>
5:13 pm - Monday April 19, 3576

ሕወሀትና ኦነግ ሸኔ....!!!  (ነአምን ዘለቀ)

ሕወሀትና ኦነግ ሸኔ….!!! 

ነአምን ዘለቀ

* ዛሬ ስልጣን ላይ ከሚገኘው መንግስት ጋር ያለንን  የየግላችንን ብሶት  በዚህ ወይም  በዚያ ጉዳይ ልዩነቶች፣ የርዕዮተ አለም፣ የፓለቲካ ፕሮግራም ሌሎችም ልዩነቶች ወደ ጎን አድርገን  ሀገር እንደ አገር እንድትቀጥል በጋራ መቆም ያለብን የተለየ  ወቅት ላይ ደርሰናል…!
በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሰላም፣ በመረጋጋት፣ በህግ የበላይነት ዙሪያ ከመንግስት ጎን መቆም፣ ከዳር እሰከ ዳር በጋራ  መንቀሳቀስ  የግድ የሚልበት ወቅት አሁን ነው።የፋሽስታዊው የህወሃትና በታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱ የኦሮሞ ጽንፈኞች ኢትዮጵያን የማፍረስና ሕዝብ ለሕዝብ ማጫረስ እጅግ አደገኛ ሴራ ለመመከትና  ለማምከን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመንግስት ጎን መቆም የግድ የሚልበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ለሃገራችንና ለህዝባችን በጋራ እንቀሳቀስ !
የፋስሽታዊው  የሕወሃት የስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ  ባወጣው መግለጫ የ”አራት ኪሎ ኣሃዳዊ አምባገነናዊ ቡድን” ብሎ በሰየመው የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግልጽ ጦርነት አውጆአል። የመግለጫው ኢላማ የዶ/ር  አብይ አህመድ መንግሥት ቢመስልም ዋነኛ ኢላማዎቹ  ግን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ ነው:: ግቡም ኢትዮጵያን የማተራመስ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱን ብሄሮች የአማራንና ሕዝቦች  ወደ ግጭትና ጦርነት ለመንዳት ያነጣጠረ ነው።
ከጅምሩም አገራችን ዛሬ በምትገኝበት ዘርና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ቅራኒዎች ውስጥ እንድትዘፈቅ፣ በህዝቦች መካከል እርስ በእርስ አለመተማመን እንዲሰፍን ዋናው ተጠያቂ ህወሃት መሆኑ ግልጽ ነው። የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ትብብር ሲጠናከር “እሳትና ጭድ” የሆኑ እንዴት አብረው ሆኑ? ብሎ ለ27 አመታት ያሰፈነው የከረፋ ስርአት ሲንገዳገድበት ብርክ ይዞት፣ በእውር ድንበር እንዳልለፈለፈ፣ ዛሬ የተሳካለት መስሎት፣ ጥቂት ቅጥረኛ የኦሮሞ ፅንፈኞችን ከጎኑ ማሰለፍ በመቻሉ የልብ ልብ አግኝቶአል።
የኢትዮጵያን ሀብትና የሕዝብ ንብረት በቢልዮኖች ሲዘርፍ የቆየው ይህ የክፋት፣የሴራ፣ የዘረኝነት፣ ክምችት የሆነ ሃይልና ድኩማን መሪዎቹ ትላንትን የረሳን መስሎአቸው የሕዝብን የማመዛዘን ችሎታም ሆነ በአገርና በሕዝብ ላይ ያደረጉትን ሁሉ ወንጀሎች አዙሮ የማስታወስ ብቃት ከቁብም ባለመቁጠር  የህወሃት መሪዎች በየሚዲያው እየቀረቡ ሲያፌዙና ሲደነፉ ለበርካታ ወራት በግርምት ስንመለከታቸው ቆየን። ዛሬ እነዚህ ዘረኞችና  የእብሪት መሪዎች የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብቶችና የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ ሆኖ ለመቅረብ በኦሮሚያ ልዩ ልዩ ቦታዎች በግፍ ስለተገደሉ ዜጎች፣ ስለ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ፣ አይን ቀቅሎ በበላ  ወሮበላነቱ ዋና ጠበቃ  ሆኖው ዛሬ  ቀርበዋል።
ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም በሀገሪቱ የሚገኙ ችግሮችን ለማባባስና በማራገብ “እኔ በበላይነት ያልገዛኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ” በሚል በሀገር ውስጥም በውጭም ከሚገኙ ከኦሮሞ  ጽንፈኞች ጋር በጋራ እንደቆመ በዚሁ መግለጫው የለየለት ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊነቱን በድጋሚ አረጋግጦልናል። የ27 አመቱ የዘረፋ፣ የከረፋ ዘረኝነትና የጥቂት የሕወሃት ትግራይ ካድሬዎች  ሁለንተናዊ የበላይነት በቂ አይደሉም’። ማእከላዊን መንግስት ዳግም ተቆጣጥሮ ያንኑ የግፍና የዘረፋ ስርአቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ለማስቀጠል በቀቢጸ ተስፋ በሽታ ያታመመ፣ የታወረ ድርጅት መሆኑን ይሄው መግለኛው ያረጋግጣል።  በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ አይን ያወጣ መንግስታዊ አፈናና  ዘረፋ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብትና ንብረት በመጋጥ አጥንት አስቀርቶ፣ በለውጡ ማግስት የዘረፈውን አግበስብሶ  መቀሌ እንዲመሽግ የተገደደው ይህ የጥፋት ቡድን፣ ሀገራችን ዛሬ ለምትገኝበት ከፍተኛ አደጋ ዋነኛ ተጠያቂ እንዳልነበረና እንዳልሆነ ይመስል፣ ዳግም ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ቀውስ ለመውሰድ በዚሁ  መግለጫው በሀገር ውስጥም በውጭ ሃገርም ለሚገኙ የጽንፈኛ የጥላቻ ሃይሎች ጥሪ አስተላልፎአል።
የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች
ኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት ፣ የህግ የበላይነት ከሌሉ የእያንዳንዳችን፣  የሁላችንም፣ የምንወዳቸው የቤተሰቦቻችን፣ የዘመድ፣ አዝማዶች፣ ወገኖችና፣ ባጠቃላይም ህዝባችን ደህንነት፣ ሰላም፣ የመኖር መሰረታዊ ህልውና  ሊጠበቁ  ፣ ሊረጋገጡ አይችሉም።  የህወሃትና ሰፊውና ታላቁን የእሮሞ ሕዝብ ፈጽሞ የማይወክሉ የኦሮሞ የጽንፍና የጥላቻ ሃይሎች የጀመሩት የጥፋት ጎዳና  ወደ አልተጠበቀ እጅግ ሀገር አውዳሚ ሂደት ሊሸጋገር ይችላል። ለዚህ ለሀገር አንድነት፣ ለሕዝብ አብሮነትና ሰላም እጅግ አደገኛ የሆነ ሂደት፣ ሕዝብ ለሕዝብ ለማጋጨት የሚተጉ ሃይሎች  በውጭ የሚገኙ ፋሽስታዊ የኦሮሞ ጽንፈኞች፣ እንዲሁም ያጣውን ስልጣን ዳግም ለመፈናጠጥ ካልቻለ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሙሉ አቅሙ 24 ሰዓት አየሰራ የሚገኘው የአሸባሪው የህወሃት ልሳን የሆነውና በውጭ የሚገኘው  የትግራይ ሚዲያ  ሃውስ  በጋራ የተቀናጀተው ነው ። የፋሽስታዊው አመለካከት ያላቸው እነዚህ የኦሮሞ  ethno-fascists እንዲሁም የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ወደ ሀገር ቤት የሚያስተላልፉት  መርዘኛ፡ ሃሰተኛ ቅስቀሳዎችና ትርክቶች የብሔር ለብሄር ፣ የዘር ፍጅት ከማድረሳቸው በፊት በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነው የተደራጀ፣ የተቀናጀ፣ የተናበበ ስራ መስራት ይገባል።  ሁሉም ባለው መሰለፍ ይገባል፣ የመጣውን ኣደጋ ለመከላከል እንደ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በጋራ መቆም አለብን።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች ባለሙያዎች ሁሉ  በውጭ የሚደረጉ የጥላቻ ቅስቀሳዎች በህግ እንዲታይና የህግ መስሪያዎችን (Legal instruments) መፈተሽና መጠቀም   በተደራጀ መልክ መደረግ እለበት። የተቀነባበረ ፣ የተደራጀ ስራ መስራት፣ በኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲሁም በመላው ሕዝባችን ላይ የተጋረጠውን  ሕዝብን ለሕዝብ አጫራሽ፣ ሀገርንም ሊያፈርስ የሚችል ትልቅ አደጋ ለመከላከል በጋራ መንቀሳቀስ ፣ መናበብ ፣ በህግም ፊት እንዲጠየቁ  በቅንጅት ከዳር እሰከዳር መንቀሳቀስ የሚገባው ጊዜው አሁን ነው። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በእሽንያ ለመንግስታት፣ ለሕዝብ ተወካዮች/ፓርላማ አባላት፣ ለአለም አቀፍ ሚዲያዎች የእነዚህ ሃይሎች የጥላቻ፣ ለሀገር ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ  ስላምና መረጋጋት የሚያመጡትን ከፍተኛ አደጋ ቀርቦ ማስረዳት፣  ማስጨበጥ እንቅስቃሴዎችን በየሀገሩ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ተደራጅታችሁ በመረጃና በማስረጃ ማሳየት መደረግ ካለባቸው እርምጃዎች ውስጥ ዋነኛዎቹ ናቸው።  የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን በየሀገሩና በየአካባቢው ለማጠናከር ሁሉም በአለው መሰለፍ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ የእንቅስቃሴያችን አካል ነው።
ዛሬ ስልጣን ላይ ከሚገኘው መንግስት ጋር ያለንን  የየግላችንን ብሶት  በዚህ ወይም  በዚያ ጉዳይ ልዩነቶች፣ የርዕዮተ አለም፣ የፓለቲካ ፕሮግራም ሌሎችም ልዩነቶች ወደ ጎን አድርገን  ሀገር እንደ አገር እንድትቀጥል በጋራ መቆም ያለብን የተለየ  ወቅት ላይ ደርሰናል። ከመንግስት ጋር በጋራ በመቆም አስፈላጊና ወሳኝ የሚሆኑት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው ፦
1ኛ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ህልውና እንዲረጋገጥ 2ኛ  ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍኑ
3ኛ፣ የደረፈረሰው የሕዝባችንን ደህንነት መንግስት በአግባቡ እንዲያረጋግጥ፣
4ኛ በሀገራችን  የህግ የበላይነት መንግስት  እንዲረጋገጥ፣
5ኛ  በሕወሃትና  ኢትዮጵያን ለማፈራረስ “በፌደራሊዝም” ስም  የተባበሩ የጽንፍና የአፍራሽ ሃይሎች ሴራና አውዳሚ ሂደት ለመመከት በጋራ ከመቆም ውጭ ምንም ሌላ አማራጭ የሌላቸው በመሆናቸው ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር  የዶ/ር  አብይ አህመድ መንግስት የሃጫሉ ሁንዴሳን  ግድያ ተከትሎ በእስር ያስቀመጣቸውን ዜጎች አለም አቀፍ የታሳሪዎች መብት ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ የፍርድ አያያዛቸውንም ሕወሃት በዘመኑ ኢትዮጵያውያንን ካስመረረበትና  ሃገራችንን ስሟን በክፉ ካስነሳበት በፍትህ ላይ የማላገጥ አሰራር በፍጹም የራቀ፣  በግልጽነት፣ በትክክለኛ የፍርድ ሂደት፣ በፀዳ መረጃዎች እና ማስረጃዎች እውነተኝነታቸው መቼም ቢሆን ጥርጣሬ በማይገባበት መሆን ይገባዋል። ሂደቱ  የፍትህ አካላትን ነፃነት እንዲያሳይ መደረግ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ የሰላም እና የዴሞክራሲ ሃገር የምትሆነው ሕዝብም በፍትህ ስርአቱ ላይ አመኔታ የሚኖረው እንደ ወያኔ ዘመን ፍትህን ማላገጫ በማድረግ ሳይሆን ሕዝብ የሚደግፈው ግልጽ፣ ፍትሃዊና ርትአዊ ሂደትን በመከተልና  በማሳየት ነው።
በአለፉት ሁለት ተኩል አመታት ለውጡ ከመጣ በኋላ በህገራችን ኢትዮጵያ ስርአተ መንግስት ላይ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት በፍጽም ባልጠበቀው ሁኔታና ፍጥነት አጥቶ መቀሌ ለመመሸግና ማድባት የተገደደው የህወሃት የወንጀለኖች ቡድን ፋታ አግኝቶ እስካሁን ደርሶአል። ከዚህ  በኋላ ከሕዝብ የዘረፈውን ሃብትና ንበረት ይዞ አገር ለማተራመስ፣ ሰላም ለማደፍረስና ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት፣ የብሔሮች ግጭት ለመቆስቆስ ከሁለት አመት ተኩል በላይ መቀሌ ተቀምጦ እንዲያስብ፣ እንዲያቅድና ፣ የጥፋት እቅዶቹንም ተግባራዊ እንዲያደርግ እድል ሊሰጠው ፈጽሞ አይገባም። በቢልዮኖች የሚቆጠር ዶላርና ብር በዘረፋ ያካበተው ይሄው የህወሃት ቡድን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ፣ የተሰናበቱ፣ የተባረሩ፣ ጡረታ የወጡ የመረጃና  የደህንነት ፣ የወታደራዊ ልምዶችና ተሞክሮ ያላቸው፣ ዛሬም ሊገድሉለት ፣ ሊሞቱለትም የተዘጋጁ “በደርግ ጊዜ እንኳን ይህን ያህል አልተበደልንም አልተዋረድንም” በሚሉ ጥልቅ ምሬቶችና ቁጭቶች የሚበግኑ ታማኞችን አቅፎ፣ መረጃ የሚያቀብሉት  አባላት በመላው ሀገሪቱ አቅፎ  የያዘ ድርጅት ፣ በጥላቻ፣ በጥልቅ ብስጭት፣ እንዲሁም ከጅምሩ በተጠናወተው የዝቅተኝነት ስሜት የታመሙ መሪዎች  አርፎው ይቀመጣሉ፣ ተኝተው ያድራሉ  ወይንም በውይይትና በድርድር የሂደቱ አካል ይሆናሉ ብሎ መገመት ስህተት ያለበትና ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብን መሰረት ያላደረገ አመለካከት መሆኑ ውጤቱን ምን እንደሆነ በበቂ አይተናል።  የሕወሃት መሪዎች የራሳችን ሀገር እንመሰርታለን የሚለውም  ቅዠትና  እኩይ ፍላጎታቸው ሌላው መገለጫ ነው። ይህ ግን ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው ትላልቆቹ ብሄሮች ሲናከሱ፣ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሲገቡ፣ የህወሃት ትግራይ ትግሬኝ ሀገር መንግስትነት ለማረጋገጥ ይቻላል።  እኛም  ሀገር እንመሰርታለን የሚለው የህወሃቶች  የክፋት መጨረሻ እቅድ  ኢትዮጵያን የማተራመስ አብይ ስትሪቴጂ አካል መሆኑን ብዙ ፍንጮች አይተናል።
የሕዝባችንን ደህንነት፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ሰላምና መረጋጋት፣ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ  የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ትልቅ ትኩረት ማድረግ የሚገባው እርምጃ ነው።  የክፋትና የጥፋት ህወሃትና የመሪዎቹን ንብረቶች፣ በሀገር ውስጥም በውጭም የተከማቹና በሕዝብ ላይ የተዘረፉ ሃብቶች፣  ልዩ ልዩ አቅሞች የሚሰጡትን የንግድ ድርጅቶች፣ በአዲስ አበባና በልዩ ልዩ ከተሞች የሚገኙ የገቢ ምንጮች ለማምከን  በተጠና መልኩ  ጠንካራና ውጤታማ እንቅስቃሴዎች መደረግ የነበረበት ዛሬ ሳይሆን ትላንት ነበር። ሁሉንም መንግስታዊ የማድረግ አቅሞች በመጠቀም በማንኛውም መንገዶች የወንጀለኛውን ቡድን የአቅም ምንጮች ሁሉ ማዳከም፡ ብሎም ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወርድ  ተጽዕኖዎችን፣ ግፊቶችን በማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ ይገባል። ሰይጣናዊ ተግባሩን በተደጋጋሚ ሰኔዎች እውን ለማድረግ ግንባሩን በማያጥፈው መቀሌ በመሸገው በዚህ የክፋት፣ የሴራና፣ የጥላቻ ክምችት ቡድን ላይ ወሳኝና ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ወቅቱ አሁን ነው።
ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለውን  የለውጥ ሂደት ወደ ስኬት ለማድረስ በትዕግስት እየጠበቁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አለምን ያስጨነቀ የኮሮና ቫይረስ ስጋትን እየተከላከሉ ባለንበት በዚህ ወቅት፣ የጭፍን  ጽንፈኛና ህልመኛ ስብስቦችን  የቀቢጸ ተስፋቸውን ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ለማሳካት ሀገራችንን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት፣ ሁሉንም አውዳሚ የምድር ሲኦልና የዘር ፍጅት እንዲገፉ ፈጽሞ መፍቀድ፣ ቆመን የምናይበት ጊዜ አክትሟል። ኢትዮጵያውያንም በሃገራችን ላይ ያንዣበበውን  ከባድ አደጋ ተገንዝበን ይህን ለመመከት ፣ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሰላም፣ በመረጋጋት፣ በህግ የበላይነት ዙሪያ ከመንግስት ጎን መቆም፣ ክዳር እሰክ ዳር በጋራ  መንቀሳቀስ  የግድ የሚልበት ወቅት አሁን ነው።የፋሽስታዊው የህወሃትና በታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱ የኦሮሞ ጽንፈኞች ኢትዮጵያን የማፍረስና ሕዝብ ለሕዝብ ማጫረስ እጅግ አደገኛ ሴራ ለመመከትና  ለማምከን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመንግስት ጎን መቆም የግድ የሚልበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ለሃገራችንና ለህዝባችን በጋራ እንቀሳቀስ !
Filed in: Amharic