>

የነሲብ ዘመን...!!! (አሰፋ ሃይሉ)

የነሲብ ዘመን…!!!

አሰፋ ሃይሉ

ሀጫሉ ተገደለ። እናስ? ወያኔ ነች ያስገደለችው። ድምዳሜው በሳቅ ይገድላል። መነኩሴው በፆም እንዳይነቃባቸው ድፍን እንቁላል በጧፍ እየለበለቡ ሲያበስሉ ሌላ መነኩሴ ደረሰባቸው። ምነው? ቢላቸው፦ ሰይጣን አሳስቶኝ ብለው እርፍ። ሰይጣን በቅፅበት ብቅ ብሎ፦ “እግዜር ይድፋኝ እመኑኝ! ይቺንስ ቴክኒክ እኔም ካለዛሬ አላየኋትም!”
አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ሲገጥማቸው- ፈረንሳዮች የሚሉት አባባል አላቸው፦  “ne peignez pas le diable plus noir que lui”። “ዲያብሎስን ከጠቆረው በላይ አጥቁረህ አትሳለው” ማለት ነው ትርጉሙ። “በተርፍላይ ኢፌክት” የሚባልም እጅግ አልተገናኝቶ የሆኑ ነገሮችን  ለማገናኘት ከመፍጨርጨር የተነሳ የሚከሰት ምክንያት አልባነትም አለ። ብራዚል ላይ የበረረች ቢራቢሮ ለናይጄሪያ መፈንቅለ መንግሥት ዋናዋ ሰበብ ነች ብሎ እንደ መደፍደፍ ነው ይሄ ደሞ።
አንዳንዴ ሳስበው ወያኔን ሳናውቀው የክፋቶቻችን ሁሉ “ኢስኬፕ ጎት” አሊያም የክፉ ድርጊቶች ሁሉ “ልማደኛ ተጠርጣሪ” (“ዘ ዩዡዋል ሰስፔክት”) አድርገናት እንዳይሆን ሥጋት አለኝ። የሥጋቴ ምንጭ ሁሉ ነገር በወያኔ ላይ እየተላከከ በሄደ ቁጥር እውነተኞቹ ክፋት ፈፃሚዎች እንደልባቸው በነፃነት የመፏልሉበት ሰፊ የወንጀል ሜዳ እየተመቻቸላቸው ስለሚመጣ ነው።
በሌላም በኩል ወያኔን ያለ ተክለሰውነቷ “ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አድራጊ፣ ሁሉን ፈጣሪ” እንዳናደርጋትም እሰጋለሁ። እርግጥ ነው ወያኔ “ሀ” ብላ በደደቢት ከተፀነሰችበት ጊዜ ጀምሮ ያልተነከረችበት የክፋት ዓይነት የለም። ብዙዎቹን ፀረ ኢትዮጵያ መርዞች ቀምማ ያሰራጨችው ወያኔ ስለመሆኗ በማንም የሚስተባበል ጉዳይ አይደለም። እና ብዙዎቻችን ያንን ሥራዋን ለዓመታት ጧት ማታ መስማትና ማኘክ ከመልመዳችን የተነሳ – ወያኔ አትፈፅመውም፣ ተፀይፋ ትተወዋለች – የምንለው ምንም ዓይነት ክፉ ነገር የለም።
እኔም ራሴ አንዳንዴ የዚሁ ቅዠት ሰለባ ሆኜ ራሴን አገኘዋለሁ። ለምሳሌ ወያኔ ከፈለገች አብይ አህመድን ከአንድ ቀን በላይ በህይወት አታሳድረውም ብዬ ከልቤ አምናለሁ። እዚህ ቅዠት ውስጥ የጨመረኝ አመለካከት ያው ለሀጫሉ ሞት ወያኔን ተጠያቂ ለማድረግ ከሚፍጨረጨረው አመለካከት ብዙም አይለይም ማለት ይቻላል። የብዙ ክፋቶች ምንጭ የሆነ እንደ ወያኔ ያለ አካል አንዲትን ክፋት ለመሥራት የሚሳነው ነገር የለም ብሎ የማመን ጉዳይ ነው።
ሎጂኩ ግን አንዳንዴ ከመጠን ወዳለፈ ስህተት ይመራናልና ከወለምታ ድምዳሜ ሰብሰብ ማለት ሳያስፈልገን እንደማይቀር አጥብቄ አምናለሁ። በዚሁ ሰው አምኖ ይቀበላል በሚለው የተሳሳተ ሎጂክ የተነሳ ለባለፉት 30 ዓመታት ሀገሪቱን እንደ ጠላት ጎተራ በላይዋ ላይ ሰፍረው ሲመዘብሯት የኖሩት የቀን ጅቦች ሁሉ ተረስተው የቀን ጅብነት በወያኔዎቹ ብቻ ተላክኮ መቅረቱን አንርሳ።
በዚሁ ወያኔን የሁሉም ክፋቶች አድራጊ-ፈጣሪ አድርጎ በሚያቀርበው የተሳሳተ ሎጂካችን የተነሳ ለዚያ ሁሉ ዓመታት የሥርዓቱ ግፍና አፈና የበኩላቸውን ያበረከቱ ሁሉ እጃቸውን እንደ ጲላጦስ በንፁህ ውሃ ታጥበው፣ ሁሉን ነገር እንደ ጦስ ዶሮ በወያኔ ላይ ብቻ ደፍድፈው ከደሙ ንፁህ ነን እንዲሉን ዕድሉን አመቻችተንላቸዋል።
ይሄ “ወያኔን ብቻ እኩይ” አድርጎ በአዕምሯችን የተሳለብን ሎጂክ .. ትናንት ከወያኔ ጋር አብረው ጅብ የነበሩት፣ ዛሬ ተገለባብጠው እኛ አህዮች ነን ብለው ጅብን እንፋረድ የሚሉበትን፣ በዳዮችም እነርሱ ተበዳዮችም እነርሱ፣ ፍትህ ከልካዮችም እነርሱ ሰጪዎችም እነርሱ፣ ገዳይና አስገዳዮችም እነርሱ፣ ሙሾ አውራጆችም እነርሱ ራሳቸው የሆኑበትን የተበሻቀጠ የፍትህ አትሮነስ አስታቅፎን እንደቀረ ለአፍታም መዘንጋት አይገባም።
ሁሉንም ክፋቶች በወያኔ ላይ ለማላከክ ያሳየነው ፈቃደኝነት ሌላው የወያኔዎቹ አባሪ-ተባባሪ ሁላ በአንዴ ከተዘፈቀበት ኃጢያት “ዋይት ዎሽድ” ተደርጎ ነጭ አብረቅራቂ መልዓክ ሆኖ የወጣበትን ባዶ “ለውጥ” ታቅፈን እንድንቀር እንዳደረገን ማወቅ አለብን።
ቀዝቃዛው ጦርነት በሚባለው ዘመን ብዙ ዜጎቻቸው “ዩፎዎችን” አየን እያሏቸው የተቸገሩት አሜሪካና እንግሊዝ በስተመጨረሻ እነዚህ ዩፎዎች (UFO’s = “Unknown Flying Objects” = የማይታወቁት በራሪ አካላት) ምንድናቸው ብለው ደመደሙ? “ሶሻሊስቷ ባላንጣችን ሶቭየት ኅብረት በሕዝባችን ላይ የስነልቦና ጦርነት ለመክፈት ዓልማ የምታመጥቅብን ሕዝባችንን የማወናበጃ ረቂቅ ሰው-ሠራሽ ሳተላይቶች ናቸው” ብለው እስከመደምደም ደረሱ። ነገር ግን ሶቭየት ኅብረት ከተንኮታኮተችም በኋላ እነዚህን ዩፎዎች ከነበራሪ ዲስካቸው “በዚህ ሥፍራ አየን” የሚሉ የዓይን እማኞች እስከዛሬም ሊጠፉላቸው አልቻሉም።
እና አንዳንዴ የኛና የወያኔም ነገር ያን የዩፎዎቹንና የሶቭየቶችን ነገር የሚያስታውሰኝ ለምንድነው? ምክንያቱ:- የክፋት ሁሉ ምንጮች ናቸው የተባሉት ወያኔዎች ከሥልጣንም ተገፍተው፣ መቀሌ ገብተው መሽገዋልም እየተባለም፣  still ግን … ባለፉት ዓመታት የለመድናቸውና በወያኔ የተሳበቡት ክፋቶች ሁሉ ተጠናክረው የመቀጠላቸውን ግራ አጋቢ ነገራችንን ስመለከት ነው ሶቭየት ከፈራረሰችም በኋላ መከሰታቸውን የቀጠሉት የዩፎዎቹ ነገር መላልሶ የሚመጣብኝ።
እና ባጠቃላይ ምን ለማለት ነው…? አሁን ማ ይሙት… የወያኔን ቀሽም የጥላቻ ድርሰት እንደ ቅዱስ የነቢያት ቃል አምኖ በ”ነፍጠኛ” እና “ነፍጠኞች” ሀሳብና ጥላቻ ተሞልቶ በአደባባይ የሚንተከተክላትን፣ “የምኒልክን ሐውልት አፍርሰን ፈረሱን እናስቀራለን (የኛ ስለሆነ)” በማለት በአደባባይ የደነፋን፣ አንድ አላዋቂ ሳሚ ድምፃዊ “ፒ አር”ዋን… ወያኔ ምን ይሁንልኝ ብላ ነው የምትገድለው? “ቡጡቡጡን ፍለጋ?”!!
ዋናው ሰውዬ (ጠቅላዩ) እያለላት፣ ስንት ሞታቸው ትልቅ ዕዳ ሊያቀልላት የሚችሉ፣ አደገኝነታቸው እያሳሰቧት የመጡ ስንት የሰቡ የረቡ ታርጌቶች እያሉላት… ለምን በያደባባዩ ራሷ ቀምማ ያመረተችውን የፀረ-ነፍጠኛ አስተሳሰብ መርዝ በያደባባዩ የሚለፈልፍላትን የዋህ ደቀመዝሙሯን ታስገድላለች? ህገመንግስቱን እንደሙሴ ታቦት በጭንቅላቷ ተሸክማ መዞር የቀራት ወያኔ፣ ገነባሁት የምትለውን ህገመንግሥታዊ ሥርዓት የሚንድ ሀገራዊ ብጥብጥና ጦርነት ቢቀሰቀስ ከሌላው አካል በተለየ የምታተርፈው ነገር ምንድነው?
እስቲ እንዲህ እንዲህ እያልን የድምዳሜ ጢባጢቤያችንን እንጫወተውና ይውጣልን ሁሉም ነገር….። መቼም አንድዬ ሲፈርድብን አንድያችንን ዕለት በዕለት በምንሆነው ነገር ሁሉ እንደ ጭራቆችና እንደ ህፃናት ሆነናልና እንጫወታቸውና ይውጡልን ጭራቃዊ ክስተቶቻችን። እንደ ህፃናት። ዘንድሮ ግን እንደ አዋቂ ከመሆን እንደ ህፃናት መሆን ሳያዋጣ ይቀራል? ቢያንስ የምድሩ መንግሥት ባይሆንልን… የሰማዩ እንዳያመልጠን?
ድሮም አልነበረ። ዘንድሮም ያው!የሚታመን ጠፋ። ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በሙያ ኤቲክስ የታጠረ፣ በዲሲፕሊን የታነፀ፣ ለሕዝብ አደራ የታመነ ወንጀል መርማሪ አካል ፈልጎ ሲያጣ… ሕዝብ በራሱ ሎጂክ፣ በራሱ መላምት ከመመራት ውጪ አማራጭ የለውም። አሁን ያለነው በዚህ መላምቶች ሰዎችን ወዳሻቸው በሚያሽከረክሩበት የነሲብ ዘመን ላይ ነው።
ዛሬ ላይ እውነቶቻችንን ሁሉ ተነጥቀናል። ምንም እውነት የምንለው ነገር የለንም። ነጋ ጠባ የሚዘንብልን የፕሮፓጋንዳ ዶፍ እውነታችንን ጠርጎ ወስዶብናል። ነሲብ ሰፈነ። እውነት መነመነ። ወንጀል ተንሰራፋ። ገዳይና ሀዘንተኛ አብረው ሀዘን ተቀመጡ። እውነት የሁሉም መሸቀጫ ሆነች። ከዚህ የነሲብ ዘመን መውጫውን ያመላክተን ፈጣሪ።
Filed in: Amharic