‹ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ?›› የጎረምሳ ኤሊ ህልም…!!!
(አሌክስ አብርሃም )
ዘረኞችና በጥላቻ የሰከሩ ሚስኪኖች ሁልጊዜም ኢትዮጵያዊነት ይከብዳቸዋል፡፡ እርምጃቸው የዘገየው አገር ስለተሸከሙ ይመስላቸዋል ፣ አገር በሌሎች የተጫነችባቸው እዳ ትመስላቸዋለች ፤የከበዳቸውን ኢትዮጵያዊነት አሽቀንጥረው ቢጥሉ እንደጥንቸል የሚሮጡ …እንደንስር ክንፍ አውጥተው የሚበሩ ይመስላቸዋል ፡፡ ‹‹ነፃነት ›› የሚሉት ያንን ነው …ሸክም ያሉት የአገር ካባቸው የተገፈፈ ቀን ሌላው ነገር ቀርቶ የጉንዳን ንክሻ መድረሻ የሚያሳጣቸው ኢምንቶች መሆናቸው አሁን ላይ አይገባቸውም …
ደፍረው መስተዋት ፊት የማይቆሙ ጥላ ቢሶች እንደሚሆኑ ዛሬ ላይ አይረዱትም … የተጋቱትን ቀቢፀ ተስፋ በወራቶች እድሜ የሚያስተፋ ኮሳሳ ማንነት ባለቤት እንደሚሆኑ ከቶ አይገለጥላቸውም! ጉራ አገርን አይተካም …የጎረምሳ ኤሊ ህልም ድንጋዩን ጥሎ እንደጢንቸል መሮጥ ነው …የሰበኳችሁ ሁሉ የሚሰብኳችሁ እናተን አክብረው ሳይሆን ከስሯ የከለለቻችሁ አገር እንደፈለጉ እንዳይጫወቱባችሁ ስለከለከለቻቸው ነው ፡፡ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም !! መፎክር ከማንነት ቀውስ አያድንም … ለዘመናት የኖርነው ‹‹ሸክም›› ያልናት አገር የደህንነታችን ዋስትና ፣የህልውናችን ከለላ ስለሆነችን ነው !! አንተም እኔም ማንም አገርን አልተሸከምናትም ከስሯ ተደብቀንባታል እንጅ !! በነፃነት ስም የደህንነት ዋስትናህን አትጣል፡፡