>

የአቶ ጃዋር ጠበቆች አቤቱታና የዕለቱ የችሎት ውሎ...!!!  (ይታገሱ አምባዬ)

የአቶ ጃዋር ጠበቆች አቤቱታና የዕለቱ የችሎት ውሎ…!!!

 ይታገሱ አምባዬ

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ከሁለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይ የተመለከተው ፍርድ ቤት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀደ።
አቶ ጃዋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ይህንንም ተከትሎ የጃዋር ጠበቃ ደንበኛቸው በዋስ ከእሰር ቤት ውጪ ሆኖ ጉዳዩን መከታተል እንዲችል እንዲፈቀድለት ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ተቀብሎታል።
በዚህ ጊዜ የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ምግብ ከቤተሰቡ የሚቀርብለት ቢሆንም ግንኙነታቸው በርቀት በመሆኑ ባለበት ከርቀት አይቶ የመለየት ችግር ቤተሰቦቹን በቅርበት እንዲያገኝ እንዳልተፈቀደለት ለችሎቱ አቤት ብለዋል።
ፖሊስም ይህንን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ታሳሪዎችና ጠያቂዎች መካከል መቀራረብ እንዳይኖር የተደረገው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወጣው ደንብ መሰረት መሆኑን ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል።
በተጨማሪም አቶ ጃዋር ታስረው የሚገኙበት ክፍል በቂ ብርሃን የሌለው መሆኑና መጸዳጃ ቤት የመጠቀም ችግርን በማንሳት አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም ደንበኛቸው ጥፋተኝነታቸው ገና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምስላቸው እየቀረበ ዘገባዎች እንደሚቀርቡና ፍርድ ቤቱም ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ለእስረኞች መጸዳጃ ቤትን በተመለከተና በማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ያለውን ብርሃን በተመለከተ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ያዘዘ ሲሆን፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለቀረበው አቤቱታም ጠበቆች ያሏቸውን ተቋማት በስም ለይተው እንዲያቀርቡ አዟል።
በዚህም መሰረት ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ፈቅዶ ጉዳዩን ለመመልከት ሐምሌ 23/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል።
የጃዋር ጠበቃ ከችሎት በፊት
ከአቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ  እንደተናገሩት አቶ ጃዋርን ባለፈው ማክሰኞ አግኝተዋቸው እንደነበር ገልፀው፤ ታስረው የሚገኙት ምድር ቤት ውስጥ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በማረፊያ ክፍሉ ውስጥም አነስተኛ ተፈጥሯዊ ብርሃን እያገኙ እንደሆነና ብርሃኑም በትንሽ መስኮት በኩል የሚገባ ብቻ መሆኑን እንደነገሯቸው አረጋግጠዋል።
ነገር ግን አቶ ጀዋርና አቶ በቀለ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረዋል ስለመባሉ ሲያብራሩም የኤሌትሪክ መብራት በክፍሉ ውስጥ መኖሩንና ችግሩ የተፈጥሮ ብርሃን አለማግኘታቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የጃዋር ቤተሰብ ምግብ ሲያደርሱላቸው የቤተሰባቸውን አባላት መለየት አለመቻላቸውን ከቤተሰቡ አባል ማረጋገጣቸውን አቶ ቱሊ ተናግረዋል።
“ጃዋርን በምን ምክንያት መለየት እንዳልቻለ ጠይቄው፤ ከቤተሰቡ አባል ጋር የሚገናኙት ከርቀት ቆመ እንደሆነና ድምጻችንን ከፍ አድርገን ነው ጮኸን የምንነጋገረው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከክፍሌ የፀሐይ ብርሃን ወዳለበት ስወጣ አይኔ አጥርቶ ማየት አልቻለም ነበር ብሎኛል” ሲሉ ጠበቃው ገልጸዋል።
አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አቶ ሀምዛ ቦረና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በሌላ ክፍል በጋራ ታስረው እንደሚገኙ አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ሸምሰዲን ጠሃ አቶ ጃዋር በቁጥጥር ስር በዋለ በማግስቱ ቦሌ ሚካኤል ከሚገኘው የጓደኛቸው ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው አቶ ቱሊ አረጋግጠዋል።
የሕክምና እርዳታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም እንዳልተፈቀደለት እነደነገራቸው አቶ ቱሊ  ገልፀዋል።
አቶ ቱሊ ሸምሰዲንን ሲያገኙት አካሉ ላይ የደረሰበትን ጉዳት እንዳሳያቸው ተናግረው ደረቱ፣ ጎኑ ላይና እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የጃዋር ጠባቂዎች የጤና ሁኔታ
የጃዋር የግል ጠባቂዎች ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ አቶ ቱሊ አረጋግጠዋል።
በእስር ቤቱ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ የተጠረጠረ ሰው መገኘቱን ተከትሎ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤት እየጠበቁ እንደሆነ ከጠባቂዎቹ አስተባባሪ መስማታቸውን አቶ ቱሊ  ተናግረዋል።
ነገር ግን እስካሁ ግን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ስለመኖር የተረጋገጠ እንደሌለ ጠበቃ ቱሊ ባይሳ  ተናግረዋል።
Filed in: Amharic