>

እ...ሳ...ቱ...!!! (ዳንኤል ክብረት)

እ…ሳ…ቱ…!!!

 

ዳንኤል ክብረት

ሰውዬው እሳት እያነደደ የሚኖር ነበረ፡፡ ጌቶቹ ሰፊ ግቢ ነበራቸውና በግቢው መካከል እሳት እያነደደ ቀን ቀን ለምግብ ማብሰያ፣ ማታ ማታ ደግሞ ለመሰባሰቢያ ይጠቅም ነበረ፡፡ ከእሳቱ ጋር ብዙ ጊዜ ስለኖረ ‹እሳቱ› ብለው ይጠሩት ነበር፡፡ እሳቱም ከእሳቱ ጋር የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ እሳቱን ተላምዶት ነበር፡፡ ከእርሱ መወለድ በፊት እሳት ምድር ላይ የተፈጠረ አይመስለውም፤ እርሱ ሲሞትም ምድር በብርድ የምታልቅ ይመስለዋል፡፡
አንድ ቀን ከጌቶቹ ጋር ተጣላ፤ አኮረፈ፡፡ ‹ቆይ እሳቱን ማን እንደሚያነድላቸው አያለሁ› አለና ግቢውን ጥሎ ወደ ማዶ ተራራ ወጣ፡፡ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ጥሎት የሄደውን ግቢ ባሻገር መቃኘት ጀመረ፡፡ ልክ ሲመሽ እሳት በግቢው ውስጥ ቦግ ብሎ ሲነድ ተመለከተ፡፡ ይሄኔ ‹እንዴ! እኔ ሳልኖር እሳቱን ማን አነደደላቸው?› አለ እሳቱ ገርሞት፡፡ እሳቱ እሳት ሲያነድ ያዩት ቤተኞች እንዲያውም ከእርሱ በተሻለ እሳቱን አቀጣጠሉት፡፡ እሳቱ ግን እርሱ ከሌለ እሳት የሚድ አይመስለው ነበር፡፡ ከእርሱም ሌላ እሳት ማንደድ የሚችል ሰው አለ ብሎ አያምን ነበር፡፡ እርሱ ካዳፈነበት ቦታ በቀር እሳት የሚገኝ አልመሰለውም ነበር፡፡ እርሱ ሳይኖር እሳት ሲነድ ያየው እሳቱ ‹ለካስ ሌላም እሳት አንዳጅ አለ› አለ ይባላል፡፡
ከፈጣሪ በታች የማይተካ ማንም የለም፡፡ አንዳንድ ሰው አንድን ነገር ለብዙ ጊዜ ይዞት ሲቆይ የፈጠረውና የሚመግበው እርሱ ብቻ መስሎ ይሰማዋል፡፡ እርሱ ከሌለ ያ ነገር የሚሠራ አይመስለውም፡፡ ‹የተዋሱት ዕቃ በእጅ ላይ ሲቆይ የራስ ይመስላል› እንደሚባለው፡፡ ግን ሌላም እሳት አንዳጅ አለ፡፡ አውራ ዶሮ ፀሐይ የምትወጣው እርሱ ሲጮኸ ይመስለዋል፡፡ እርሱ ግን የፀሐይዋን መውጣት ይነግረናል እንጂ ፀሐይዋን አያወጣትም፡፡ ለውጥ መምጣቱን መናገርና ለውጥን ማምጣት የተለያዩ ናቸው፡፡ ‹ያለ እኛ አትኖሩም› የሚሉን ነበሩ፡፡ ‹ያለ እኛ ለውጡ አይኖርም› የሚሉን እንዲተኳቸው አንፈልግም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የማይተካ ሚና ያላት ራሷ ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡
Filed in: Amharic