>

ብፁዕ አቡነ ሔኖክ ከጽንፈኞች ግድያ ተረፉ! (አባይ ነህ ካሴ)

ብፁዕ አቡነ ሔኖክ ከጽንፈኞች ግድያ ተረፉ!

አባይ ነህ ካሴ

* ግድያ፣ ቃጠሎ፣ ውድመትና መፈናቀል በምዕራብ አሩሲ ሀገረስብከት ብቻ፦
 
• 19 ምእመናን በግፍ ተገድለዋል።
• 934 ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
• 4 ትምህርት ቤቶች ተቃጥለዋል።
• 493 መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል።
• 72 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።
• 1 ቤተ ክርስትያን ተቃጥሏል።
•  3362 ምእመናን በየ አብያተ ክርስቲያናቱ ተጠልለው እንደሚገኙ ብፅዕ አቡነ ሄኖክ የምዕራብ አሩሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቨዥን ተናግረዋል። 
ይሄ የምዕራብ አሩሲ ብቻ ነው። ሻሸመኔ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ወድማለች።
እስካሁን ግድያው በምእመናን፣ በካህናት እና በመነኮሳት ላይ ብቻ ነበር። አሁን ግን ገዳዮች ለማንም እንደማይመለሱ አረጋገጥን። አርምሟችን ጳጳሳትንም ሊያስበላ እንደሚችል እኛም አልተረዳንም።
በሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በሻሸመኔ ከተማ የደረሰው እልቂት በቀጥታ ክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ እንጅ የጎሳ ፍጅት አልነበረም ያሉት ሊቀ ጳጳሱ መንበረ ጵጵስናቸው ድረስ የመጡ ነፍሰ ገዳዮች እንደነበሩ ተናገሩ።
ነገር ግን መንበረ ጵጵስናውን ከብበው የሚኖሩት ደገኛ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በራቸው በኃይል ሲደበደብ ሰምተው ገዳዮችን ተለማምጠው በመመለሳቸው መትረፋቸውን ተናግረዋል። እየመሩ እና እያስተባበሩ የነበሩትም በጉልምስና ደረጃ ያሉ እንጅ በተለምዶ እንደሚባለው ወጣቶች ብቻ አይደሉም ብለዋል።
በሀገረ ስብከታቸው ምዕራብ አርሲ ብቻ ፲፱ ክርስቲያኖች አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። በተለይም በአርሲ ነገሌ መግደል አላረካቸው ስላለ ዘቅዝቀው የሰቀሉት ክርስቲያን እንዳለ በከፍተኛ ሐዘን ይናገራሉ። አንድ የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል። የነደዱትና የፈራረሱት የንግድ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች እየተመረጡ ሲኾን የክርስቲያኖች ንብረቶች ናቸው በማለት አስረድተዋል።
እንግዲህ ምን እስክንኾን እንጠብቃለን? ምእመናን ራሳችሁን ቤተ ክርስቲያናችሁንም ጠብቁ ሲሉ አሳስበዋል።
በደንብ እናስብ፤ ለሕልውናችን እንምከር፤  ብዙ የታሰበበት የተደራጀ እና ረዣዥም እጆች የሚደግፉት ጽንፈኛ ሁል ጊዜም እኛን ለመፍጀት በተጠንቀቅ ቆሟል። አዚማችንን አስወግደን እንዘገጃጅ። ዘመኑን ያልዋጀ ጥቅስ እየጠቀስን አንሟዘዝ።
Filed in: Amharic