማደራጀት፤ ኢትዮጵያውያን የዘር ሃረጋቸውን በመምዘዝና ዘራቸውን ምክንያት በማድረግ ጥቃት የፈጸሙባቸው ሰዎች፣ ቡድኖችና አካላት በመለየት ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በአፋጣኝ ተመጣጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንዲያደርግ እና በየጊዜውም ውጤቱን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያሳውቅ፤
6. የጉራጌ ተወላጆች በነፃነት ያለፍርሃት የመኖር፣ በሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና የመስራት እንዲሁም ሃብት የማፍራት ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። ሆኖም እነዚህ መብቶች በሚያሳፍር ሁኔታ እየተጣሱ ብቻ ሳይሆን ወገኖቻችን ወደር በሌለው ጥቃት በጉራጌነታቸው ብቻ ተጠልተው በህይወታቸውና በቤተሰባቸው ህይወት በንብረታቸውም ጭምር ዋጋ እንዲከፍሉና እንዲባረሩ እየተደረገ ስለሆነ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ዳግም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም እንዲሰራ
7. ይህ ዘግናኝ፤ አስነዋሪና ኢሰብአዊ ወንጀል ለወደፊቱ የኦሮሞ ሕዝብ የታሪክ መገለጫ (ጥቁር ነጥብ) እንዳይሆን መላው የኦሮሞ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሽማግሌዎችና የመንግስት አመራሮች በሚያደርጉት ጥረት የጉራጌ ሕዝብና ማሕበራችን ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን እያረጋገጥን፤ አሁንም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሆነው ይህንን ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ ጥቂት የኦሮሞ ወንጀለኞችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡
8. በመጨረሻም እኛም ባንድ በኩል ከፍ ብሎ የጠየቅናቸው ጉዳዮች ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ተቀናጅተን የምንሰራ መሆኑን እየገለጽን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ እንዲፈቀድ ሠላማዊ በሆነ መልኩ አጠናክረን ጥሪ ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም
Filed in: Amharic