>

የአዲስ አበባ ህዝብ ጉሮሮው ላይ የቆመበት  እንጂ የቆመለት አመራር የለውም ...!!! (ግርማ ካሳ)

የአዲስ አበባ ህዝብ ጉሮሮው ላይ የቆመበት  እንጂ የቆመለት አመራር የለውም …!!!

ግርማ ካሳ

አቶ ለማ መገርሳ ብልጽግና ፓርቲ እስኪቋቋምና ኦህዴድ እስኪፈርስ ድረስ  በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሞ ክልል ዋናው ሰው ነበር። አቶ ለማ ደግሞ ከነ ጃዋር ጋር ተቃቅፎ እጅና ጓንት  ሆኖ ይሰራ የነበረ ሰው። የነጃዋር መሪ ነበር።
የነ አቶ ለምና ጃዋር ትልቁ አጀንዳቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቆጣጠር ነበር። ኢኮኖሚዉን ካልያዙ በዘለቄታ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችሉ ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህ አዲስ አበባንና አዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን ማህበረሰብ በመዳፋቸው ውስጥ ማስገባቱ ትልቁ አላማቸው ነበር።
ለዚህ አንዱ ስራ አድርገው የወሰዱት ዴሞግራፊን መቀየር ነው። ይሄን ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ ራሱ በግልጽ የተነጋረው ነገር ነው።
ከሶማሌ ክልል ጋር በነበረው የጎሳ ግጭት፣  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች ከቅያቸው ተፈናቅለው ነበር። ተፈናቃዮች ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ወደ ቅያቸው እንዲመለሱ አልተፈለገም። ወይም ደግሞ  እንደ ሃረር፥ ድረዳዋ፣ አወዳይ በመሳሰሉ፣  በአቅራቢያ ባሉ ከተሞች ተፈናቃይችን ማቋቋም አልተሞከረም። ሆኖም ያ፤ለ ፍላጎታቸው በርካታ ተፈናቃዮችን በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሰፍሩ ተደረገ።፡የተፈናቃይ ልጆችና ወጣቶች መልምለው ለራቸው ተልእኮ መጠቀም ጀመሩ።
በዚያ ብቻ አልተወሰኑም።
በጣም ብዙ ወጣቶችን አደራጅተው በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ መዋቅር ዘርግተው፣ በተለያዩ ቦታዎች አስቀምጠው ማንቀሳቀስ ጀመሩ።
ወጣቶቹ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር እነ አቶ ለማ መገርሳና ጃዋር #ሲያፏጩላቸው ልክ እንደ ፈጣን ፖሊስ ብቅ ይላሉ። ባልደራስ ስብሰባ ሊያደርግ ሲል እየተላኩ ሲረብሹ የነበሩት እነዚህ የተደራጁ ወጣቶች ነበር።
ሌላው ስራ የአዲስ አበባን መስተዳደር ፣ ክፍለ ከተሞችን #መቆጣጠር ነው።
ኢንጂነር ታከለ ኡማን ያስቀመጠው፣ ዶር አብይን በድርጅታዊ አሰራር እጅ ጠምዝዞ፣ አቶ ለማ መገርሳ ነበር።
የአዲስ አበበ በርካታ የክፍለ ከተሞች ሃላፊዎች በቀጥታ #የሾመው አቶ ለማ መገርሳ ነበር።
ኢንጂነር ታከለ ኡማም ሆነ የክፍለ ከተማ ሃላፊዎች ቤቶች፣ መሬቶች፣ መታወቂያዎችን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ እነ አቶ ለማ ላደራጇቸው ወጣቶች እየሰጡ ፣ የወጣቶችን አደረጃጀት አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ #ይደግፉ ነበር።
የከተማው #ፖሊስ ውስጥም  የነርሱን ሰዎች በብዛት በማስቀመጥ፣ እነዚህ ወጣቶች ላይ እርምጃዎችና ሕግን የማስክበር ስራዎችን #እንዳይሰራ ያከላክሉ ነበር።
በአንጻሩ ግን እነዚህ ወጣቶቹ በሚያደረጉት ጥፋት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል ሲሞክሩ ፣ የአዲስ አበባ ልጆች ላይ ዱላቸውን ከማሳረፍ ወደ ኋላ #አይሉም።
መልካም ሞላ የተባሉ ሰው የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በአዲስ አበባ በአንድ ቦታ የሆነውን አሳዛኝ ክስተት እንደሚከተለው ጽፈዉታል
“ሀጫሉ የተገደለ እለት በርካታ ቄሮዎች ቆንጨራ ገጀራ እና ብረት ይዘው ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመሩ። ግርር ብለው ያገኙትን መሰባበር ጀመሩ። ጥቃቱን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች አልተቆጣጠሩትም። 7 ቤተክርስቲያን ለማቃጠል እና ለማውደም ሙከራ አደረጉ። ከቤተክርስትያን በተደወለው ደወል የአካባቢው ህዝብ ወደቤተክርስቲያኑ ተመመ። ቄሮን አባረረ። ሌላውም በየሰፈሩ ራሱን እያደራጀ አካባቢውን ከውድመት ጠበቀ።
ቃሊቲ አካባቢ አንድ ሰውየ ቄሮ ግርር ብሎ ሊያጠቃው ሲመጣ ጥይት ወደ ሰማይ ተኩሶ በታተናቸው። ወዲያው የመንግስት ታጣቂዎች ደርሰው ሽጉጡን ቀምተው ልጁን ለመንጋው ትተውት ሄዱ። መንጋውም አንበሳ ገድሎ እንደሚፎክር ጀግና ገድለውት ሬሳውን በአዲስ አበባ ጎዳና ጎተቱት። ህዝቡ ያንን አየ።”
ኢንጂነር ታከለ ኡማና በየክፍለ ከተማው ያሉ የአቶ ለማ መገርሳ ሹመኛ ሃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ የፖሊስ አዛዦች ሙሉ ለሙሉ ካልተቀየሩ ፣ ከጽንፈኞች ጋር ሲተባበሩ የነበሩም ለሕግ ካልቀረቡ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ መቼም ቢሆን ሰላም አያገኝም።
እነ ወ/ሮ አዳነኝ አበቤ “አሰርን ፣ በቁጥጥር ስር አዋልን..”   ይላሉ። ያ በቂ አይደለም። እነዚህን ጽንፈኞች ሲረዱ፣ ሲደግፉ፣ ስፖንሰር ሲያደርጉ፣ ሲጠብቁ፣ ሲያሰማሩን  ሲንከባከቡ  የነበሩ  የቀድሞ ኦህደድ አሁን የብልጽግና ሃላፊዎችም መነሳት አለባቸው።
የዶር አብይ መስተዳደር ጣቶቹን ሕወሐት ላይ ያደርጋል። በአዲስ አበባ  አስክሬኑ በጎዳና ላይ እንዲጎተት የተደረገውን ወንድምን ያስገደሉት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ናቸው።
ይሄን በግልጽ #የሚያሳየው በአዲስ አበባ ያለው አመራርና መስተዳደር ለአዲስ አበባ ህዝብ የቆመ፣ ለአዲስ አበባ ህዝብ የተነሳ ሳይሆን፣ የአዲስ አበብና ሕዝብ #የሚያስጠቃና በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ የተነሳ አመራርና መስተዳደር መሆኑን ነው።
ዶር አብይ አህመድ በአቶ ለማ ማገርሳና በነጃዋር ያለርሱ ፍቃድ፣ እጁ ተጠምዝዞ፣ የተሾሙትን ጽንፈኛ አመራሮች ከአዲስ አበባ ጠራርጎ #እንዲያስወጣና የአዲስ አበባን ህዝብ የሚመጥን ጊዚያዊ አመራር እንዲስቀምጥ እጠይቃለሁ።
ማንም ከሕግ በላይ አይደለም።
ወንጀለኞችን የቆጣጠርና ህዝክን የማስክበር ስራው ተገቢ ብቻ ሳይሆን በጣም #የረፈደ ፣ ቀደም ሲልም መደረግ የነበረበት ቢሆንም፣ ሕግን በማስክበር ስም፣ አጋጣሚዉን በመጠቀምና ጽንፈኞችን ለማባባል በሚል፣  ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው #አፈና መቆም አለበት።
የባልደራሶች መታሰር ፍጹም ስህተት ነው።
በቶሎ መታረም አለበት።
በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ ራሳቸውንና ሰፈራቸው ከአሸባሪዎች ለመከላከል ሞክረዋል።  የአዲስ አበባ ወጣቶች በመኪና ተጭነው አምቦ፣ ወይም ወሊሶ ሄደው በዚያ የሚኖሩትን ሰላማዊ ዜጎች አላሸበሩም።
ነገር ግን በሰፈራቸው ሊያቃጥልና ሊያወድም የመጣውን ነው የመከቱት።
ለዚህ ሊመሰገኑ፣ ሊሸለሙ እንጂ በፖሊስ ወከባና እስር ሊገጥማቸው አይገባም።
Filed in: Amharic